ስብከተ ወንገልና ሐዋርያዊ ተልእኮ

1. ስብከተ ወንጌል

1.1. የወንጌል ምንነት 

ስለ ስብከተ ወንጌል ለመናገር ከተፈለገ አስቀድሞ ስለ ወንጌል መናገር የግድ ይሆናል፤ ወንጌል ዋናው መልእክቱ ስብከተ ወንጌል ደግሞ መልእክቱ የሚተላለፍበት ዘዴ ነውና፡፡ በግእዝና በአማርኛ ወንጌል ተብሎ የተተረጐመው ቃል በግሪክኛ “ዩአንጌሊዮን” የሚለው ቃል ሲሆን ትርጒሙም “የምሥራች” ማለት ነው፡፡ “ወንጌል ብሂል በልሳነ ፅርዕ ወትርጓሜሁ ስብከት” ማለትም “ወንጌል የሚለው ቃል ከፅርዕ ቋንቋ የተገኘ ነው፤ ትርጓሜውም ስብከት ወይም የምሥራች ማለት ነው” የሚለው ቃልም ይህን ያመለክታል፡፡

በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ወንጌል” የሚለው ቃል 101 ጊዜያት ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ በእንግሊዝኛው ደግሞ 96 ጊዜያት ተጠቅሷል፤ ይህን የመሰለ ልዩነት ሊኖር የሚችለው ሐዲስ ኪዳን ከግሪክኛ ቋንቋ ወደ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ሲተረጐም “ዩአንጌሊዮን” የሚለው ቃል ተመሳሳይ በሆኑ አቻ ቃላት ሊተረጐም ስለሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ፡ ወንጌልና የምሥራች ተመሳሳይ መልእክት ያላቸው ቃላት ናቸው፡፡ ስለዚህ ዮአንጌሊዮን የሚለው ቃል ወንጌል ወይም የምሥራች ተብሎ ሊተረጐም ይችላል ማለት ነው፡፡

ሆኖም ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ በልዩ ልዩ መንገድ የሚናገር ወንጌል ነው፤ በሕግ፣ በትንቢት፣ በምሳሌ፣ በታሪክ፣ በመዝሙር፣ በቅኔና በጥበብ፣ እና በመሳሰሉት መልኩ ቢነገርም በአንድም ይሁን በሌላ የሚመራው ወደ ክርስቶስ፣ የሚናገረውም ስለ ክርስቶስ ነው፡፡ ለምሳሌ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ወንጌል የሚለው ቃል አንድ ጊዜ እንኳን ተጠቅሶ አይገኝም፣ ነገር ግን ከዮሐንስ ወንጌል የበለጠ ወንጌል የለም፡፡ ዮሐንስ በመልእክቶቹም ወንጌል የሚለውን ቃል አልጠቀሰም፤ በተመሳሳይ መልኩ በሌሎችም አንዳንድ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ወንጌል የሚለው ቃል አይገኝም፤ ነገር ግን ሙሉ ሐዲስ ኪዳን ወንጌል መሆኑ የታወቀ እውነት ነው፡፡

ወንጌል የሚለው ቃል ከሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት መካከል ለዐራቱ መጠሪያ ቢሆንም ከመልእክት አንጻር ሲታይ በመክብባቸው በወንጌል ሁሉም የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ወንጌል ናቸው፡፡ ወንጌል ትምህርትና እምነት ስለሆነ አንድ ነው፤ ዐራት ወንጌላት ተብለው የሚጠሩ መጻሕፍት ቢኖሩንም ወንጌል አንድ ብቻ ነው፡፡ በተለያዩ ዘመናት፣ በተለያየ ዘዴ፣ ለተለያዩ ሰዎች፣ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የሚሰበከው የዘለዓለም ሕይወት የሚገኝበት ወንጌል አንድ ነው፡፡

ስብከተ ወንጌል በቤተ ክርስቲያን አንድ የሥራ ዘርፍ አይደልም፡፡ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን ሥራዎች ሁሉ መሠረት ስብከተ ወንጌል ነው፡፡ ሁላችንም ሰባክያነ ወንጌል ነን፤ ስብከተ ወንጌል እምነትና እውቀትን እንጂ ሹመትን አይጠይቅም፡፡ የስብከተ ወንጌል ኀላፊነት እንደሌሎች የሥራ ኀላፊነቶች በደብዳቤ የሚሰጥና በደብዳቤ የሚነሣ ተግባር አይደለም፡፡ ክርስቶስ “ሂዱ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” ብሎ የተናገረው ቃል እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለክርስያኖችና ወንጌልን መስበክ ለሚፈልጉ ሁሉ መመሪያ ሆኖ ይኖራል፡፡ ይህ ማለት ግን በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ሥርዐትና ሕግን ሳይከተሉ እንደፈለጉ መስበክ ይቻላል ማለት አይደለም፡፡ ወንጌልን የመስበክ ኀላፊነት አምላካዊ ትእዛዝ መሆኑን ለመናገር ነው እንጂ፡፡ ይህን የተረዳው ሐዋርያ “ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ” (1ቆሮ.9÷6) ሲል የጻፈውም በዚህ ምክንያት መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡

ወንጌል የቅኔ፣ የዜማ፣ የትርጓሜ መጻሕፍት፣ የሊቃውንት ምሥጢር፣ የቅዱሳን ገድል፣ የጻድቃን ጽድቅ፣ የሰማእታት ጽንአት የፈለቀበት የጥበባት ሁሉ መገኛ ነው፡፡ የልዩ ልዩ ጥበባትና ዕውቀቶች ሁሉ ምንጭ ወንጌል ነው፡፡ ወንጌል ውቅያኖስ (ባሕር) ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ሙያዎች (ትምህርቶች) ደግሞ ከወንጌል የተቀዱና በልዩ ልዩ መንገድ የሚፈስሱ ወንዞች ናቸው፡፡ የምናጠምቃቸው፣ የምናቆርባቸው፣ ቢሞቱ ፈትተን የምሸኛቸው፣ በተክሊል በቁርባን የምናጋባቸው፣ ምእመናን ሁሉ የወንጌል ፍሬዎች ናቸው፡፡ ወንጌል የሚሰበክባት ዐውደ ምሕረትም እንደ ስሟ ምሕረት የሚታወጅባት የወንጌል መድረክ ናት፡፡

1.2. የስብከተ ወንጌል አስፈላጊነት

የቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ዓላማና ተግባር ምንድን ነው ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ወንጌልን መስበክ እንደሆነ ከማንም ክርስቲያን አእምሮ የተሠወረ አይደለም፡፡ ስለዚህ ስብከተ ወንጌል ለቤተ ክርስቲያን ህልውና እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡

ስብከተ ወንጌል ለምን አስፈለገ?

ስብከተ ወንጌል ያስፈለገባቸውን ምክንያቶች በሮሜ 10÷13-17 የሐዋርያው ቃል እንዲህ ይላል፤ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና፤እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ? ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና። እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።” ይህ ቃል የስብከተ ወንጌል ዐቢይ ተልእኮ ሰዎች የወንጌልን ቃል ሰምተው በማመን የእግዚአብሔርን ስም ጠርተው እንዲድኑ ወይም የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኙ ማስቻል ነው፡፡

2. ሐዋርያዊ ተልእኮ

2.1. ሐዋርያ ማለት ምን ማለት ነው? (የሐዋርያነት ትርጒም)

“ሐዋርያ” የሚለው ቃል “ሖረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን “መንገደኛ፣ መልእክተኛ፣ ቀላጤ” የሚል ትርጒም አለው፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱን ተከትለን ስንተረጒመው “ሐዋርያ” የሚለው ቃል በአማርኛም በቁሙ ሐዋርያ ተበሎ ከመተርጐሙ በተጨማሪ “መንፈሳዊ ሹም፣ መምህር፣ ዙሮ የሚሰብክና የሚያስተምር፣ ባለምሥራች፣ ዐዋጅ ነጋሪ” የሚል ፍቺ አለው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ 1948 ዓ.ም. ገጽ. 437)፡፡ መልእክቱም የጌታ ወንጌል ነው፤ ስለዚህ የሐዋርያነት መሠረቱ ወንጌልን መስበክ ይሆናል ማለት ነው፤ለሰው ልጆች ሁሉ ይደርስ ዘንድ የተላከው የጌታ መልእክት ወንጌል ስለሆነ ወንጌልን ሳይይዙ ወይም ሳይሰብኩ ሐዋርያ መሆን አይቻልም፡፡
በላቲንና በእግሊዝኛ ቋንቋዎች “apostle” የሚለው ቃል ከግሪክኛው “Apostolos” ከሚለው ቃል የተወሰደ ነው፤ ግሪክኛውም ከሁለት የግሪክ ቃላት ማለትም “apo” እና “stellen” የተገኘ ጥምር ቃል ነው፤ “apo” የሚለው “ወዲያ” ወይም “ሩቅ” ማለት ሲሆን “stellen” ደግሞ የተላከ የሚል ትርጒም አለው፤ አንድ ላይ “ወደ ሩቅ ቦታ መልእክተኛ ሆኖ የተላከ” የሚለውን ዐሳብ ይገልጣል፡፡ (ምጭ፡ Dictionary of Word Origins)

ሐዋርያነት ስልጣን ነው፡፡

ሐዋርያ መልእክተኛ ቢሆንም በላኪው ስለሚመረጥና ስልጣንን ተቀብሎ የላኪውን ትእዛዝ ስለሚፈጽም ባለሟል ወይም እንደራሴ ነው፤ “ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲያወጡአቸው፣ በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ስልጣን ሰጣቸው” የሚለው የወንጌል ቃልም ይህን ያረጋግጣል (ማቴ.10፥1) ፡፡ የማቴዎስ ወንጌል ትይዩ ንባብ የሆነውና በማርቆስ ወንጌል የተጻፈው የሐዋርያትን ጥሪና መመረጥ የሚናገረው የወንጌል ቃል ደግሞ እንዲህ ይላል፤ “ራሱም የወደዳቸውን ወደ እሱ ጠራ፤ ወደ እርሱም ሄዱ፤ ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፣ ድውዮችንም ሊፈውሱ፣ አጋንንትንም ሊያወጡ ስልጣን ይሆንላቸው ዘንድ ዐሥራ ሁለት አደረገ” (ማር.3፥13-15) ፡፡
በዚህ ቃል ውስጥ ስለ ሐዋርያነት ብዙ ነገሮች ተገልጠዋል፤ እነዚህም፣ በራሱ በጌታ መወደድ፣ መመረጥና መጠራት፣ ወደ እርሱ መሄድና ከእርሱ ጋር መኖር፣ ወንጌልን ለመስበክ መላክ፣ ድውዮችን ለመፈወስና አጋንንትን ለማውጣት ስልጣንን መቀበል ናቸው፤ ሐዋርያነት አንድ ነገርን ብቻ ወይም ጥቂት ነገሮችን ብቻ የያዘ ኀላፊነት እንዳልሆነ ከዚህ ቃል በግልጽ እንመለከታለን፡፡

ሐዋርያነት መሠረትነትና ቀዳሚነት ነው፡፡

በዕብራውያን መልእክት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሐዋርያ” ተብሎ ተጠርቷል፤ ይህም ሐዋርያነት መሠረትነት፣ ጀማሪነት፣ ጥንትነት፣ ፊታውራሪነት፣ አበጋዝነት፣ አስታራቂነት መሆኑን ያስረዳል፤ ኢትዮጵያውያን የአንድምታ ትርጓሜ ሊቃውንት “ርእይዎ ለዝንቱ ሐዋርያክሙ” ያለውን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል ሲተረጒሙ “ፊታውራሪያችሁ፣ አበጋዛችሁ፣ አስታራቂያችሁ ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርጉት” ብለውታል (የዕብ. 3፥1 አንድምታ ትርጓሜን ተልከት)፤ የነቢያትና የሐዋርያት መሠረትነት ቀደምት አማንያንና ለክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የዐይን ምስክሮች መሆናቸው ነው፡፡

በሌላ ስፍራ ቅዱስ ጳውሎስ “እስመ ተሐነጽክሙ ዲበ መሠረተ ሐዋርያት ወነቢያት” ያለውን የሐዋርያ ቃል የአንድምታ ትርጓሜ መምህራን “ነቢያት ሐዋርያት ባመኑበት እምነት ጸንታችኋልና” ብለው መተርጐማቸው ለዚህ ምስክር ነው፤ “አንተ ኰኵሕ ወዲበ ዛቲ ኰኵሕ አሐንጻ ለቤተ ክርስቲያንየ” ያለውን የወንጌል ቃልም “እኔ መሠረት ነህ ብዬ መሠረት እንደሆንህ እናገርልሃአለሁ” በማለት ይፈቱትና “መሠረትነቱ የሃይማኖት የሹመት ነው” ይላሉ፤ ግእዝ በግእዝ ትርጓሜ ወንጌልም “ወኰኵሕሰ ዘተብህለ በአፈ ጴጥሮስ ሃይማኖተ ጴጥሮስ፤ እስመ ይቤ ወዲበ ዛቲ ኰኵሕ አሐንጻ ለቤተ ክርስቲያንየ ከመ ዘይቤ ወዲበ ዛቲ ሃይማኖትከ” ብሎ ይተረጒመዋል፤ በአማርኛ “ዐለት የተባለው በጴጥሮስ አንደበት የተነገረው ሃይማኖት ነው፤በዚህች ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ ብሏልና፤ ይህም በዚህች ሃይማኖትህ ላይ እንደማለት ነው” የሚል ነው፤ የሃይማኖትና የሹመት መሠረት የመሆን ሐዋርያዊ እምነትና ትምህርትም ይህ ነው፡፡
ሐዋርያት የሰበኩት መሠረት ክርስቶስ ነው፤ እነርሱ ከሰበኩት ክርስቶስ የተለየ ሐሰተኛ ክርስቶስን የሚሰብክ ቢኖር ከእውነተኛው እምነት የወጣና በፍርድ ቀን የሚቀጣ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ በሚከተለው መልእክቱ ያስጠነቀቀውም በዚህ ምክንያት ነው፤ “የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል” (1ቆሮ.3፥10-12) ፡፡

ሐዋርያነት አብነት/አባትነት ነው፡፡

አብነት የሚለው ቃል “አብ” ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም “አባትነት፣ ጌትነት፣ ባለቤትነት፣ አርአያ፣ ምሳሌ፣ መድኃኒት፣ ነባር፣ ጥልቅና ትልቅ ዕውቀት ያለው፣ ምስክር ፣ተጠያቂ፣ አዋቂ፣ ሊቅ፣ አባት፣ ወይም ለምስክርነትና ለተጠያቂነት የበቃ ሊቅ አዋቂ” ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አብነት የሚለው ቃል ለተጠያቂነት ከመብቃት፤ለአንድ ሙያ (ዕውቀት) በቂ ትምህርትን ከመያዝና ምስክር ሆኖ ከመገኘት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያይቱ የቆሮንቶስ መልእክቱ “በክርስቶስ ብዙ ሞግዚቶች ቢኖሩአችሁም ብዙ አባቶች የሉአችሁም፤ እኔ በክርስቶሰ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና” (1ቆሮ.4፥15) ይላል፡፡ ከዚህም በመነሣት “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” ብሎ ልጆቹን ይመክራል (1ቆሮ.11፥1) ፡፡ ዛሬም የሚያስፈልገን ሐዋርያዊ አባት እንዲህ ክርስቶስን መስሎ እኔን ምሰሉ የሚልና በወንጌል ለወለዳቸው ልጆች አባት የሚሆን፣ አብነት/አርኣያ የሆነ ሕይወት ያለው ሊሆን ይገባዋል፡፡

2.2. ሐዋርያዊ (የሐዋርያት) ተልእኮ ማለትስ ምን ማለት ነው? የሐዋርያት ተልእኮ ምን ነበር?

ሐዋርያዊ ተልእኮ ዘርፈ-ብዙ፣ እግዚአብሔርንና ሰውን ማገልገልን የሚያካትት ሰፊ ኀላፊነት ነው፤ ሐዋርያት በቤተ ክርስቲያን ያላቸው ኀላፊነት ሁለንተናዊ እንጂ በአንድ ወይም በጥቂት ጉዳዮች ላይ የሚያተኵር ብቻ አይደለም፤ ሆኖም ግን ለዚህ አጭር ጽሑፍ በሚሆን መልኩ ዋና ዋና ነገሮችን እንጠቅሳለን፡፡

ወንጌልን መስበክ

የአንድ ሐዋርያ ወይም የሐዋርያትን መንበር የወረሰና በእግራቸው ተተክቶ ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግል አባት ዋና ተልእኮ ወንጌልን መስበክ ነው፤“ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው፤… ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” የሚለው የወንጌል ቃል ይህን ታላቅና የከበረ ተልእኮ የሚያስረዳ ነው (ማር.16፥8፡15) ፡፡

ሐዋርያት የተመረጡት፣ ከዓለም የተለዩት፣ ክርስቶስ ከዋለበት ውለውና ካደረበት አድረው ትምህርትና ተአምራት ሳይከፈልባቸው ሁሉን ያዩትና የተማሩት፣በመጨረሻም ሰማያዊ ኀይልን የተቀበሉትና በጸጋ መንፈስ ቅዱስ የተሞሉት ለዚህ ታላቅና ክቡር ተልእኮ መሳካት ነው፤ በዚህ መልክ የክርስቶስ ምስክሮች ሆነው የወንጌሉን ቃል ከኢየሩሳሌም ጀምሮ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ሰበኩ፤ “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም፣ በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም፣ እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” (የሐዋ.1፥8) ብሎ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርት ያዘዘው ትእዛዝ መዳረሻውም መላውን ዓለም በወንጌል መድረስና በዕርፈ መስቀል ማረስ እንደ ሆነ ያሳያል፤ ለዚህም አስቀድሞ “ውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ፤ ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ” ማለትም “ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ፣ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ” የሚል ትንቢት አስቀድሞ ተነግሮ ነበር (መዝ.18፥4፤ሮሜ 10፥18) ፡፡

ይህን ተልእኮ 12 ሐዋርያት ብቻ ሊፈጽሙት እንደማይችሉ፣ተልእኮውም ለነርሱ ዘመን ብቻ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤ በሐዋርያት መንበር የተተኩ አባቶች በየዘመኑ ይህን ሐዋርያዊ ተልእኮ ተረድተውና ሐዋርያዊ ቅብብሎሽን ጠብቀው እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ድረስ በትጋት ሊፈጽሙት ይገባል፤“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ.28÷19) በሚለው የክርስቶስ ቃል ውስጥ “እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” የሚለው የወንጌል ቃል ተልእኮው እስከ ዓለም ፍጻሜ እንደሆነ ያሳያል፤ስለዚህ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በቀዳሚነት፣ ካህናትና ምእመናን ደግሞ በአበው መሪነት በዚህ ታሪካዊና መንፈሳዊ ሂደት ውስጥ ዛሬ ላይ ይህን ታላቅና ክቡር ኀላፊነት እየተወጡ ነው፡፡

ጥሙቃንን በትምህረተ ወንጌል ማጽናትና መጠበቅ

“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” (የሐዋ.20፥28) የሚለው የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ጥሙቃንን የመጠበቅ ኀላፊነት ለጳጳሳት የተሰጠ ሐዋርያዊ ተልእኮ መሆኑን ያስረዳል፤ ቅዱስ ጳውሎስ “አኔ ተከልሁ፤ አጵሎስ አጠጣ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር” (1ቆሮ.3፥6) እንዳለ መትከል ዐዳዲስ አማንያንን አስተምሮ ማጥመቅና ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ማስገባት ነው፤ ማጠጣት ደግሞ አማንያንን በትምህርተ ወንጌል ማጽናትና ማሳደግ ነው፤ የሚተክልና የሚያጠጣ ሁለቱም አገልጋዮች ናቸው፤ ባለቤቱ እግዚአብሔር ሕይወትን ይሰጣል፤ ያሳድጋልም፡፡ ጥሙቃንን (አማንያንን) የመጠበቅና የማሳደግ ሐዋርያዊ ተልእኮ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ በዘመነ ሊቃውንትና በዚህም ዘመን ቤተ ክርስቲያን ያለምንም መቋረጥ እየፈጸመችው የኖረና ያለ ሐዋርያዊ ተግባር ነው፡፡

የሐሰት (የስሕተት) ትምህርቶችን መቃወምና እውነተኛውን ትምሀርት መጠበቅ

ሐሰተኛ ትምህርት /ምንፍቅና/ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ደዌ ነው፤ ከአባላት መካከል በአንዱ ወይም በብዙ አባላት ላይ የሚታይና ሌላውን ጤነኛ አባል/የአካል ክፍል/ በቅርበት የሚጐዳ ይሆናል፤ ከዘመነ ሐዋርያት ቀጥሎ በነበረው ዘመነ ሰማእታት ቤተ ክርስቲያን ከዓላውያን ነገሥታት በሚመጣ ከፍተኛ ስደትና መከራ ውስጥ አልፋለች፤ እንደ አውሮፓውያን አቈጣጠር ከ312 ዓ.ም. በኋላ ሰላም ሲገኝ ደግሞ ቀድሞም በመጠኑ የነበረ ቢሆንም የመናፍቃን መነሣትና የስሕተት ትምህርቶች መስፋፋት ቤተ ክርስቲያንን ከውስጥ ፈተናት፤ ወደ ውጭ መዘርጋትና ያላመነውን ዓለም በወንጌል የማሳመን ተልእኮዋን በማደናቀፍ የውስጥ ችግሮችን በመፍታት ላይ እንድትጠመድ አደረጋት፤ በመስፋፋት ፈንታ ተሰበሰበች ወይም መስፋፋትዋ ተገታ፤ማውገዝና መናፍቃንን ከቤተ ክርሰቲያን መለየት የግድ ስለሆነ በክርስቲያኖች መካከል መለያየቱ እየሰፋ ሄደ፤ቤተ ክርስቲያን በዚህ ችግር ለ300 ዓመታት ስትፈተን ከቆየች በኋላ ችግሯን የበለጠ የሚያባብስ የእስልምና መነሣት ተከሠተ፤ ይህ ሁሉ ታሪካዊ ሁኔታ የሚነግረን የሐሰት ትምህርትን መከላከልና እውነተኛውን ትምህርት ማስተማር በሐዋርያዊ ተልእኮ የግድ መሆኑን ለማሳየትና ይህን ኀላፊነት በትክክል አለመወጣት ሁለንተናዊ ጥፋት የሚያመጣ መሆኑን ለማመላከት ነው፤ ስለዚህ ብፁዓን አባቶች፣ ካህናትና ምእመናን ከቅዱሳን ሐዋርያት የተቀበልነውን እምነትና ትምህርት መጠበቅና ሳይበረዝ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባቸዋል፡፡

ሐዋርያዊ ቅብብሎሽንና የቤተ ክርስቲያንን ቅዱስ ትውፊት በመጠበቅ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ማጽናት

ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ የሚባለው ቃል የ12ቱ ሐዋርያት ስልጣን በተለይ በኤጲስ ቆጶሳት (ጳጳሳት) በኩል እስከ ዛሬ የቀጠለበት፣ ወደፊትም የሚቀጥልበት ክህነታዊ ሰንሰለት ነው፤ ዋናው ዐሳብ የዛሬዋ ኦርቶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ሐዋርያት ከሰበሰቧትና ከመሯት ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር በእምነትና በትምህርት አንድ መሆንዋን የሚያረጋግጥ ቅብብሎሽ ነው፤ ከጥንት ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ቀሌምንጦስ ዘሮምና አግናጥዮስ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ምን እንደሆነ አስተምረዋል፤ ግኖስቲካውያን ስዉር እንቅስቃሴ በመፍጠርና ይህን ስዉር እንቅስቃሴ ትክክለኛው የሐዋርያት ትምህርትና እምነት ወራሽ እንደሆነ በማስተማር ክርስቲያኖችን ማሳት ሲጀምሩ ቀሌምንጦስና አግናጥዮስ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያትን ተልእኮ በስዉር ሳይሆን በዐደባባይ እየሰበከች ጠብቃ ያለች መሆንዋንና ስዉር እንቅስቃሴ ያደረጉ መናፍቃን ከእውነተኛው ሐዋርያዊ ሰንሰለት ራሳቸውን እንደለዩ በማስተማር የሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ትምህርት ምን እንደሆነ የሚያሳይ መሠረት ጥለዋል፤ ከትምህርትና እምነት ይዘት በተጨማሪም ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ እጅ በመጫን የሚገለጥ ክርስቲያናዊ የሢመተ ክህነት መስመርም ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚገለጠው በእምነትና በትምህርት ኦርቶክሳዊነት (ርቱዕነት)፣ በሐዋርያዊ ቅብብሎሽ፣ በቀኖና ወጥነትና በመዋቅር አንድነት መጽናት ሲቻል ነው፤ የትምህርት ትክክለኛነት የእምነትን ትክክለኛነት ያመጣል፤ በትምህርት የተከፋፈለች ወይም ሐሰተኛ ትምህርትን የማትቃወምና የማታወግዝ ቤተ ክርሰቲያን ውስጣዊ ጥንካሬዋና አንድነትዋ ይዳከማል፤ እንዲህ ባለ ሁኔታ ያለች ቤተ ክርስቲያን በቀኖና እና በመዋቅር አንድነት ሊኖራት አይችልም፤ከሐዋርያዊ ቅብብሎሹ ያፈነገጠና ቀኖናን የጣሰ አሠራር ሊስፋፋባት ይችላል፤ ሐሰተኛ ትምህርትን መከላከልና እውነተኛውን ትምህርት መጠበቅ የሐዋርያት ትልቅ ተልእኮ እንደሆነም አስቀድመን ተመልክተናል፤ የቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ትውፊትንና ሐዋርያዊ ቅብብሎሽን (Apostolic succession) መጠበቅ የቀኖና አንድነት መሠረት ይሆናል፤ የትምህርት፣ የእምነትና የቀኖና አንድነት ካለ የቤተ ክርስቲያን ሕጎች ወጥና ተፈጻሚነታቸው ከፍተኛ፣ የቤተ ክርስቲያን መዋቅርም አንድነቱ የጸና ይሆናል፤ ሐዋርያነት ይህ ነው! የዛሬ ዘመን አባቶች ኀላፊነትም ይህን ጠብቆ ማስጠበቅ ነው፡፡

በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙትን መፈወስ

ሕማምና ደዌ ልዩ ልዩ ዐይነት ነው፤ አካላዊ፣ ሥነ ልቡናዊ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ መልክ ያላቸው ልዩ ልዩ ደዌያት አሉ፤ደዌ ነፍስ በትምህርት፣ ደዌ ሥጋ ደግሞ በተአምራት ይርቃል፤ የነፍስ ደዌ ለሥጋ እንደሚተርፈው ሁሉ የነፍስ በትምህርተ ሃይማኖት መፈወስም የሥጋዊ ጤንነትን ያስገኛል፤ ደዌያት እርስ በእሳቸው የተሳሰሩ ናቸውና፤ አባቶች ሐኪሞች ናቸው፤ የሰው ልጆችም በኀጢአት በሽታ ከተያዙ ዘመናት ተቈጥረዋል፤ በሽታው እያስከተለ ያለው ሁለንተናዊ ሥቃይም ለአንድ መንፈሳዊ ሐኪም የተገለጠ ነው፡፡

እንግዲህ ሐኪሞች ምን ያህል ለሕዝቡ ሥቃይ ያዝናሉ? ለማከም ምን ያህል ይተጋሉ? ምን ያህል የሙያ ብቃትና ዝግጅት አላቸው? የሚሉት ጥያቄዎች አሁንም መልስ ይፈልጋሉ፤ ደዌ ነፍሱ በስብከተ ወንጌልና በትምህርተ ሃይማኖት ይርቃል ብለናል፤ መንፈሳዊ ጤንነቱ ለሥጋዊ ጤንነት መሠረት እንደሚሆነውም ዐይተናል፤ ከዚህ ቀጥሎም በጸሎትና በጸበል ሕሙማንን መርዳት፣ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት፣ የሕፃናት ማሳደጊያዎችንና የአረጋውያን መደገፊያ ተቋማትን መመሥረት፣ የጤና ተቋማትን መገንባትና ባለሙያዎችን በሳይንስና በመንፈሳዊ ሥነ ምግባር ማሰልጠንና ማብቃት፣ ወጣቶችን በእውነተኛ ትምህርተ ሃይማኖት ማሳደግ፣ የማኅበረሰብ ፈውስ መሠረት ናቸው፤ ዘርፈ ብዙ ሕማምና ሥቃይ እየደረሰበት ያለውን የሰውን ልጅ ለመርዳት ዘርፈ ብዙ ዐቅምና ችሎታ ያለው አገልጋይ ያስፈልጋል፡፡