የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ኅትመት አጀማመር ታሪካዊ ዳሰሳ፣

መግቢያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን፣ ትምህርቷን፣ ትውፊቷን፣ ታሪኳን እና መንፈሳዊና ልማታዊ አገልግሎቶችን ለተከታይ ምእመናኖቿ በኅትመት ሚዲያ ስታስተምር መቆየቷን ታሪክ ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኅትመት ሚዲያ ታሪክ ከ፲፱፻፴/1930ዎቹ ጀምሮ የሚጠቀስ ሲኾን በዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ የኅትመት ውጤቶች እየታተሙ ለምእመናን ይሠራጩ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምያ ለመጀመሪያ ጊዜ በትምህርተ ሃይማኖት ላይ ያተኮረ ‹‹ተክለ ሃይማኖት›› የተሠኘ ጋዜጣ ኅዳር ወር ፲፱፻፴፰/1938 ዓ.ም ታትሞ ለንባብ በቃ፡፡
በመቀጠልም በ፲፱፻፵/1940 ዓ.ም ‹‹ዜና ፡ ቤተ ፡ ክርስቲያን ፡ ዘኢትዮጵያ›› ጋዜጣ መታተም ጀመረ ሲኾን ዜና፣ የክብረ በዓላት ታሪክ፣ ወቅታዊ ዘገባዎች፣ እና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚያቀርብ ነበር፡፡ እነዚህ ጋዜጦች በየ፲፭/15 ቀኑ እየታተሙ ይሠራጩ የነበረ ሲኾን በሂደትም ወደ አንድ ጋዜጣነት ተጣምረው በየሳምንቱ እሑድ እንዲወጡ ተደርጎ ነበር፡፡

ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በቤተ ክርስቲያን ኅትመት ሚዲያዎች ዕድሜ ጠገብ እና በታሪክም ትልቅ ሥፍራ የሚይዝ ነው፡፡ ዜና ቤተ ክርስቲያን በረጅም ታሪኩ በርካታ ዓምዶችን በመክፈት የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮችን በስፋት ሲያስተናግድ የቆየና የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን ኾኖ የዘለቀ አንጋፋ የሕትመት ሚዲያ ነው፡፡

ጋዜጣው በዋነኛነት የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ሓላፊዎች የሚያከነወኗቸው ሥራዎችን ፣ ጉባኤዎችንና ስብሰባዎችን ፣ እንዲሁም በአህጉረ ስብከትም ኾነ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚከናወኑ ልማታዊና መንፈሳዊ እንቅስቀሴዎችን በመዘገብ ለአንባብያን ሲያደርስ የቆየ መንፈሳዊ ጋዜጣ ነው ፡፡

ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በሀገራችን እንደ ዛሬው የሚዲያ አማራጭ በሌለበት በዚያ ዘመን የቤተ ክርስቲያኒቱን መልካም ተግባር እየዘገበ በማስነበብ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ክብር ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ አገልግሎት ተደረሽነቷ ፣ በተለይም በድርቁ ዘመን ለተጎዱ ወገኖች ታደርገው የነበረውን ሰብአዊ ድጋፍ በዜና ሽፋን ከትቦ ለመላው ዓለም በማሳወቅ ረገድ ፣ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ያከናወነው ተግባር በወቅቱ ተወዳዳሪ አልባ ጋዜጣ እንዲኾን አስችሎታል ፡፡

ዓምዶች፣

ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በዋነኛነት የሚያተኩረው የዜና ሽፋን በመዘገብ ላይ ቢኾንም የጋዜጣው ወቅታዊ መልእክት ማስተላለፊያ በጥንቱ ርእሰ ነገር በኋላም ርእሰ አንቀጽ የተሰኘ ዓምድ ይዞ ዘልቋል፡፡
በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የሚሻሻልበትን ፣ የገቢ ምንጭ የሚስፋፋበትን ፣ መሪዎቿ የሚመረጡበትንና በተሐድሶ ጎዳና የምትራመድበትን መንገድ በማብራራት እና በማስረዳት የሚቀርቡና የቤተ ክርስቲያንን ታሪክም ኾነ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርት በጠቅላላውም መንፈሳዊውን ፍልስፍና ተተንትነውና ተመሥጥረው ለግንዛቤና ለምርምር የሚቀርቡ ጽሑፎች የሚሠፍርበት፡- ‹‹ተሐድሶ ፡ ዓምድ ፡ ለውይይት›› በኋላም ‹‹የተሐድሶ ፡ ዓምድ ፡ ለውይይትና ፡ ለትምህርት›› የተሰኘ ዓምድ እስከ ፲፱፻፹፩/1981 ዓ.ም ይዞ ዘልቋል፡፡

እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያትም የተለያዩ ዓምዶችን በመክፈት ጽሑፎችን ያሰፍር የነበረ ሲኾን፡-
‹‹ከመንፈሳዊ ፡ ዓለም›› ፣
‹‹የሴቶች ፡ ዓምድ›› ፣
‹‹ምን ፡ ይላሉ ? የአስተያየት ፡ ዓምድ›› ፣
‹‹ኢትዮጵያ ፡ በዘመነ ፡ ኦሪት ፡ የታሪክ ፡ ዓምድ›› ፣
‹‹የሊቃውንት ፡ ዓምድ›› ፣
‹‹ወጣቶችና ፡ ቤተ ፡ ክርስቲያን ፡ የወጣቶች ፡ ዓምድ›› ፣
‹‹ኢትዮጵያ ፡ በዘመነ ፡ ሐዲስ ፡ የታሪክ ፡ ዓምድ››
‹‹ትዝብትና ፡ ምክክር ፡ ዓምድ›› ፣ የመሳሰሉትን ዓምዶች በመክፈት ትምህርትንና ታሪክን ለትውልድ ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡

አዘጋጆች፣

ከጋዜጣው ምሥረታ ጀምሮ በርካታ በቤተ ክርስቲያንንም ኾነ በዘመናዊ ትምህርት አንቱ የተሠኙ አንጋፋ ሊቃውንት የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ፣ ምክትል አዘጋጅ እና የጽሑፍ አዘጋጅ ኾነው ተሳትፈውበታል፡፡
በምሳሌነት ለመጥቀስ ያክል፡-
በ፲፱፻፶/1950ዎቹ ዓ.ም አባ ተፈራ (ገብረ ሕይወት) መልሴ፣ ቀሲስ ክንፈ ገብርኤል አልታየ ናደው (ሊቀ ካህናት) ፣
በ፲፱፻፷/1960ዎቹ ደግሞ የጋዜጣው ዕድገት ጠባቂዎች በሚል ፩ኛ ቀሲስ ሰሎሞን ገብረ ሥላሴ ፣
፪ኛ አቶ ኢሳይያስ ዓለሜ፣
፫ኛ አለቃ ብርሃኑ መኰንን ፣
ዋና አዘጋጅ ፡- ቀሲስ ክንፈ ገብርኤል አልታየ (ሊቀ ካህናት) ቀጥሎም ፡-
፩ኛ ክቡር አቶ መኰንን ዘውዴ ፡- በም/ሚኒስቴር ማዕረግ የጠ/ቤተ ክህነት ም/ሥራ አስኪያጅ ፣
፪ኛ ዶክተር ዕጓለ ገብረ ዮሐንስ፣
፫ኛ አቶ ኢሳይያስ ዓለሜ ፡- የታሪክ፣ ድርሰትና ስብከት ክፍል ሹም ፣
ዋና አዘጋጅ ፡- ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ (መጋቤ ምስጢር) በመቀጠልም ፡-
፩ኛ ክቡር ንቡረ ዕድ ኤርምያስ ከበደ ፡- የጠ/ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ፪ኛ ዶክተር ዕጓለ ገብረ ዮሐንስ ፡- በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪ ፣ ፫ኛ ቀሲስ ሰሎሞን ገብረ ሥላሴ ፡- የታሪክ፣ ድርሰትና ስብከት ክፍል ተ/ሹም ፣ ዋና አዘጋጅ ፡- ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ (መጋቤ ምስጢር) ኾነው የጋዜጣውን ሕትመት ያስቀጠሉ ሲኾን ዋና አዘጋጅ ኃይለ ልዑል ወልደ ገሪማ፣ ተ/ዋና አዘጋጅ ይቁም ግዛው ፣ እንዲኹም ም/አዘጋጅ መልአከ ምሕረት ዓምደ ብርሃን ገብረ ጻድቅ የመሳሰሉት ሊቃውንት በመሪነት ተሳትፈውበታል፡፡

በተለይም መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ለረጅም ዓመታት የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ኾነው በማገልገል የጋዜጣው ምልክት እስከ መኾን የደረሱ ናቸው፡፡

ሥያሜና አርማ፣
የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ኅትመት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የጋዜጣው ስም እና አርማ (ሎጎ) በየጊዜው እየቀያየር መጥቷል፡፡

በጥንቱ፡- ዜና ፡ ቤተ ፡ ክርስቲያን ፡ ዘኢትዮጵያ ፡ በሚል ሥያሜ አርማው (ሎጎው) የእጅ መስቀል የነበረው ሲኾን በሂደትም አርማው (ሎጎው) የቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ፣ ሠናይ ፡ እገሪሆሙ ፡ ለእለ ፡ ይዜንው ፡ ሠናየ ፡ ዜና ፡ ሮሜ ፡ ም፡ ፲ ቍ ፲፬ የሚል መሪ ቃል በክብ ቅርፅ ተጽፎበት ይታተም ጀመረ፡፡

በመጨረሻም፡- አርማው (ሎጎ) የቤተ ክርስቲያን ጉልላት መስቀል ኾኖ ‹‹ሠናይ ፡ እገሪሆሙ ፡ ለእለ ፡ ይዜንው ፡ ሠናየ ፡ ዜና››፡፡ መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ፡፡ የሚል መሪ ቃል ይዞ በተለያየ ቀለም ማለትም በጥቁር ፣ በሰማያዊ ፣ በቀይ ቀለማት ዘመኑን በዋጀ ኅትመት (ወረቀት) ‹‹ይህ ጋዜጣችን የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን እምነትና ትምህርት ፣ ሥርዓትና ባሕል ፣ ታሪክና ዜና የሚያትም ስለሆነ ዜና ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ተሠየመ›› ፡፡ ተብሎ እየታተመ እስከ አሁን ዘልቋል ፡፡ጋዜጣው ዋጋ ተተምኖለት በሽያጭ ለአንባብያን የሚሠራጭ እንደ መኾኑ መጠን በጥንቱ 0.10 የነበረ ሲኾን በየዘመናቱ የዋጋ ክለሳ እየተደረገበት በአሁኑ ወቅት ዋጋ ብር 40 ለውጭ ሀገር እጥፍ ይኾናል በሚል እየታተመ ይገኛል ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልሣን ኾኖ የዘለቀው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በብዙ ውጣ ውረድ አልፎ በአሁኑ ሰዓት 66ኛ ዓመት ቁጥር 167 ደርሷል፡፡ እነሆ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የሚዘጋጀው ይህ አንጋፋ ጋዜጣ ይዘቱን እና ኅትመቱን በማሳደግ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ለትውልዱ ተደራሽ እንዲኾን እየሠራ ይገኛል፡፡

መምህር ማርቆስ ተበቃ ኬሬ
የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ

 

 

 

፫ኛው ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን የመክፈቻ መርሐ ግብር በየረር ጎሮ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል እጅግ ደስ በሚል መንፈሳዊ ድምቀት ተከናውኗል

“በወንጌል ኮነ ሕይወትነ – በወንጌል ሕይወታችን ሆነ” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው ፫ኛው ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን የመክፈቻ መርሐ ግብር ሚያዝያ ፲፰ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ አማካኝነት የተዘጋጀ ሲሆን
በዕለቱ የወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስና መካነ ጎልጎታ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ ሊቀ ሊቃውንት ሥሙር አላምረው “ወቦአ ከመ ይኅድር ምስሌሆሙ፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ” ሉቃ. ፳፬፥፳፱ የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ እንዲሁም የዘመነ ትንሣኤ ሦስተኛ ሳምንት በሆነችው በዚህች ሰንበት ዘመነ ፋሲካን የዋጀ ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲሆን፤
“ይህ የወንጌል ቀን መዘከር ያስፈለገውም በጨለማ ውስጥ ያለነውን ወደ ብርሃን ለማውጣት፣ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ ለመመለስና ሌሊት የሆነውን ሕይወታችንን ወደ ቀን በንስሐ ለመመለስ ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው አስተምረዋል።
በመቀጠልም የመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ጸሐፊ መ/ር ሽፈራው እንዳሻው መምርያው ያለበትን አሁናዊ ሁኔታና ይህ የስብከተ ወንጌል ቀን ክብረ በዓል ያስፈለገበት፣ ተደራሽነትና አላማ ምን እንደ ሆነ ገልጸው ማኅበረ ምእመናኑ የመምርያውን ድኅረ ገጽና በebs tv በየሣምንቱ የሚያቀርበውን እየተከታተሉ እንዲማሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

፫ኛው ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን መክፈቻና ማብሰሪያ መርሐ ግብር በተመረጡ 12 አብያተ ክርስቲያናት ተከናወነ!!

ሚያዝያ ፲፰ ቀን ፪፻፲፰ ዓ.ም.)
ስ/ወ/ሐ /ተልእኮ ሚዲያ /አ/አ/
የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በወንጌል ሕይወታችን ሆነ” በሚል መሪ ቃል ለ፫ኛ ጊዜ ሀገር አቀፍ በሆነ መልኩ በቅድስት ሥላሴ ዩንቨርስቲ ሁለገብ አዳራሽ ሚያዝያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም የሚያከብረውን “የስብከተ ወንጌል ቀን” የማብሰሪያ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት በተመረጡ አድባራትና ገዳማት በተመሳሳይ ሰዓት በስብከተ ወንጌል ጉባኤያት ተከብሮ ውሏል።
በዚህ ፫ኛው የስብከተ ወንጌል ቀን ማብሰሪያ በአዲስ አበባና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ከተማ ሥር በሚገኙ የተመረጡና ከፍተኛ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ በሚደረግባቸው 12 ገዳማትና አድባራት የተደረገ ሲሆን በዕለቱም በመምሪያው ጋባዥነትና የወንጌል መምህራንና ዘማርያን ተጋብዘው ሰፊ አገልግሎት ተሰጥቷል።
በየቦታው በተመደቡ አስተባባሪዎች አማካኝነት የስብከተ ወንጌል ቀንን ዓመታዊ ጉባኤ በማድረግ መዘከር ያስፈለገበት በጨለማ ውስጥ ያለነውን ወደ ብርሃን ለማውጣት፣ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ ለመመለስና ሌሊት የሆነውን ሕይወታችንን ወደ ቀን በንስሐ ለመመለስ
መሆኑ ተወስቷል።
በተጨማሪም መምሪያው ከሁሉም አህጉረ ስብከትና የትምህርት ተቋማት ጋር በመናበብና በመተባበር የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴን ለማጠናከር እያከናወነ ያለውን ተግባር ተስፋ የሚጣልበት መሆኑ በብዙዎች ምስክርነት አግኝቷል።
መርሐ ግብሩ ነገ ሰኞ ሚያዝያ ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፪፻፲፰ ዓ.ም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን፣ “ሀገር አቀፍ ዓመታዊ የወንጌል ቀን እና የምክክር ጉባኤ” በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሁለገብ መሰብሰቢያ አዳራሽ ከረፋዱ 2:30 ጀምሮ እንደሚካሄድ ታውቋል።

በበርካቶች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ድረ-ገጽ አገልግሎት ጀመረ

ሚያዚያ ፲፭ ቀን ፳፻፲ወ፰ዓ.ም.
ኢኦተቤክ ቤሕአልድ
አዲስአበባ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለዘመናት በመኳንንት፣ በወይዛይርትና በግለሰቦች አማካኝነት በውርስ፣ በኑዛዜና በስጦታ መልክ የተሰጧትንና በይዞታ አስከብራ ያቆየቻቸውን ቤቶች፣ ሕንፃዎችና ይዞታዎች ረጅም ዘመናት በድርጅቱ ባሳለፉ ቅን የድርጅቱ ሠራተኞች አእምሮ ከመያዝ ባሻገር የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲያውቁት በሚስችል መልኩ ተሰንዶ አለመቀመጡ ድርጅቱ በሥሩ የሚገኙ ደንበኞችን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚቸገር ከመሆኑም በላይ የሚባክኑ ይዞታዎች መኖራቸውን ይነገራል ።
ይህንን የተረዱት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪጅ ሊቀ ስዩማን እስክንድር ገብረክርስቶስ በድርጅቱ ሥር የሚተዳደሩ ቤቶች ፣ ሕንጻዎችና ይዞታዎች መላ ታሪካቸው ተመዝግቦና ተሰንዶ ለሚመለከታቸው አካላት ከማቅረብ ባሻገር በዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተጫኑ እንዲሰነዱ ለማድረግ ለድርጅቱ የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ክፍል ከማቋቋም ጀምሮ በመላው ዓለም ተዳራሽነቱን ለማስፋት የድርጅቱን ድረ-ገጽ ማበልጸግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ወደ ሥራ ተገብቷል።
በዚህ ሥራ ላይ ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ቆርጠው የተነሱ ቅን የቤተክርስቲያን ልጆችን በማስተባበር የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የሚል ድረ-ገጽ በልፅጎ በዛሬው እለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፤
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብጰት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንና የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣
ክቡር ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ የጠቅላይ ቤተክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ፤
ክቡር ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ባቱ የጠቅላይ ቤተክህነት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ፤ ክቡራን የጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎችና የየድርጅቶች ሥራ አስኪያጆች፤ ክቡራን እና ክቡራት የድርጅቱ ሠራተኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በታላቅ መንፈሳዊ ስነ-ስርዓት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
©የቤቶችና ሕንጻዎች ሚዲያ

በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በተደረገው ስምሪት በጎፋ ሳውላ ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና እና የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ተጠናቀቀ!!

ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም
ስ/ወ/ሐ/ተ ሚዲያ /አዲስ አበባ/
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ካለፈው የካቲት 26 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ በተመረጡ 32 አህጉረ ስብከት ሲያካሂድ የቆየው ስምሪት በአብዛኛው አህጉረ ስብከት እጅግ ስኬታማ በሆነ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን በቀሪዎቹ ደግሞ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ስምሪቱ በዋናነት ትኩረት ያደረገው ምዕመናንን በሃይማኖታቸው ለማጽናት፣ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ለማስፋፋትና ወንጌል በስፋት እንዲደርስ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ቀደም ሲል ተገልጿል።
ከሚያዝያ 12 እስከ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት ቀናትም በጎፋና ባስኬቶ ሳውላ በጋሞና አካባቢው አርባ ምንጭ አህጉረ ስብከቶች ለአህጉረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ ካህናትና ለ/ሰ/ት/ ቤት ወጣት ተወካዮች በመ/ሐ ቃለ ጽድቅድ አሰፋ እና በመ/ር ዘማርያም ጌጡ ፦ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ፣ዕቅበተ እምነት ፣የወንጌል አገልግሎታችንና የቤተክርስቲያን ታሪካዊ ጉዞ በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሥልጠና ተሰጥቷል።
በመጨረሻ በአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በተሰጠው መልእክት ስብከተ ወንጌልን ማጠናከር ሥራ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ባለ ድርሻ አካላት መሆኑን ተገልጾና መመሪያ ተላልፎ ሥልጠናው ተጠናቋል።
©የመረጃው ምንጭ ጎፋ ሳውላ ሀገረ ስብከት

ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ “በወንጌል ሕይወታችን ሆነ” በሚል ሕያው ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ “የስብከተ ወንጌል ቀን” እንዲሚያከብር ገለጸ!!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
«በወንጌል ኮነ ሕይወትን»
በወንጌል ሕይወታችን ሆነ
በመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ቤ/ክ/የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ «የስብከተ ወንጌል ቀንን» አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ፣
የስብከተ ወንጌል ቀን በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት መከበር ከተጀመረ ለ3ኛ ጊዜ ሲሆን በዚህ በጀት ዓመት ከሚያዝያ 18 ቀን እስከ ሚያዝያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የሚከናወን መርሐ ግብር ነው፡፡
በመሆኑም በመጀመሪያው ቀን ማለትም ሚያዝያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ በ8 ክ/ከተማ ቤተክህነት በተመረጡ 9 አድባራትና ገዳማት ማለትም፡-
1.በአራዳ ጉለሌ ጽ/አ/ቅ/ሩፋኤል ቤተክርቲያን
2.በየካ ክ/ከ/በየካ ደ/ሣ/ቅ/ሚካኤል ቤተክርቲያን
3.በአዲስ ከተማ በማህደረ ስብሐት ቅ/ልደታ ቤተክርቲያን
4.በኮልፌ ቀራንዮ በአየር ጤና አንቀጸ ብርሃን ኪዳነ ምሕረት ቤተክርቲያን
5.በለሚ ኩራ በጐሮ ደ/ም/ቅ/ገብርኤል ቤተክርቲያን
6.በቦሌ በገርጂ ደ/ገ/ቅ/ጊዮርጊስ ቤተክርቲያን
7.በአቃቂ ቃሊቲ መ/ብ/ቅ/ገብርኤል ቤተክርቲያን
8.በነፋስ ስልክ በጀሞ ፈ/ዮ/ቅ/ዮሐንስና ማርያም ቤተክርቲያን
9.በሸገር ሀገረ ስብከት አድባራት ማለትም
10.በዓለም ገና ደ/ም/ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል
11.በወይብላ ማ/መ/ቅ/ማርያምና ቅ/ሚካኤል ካቴድራል
12.በካዬ ፈጬ ደጉ ደ/ኃ/ቅ/ገብርኤል ቤተክርቲያን ልዩ መንፈሳዊ ጉባኤያትን በማዘጋጀት በታላላቅ መምህራን ዕለቱን በማስመልከት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥ ሲሆን በተጨማሪም በዘማሪያን አማካኝነት በዝማሬ እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ቀን ይሆናል፡፡
በሁለተኛው ቀን ሚያዝያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱሰ አባታችን ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ የቅዱስ ሊኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዓን አበው ሊቀነ ጳጳሳት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያውና የድርጅት የሥራ ኃላፊዎች ፤ የሁሉም አህጉረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍል ሐላፊዎች፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ዋና ክፍል ኃላፊና ም/ኃላፊ የ8ቱ ክ/ከ/ቤ/ክ/ሥራ አስኪያጆችና የስ/ወ/ኃላፊዎች የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎችና የስ/ወ/ኃላፊዎች እንዲሁም የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና የሀ/ስ/የስ/ወ/ ዋና ክፍልና ም/ኃላፊ የክ/ከተማ ቤ/ክ ሥራ አስኪያጆችና የስ/ወ/ኃላፊዎች እንዲሁ ተጋባዥ እንግዶችና የመምሪያው አጋሮች በተገኙበት የጥናት የውይይትና የምክክር መርሐ ግብር በልዩ ሁኔታ ለሙሉ ቀን የሚካሄድ ሲሆን በመጨረሻም የጋራ የአቋም መግለጫ በማውጣት መርሐ ግብሩ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡
በመሆኑም ይህን መልእክት በመከታተል ላይ የምትገኙ የሚመለከታችሁ ጥሪ የተላለፈላችሁ አካላት በተጠቀሱት ቀናትና ቦታ በሰዓቱ በመገኘት ተሳትፎ እንድታርጉና ለቅ/ቤ/ክ/የሚጠቅመውን ምክረ ሐሳባችሁን እንድትለግሱ በመምሪያው ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በተጨማሪም በቅድስት ቤተክርስቲያን የስ/ወ/ቀን ያልሆነ ዕለት ባይኖርም በተለየ ሁኔታ ቀኑን በማሰብ የስ/ወ/አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት ያመች ዘንድ በሁሉም አገልጋዮችና አማኞች ዘንድ የወንጌልን እውነት ለማስረፅ የተደረገ /የተዘጋጀ/ መርሐ ግብር ነው፡፡
በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ እያስገነዘብን በተለይም በሚዲያ ሥራ ላይ ተስማርታችሁ የምትገኙ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በጉባኤያቱ ቦታዎች ላይ በመገኘት የሚዲያ ሽፋን እንድትሰጡልንና የስ/ወ/ተደራሽነትን አጠናክረን እንድንቀጥል ጥራያችንን በድጋሜ በቤተክርስቲያን ስም እናስተላልፋልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ማኀበራዊ ጉዳይ

የኢትዮጵያ ቤት ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተዋጽኦ የሚመነጨው ከዐሥርቱ ሕግጋት እና ከስድሰተቱ ቃላተ ወንጌል ነው፡፡ ዐሠርቱ ቃላተ ኦሪት እና ስድስቱ ቃላተ ወንጌል በመተባበር ማኅበራዊ ሕግጋትን ያስተምራሉ፡፡

ማኅበራዊ ሕጎች በአንድ የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ የእረስ በእርስ ትስስር እና መተሳስብን ፍቅርንና አብሮ በሰላም የሚኖርበት አንድነትን የሚያጠብቁ መሠረቶች ናቸው፡፡ በመልካም መሠረት ላይ የሚኖር የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ በጊዜ ሂደት የራሱ የሆነ ባህል ይፈጥራል፡፡

ባህል ደግሞ የማንነቱ መገለጫ ከሌላ የኅብረተሰብ ክፍል የሚለይበት ኦርቶዶክሳዊ ማንነቱ የሚታወቅበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚከተሉትን ማኅበራዊ አሰተዋጽኦዎች አድርጋለች እያደረገችም ነው፡፡

ማኅበራዊ አስተዋጽኦ

፩∙ በበጎ አድራጎት አገልግሎት መሳተፍ

የበጎ አድራጎት መነሻው ቅድሳት መጻሕፍት ሲሆኑ በኅብረተሰብ መካከል መተሳሰብን እና ሰብአዊ ርህራሄን ከማጎልበት ባሻገር ለነፍስ ዋጋ የሚያሰጡ ትምህርቶችንም የያዙ ናቸው፡፡

ስለሆነም የመንፈስዊ አገልግሎት ዋጋ ከመስጠቱም ባሻገር በህብረተሰቡ ዘንድ የመተሳሰብና የሰብአዊ ርኅራኄ መንፈስ ለማዳበር እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ የህንንም ለማድረግ ጠቃሚ የሆኑት ስልቶች ሕዝቡን ማስተማር፤ ማደራጀት፤ ማስተባበር እና ተቋማትን መክፈት ናቸው፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መነሻውም ሃይማኖት ነው፡፡
እግዚአብሔር ራሱ ያለምንም ከፍያ /በጸጋ/ ፍጥረትን ሁሉ መልካም መሆናቸውን እያረጋገጠ ከመፍጠር የዕለት ተዕለት ፈላጎታቸውን እሰከ መስጠት ድረስ መሠረት ሆአኖል፡፡ አምላካቸውን የተከተሉ ሰዎችም ከአምላካቸው ተምረው ይህንኑ የበጎ ፋቃድ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡ አበ ብዙኀን አብርሃም ያለምንም ክፍያ መንገደኞችን ማብላቱንና ማጠጣቱ ዋና ማስረጃ ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅድስ ውስጥ የተዘረዘሩ ብዙ አገልግሎቶች በበጎ ፈቃድ የተከናወኑ ናቸው፡፡ ሰው የተቸገረ ወገኑን እንዲሁም እንግዶችን እየተቀበለ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በጉልበት ያለውን ለሌለው መርዳትና ማገዝ ይጠበቅበታል፡፡ ደጉ ሳምራዊ ተጎድቶ፣ ቆስሎ ያየውን ሰው፤ ማንም ሳያስገድደው በፈቃዱ አንስቶ፤ ቁስሉን በዘይት ቀብቶ፤ ለሚረዱት ሌሎች ሰዎች ገንዘብ ሰጥቶ፤ ተመልሶ እንደሚረዳው ቃል ገብቶ መሄዱ የሚታወስ የቤተ ክርስቲያን ተግባር ነው፡፡ አሁንም በቤተ ክርስቲያን ካህናት፤ ዲያቆናት፤ ምእመናን ብዙ ነገሮችን በበጎ ፈቃድ የሠራሉ፡፡
የሕፃናት ማሳደጊያ እና የአረጋውያን መጦሪያ ተቋማት መከፈት

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲየን ድሆችን የመርዳት የቆየ ባህል አላት፡፡ ምጽዋት ከመሥዋዕት ይበልጣል እንዲል፡፡ /ማቴ ፱፥፲፩፤ሆሴ ፮፥፮፤ አረጋዊ መንፈሳዊ/፡፡ ብራብ አበልችሁኝ፤ ብጠማ አጠጣችሁኝ፤ ብታረዝ አለበሳችሁኝ፤ የሚለው የምጽዋት ዋጋ በቅዱስ መጽሐፍ፣ በብዙ ገድላትና ድርሳናት ጎልቶ ስለተሰበከ ምጽዋትን ለተቸገሩ መስጠት በጠቅላላ የኢትዮጵያውያን ታላቅ መንፈሳዊ እሴት ነው፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ የማኅበረሰባችን ማኅበራዊ ዋስትና ይኸው ክርስቲያናዊ ባህላችን ነው፡፡ የቀድሞው፣ የዛሬውም የቆሎ ተማሪ የተማረው እና እየተማረ ያለው ቤተ ክርስቲያን በዘረጋችውና በሺሕ በሚቆጠሩ ዓመታት በዘለቀው በዚሁ ተቋም አካል ጽኑ ሃይማኖታዊ ባህል እንጂ በመንግሥት ወይም በሌሎች ድጋፍ አይደለም፡፡

በአጠቃለይ ቤተ ክርስቲያን ለተራቡት ቀለብ፣ ለታረዙት ልብስ፣ ለሕሙማን ፈውስ፣ ለአረጋውያን መጦሪያና ለእጓለምውታን ማሳደጊያ የሆነ ማኅበራዊ ዋስትና ለማረጋጥ በማስተባበር የተቻላትን ሁሉ ስታደርግ ቆይታለች፡፡

እነዚህ መኅበራዊ ተቋማት እንደዘመናችን ዓይነት መዋቅር ባይኖራቸውም በስንበቴና በጡት ልጅ እና በመሳሰሉት ማኅበራዊ መጠሪያዎች የሚታወቁ ማኅበራዊ ዋስትናዎች ነበሩ፡፡ ዘመናዊ የማኀበራዊ ዋስትና በኢትዮጵያ እሰከሚጀመርበት ድረስ ጧሪ የሌላቸው ሰዎች እና አሳዳጊ ያጡ ሕፃናት በዚህ መንገድ ሲረዱ ኑረዋል፡፡

እነዚህ ተቋማት ከተመሠረቱም በኋላ ቤተ ክትስቲያን አዲሶቹን ተቋማት መሥርታ የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎቷን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ በድርቅ ጊዜ ርዳታን በማስተባበር ስደተኞችን መርዳት ቤተ ክርስቲያን የተቸገሩትን መርዳት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተግባሯ በመሆኑ ተግባሩን ስታከናውነው ኖራለች፡፡ ዛሬም በዘመናዊ መልክ ልማትና ተራድኦ ኮሚሽን በማቋቋም ድንገተኛ አደጋ ሲከሰት እህል ዘይት እና ሌሎች ምግቦችን በማቅረብ የሰብአዊ እርዳታና መልሶ ማቋቋም ተግባር አከናውናለች እያከናወነችም ትገኛለች፡፡

መንፈሳዊ ማኀበራትን መደራጀት

ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ምሳሌ የሚሆኑ ዝክሮች፣ ሰንበቴዎችና ማኅበሮች ወዘተ በስፋት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የተቀደሱና ጠናካራ ትውፊቶች የበጎ አገልግሎት ለመሰጠት አመቺ ናቸው፡፡ በገጠሩ አካባቢ በስፋት ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በድንገት ሀብት ንብረቱ ቢቃጠልበት ርዳታ ያደርጉለታል፡፡ እንዲሁም ጧሪ ዘመድ ሳይኖረውና የሚሠራ ጉልበቱ ሲደክም ከቤታቸው በማስቀመጥ ተፈራርቀው የጦሩታል፡፡ ይህም ተግባር መጽሐፍ ቅድሳዊ ተግባር በመሆኑ በሕዝቡ አኗኗር ላይ በጎ ተጽዕኖ በማሳደሩ ለዚህ ድርጊት የቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ ክፍተኛ ነው ::

፪ መልካም ዜጋን በማፍራት

ሰው ሁሉ ለሚኖርባት ዓለም ነጻና ክቡር ዜጋ ነው፡፡ዜግነት የተፈጥሮ ሲሆን መልካም ዜግት ግን የመልም ጠባይና ምግባር ውጤት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛና ቅድስት በመሆኗ ዜጎች ሁሉ በሃይማኖትና በምግባር ለሀገራቸውና ለሰማያዊት ርስታቸው መልካምና ታማኝ እንዲሆኑ ከማስተማርና ከመምከር የተቆጠበችበት አፍታ ጊዜ የለም፡፡ ምንም እንኳን በሥልጣኔ ስም የሚመጡ ጉዳዮች የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቢፈታተኑትም ቤተክርስቲያን ግን ከጥንት ጀምሮ ልጆቿ በሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው የሀገርና የወገን አለኝታዎች እንዲሆኑ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርታለች፡፡

፫ የሥራ ባህልን በማዳበር

ሥራ የኑሮ መሠረት መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡የምትመራባቸው ቅዱሳት መጻሕፍትም የሥራን ጠቃሚነት በስፋት የሚተነትኑና የሥራን ባህል የሚያዳብሩ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአባታችን አዳም ገነትን ያበጃት ይጠብቃትም ዘንድ ሓላፊነትን ሰጥቶት ነበር፡፡ አዳም ከተሳሳተም በኋላ ጥሮ ግሮ በወዙ እንዲበላ፣ በስንፍና ተዘልሎ እንዳየቀመጥ፣ በወገኖቹ ላይ ጥገኛ ሆኖ እንዳይከብድባቸው ይልቁንም የድካሙን ፍሬ ቢመገብ መልካም እንደሚሆንለት ተነግሮታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት መሠረት በማድረግ ልጆቿ ዘወትር በሥራ የተጠመዱ እንዲሆኑ ይህ ካልሆነ ግን አእምሮአቸው የዲያብሎስ ተገዥ እንደሚሆን ታሰተምራለች፡፡ ከዚህ አኳያ ቤተ ክርስቲያን የሕዝቡን ሁለንተናዊ እድገት በማጽናት ለኢኮኖሚ ጤናማ እድገት፣ ለሕዝቡ ልማትና ደኅንነት መጠበቅ የበኩሏን ድረሻ እየተወጣች ነው፡፡

፬∙ሥነምግባርን በማሰተማር

ሥነምግባር የሚለው ቃል በሥራ ማማር፣ የሥራ መልካምነት ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ክርሰቲያኖች በጎ ሥራን እንዲሠሩ፣ ሰዎችን ያለምንም ልዩነት እንዲወዱ፣ የራስን ሰውነት ሕይወትና ክብር ከሚጎዱ ዲርጊቶች እንዲረቁ ሕይወታቸውን በቅድስና መንፈሳቸውን በንጽሕና እዲያዙ ታሰተምራለች፡፡ ከዚህም ትምህርቷ የተነሣ ምእመኖቿ በጎ ሕሊና እንዲኖራቸው፣ ከአንደበታቸው መልካም ቃል እንዲወጣ ንግግራቸው ሁሉ ከቁጣና ከትዕቢት የራቀ ጠብን ከመጫር ይልቅ ሰላምና እርቅ አንድነት እንዲያወርድ ወደ እግዚአብሔር መቅረብና ከእርሱ ጋር ሊያኖር የሚችል መልካም ሥራን መሥራትን የሚፈልጉ እንዲሆኑ አድረጋለች፤ እያደረገችም ነው፡፡ በማኅበራዊ ሕይወትም የሌላውን ድካምና ስሕተት ለቅመው ከመክሰስና ከመተቸት ይልቅ ባለማወቅ ያጠፋነውን ወደ ማወቅ አድርሰው ያርሙታል፣ የደከመውን ያበረቱታል፡፡ ክፉውን ወደ መልካም ይለውጡታል፡፡ ሕይወታቸው በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ሳይሆን በሰውም ፊት የተገለጠ ሰለሆነ በኅብረተሰቡም ፊት መልካም የሆነውን የፈጽማሉ፡፡ ‘’ስለምናገለግለው ስለዚህ ለጋስ ስጦታው ማነም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን በጌታ ፊት ብቻ ያይደለ  ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን እናስባለንና’’ ፡፡ በአጠቃለይ ቤተ ክርስቲያን ባላት የሥነ ምግባር ትምህርቷ ኅብረተሰቡ ለእግዚአብሔር እንዲሁም ለሀገሩና ለባልንጀራው ታማኝ እንዲሆንና ሓላፊነቱን፤ ተጠያቂነቱን በአግባቡ እንዲወጣ፤ ያለ እድልዎ ሥራን እንዲያከናውን በማሰተማር ሙስናን በመከላል ለሀገር ዕድገት አስተዋጽኦ ስታበረክት ቆይታለች እያበረከተችም ትገኛለች፡፡
ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን ፤ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን ፤መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ፡፡ በሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ መሠረት ቤተ ክርስቲያን የእንግዚአብሔር የሆነውን አሥራት በኩራት ለቤተክርሰቲያን ግብርን ደግሞ ለመንግሥት በወቅቱ እንዲከፍሉ ለማድረግ የማይናቅ ድርሻ ተወጥታለች፡፡ ይህን ማለት የሚያሰደፍረውም፡-
• አስተምህሮዋ አንዱ ለአንዱ እንዲታዘዝ፤ በትሕትና እንዲኖሩ ፈረሃ እግዚአብሔር እንዲኖረው ከሱስ ከባዕድ ተግባር ራሱን እንዲጠብቅ እና መልካም ዜጋ እንዲፈጠር የሚያደርግ በመሆኑ ነው፡፡
• ለረጅም ዘመናት በቄስ ትምህርት ቤት ትውልድን በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ ለሓላፊነት የሚበቃ እና ጠንካራ ዜጋ ለምድረግ ከሥር ኮትኩታ በማስደግ ያደረገችው እሰተዋኦም የሚዘነጋ አይደለም፡፡
• እሰከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የግብረ ገብ ትምህርት ከመደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን እንዲሰጥና በሥነ ምግባር የታነጹ ዜጎች እንዲኖሩ ያደረገችው አሰተዋኦ  ከፍተኛ ነው፡፡
በተለይም በዚህ በዘመነ ሉላዊነት /Globalization/ በተለያየ መልኩ የሥነ ምብናር ችግር እየገጠመው ያለውን ትውልድ፣ በተሻለ መለኩ ለመቅረጽ መንግሥት በኮሚሽን ደረጃ አቋቁም የሚታገልበትን ሙስና ከሥሩ የሚነቅል ሥራ ለመሥራት ቤት ክርስቲያን ካለባት ሓላፊነት አኳያ እያደረገችው ያለው ትውልድን በሥነ ምብባር የማነጽ ሥራ የሃይማኖቱ ግዴታ እንደሆነ ያመለክታል፡፡

፭∙ በጤና ጥበቃ ዘርፍ በመሳተፍ

ጤና ማለት የበሽታ አለመኖር ብቻ ሳይሆን የአንድ ሰው /ማኅበረሰብ/፣ አካላዊ /physical/፣ ሥነ ልቡናዊ /psychological/ ማኀበረሰባዊ /social/ አእምሮአዊ /mental/ እና ሃይማኖታዊ ደኅንነት / Spritual wellbeing /  ነው፡፡ አስከፊ በሆነ ድህነትና ችግር ውስጥ ላለ ኅብረተሰብ የጤና ችግር ትልቁን ቦታ የሚይዝ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ከሥጋ ሕመም ባሻገር የሚፈጥረው የአእምሮ ጭንቀት የአንድ ኀብረተሰብ ክፍልን ምርታማነትና ውጤታማነት እጅጉን ይጎዳል፡፡ ቤተ ክፍስቲያን የጤናውን ችግር ለመቅረፍ ያላትን አስተዋጽኦ የሚከተሉትን መዘርዘር/መጥቀስ ይቻላል፡፡
• መንፈሳዊ እና ሥጋዊ ደኀንነትን በመስጠት
• አዕምሮአዊ ጤንነት እንዲኖር በማድረግ
• ሥነ ልቡናዊ ጤንነት በመስጠት
• ዘመናዊ ጤና ተቋማት ማስፋፋትና የመሳሰሉትን

፮∙ በትምህርት ዘርፍ

ባለአእምሮ ሰው በደማዊነት አእምሮው እያዘገመ እንዳይኖር በትምህርት ድንቁርናን አርቆ፣ ክፉና ደጉን ለይቶ በዕውቀት ዓለም እንዲኖር ልቡናን የሚያጠራና የሚወለውል፣ ማኅበራዊ ነጻነትን የሚጎናጽፍ ዕውቀት ማግኘት ያስፈልገዋል፡፡ ሥጋዊና መንፈሳዊ ዕውቀት በሰው ልጆች አእምሮ ተቀርጾ ማህበራዊ፣ ባህላዊ እና ኢኮኖሚዊ ሕይወታቸውን ጥበብ በተሞላበት የአኗኗር ዘይቤ እንዲመሩ የዕውቀት በር መክፈቻ ቁልፍ ነው፡፡
የዚህም ዓላማ፣
ጊዜውን የሚዋጅ ንቃተ ኅሊናው የዳበረ ትውልድ ወይም ዜጋ ለመፍጠር ከቄስ ትምህርት ቤት እስከ ከፍተኛ ተቋማት ሥርዓተ ትምህርትን መቅረጽ እና መረጃ መሳሪያዎች ማዘጋጀት የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ ፊደልን ከነአገባቡ ይዛ የዓለም የራሳቸው ፊደላት ካሏቸው ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን መገለጫዋም የግእዝ ፊደላት ባለቤት መሆኗ ነው፡፡ በመሆኑም በተለያዩ ውጭ ሀገራት የግእዝ ትምህርት በፋኩልቲ ደረጃ መቋቋም ለጥናትና ምርምር ዓይነተኛ እገዛ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ከ1930ዎቹ በኋላ እንደ ትምህርት ሚኒስቴርነ ስታገለግል የቆየችው ቤተ ክርስቲያን የዘመናዊ ትምህርት ቤት በሀገራችን መስፋፋት ከጀመረበት ጊዜ በኋላም ቢሆን የራሷ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ልጆችና ወጣቶች በሥነ ምግባር እየታነጹ፤ ለሕዝብና ለመንግስት የሚያገለግል አገር ወዳድ ዜጎችን በማፍራት በዘማናዊው ትምህርት ድርሻዋን እየተወጣች ትገኛለች፡፡

፯. ታረክን እና ጥበብን በመመዝገብ

ለኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ መነሻው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ ብዙው ዓለም ገና የጽሕፈትን ጥበብ ገንዘብ ባላደረገበት ዘመን የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ከበግ፣ ከፍየልና ከልዩ ልዩ እንሰሳት ቆዳ ብራና ፍቀው፣ ቀለማትን በጥብጠው ብርዕ ቀርጸው የኢትዮጵያ ብሎም የውጭ ሀገራትን ታሪክ በመመዝገብ ለጥናትና ምርምር መነሻ ሆነዋል ማለት ይቻላል፡፡

፰.  የባህል አስተዋጽኦ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲን መሰረቷ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የምትሰብከውም ሃይማኖትን ከትውፊት፣ ትውፊትን ከሥርዓት፣ ሥዓትን ከባህል ጋር በማቀናጅት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲን በሥነ ምግባር ትምህርቷ በኢትዮፕያ ውስጥ ለሚደረግ መልካም ባህሎች መነሻ ናት፡፡ በዚህ መሰረት ቤተ ክርስቲያን ያላትን ባህላዊ አስተዋ    ጽኦ ለመመልከት ያህል እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡፡
• በአንድ ማዕድ የመመገብ ባህል /የአመጋገብ ሥርዓት/፣
• የአነጋገር ሥርዓት፣
• የእንግዳ ተቀባይነት ባህል፣
• አለባበስ/ ነጭ ልብስ፣ ወንድ የወንድን ሴት የሴት ወ.ዘ.ተ/፣
• ጋብቻን የማክበር ባህል
• የጀግንነት እና የሀገር ፍቅር ባህል፣
• ተከባበሮ የመኖር  እና የአብሮነት ባህል፣ ወዘተ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

መንፈሳዊ ትምህርት (ሥልጠና)

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በቅዳሜ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ /በመጀመሪያ እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን ከፈጠረ በኋላ በመጀመሪያው የሥነ ፍጥረት ቀን ቅዱሳን መላዕክትን ፈጥሮ ተሰወረባቸው መላዕክትም መኑ ፈጠርነ ወእምአይቴ መጻዕነ ማን ፈጠረን ከየትስ መጣን /ተገኘን / የሚለውን የምርምር ሐሳብ አንስተው ሲወያዩ አላዋቂ ዲያብሎስ ሁሉም ቅዱሳን መላዕክት በቦታ አቃማመጥ ከእርሱ በታች ሁነው ስለአያቸው እኔ ፈጠርኳችሁ አላቸው ቅዱሳን መላዕክትም በቦታ ከሆነ እኛ ከእኛ በታች የሆኑትን አልፈጠርንም በማለት የመመራመር ሥራቸውን ቀጥለው በአሉበት ሰዓት ሊቀ መላዕክት ቅ/ገብርኤል “ንቁም በበህላዌነ እስከ ንረክበ ለአምላክነ” ፈጣሪያችን አምላካችን እግዚአብሔርን እስከ ምናገኘው ድረስ ሁላችንም በተፈጠርንበት ሕልውና ፀንተን ልንኖር ይገባናል የሚለውን ትምህርት ለቅዱሳን መላዕክት በመንገሩ /በማስተማሩ/ የማረጋጊያ፣ የማጽናኛ ፣ ትምህርት ሰጥቷል ይህንን የማረጋጊያ ትምህርት በአግባቡና በጥልቀት ሰንመለከተው የመማር ማስተማር ሥራ የተጀመረበት ወቅት መሆኖን ቅዱሳን መጻሕፍትና ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን ያረጋግጡልናል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ የሰው ዘር የሆነውን አዳምን በመልኩና በምሳሌው ከፈጠረ በኋላ ባለግዕዛን አእምሮ /ነጻ አእምሮ/ ሰጥቶ የማወቅ የመመራመር ጥበብንና እውቀትን ከመሰጠቱም ሌላ የሚበሉና የማይበሉ ዕጽዋትን ነግሮና አስተምሮ የማይበላው የተከላከለውን በልቶ ቢገኝ የሞት ሞት እደሚሞት አምላካችን በሰው ዘር ታሪክ የመፍጠርና የማስተማር ሥራውን በአዳም እንደ ጀመረ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡

የአዳም ሦስተኛ ዙር የሆነውና እግዚአብሔርን በማገልገል የሚታወቀው ደገኛው ሰው ሄኖስ በሰማይ ላይ የተጻፈ ጽሁፍን አይቶና ተመልክቶ ዛሬ ለብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት መጻፍና በዓለም ለሚገኙ ልዩ መጻሕፍትና የምርምር ሥራዎች መከናወን በዚያን ጊዜ ለነቢዩ ሄኖስ በደፍደፈ ሰማይ ተገልጦ የታየው ጽሁፍ እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ምንም እንኳን ያ ዘመን ትምህርቱም ሆነ ታሪኩ የሚነገረውና የሚተረክው ጽሁፍ የማይከናወንበት የሕገ ልቡና ዘመን ቢሆንም የአጻጻፍ ሁኔታ /ጽሁፍ/ የተገለጠበት ጊዜና ወቅት ነበርና የጽሁፍ ትምህርት የተጀመረበት እንደሆነ ሊቃውንት በምርምር ሥራቸው ዘግበውት ይገኛል፡፡

ሰዎች በምድር ላይ እግዚአብሔርን መበደል በጀመሩበት ወቅት ጻድቁንና ንጹህ ሕሊና ያለውን ኖኅን አስነስቶ የበደሉ ሰዎችን አስተማሪ ትምህርቱን አልቀበል በማለት በደላቸው እየበዛ በሄደ ቁትር ኖኅና ልጆቹ የሚድኑበትን የጥበብና የእምነት ትምህርት ኖኅ ተምሮና ተመራምሮ ከእግዚአብሔር ቁጣና መቅሰፍት ራሱንና ቤተሰቡን አዳነ ከጥፋት ውሃ በሰላም ኖህ በተማረው ትምህርት ለእግዚአብሄር መስዋዕት አቀረበ የእግዚአብሔርን አዳኝነት ለልጆቹና ለቤተሰቡ አስተማሪ ከእግዚአብሔርም በረከትን አገኘ፡፡

የእውነተኛው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ የሆነው አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሲመቱ ለመልከ ጼዴቅ ተብሎ የተነገረለት አባት እናት የትውልድም ዘመን የሌለው ለዘመኑ ጥንት ለሕይወቱም ፍፃሜ የሌለው መልከ ጼዴቅ ከእግዚአብሔር የተማረውንና በተሰጠው የሥልጣነ ካህናት ማዕረግ አብርሃምን እንዳሰተማረው እንደባረከውና አብርሃም ከአገኘው ሀብት ሁሉ ከአሥር አንዱን /አስራቱን/ ለእግዚአብሔር መስጠት እንዳለበት የነገረውና የሐዲስ ኪዳን መስዋዕት ምሳሌውን አብርሃም ያወቀውና የተማረው ከመልከ ጼዲቅ እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍና መተርጎማን ሊቃውንት ይነግሩናል፡፡

አበ ብዙኃን ተብሎ የተነገረለት አብርሃምም የእግዚአብሔርን ህልውና /መኖር/ ተመራምሮ የአወቀ ከመልከ ጼዲቅና ከእግዚአብሔር በአገኘው ትምህርትና በረከት ለልጆቹና ለተከታዮቹ ነገረ አስተማረ፡፡
ከዚህ በላይ ያለው አጭር ታሪክ ስንመለከት ሕገ ኦሪት መጻፍ እስከ ጀመረበት ጊዜ ብዙ ቅዱሳን አበው ከእግዚአብሔር በአገኙት ጥበብና ዕውቀት ተምረውና ተመራምረው ከመዝ ይቤ እግዚአብሔር እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እያሉ ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር፡፡

እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልኩ ከእርሱ በስተቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ የአስተማሩበትና ዘመኑም ሕግ ያልተጻፈበት በሕገ ልቡና እግዚአብሔርን አውቀውና አዳኝነቱንም ተረድተው ያአስተማሩበት እንደሆነ የታሪክ ሂደት ያስረዳናል፡፡ ይህን ታሪክ ስንመለከት በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን ዘመን ለተነሱት ታላላቅ ቅዱሳን ነቢያት ሐዋርያት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የትምህርትና የምርምር ሥራዎቻቸው ዋና መነሻ ታሪክ እንዲሆን ተረድተናል /እንረዳለን/፡፡

የመንፈሳዊ ትምህርት አሰጣጥ

በሕገ ኦሪት

እግዚአብሔር አምላክ ለሙሴ የእምነት ሕግንና ሥርዓትን አስተምሮ ሰጠው ለልጆቹም ሆነ ለሕዝበ እስራኤል የሚያስተምርበትን የሕግ መጽሐፍ ጽፎ እንዲይዘውና እንዲያስተምር ታዘዘ በተለይም በዘዳግም ምዕራፍ 6፡4-9 ያለውን ኃይለ ቃል ስንመለከተው የመማር ማስተማር ሥራና ተግባር በቃልም በጽሁፍም የተጀመረበትና የተከናወነበት ጊዜ እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ ቃሉም “እስራኤል ሆይ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም  ዛሬ አንተን የማዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ፡፡

ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም ስትነሳም ተጫወተው፣ በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው በአይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው”፡፡ በማለት እግዚአብሔር አምላክ ለሙሴ እንዳሰተማረውና ሙሴም የተማረውን ትምህርትና የተቀበለውን ሕገ ኦሪት ለልጆቹና ለሕዝብ እስራኤል በትጋት ፣ በቅንነትና ፍጽም በሆነ ፍቅር አስተማረ 5ቱን የሙሴ መጽሐፍ ተብለው የሚነገርላቸውን ሕገ ኦሪትም ኦሪትም ለትውልድ በማስተላለፍ እስከ አሁን ድረስ እንማርበታለን ዘመኑም 3500 ዓመት እንደሆነው ከቅዱስ መጽሐፍ ታሪክ እንረዳለን /ከሙሴ እስከ አሁን ያለው ዘመን)
እግዚአብሔር አምላክ ክህነትን ከምስፍና ጋር አጣምሮ የያዘውን ሙሴን የሚረዳና የክህነት አገልግሎትንም ከምስፍና ለመለየት ስለፈለገ ወንድሙን አሮንን ካህን አድርጎ እንዲሾመው ካህኑ አሮንንም የሙሴ አፈ ጉባኤ /አፈ መምህር/ ሁኖ የክህነት አገልግሎትን እርሱና ልጆቹ ተሾመ የማስተማር ሥራ ወይም ቀጥሎ አስተማሪ /ዘጸ 28፡1 ፣ 29፡1/ የአሮንን ፈለግ በመከተል ሌዋውያኑ የማስተማር ስራቸውን አስተምረዋል፡፡

የክህነት አገልግሎትንም ሰጥተዋል፡፡ ሌላው በዘመነ መሳፍንትና ዘመነ ንግስታት የተነሱት ካህናትና ነቢያት ስለእግዚአብሔር ሕልውና ሳያፍሩና ሳይፈሩ አስተምረዋል፡፡ ሕዝቡ በምክረ ካህን ፣ በፍቃደ ካህን እንዲጓዝ ምክርና ተግሳጽ ሰጥተዋል ከእነዚህም በዋናነት የሚጠቀሱት ኢያሱ፣ ዳዊት፣ ሰሎሞን፣ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል ዳንኤልና ሌሎችም ነቢያት የማስተማር ሥራቸውን በብቃትና በንቃት ተወጥተዋል ታላቁንና የመጨረሻውን የክብር አክሊል ከፈጣሪያቸው ተሸልመዋል፡፡

የመንፈሳዊ ትምህርት አሰጣጥ በአዲስ ኪዳን

በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል የነበረው መጥምቀ መለኮት ቅድስ ዮሐንስ “ነስሑ ወእመኑ እስመ ቀርብት ይእቲ መንግስተ ሰማት” መንግስት ሰማት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ያስተምር እንደነበረ የንስሐ ጥምቀትም ያጠምቅ እደነበረ ብዙ ተከታይ ተማሪዎችም እንደነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ይነግረናል፡፡ /ማቲ 3፡2 ፣11፡2/

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው 12 ዓመት በሆነው ጊዜ በኢየሩሳሌም ከበነበሩ መምህራን መካከል ተገኝቶ እንደተማረና ለመምህራኑም ልዩ ልዩ ጥያቄ እንዳቀረበላቸው በመልስና ከቃሉ ንግግር ማማር የተነሳ የሰሙትና ይገረሙ እንደነበር ከቅዱስ ቃሉ መረዳት ይቻላል /ሉቃ 2፡46/

ከዚህም በተጨማሪ ጌታችን መድኃኔታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ይግባውና እንደ አምላክነቱ ሳይሆን እንደ ሰውነቱ ቀስ በቀስ በሚያድግበት ወቅት ዕድሜው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ ትምህርት ቤት ገብቶ እንደተማረ መምህራኑ በሚያስተምሩት ጊዜ ልዩ ልዩ ጥያቄ ያቀርብ እደነበርና የተግባረ ዕድ ሥራንም መምህራኑን ይረዳቸው እንደነበር በተአምረ ኢየሱስ ተጠቅሶ /ተጽፎ/ ይገኛል፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ በመዋዕለ ሥጋዌው 30 ዓመት ሲሞላው ተጠምቆ ገዳመ ቆሮንጦስ ገብቶ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ የማስተማር ሥራውን ጀመረ ደቀ መዛሙርቱንም ከተለያዩ ተግባረ ሥራ ለወንጌል አገልግሎት መረጠ /ማሬ 4፡17/ 12ቱን ሐዋርያት ደቀ መዛሙርት መርጦና አስተምሮ ሙሉ ሥልጣንም ሰጥቶ በዓለም ዙሪያ ወንጌልን እንዲያስተምሩ ከተሟላ የእምነት ትጥቅ ጋር ተላኩ /ማቴ 10፡1-42/
በመቀጠልም በድንቁርና ዓለም ውስጥ ያለው የሰው ዘር ያውቅ ይረዳና ይማር ዘንድ ሌሎችን ሰባ መምህራንን መርጦ አሰልጥኖና ባለሙሉ ሥልጣን አድርጎ አልጫ የሆነውን ዓለም በትምህርት ጨው እንዲያጣፍጡ ሾማቸው /ሉቃስ 10፡1/

በአጠቃላይ በ3 ዓመት ከ3ወር ውስጥ ዓለምን ዞረው የሚስተምሩ ደቀ መዛሙርትን መርጦና ሹሞከመላኩም ሌላ የ5 ገበያ ከ5,000 ሕዝብ በላይ ይከተለው እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል ከዚህ ላይ መርዳትና መናገር የምንችለው የመማር ማስተማር ሥራ ቀደም ሲል የነበሩት መምህራን ነቢያት የጀመሩትና ያስተማሩ ቢሆንም የህግና የሥርዓት ጀማሪውና ፈጸሜው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመማርንና የማስተማርን ጥቅም የሰው ልጅ አውቆና ተረድቶ እንዲማር ራሱ ለሰው ልጆች አርአያ ምሳሌ ለመሆን የጥበብና የዕውቀት ምንጭና ፈጣሪ ቢሆንም እንደሰውነቱ ትምህርት ቤት ገብቶ ተምሮአል አስተምሮአል ባለሙሉ ሥልጣን አድርጎ ሐዋርያትን ሰባ ሁለቱን ደቀ መዘሙርት መርጦ የሰማይና የምድር ስልጣን ሰጥቶ ስለላካቸው ዓለምን በ4 ማዕዘን ዙረው አስተማሩ።

የነቢያትንና የሐዋርያትን ፈለግ በመከተል ብዙዎች መምህራን ሊቀውተ ቤተ ክርስቲያን የማስተማር ጠቀሜታን አውቀውና ተረድተው ዋጋቸው ከልዑል እግዚአብሔር ለመቀበል ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው አስተምረዋል መክረዋል ፡፡

ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ የመንፈሳዊው የትምህርት አሰጣጥ እንዴት እንደነበር በአጭሩ ስንመለከተው በቀዳማዊው ምንሊክ ዘመን /በ900 ዓመተ ዓለም አካባቢ/ ጽላተ ሙሴና ሰባው ለቃውንት /የብሉይ ኪዳን መምህራን/ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ሀገራችን ኢትዮጵያን በፈጣሪ  የምታምንና ሕገ እግዚአብሔርን የምታስተምር እደነበረች ታሪክ ቢነግረንም የሕገ ኦሪት ትምህርት መስፋፋትና መጠናከር የጀመረው ከቀዳማዊ ምንሊክ ከታቦተ ሙሴ መግባትና በሊቀ ካህናቱ አዛርያስ መሪነት የሰባው ሊቃውንቱ  ወደ ሀገራች መምጣት ከእነርሱም ጋር የመጡት መጻህፍተ ብሉያት መገኘት ሲሆን የክርስቶስንና የሐዋርትን አስተምሮ ተከትሎ በ34 ዓ.ም ጥቅምት ወደ ሀገራችን በኢትዮጵያው ጀንደረባ አማካኝነት መግባት /የሐ.ሥራ 8፡26-40 / በመቀጠልም በ4ኛው ክፍለ ዘመን በአብርሃና አጽብሃ ዘመነ መንግስት በከሳቴ ብርሃን አባ ሰላማ አማካኝነት የሀዲስ ኪዳን እምነትና ሥርዓትን ተቀብላ ዲያቆናትን፤ቀሳውስትን፤ መምህራን፤ በማስተማርና ሥልጣነ ክህነትን በመስጠት ቤተ ክርስቲያን እንድትሰፉና እንድትስፋፋ ሆነች፡፡

አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትም እንዲሠሩ ሆነ በመቀጠልም በ5ኛ ክፍለ ዘመን የ9ኑ ቅዱሳን ወደ ሀገራችን መግባትና ገዳማትን መመሥረትና ማስተማር የቤተ ክርስቲያን መጠናከሪያ የወንጌል ማስተማር ሥራ በመስፋፋት ላይ እደነበር ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለመረዳት ይቻላል፡፡

ጠቅለል ለማድረግ የትምህርትና የሌሎችንም የሥራ ዘር ማዕከል የነበረችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአሠራር መላላት፣ የተጠናከረ የአደረጃጀት ሥልትና ዘዴ ያለመኖር፣ የእኔነት ስሜትና ፈላጎት ያለመኖር ይሁን ወይም ባልታወቀ ምክንያት የመንፈስ ቅዱስ ብርሃን በልዩ መልክ ያበራላትና የተቀደሰ ተግባሯንና ዓላማዋን በልዩ የመንፈስ ቅዱስ ምርጫ ታከናውንና ታስተምር የነበረችው ቤተ ክርስቲያን የመማር ማስተማሩ ሥራ ቀዝቅዞ ይታያልና በከፍተኛ ሁኔታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት አደረጃጀቱም ሆነ አሠራሩ የቤተ ክርስቲኒቱ አስተምህሮ እንዳለ ሆኖ ዘመኑ በሚፈቅደው መልኩ ለሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ ሠራተኞች የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠትና ሠራተኞችን በማብቃት እንደ አባቶቻችን ለቤተ ክስቲያን ብዙ ሥራ መስራት ይቻላል ፡፡

የቅዱሳን ሕይወት(ክብረ ቅዱሳን)

በሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረአማኑኤል

ቅድስና በምንልበት ጊዜ ቅድስናን በሁለት ከፍሎ ማየት ተገቢ ይሆናል፤ ይኸውም፡-
• ሀ. የባሕርይ ቅድስና ፤
• ለ. የጸጋ ቅድስና ማለት ሲሆን የባሕርይ ቅድስና በምንልበት ጊዜ ለእግዚአብሔር ብቻ የምንገልጸው ልዩ አገላለጽ ነው፡፡ የጸጋ ቅድስና በምንልበት ጊዜ ደግሞ ሰማያውያን መላዕክትና ምድራውያን ሰዎች ራሳቸውን ለቅድስና አዘጋጅተው ሲገኙ ቅድስናውን የሚያገኙት የቅድስና ባለቤት ከሆነው ከእግዚአብሔር የሚገኝ ልዩ ስጦታ ነው፡፡ በተለይ ምድራውያን ሰዎች በሃይማኖት ጸንተው፤ በበጎ ሥራ ተቃኝተው በቅን ልቡና አግዚአብሔርን ሲያገለግሉ ቅዱሳን ይሆናሉ፤ ቅዱሳንም ይባላሉ፡፡ ‹‹እኔ አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ›› ተብሏልና፡፡ (ዘሌ 19፡2)

የኢትዮጽያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን በምንልበትም ጊዜ ብሔራዉያን ቅዱሳንንና ከዉጪ ወደ ኢትዮጽያ መጥተዉ ያበረከቱትን ከፍተኛ መንፈሳዊ አገልግሎት ከግምት ዉስጥ በማስገባት የኢትዮጽያ ቤተ ክርስቲያን ቅድስናን ሰጥታ፣ በየስማቸዉ ቤተ ክርስቲያን አንፃ፣ ፅላት ቀርጻ፣ ገዳም ገድማ ያከበረቻቸዉና የምታስከብራቸዉ ቅዱሳን በርካታዎች ሲሆኑ በዚህ ፅሁፍ አጠቃሎ መግለጽ ባይቻልም ለግንዛቤ ያህል የአገር ዉስጥና የዉጭ ሀገር ቅዱሳን በማለት በሁለት ዐበይት ክፍሎች ከፍሎ መግለፅ ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ ከላይ እንደተገለፀዉ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸዉን ፈፅመዉ ዘለዓለማዊ ዕረፍታቸዉን በኢትዮጽያ ምድር በማድረጋቸዉ ብሔረ ሙላዳታቸዉን ለመግለፅ ያህል ታስቦ የተገለፀ ጽሑፍ መሆኑ ከግንዛቤ ዉስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡

የኢትዮጽያን የሁለት ሺህ ዘመን ቅዱሳን ታሪክ በዚህ ጽሑፍ አምልቶና አስፍቶ መግለፅ ባይቻልም ዝርዝር ታሪኩን ለታሪክ ጸሐፊዎች በመተዉ የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ አለኝታ የሆኑትን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ዐበይት መምህራንን፣ እንደዚሁም በቤተ ክርስቲያናችን ስም በየአረፍተ ዘመናቱ መላ ሕይወታቸዉን የሰዉ ዘር የሆነዉን ሁሉ በሥራና በጸሎት በማገልገል፣ እግዚአብሔርን በማመስገን ሕይወታቸዉን መሥዋዕት አድርገዉ ያቀረቡትንና እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነዉን ገድል የፈጸሙትን ሁሉ ቤተክርስቲያናችን የጾታ ልዩነትን ሳታደርግ በገድላቸዉ ጽናትና በትሩፋታቸዉ ብዛት ብፁዕና ብፅዕት፣ ቅዱስና ቅድስት ሊያሰኝ ከሚችል የብፅዕናና ቅድስና ማዕረግ የደረሱ መሆናቸዉን በማረጋገጥና በስማቸዉም ቤተክርስቲያን እንዲታነጽ፣ ገዳም እንዲገደም፣ ደብር እንዲደበር፣ ገድልና ድርሳን እንዲጻፍላቸዉ፣ ወርሃዊና ዐመታዊ በዓላቸዉ እንዲታሰብና እንዲዘከር በማድረግ በቅዱስነት ያወቀቻቸዉንና ያሳወቀቻቸዉን ኢትዮጰያዉያንና ብሔረሙላዳታቸዉ ከኢትዮጰያ ዉጪ የሆኑትን ቅዱሳንና ቅዱሳትን ስም ዝረዝር በከፊልም ቢሆን እንደሚከተለዉ ለመግለጽ እንሞክራለን፡፡

ኢትዮጰያዉያን ቅዱሳንና ቅዱሳት

1. ሕጽዋ ለሕንደኬ ንግስተ ኢትዮጰያ

የክርስትና እምነት ወደ ኢትዮጰያ የገባዉ ወይም ኢትዮጰያና የክርስትና ሐይማኖት የተዋወቁት ሐዋርያዉ ቅዱስ ሉቃስ በግብረ ሐዋርያት 8፡26-40 ላይ እንደመዘገበው ጃንደረባው እንደ ብሉይ ኪዳን ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዞ ሥርዓተ አምልኮትን ፈጽሞ በፍኖተ ጋዛ ሐዋርያው ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ባጠመቀው ጊዜ ነው፡፡ ዘመኑም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ34 ዓ.ም. ነው፡፡
‹‹የቤተ ክርስቲያን አባት›› እየተባለ የሚጠራው አውሳብዮስ የወንጌላዊው ሉቃስን ግብረ ሐዋርያት መሠረት አድረጎ ‹‹ሕጽው ለወገኖቹ ሆነ የኢትዮጵያ ሐዋርያ እሱ ነው›› በማለት ጽፎአል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ገጽ 18 ላይ ይመለከቱ፡፡

2. ቅዱሳን ነገስታት አብርሃ ወአጽብሓ

አብርሃ ወአጽብሓ የተሰኙ ቅዱሳን ነገስታት(ወንድማማቾች) እንደ አንድ ልብ መካሪ፤ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን ፍጹም በሆነ ስምምነት ለ15 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን በጋራ ከአስተዳደሩ በኋላ እንደ አበው ሐዋርያት ዕጣ ተጣጥለው አብርሃ በአክሱም፤ አጽብሓ በሸዋ መናገሻ ከተማውን ኤረር በማድረግ መንበረ መንግሥታቸውን ዘርግተው እየተመካከሩ ኢትዮጵያን በማስተዳደራቸው፤ ለሀገሪቱና ለቤተ ክርስቲያን ያደረጉትን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሁለቱ ወንድማማች ነገሥታት የቅድስና ማዕረግ ሰጥታቸዋለች፡፡ በስማቸውም ቤተ ክርስቲያን አንጻለች፡፡ ወርኀዊና ዓመታዊ በዓላቸውንም በየዓመቱ ጥቅምት 4 ቀን እንዲታሰብና እንዲከበርም አድርጋለች፡፡ (ታሪከ ነገሥት አብርሓ ወአጽብሓ ከመምህር ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ 1989 ዓ.ም አዲስ አበባ)

3. አፄ ካሌብ

ከአብርሃና አጽብሓ ቀጥሎ ከተነሡት ቅዱሳን ነገሥታት ክርስትናን በማስፋፋትና በመንከባከብ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያደረጉት ከ485-515 ዓ.ም. የነበሩት አፄ ካሌብ ናቸው፡፡
አፄ ካሌብ ስለ ክርስትና መስፋፋት፤ ስለ ክርስቲያኖች አንድነት ብዙ ተጋድሎን ከተጋደሉና ከአሳለፉ በኋላ መንግሥታአውን ለልጃቸው ለአፄ ገብረ መስቀል አስረክበው፤ መንነው፤ ልብሰ ምንኩስናን ለብሰው ከአክሱም ወደ ሰሜን ምሠራቅ በሚገኘው በአባ ጰንጠሌዎን ገዳም በሚገኘው ዋሻ የምናኔ ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከዚህም ጋር ቤተ መንግሥታቸውን ለቀው በመነኑበት ሰዓት እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነውን ማለትም የነገሡበትን ዘውድ ወደ ጌታ መቃብር ጎልጎታ ልከው በምናኔ 12 ዓመታት ከተጋደሉ በኋላ በ536 ዓ.ም. ግንቦት 20 ቀን አርፈዋል፡፡ አፄ ካሌብ በምንኩስናና በምናኔ ሕይወት የቅዱሳንን አሠረ ጽድቅ ፈጽመው ያለፉ ደገኛ ንጉሥ ስለነበሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቁጥራቸው ከቅዱሳን ነው፡፡ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ 1974 ዓ.ም.)

4. አባ ዮሐኒ

አባ ዮሐኒ ብሔረ ሙላዳችው በክልል ትግራይ፤ በተንቤን ልዩ ስሙ ሀገረ ሰላም ከተባለው ቀበሌ ሲሆን የነበሩበትም ዘመን በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በቆላ ተንቤን ደብረ አንሣ(ዓሣ) ከተባለው በረሓ በጾምና በጸሎት ተወስነው ይኖሩ ከነበሩት ከአባ አሞኒ ጋር እንደ ኖሩ፤ ዕድገታቸውም በእናት ጡት ሳይሆን ቶራ እያጠባች እንዳሳደገቻቸው በገድለ አቡነ ዮሐኒ ተመዝግቧል፡፡ ገዳማቸውም ደብረ አንሣ(ዓሣ) ተብሎ የተሰየመ ሲሆን ወርኀዊና ዓመታዊ በዓላቸውም ህዳር 5 ቀን ይታሰባል፡፡ ( ምንጭ፡- 1. የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት ከዶ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ 2. Journal of Ethiopian Studies. Vol 3 No. 2 July 1975)

5. ቅድስ ያሬድ

ቅዱስ ያሬድ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ505 ዓ.ም. የተነሣ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በዓለም በሚታወቅበት ሙያውና ዕውቀቱ በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ የመንፈሳዊ ዜማ ደራሲ የቅኔ ተመራማሪ፤ ኪሩቤልን በሚያስምስለው ጣዕመ ዝማሬ የተወደደና ድምፅ መልካ ማሕሌትዊ ነው፡፡
ቅዱስ ያሬድ ድጓ፤ ዝማሬ መዋሥእትና ምዕራፍ የተሰኙ የዜማ መጻሕፍት አሉት፤ የብሉያት የሐዲሳትና የሊቃውንት መጻሕፍት ትርጓሜም ሊቅ ነው፡፡ እነዚህ ከብሉያት ከሐዲሳት ከሊቃውንት መጻሐፍት ለጸሎትና ለማሕሌት የሚስማሙትን ቃላት እየመረጠ ምሥጢራትን ከትርጓሜ እያስማማ ዜማዎቹን በዐራቱ ክፍላተ ዘመን በመፀው፤ በሐጋይ፤ በጸደይና በክረምት በመክፈል የየወቅቱን የተፈጥሮ ሥነ ባሕርይ በአንክሮና በምስጋና በሚገልጽ ጣዕም እንዲዘምሩና እንዲጸልዩ ያደረገ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ነው፡፡ ዜማውንም ግዕዝ፤ ዕዝል አራራይ በሚል በሦስት የዜማ ስልት ከፍሎ ዘምሮታል፡፡
ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰቱን ያዘጋጀው ከ540-560 ዓ.ም. ባለው ዘመን ነው፡፡ ማሕሌታዊው ቅዱስ ያሬድ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍሎች ለ11 ዓመታት እየተዛዋወረ ሲያስተምር ቤተ ክርስቲያንን ያገለግልና ሲያስገለግል ቆይቷል፡፡

በመጨረሻም በሰሜን ተራራዎች ሥር ካሉት ገዳማት በአንዱ ዋሻ ውስጥ ገብቶ በጾም፤ በጸሎት፤ በብሕትውና ዘመኑን አሳልፎአል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ እስከ ዛሬ እልፈትና ውላጤ ያላገኘው በጣዕመ ዝማሬው በምልክቱ ልዩ የሆነ የዜማ ድርሰቱን ለኢትዮጰያ ቤተ ከርስቲያን ያበረከተ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሊቅ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዝክረ ስሙን በጥንቃቄ ጠብቃ፤ በስሙ ጽላት ቀርፃ፤ ቤተ ክርስቲያንን አንጻ፤ ገድሉን ጽፋ በዓለ ዕረፍቱን በየዓመቱ ግንቦት 11 ቀን ታከብራለች፡፡ (ምንጭ፡- The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Faith, order of worship and Ecumenical relations, July 1996)

6. ሌሎች

• ቅዱስ ይምርሃነ ክርሰቶስ
• ቅዱስ ሐርቤ(ገ/ማርያም)
• ቅዱስ ላሊበላ
• ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ

እነዚህ ቅዱሳን የነበሩበት ዘመን ከ11ኛው እስከ 12ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን ምስፍንናን ከክህነት፤ ክህነትን ከምንፍስና ጋር አስተባብረው በመያዝ ለክርስትና መስፋፋት፤ ለቤተ ከርስቲያን ዕድገት፤ ለአገር አንድነት የከፈሉት መስዋዕትነት፤ ያቆዩት መንፈሳዊ ቅርስ በዐይን የሚታይ በእጅ የሚዳሰስ ከመሆኑም በላይ ለሀገር ኢኮኖሚ የደም ሥርና የጀርባ አጥንት ሆነው የሚታዩት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡ በመሆኑም እናት ቤተ ክርስቲያን ከላይ ስማቸው ለተጠቀሱው መንፈሳውያን ነገሥታት የቅድስና ማዕረግ ሰጥታ፤ ገድላቸውን ጽፋ ለትውልደ ትውልድ አቆይታለች፡፡
(ምንጭ፡- 1. የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትናንትና ዛሬ መስከረም 1990 ዓ.ም 2. ዜና መዋዕል ዘብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ነሐሴ 1978 ዓ.ም. 3. የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት ከዶ/ር ሥርግው ሐብል ሥላሴ 1981 ዓ.ም.)

ነገረ መለኮት (Theology)

<<Theology >> የሚለው ቃል ከሁለት የግሪክ ቃላት ማለትም ‹‹Theo›› እና ‹‹logy›› የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹ Theo›› ማለት ‹‹God›› ማለት ሲሆን ‹‹logy›› ደግሞ study or knowledge የሚል ቀጥተኛ ትርጉም አለው፡፡ በመሆኑም ‹‹Theology›› (የነገረ መለኮት) ማለት ስለ እግዚአብሔር የማይጨበጠውን፣የማይላጠውን፣ የማይገመተውን እንዲሁም ከሰዎች አእምሮ በላይ የሆነውን ጌትነቱንና አምላክነቱን መንፈስ ቅዱስ በገለጠላቸው መጠን ሰዎች የሚረዱበት ጥበብ ነው፡፡

እግዚአብሔር ተብሎ ወደ ግዕዝ የተተረጉመው በዕብራይስጡ ቋንቋ ኤል ወይም በብዙ ቁጥር ኤሎሄም የሚለው ቃል ነው፡፡ ኤል ማለት  ኃይል ማለት ነው፡፡ በታላቁ መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ሌሎች የእግዚአብሐር ስሞችም ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህዌ ማለት የነበረ ያለና የሚኖር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚለው የግዕዝ ቃል ወደ አማርኛው ሲተረጎም የሀገር  ወይም የዓለም ጌታ ማለት ነው፡፡

በምድራችን ላይ በርካታ ሃይማኖቶች፤ እምነቶችና አመለካከቶች የመኖራቸውን ያህል ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረና (ያስገኘ) እና የየዕለት ሁኔታዎችን  የሚመራ እና  የሚቆጣጠር አንድ ከሰዎች በላይ የሆነ የማይታይ ትልቅ ኃይል ያለ መሆኑን አብዛኛው ወገኖች ይስማማሉ፡፡ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ሃይማኖት የራሱ የሆነ መመሪያና ትምህርት አለው፡፡

በዚህ መሰረት የክርስትና ነገረ መለኮት  ስንል ስለ እግዚአብሔር ህልውና ስለጠባዮቹ ስለመለኮታዊ አንድነቱ ሶስትነቱ ለፍጥረቱ ስለሚያደርገው ጥበቃ (መግበቱ) ከሶስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ ዓለምን ማዳኑንና በአጠቃላይም ለዚህ ሁሉ ትምህርት ምንጭ በሆነው አምላካዊ መጽሀፍ የተገለጸው ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚመረምር ትምህርት (ዕውቀት) ማለታችን ነው፡፡

መሆኑም በዚህች አጭር ፅሁፍ ውስጥ ይህንን ሀሳብ በስፋት ለማየት አባይን በጭልፋ ያህል ከባድ ስለሆነ በነገረ መለኮት ትምህርት ውስጥ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርዶቶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለውን አስተምሮ በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን፡፡

ሀልወተ እግዚአብሔር
ለእግዚአብሔር ህላዌ ማስረጃነት ከሚቀርቡት በርካታ ጉዳዮች መካከል በተለይ የፍጥረታት ሥነ ሥርዓትና አሠራሩ፣ የህሊና ምስክርነት ፣የሠው ልጆች የተፈጥሮ ዝንባሌ፣ የቃለ እግዚአብሄር፣ የታሪክ ምስክርነት ወዘተ….. ይገኙበታል፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ ወፎችንና እንስሳትን ብትጠይቋቸው ብዙ ሊያስተምሯችሁ በቻሉ ነበር፡፡ በምድር ላይ እና በባህር ውስጥ የሚኖሩትን ፍጥረቶች ጥበብ እንዲያስተምሯችሁ ብትጠይቋቸው ሁሉም እግዚአብሔር አንደሰራቸው ያስረዱአችኋል፡፡ የፍጥረቶቹን ሕይወት የሚመራ እግዚአብሔር ነው፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ነፍስ በእግዚአብሔር ሥልጣን ስር ነው፡፡›› (መ.ኢዮ 12÷7-10) በማለት ዓለምን ያስገኘ እግዚአብሔር መሆኑን በግልጽ ያስተምራል፡፡ መዝሙረኛው ቅ/ዳዊትም ይህንን ሀሳብ ሲያጠናክረው ‹‹ሰማያት የእግዚአብሔር ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይ ጠፈሮችም የእግዚአብሔር ሥራ ያውጃሉ፡፡›› (መዝ19፡1) በማት ከእግዚአብሔር ውጭ ይህች ዓለም ሌላ አዛዥና ባለቤት እንደሌላት ምስክርነቱን አስቀምጧል፡፡

በአንድ ወቅት በአቴና ከተማ የሚኖሩ ሰዎች ስለ እግዚአብሄር ሀልወት ለማመንና ለመቀበል ተቸግረው መስዋዕት እያቀረቡ መስዋዕት የሚያቀርቡለትን አምላክ ባለማወቃቸው ‹‹ ለማይታወቅ አምላክ›› ብለው ጽፈው ሲያመልኩ ግን የሚያመልኩትን አምላክ ሳያውቁ እንደነበረ ሀዋርያው ቅ/ጳውሎስ አርዮስፋጐስ በተባለው ሥፍራ ቆሞ የክርስትናን ሃይማኖት እንዴት እንደሰበካቸውና የማይታወቀውን አምላክ ሲገልጽ ‹‹ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሠማይና የምድር ጌታ ነውና….›› (የሐዋ 17፡24) በማለት ስለእግዚአብሔር ሀልወት ለአቴና ሰዎች ገልጧል፡፡

የእግዚአብሔር ጠባዮች
የእግዚአብሔር ጠባዮች በሁለት  አጠቃለን ለማየት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው በማናቸውም መልኩ ለእግዚአብሄር እንጂ ለፍጡር የማይነገር የእርሱ የብቻው የባሕርይው መገልጫዎች ናቸው፡፡ እነርሱም በማንኛውም ሁኔታ ውሱንነት የሌለው መሆኑ፣ በራሱ የሚኖር መሆኑ፣ የማንም እርዳት የማያስፈልገው መሆኑ፣ ዘለዓለማዊነቱ አለመለወጡ፣ በሁሉም ቦታ የሚገኝ መሆኑ አለመታየቱ፣ አልፋና ኦሜጋ መሆኑ ወዘተ የመሰሉት ጠባዮች ይገኙበታል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር ባለው ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነው ይህም ሁሉን ዐዋቂነቱ፣ ጥበበኛነቱ፣ ሁሉን ቻይነቱ፣ ቅዱስነቱ፣ ትክክለኛ ዳኝነቱ፣ ፍቅሩና ደግነቱ፣ እውነተኛነቱና ታማኝነቱ…. ወዘተ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ እነዚህን ሰዎች በጸጋ በተለያየ መጠን ያግኙ  እንጂ የእግዚአብሔር ግን የባሕርይው ናቸው፡፡

ምስጢረ ሥላሴ
የክርስቲያን ሃይማኖት ከሌሎች ሃይማኖቶች ተለይቶ ከሚታወቅባቸው ዋንኞቹ ርዕሶች መካከል ምሥጢረ ሥላሴ ወይም የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት እምነት አንዱ ነው፡፡ በክርስትና እምነት መሰረት እግዚአብሄር አንድ ነው አንዱ አምላክ ሦስት አካል አለው፡፡ ይህም ማለት እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስት አካል አለው ማለት ነው፡፡

በሌላ አባባል አንድ መለኮት ሦስት አካል፣ ወይም ሦስት አካል ያለው አንድ መለኮት ማለት ነው፡፡ የሥላሴ አንድነት እና ሦስትነት ምስጢር ግልጽ ሆኖ በመጽሀፍ ቅዱስ ተቀምጧል፡፡ ሊቀነቢያት ሙሴ በጻፈው በመጀመሪያ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍል ‹‹እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰማይና ምድርን ፈጠረ›› ( ዘፍ 1፡1) በማለት አንድነቱን ገልጾ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን በአምሳያችን እንፍጠር ( ዘፍ 1፡26) በማለት በአንድ ምዕራፍ የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ (ዘፍ 3፡22 ፣ ዘፍ 11፡7፣ ኢሳ 6፡3፣ ዘኑ 6፡24)
ከመጀመሪያው ጀምሮ በሐዲስ ኪዳን ውስጥ ስለአንድነት እና ስለሦስትነት ትምህርት ግልጥ ሆኖ በስም ቀርቧል፡፡ ወንጌላዊው ቅ/ማቴዎስም እንግዲህ ወደ ዓለም ሕዝብ ሁሉ ሂዱ፡፡ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኃቸው የኔ ደቀመዛሙርት አድርጓቸው›› (ማቴ 28፤19) በማለት አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ተጽፎ የሚገኘውን የሦስትነቱን ምስጢር በግልጽ በስም ጠቅሶ ይገኛል፡፡(ማቴ 3፡13-17 ፣ ማር1፡19-11፣ ሉቃ 3፡21-22፣ ማቴ17፡5፣ሉቃ 1፡35፣ዮሐ1፡33)

በተለያየ ዘመናት በነገረ መለኮት ላይ ለሚነሱ ክህደት የቤተክርስቲያን ሊቃውንት የትምህርቱ ስርወ እምነት እንዳይበረዝ በተለይ በኒቂያና በቁስጥንጥንያ ጉባዔያት የሐይማኖት ቀኖናዎች የአንድነቱን፣ የሦስትነትን እምነት አረጋግጠዋል፡፡ ይህም ፀሎተ ሃይማኖት በሚባለው የሃይማኖት ጸሎት ውስጥ ተካቶ ይገኛል፡፡

‹‹ሁሉን በያዘ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፡፡›› ይህን ስለ እግዚአብሄር አብ፤ ‹‹ከዘመናት ሁሉ በፊት ከአብ የተወለደ በእግዚአብሔር አንድያ ልጅ በአንዱ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፡፡›› ይህን ስለ እግዚአብሔር ወልድ ‹‹ሕይወትን በሚሠጥ ጌታ፣ ከአብ ከሰረፀ፣ ከአብና ከወልድ ጋር በሚሰገድለት በነቢያት አድሮ በተናገረ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን›› ይህንን ደግሞ ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በቀኖናቸው ደንግገዋል፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ክብር

በንጉስ ቁስጢንጢኖስ ዘመነ መንግስት በ325 ዓ.ም በኒቅያ ከተማ በተሰበሰቡት 318 የዓለም ኤጲስ ቆጶሳት ውሳኔ መሰረት ከተወገዘው ከአርዮስ ጀምሮ የጌታችን የባሕርይ አምላክነትና ከአብ ጋር ያለው እኩልነት የሚክዱ የአርዮስ ወገኖች ነበሩ አሁንም አሉ፡፡ ለዚህም ምላሽ ወንጌላዊው ቅ/ዮሐንስ ‹‹ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳችስ ስንኳ ያለእርሱ የሆነ የለም›› (ዮሐ1፡3) በማለት ስለክርስቶስ ክብር ተናግሯል፡፡ ይህም ማለት (ዘፍ1፡1) ሰማይንና ምድርን እንዲሁም በእነርሱ የሚገኙትን ፍጥረቶች ሁሉ የፈጠረው እግዚአብሔር እርሱ ነበር ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ እውራንን ያበራ፣ አንካሳን ቀጥ ያደረገ፣ ዱኩማንን ከድካማቸው ያሳረፋቸው፣ ሙታንን ያስነሳ፣ ህሙማንን የፈወሰ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ መሆኑን ነቢያት እንደተናገሩት፣ ሃዋሪያት እንደሰበኩት መምህራን እንዳስተማሩት ይልቁንም ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  እንዳረጋገጠልን ይህንን የሐይማኖት መሰረት አድርገን እናምናለን፡፡ ‹‹የሥጋን ህማም ለመለኮት ገንዘብ በአደረገ ጊዜ እግዚአብሔር በባህርዩ በግድ ሕማምን አልተቀበለም ሕማም በሚስማማው ባህርዩ ኃይልን እንጂ ሞትም ለእግዚአብሔር ቃል ገንዘብ በሆነ ጊዜ ሞትን አጠፋ ከሞተም በኋላ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አጠፋ›› (ሃይ አበ.ገጽ 175) ቅዱስ ቴዎድጦስ የዕንቁራ ኤጲስ ቆጶስ፡፡

የመንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ክብር
መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል መሆኑን ቤተክርስቲያን ታምናለች (ታስተምራለች) ይህም ማለት በባህርይ በጠባይና የመለኮት ግብር በሆኑ ነገሮች ሁሉ ከአብና ከወልድ ጋር እኩል ማለት ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንዱ ከሌላው የሚበልጥ ወይም የሚያንስ ሳይሆን ሦስቱም አካላት በከሃሊነት፣ በክብር በሥልጣን፣ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም እኩል ናቸው፡፡

የመንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ክብር ከአብና ከወልድ ጋር በባህርይ እኩል መሆኑን ቅዱሳት መጻህፍት በበቂ ማስረጃዎች አረጋግጠዋለሁ፡፡ በቅዱሳት መጻህፍትም በግልጥ የቀረበ በመሆኑ ቤተክርስቲያን ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ አካልነት ማለት ከሶስቱ አካላት አንዱ መሆኑን ታምናለች፡፡ ይሁን እንጂ የመንፈስ ቅዱስን መለኮታዊ ክብር የሚክዱ መናፍቃን በተለያዩ ዘመናት ተነስተዋል፡፡ እንደ አርዮስ፣ ሰባልዮስ እና መቅዶንዮስ ያሉ ናቸው፡፡

ለእነዚህም መናፍቃን ሊቃውንት ‹‹ወንአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማህየዊ ዘሠረፀ እመ አብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሆ ምስለ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ……›› በማለት በሃይማኖት ፀሎት ደንግገዋል፡፡ ሀዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ እንደፈቀደ ለእያንዳንዱ ሰው የተለየ ስጦታን ይሰጠዋል፡፡ (1ቆሮ 12፡11) በማለት የመንፈስ ቅዱስን መለኮታዊ ክብር ገልጧል፡፡ ከላይ ለማየት እንደተሞከረው በነገረ መለኮት ትምህርት ውስጥ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ያለመጠራጠር ለልጆቿ የሥላሴን አንድነትና ሶስትነት ያለመቀላቀል ያለመለያየት ስታስተምር ኖራለች ወደፊትም ታስተምራለች፡፡

የሥላሴ ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን  አሜን!!!