የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

የጥናቱ አስፈላጊነት

• የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የእምነቱ መሠረትና መነሻ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን በሚገባ ለማወቅና ለመረዳት እንዲሁም ለሌላውም ለማሳወቅና  ለማስረዳት ስለሚያስችል፤
• መጽሐፍ ቅዱስን በግልም ሆነ በማህበር ስናነብና ስናጠና ዋና ሀሳቡንና ትርጉሙን በቀላሉና በቶሎ እንዲገባን ሊያደርግ የሚያስችል በመሆኑ፣
• በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ በቂ መረዳትና ችሎታ እንዲኖር፣ የአጠናን ዘዴዎችን ከአወቁ በኋላ መልስ ለመስጠት የተዘጋጀን እንድንሆን፣
• የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ስብከትና ትምህርት ሲሰጡ በምንማርበትና በምንሰማበት ጊዜ እየተረዳንና እየገባን በፍጥነት መከታተል እንችላለን፡፡
• በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነሱ ማንኛውንም ጥያቄ ለመመለስ ከማስቻሉም በላይ ለሌሎች ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ለመመስከር እና ለማስተማር እንድንችል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሚገባ ያስተዋውቀናል፡፡ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር እንዲኖረን ያለማምደናል፡፡

የትምሕርቱ ዓላማ( የጥናቱ ዓላማ)

• መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለሰዎች የሰጠው የፍቅር ምልክት እንደመሆኑ መጠን ዓላማው ሰዎችን የመጥቀምና ሕይወትን የሚሰጥ የፍቅር ዓላማ ነው፡፡
• በዓለም ላይ ያለውን የአለፈውን የአሁኑንና የወደፊቱን ሁኔታ የሚታየውንና የማይታየውን ድርጊት እግዚአብሔር የሚሠራውን ሥራ ሁሉ ማስረዳት፣
• የእግዚብሔር ሐሳብ እና የእግዚአብሔርን የፍቅር ሥራ እቅዱን፣ ፈቃዱን ለሰው ማሳወቅ
• ሰዎችን ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እንዲያምኑና አምነውም በደሙ ሕይወት እንዲሆንላቸው መግለጽ፡፡ ዮሐ.2ዐ-30
• የመዳንን መንገድ ማሳወቅ ፣  ዮሐ.6፡4ዐ ፣አቆሮ 1፡21    ዮሐ.2ዐ፡31
• ለሐጢአተኞችና ለጻድቃን የሚከፈለው ዋጋ ማሳወቅ
• የመጽሐፍ ቅዱስን ዓላማ ማስተማር  ዮሐ.2ዐ፡31
• አጠቃላይ መግቢያ መስጠት እንዴት፣ በእነማን፣ የት አካባቢ እንደተጻፈ ማሳየት
• 81 መጽሐፍት አጠቃላይ ሁኔታ ስም፣ ይዘት፣ ወዘተ… ማስጠናት
• በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ አውቆ ለመመለስ ማስቻል
• በቅዱስ መጽሐፍ መመሪያ እና ሥርዓት ለመኖር ማሳየት
• መጽሐፍ ቅዱስ የፍቅር ምልክት ስለሆነ ሰዎች ሁሉ ተፋቅረው እግዚአብሔርን በመውደድ ለቃሉም በመታዘዝ የክብር ትንሳኤና ዘለዓለማዊነት፣ በተስፋ እንዲጠብቁ ይገልጻል፣ ያነቃቃል፡፡

መግቢያ

መጽሐፍ ቅዱስ እስከዛሬ በዓለም ካሉት መጻሕፍት ይልቅ እጅግ ታላቅ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህም ረጅም ዘመናት በመቆየት በዓለም ላይ ተወዳጅ ከመሆኑም በላይ ብዙ አንባቢዎችን በማግኘት ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ሌሎችን መጻሕፍት ብናነባቸው እውቀትን ከመስጠት የሚያልፉ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ለሰዎች ሕይወት ብርሃንና መንገድ ነው፡፡‹ እኔ የነገርኳችሁ ቃል መንፈስ ነው፡፡ ሕይወትም ነው፡፡› እንዳለ ዮሐ. 6፡63 ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስ ለጊዜው አንብበን የምንተወው መጽሐፍ አይደለም፡፡
ምክንያቱም፡- መጽሐፍ ቅዱስ የክርስትና ሃይማኖት መመሪያ እንደመሆኑ መጠን የቤተ ክርስቲያን ልጆች አማንያን ሁሉ ይልቁንም አገልጋዮች በሚገባ ሊያውቁት ያስፈልጋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሥራቹ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን ፍጹም አምላክ ቢሆንም ደግሞም ፍጹም ሰው ነውና በልጅነቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሊማር ት/ቤት ገብቶ እንደነበረ ‹ ተአምረ እየሱስ‹ የተባለው የቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍ ይናገራል፡፡ በሉቃ.2፡48 ላይ እንደተገለጸው ገና በአሥራ ሁለት ዓመቱ ከመምሕራን ጋር በቤተ መቅደስ ተገኝቶ ጥያቄ ሲጠይቅ ለሚጠይቁት መልስ ሲሰጥ መጻሐፍትንም ሲጠቅስ የሚሰሙት በማስተዋሉና በእውቀት መመለሱ ሁሉንም አስገርሞአል፡፡ ጌታ በጥበብና በቁመት በሞገስም ያድግ እንደነበረ ተጽፏል፡፡ ሉቃ.2፡52፡፡
በማስተማር ዘመኑም ቢሆን ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጥቀስ ለሚሰሙት በቂ ትምህርት ለሚጠይቁትም አጥጋቢ መልስ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም አስቀድሞ የጽሑፍን ጥበብ ለሰው ልጆች የገለጸው አምላካችን እግዚአብሔር በሄኖክ ዘመን የፊደላትን መልክ በሰማይ ሰሌዳ ላይ አሳየ፡፡ ዘፍ.4፡26፡፡ ከዚያም በኋላ የሰው ልጆች የፊደላትን መልክ ለይተው ማወቅና ማጥናት በሕሊና የሚመላለስ ሀሳብ በአፍም የሚነገር ቃል እንዳይረሳ በመጽሐፍ ተጽፎ የታወቀ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ባገኘው ትውልድ በሄኖክ ዘመን ለሰው ልጆች ጽሕፈትን አስተማረ፡፡ ኩፋ.5፡22-24፡፡ ሁሉን በጊዜው ገልጦ ያሳየ አምላክ በስጋ ተገልጦ ሰው ሆኖ በሚመላለስበት ጊዜ እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡     ‹መጻሕፍትን ካላመናችሁ ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?› ዮሐ. 5-47፡፡ ላይ በማለት እምነት በቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት መሆኑን ገልጿል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ከተነሳ በኋላ እንኳን በኤማሁስ መንገድ ለተገለጠላቸው ሁለቱ ቀደመዛሙርት ባለማስተዋላቸው ከገሰጻቸው በኋላ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ያለውንና የተነገረውን ተርጐሞላቸዋል፡፡ ለሐዋርያትም ቢሆን መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከተፈላቸው፡፡ ሉቃ.24-27፡፡
ከዚህ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ  እየተመሩ ቅዱሳን ሰዎች የጻፉት ስለሆነ ስሕተት የሌለበት መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ታምናለች፡፡ ይህንንም ታስተምራለች፡፡ እግዚአብሔር በቅዱሳን ሰዎች ላይ አድሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዲጽፉ ምስጢርንና እውቀትን ከሚገልጽባቸው መንገዶችና ዘዴዎች መካከል፣
1ኛ. ቃል በቃል፡- ባርያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ እርሱ በቤቱ ሁሉ የታመነ ነው፡፡ እኔ አፍ ለአፍ በግልጽ እናገረዋለሁ፡፡ በምሳሌም አይደለም፡፡ ዘኁ.13፡7-8
ልበ አምላክ ዳዊትም፡-የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነበረ፡፡ 2 ሳሙ.23፡2፡፡
2ኛ.  በሕልም፡- ዮሴፍም ሕልምን አለመ ለወንድሞቹም ነገራቸው፡፡ ዘፍ.37፡5፡፡
3ኛ.  በራዕይ፡- በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ በራዕይ እገለጽለታለሁ፡፡ ዘኁ.12፡6
ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ፡፡ 2.ጴ.ጥ.1.21
4ኛ. በመጽሐፍ እንዲጽፉ፡-በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፡፡ በኋላየም የመለከትን ድምጽ የሚመስል ትልቅ ድምጽ ሰማሁ፡፡ የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ለአብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ፡፡ ራዕ.1፡1ዐ፡፡ ወዘተ ይገኙበታል፡፡ እንዲህ ከሆነ ቅዱስ መጽሐፍ በቅዱሳን ሰዎች እንደተጻፈ ቢነገርም በራሳቸው ሀሳብ ወጥተው ወርደው አመንጭተው ሳይሆን በመንፈሰ እግዚአብሔር ተመርተው ጽፈዋቸዋል፡፡ ብዙ ሊቃውንትም የሚስማሙበት አንድ የሚሆኑበት ቃል የመጽሐፍ ቅዱስ ሥራ መለኮታዊ ነው ይላሉ፡፡
ይህም ማለት የሰዎች ቃልና የሀሳባቸው ፍሬ ሳይሆን እግዚብሔር መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ከናፍር ያናገራቸው በሰዎች ብዕር ያጻፋቸው ናቸው ማለት ነው፡፡ ኢሳ.34፡16፣ ኤር.36 በሌላ አነጋገር መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ዓይነት ደራሲ(አዘጋጅ)አለው፡፡ ሰው ሁለተኛው ደራሲ ሲሆን መጀመሪያውና ዋናው ደግሞ በእያንዳንዱ ደራሲ ላይ አድሮ ያሳሰበ፣ የመራ ያመለከተ እንዲሁም በእውቀትና በጥበብ ተሞልቶ የገለጠ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

ከዚህ የተነሳ ልዑል እግዚአብሔር የፈለገውን እንዲጽፍ፣ እንዲናገር ሰዎችን የሚያነሳሳ መሆኑ ከታወቀ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት የራሱ የእግዚአብሔር እስትንፋስ እና ቃል ናቸው፡፡ ይህም ኦሪት፣ ነቢያት፣ ጽሕፋት እንዲሁም ሐዋርያት በወንጌላቸውና በመልእክታቸው በሰፊው ጽፈዋል፡፡ ነገ.2፡8-16፡፡ ነህ.8፡ኤር.25፡1-23  2ጢሞ 3፡17፡፡
ከላይ እንደተመለከትነው የሰዎች ድርሻ ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን በጽሑፍም ሆነ በቃል ማስተላለፍ ሲሆን በሁለተኛ ደራሲነታቸው በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በቅርፀት፣ በጽሕፈት የመጣላቸውንና የተገለጠላቸውን ቃል አስተውሎና ጠንቅቆ በመያዝ እንዲሁም በተሰጣቸው እውቀት በጽሑፍ በማስተላለፍ አስተዋጾ አላቸው፡፡ ከዚህ በቀር ለመናገርም ሆነ ለመጻፍ እግዚአብሔር የገለጠላቸውን እንጂ ከራሳቸው አመንጭተው እግዚአብሔር እንዲህ አለ በማለት አይናገርም፡፡ ኤር.1፡7፡፡ ሕዝ.2፡7፣ አሞ.3፡7፣ 1ነገ 22፡7፡፡

ምክንያቱም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተውና ተነድተው መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉ ሰዎች ከተለያዩ የሥራ መስክ የተጠሩ ናቸው፡፡ ከዚህም  ሌላ በተለያዩ ዘመንና በተለያዩ አህጉር የኖሩ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹም አይተዋወቁም ነበር፡፡ ሆኖም የጻፉአቸውን መጻሐፍት የጻፋቸው አንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ ቃሉም ሆነ መልእክቱ ፈጽሞ አይጋጭም፡፡(አይጣላም፡፡)
ጸሐፊዎች በችሎታቸውና በእውቀታቸው የተለያዩ ሆነው ሳለ በእግዚአብሔር መንፈስ የጻፉአቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ግን ዋና ሀሳብና መልእክታቸው አልተለያየም፡፡ በዚህም ምክንያት እኛ ለሕይወታችን መመሪያ መጽሐፍ ቅዱስን የበላይ አድርገን ተቀብለነዋል፡፡ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ስልጣን ይባላል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍትን በውስጡ የያዘ የእግዚአብሔር የቃሉ መዝገብ ነው፡፡ በተለያዩ ሰዎች በተለያዩ ዘመናት የተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍት በኋላ ዘመን በአንድነት ተሰባስበው የሚገኙበት መጽሐፍ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም በአንድነት እርስ በእርሳቸው ሳይፋለሱ የሚናገሩት ለሰው ልጆች የተላለፈውን የእግዚአብሔርን መልእክት ነው፡፡
ስለዚህ ከልጅነታችን ጀምሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን መማር፣ ማወቅ፣ ማጥናትና ማስተዋል እንደሚገባ እንረዳለን፡፡ ሐዋርያት ያስተምሩ የነበረውም ቅዱሳን መጻሕፍትን በመጥቀስ ነበር፡፡ ምክንያቱም አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፏልና፡፡ ሮሜ.15፡4

ስለሆነም ለማንኛውም ትምህርት መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሆነ ከሕጻንነታችን ጀምሮ ማወቅና ማጥናት አለብን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በተማረውና በተረዳው ነገር ጸንቶ እንዲኖር ከመከረው በኋላ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡ የሚችሉ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንደሚያውቅ መስክሮለታል፡፡ 2ኛ ጢሞ.3፡114-15 ራሱም ቅዱስ ጳውሎስ የሚያነባቸው ቅዱሳን መጻሕፍት ነበሩት፡፡ 2ኛ.ጢሞ.4፡13፡፡
ነገር ግን ቅዱሳን መጻሕፍትን ስንማርም ሆነ ስናጠና በመንፈስ እንጂ በሥጋ መሆን የለበትም፡፡ በሥጋዊ ስሜት መጻሕፍትን መመርመር ሕይወት አይገኝበትም ‹እናንተ መጻሕፍት የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ ጌታ የተናገረው ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ.5፡39›

ስለዚህ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመንፈስ ሆነን እግዚአብሔር በሚሰጠው ማስተዋል መርምረን በሕይወታችን እየተረጐምን እንደ መጻሕፍት ሁሉ እኛም ስለጌታችን ልንመሰክር ይገባናል፡፡ በዚሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ሁሉን ለይተን እንድናውቅ የሚረዳንን ጽሑፍና እውቀት አምላካችን ይስጠን አሜን፡፡

መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች

የቤተክርስቲያን መሠረታዊ ተልእኮ ለሰው ልጆች መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን መስጠት ነው ለዚህም ነው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለዘመናት ያለምንም የሃይማኖት፣ የዘር፣ የጾታ ልዩነት ከሕዝቦች ሁሉ ጋር ተቀራርባ በመሥራት ሰብአዊ ተግባራትን የሞትፈፅመው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ልማት መስፋፋት የራሷን ልዩ አስተዋፅኦ በማድረግ የሀገሪቱን ልማት የምታለማና የምትደግፍ ብሔራዊት ቤተክርስቲያን ናት፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የትምህርት ታሪክ እንደሚያስረዳን ቤተክርስቲናችን የትምህርታዊ ሥነጽሑፍ ሥርዓት ምንጭ እንደሆነች ያስረዳል፤ ይህም የቤተክርስቲያኒቱ ትምህርታዊ አገልግሎት በኢትዮጵያ የግዕዝ ፊደላትን ፣ የቀን መቁጠሪዎችና ቋንቋዎችን ከመቅረጽና ከማሳደግ ይጀምራል፤ የታሪክ ቅርሶች፣ የጥናትና ምርመር ሊቃውንት እንዲሚያረጋግጡት በኢትዮጵያ የጽሕፈት ሥራ የተጀመረው ከክርስቶስ ልደት ከ1000 ዓመት በፊት ጀምሮ ነው፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የፅህፈት ሥራ ላይ ያዋለችው እምነቷን ማስፋፋት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ስለሆነም የግዕዝ ቋንቋና ፊደላት በአክሱም ዘመነ መንግስት የበላይነትን እያገኙ በሀውልቶችና በሌሎች ነገሮች የሚጻፉ ጽሑፎች በግዕዝ ቋንቋና ፊደላት በመጠቀም የትምህርት ሥርዓቷን ማሳደግ ችላለች፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በህዝቦቿ ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊና ትምህርታዊ ህይወት ውስጥ ታላቅ ድርሻ አበርክታለች እያበረከተችም ትገኛለች፡፡

የጥንቱ ትምህርት መለያ ባህሪ ያገኘው ልዩ ከሆነው ከሀገሪቱ ክርስቲያናዊ ውርስ ነው ክርስትና በተሰፋፋባቸው የኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ቤተክርስቲያኒቱ ዋናውን የኢትዮጵያን ጥንታዊ ባህል መሥርታለች ከዚህም የተነሳ ለብዙ መቶ ዓመታት ጥንታውያን ትምህርት ቤቶችን ማቋቋምና ማስፋፋት ችላለች የቤተ ክርስቲያን የትምህርት ሥርዓት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ትምህርት ጠብቆ ለማቆየት አገልግሏል ለትውልድም ሊተላለፍ የቻለው በዚህ ሥርዓት አማካንነት ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን የትምህርት ሥርዓት የሚከተሉት ዋና ክፍሎች አሏት እነርሱም፡-
• ንባብ ቤት
• ቅዳሴ ቤት
• ዜማ ቤት
• ቅኔ ቤት
• መጽሐፍ ቤት ናቸው

መንፈሳዊ ዜማ ቤት

የቤተክርስቲያን መዝሙር በሰፊው የሚሰጥበት ት/ቤት ዜማ ቤት በመባል ታወቃል፣ ዜማ ማለት በግዕዝ፤
በዕዝል እና በዓራራይ የሚነገር ከሰማየ ሰማያት የተገኘ መንፈሳዊ የመላእክት መስጋና ማለት  ነው፤ ይህም ግዕዝ በአብ፤ዕዝል በወልድ እና ዓራራይ በመንፈስ ቅዱስ የሚመሰል ነው፡፡ በታወቀው የዜማ ደራሲ በቅዱስ ያሬድ እንደተደረሱ የሚነገርላቸው የተለያዩ የዜማ ዓይነቶች አሉ ከእነዚህም መካከል አንዱና ዋናው ድጓ ነው፡፡

ቅዳሴ ቤት

ይህ ትምህርት ቤት ዲያቆናትና ቀሳውስት የቅዳሴን ዜማ በጥልቀት የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነው፤ የቅዳሴ ትምህርት ሰደድኩላና ደብረ ዓባይ በሚል በ2 የዜማ ዓይነቶች ተከፍሎ የሚሰጥ ነው፡፡

ቅኔ ቤት

በዚህ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በግዕዝ ቋንቋ  ግጥምችን እንዲገጥሙ ትምህርት ይሰጣቸዋል፤ ቅኔ ፣ የዜማና የግጥም ምጣኔ ያለው በእንግሊዝኛ ናፖይትሪን ከተሰኘው ቃል ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው በቅኔ ቤት ተማሪዎች የሚማሩት የቅኔ ግጥም መግጠም ብቻ ሳይሆን የግዕዝ ቋንቋን ከሰዋሰዋዊ ህግጋቱ ጋር ነው በመሆኑም ቅኔ ማጥናት /መማር የግዕዝን ሥነ ጽሑፍ ለመረዳት ዋና ቁልፍ ነው፡፡

መጽሐፍ ቤት

ይህ ትምህርት ቤት የብሉይና የሐዲስ የመፃሕፍተ ሊቃውንትና የመፃህፍተ መነኮሳት ትርጓሜ የሚሰጥበት ትምህርት ቤት ነው፡፡በዚህ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የቤተክርስቲያንን ትውፊት፣ ዶግማ፣ታሪክና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በእያንዳንዱ ትርጓሜ አማካኝነት ይማራሉ፡፡
የቤተክርስቲያን ት/ቤቶች ጠቀሜታና አስፈላጊነት እስከ 19ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ቤቶች በሀገሪቱ ውስጥ ለማበራዊም ሆነ ለመንፈሳዊ ትምህርት ብቸኞች የትምህርት ተቋማት ሆነው አገልግለዋል ቀሳውስቱና የሀገሪቱ ሚኒስትሮች  የእነዚህ ት/ቤት ተቋማት ውጤቶች ነበሩ፡፡

የሕግ ባለሙያዎች፣ ዳኞች፣ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ጸሐፊዎች ወዘተ ሥልጠና የሚያገኙት ከእነዚህ ት/ቤቶች ወይማ ገዳማት ነበር በአጠቃላይ ከዚህ መረዳት የምንችለው የቤት ክርስቲኒቱ ት/ቤቶች ለሃይማኖታዊ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን  ለማህበራዊ፣ ህጋዊ ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ አገልግሎቶች እጅግ በጣም አስፈላጊዎች እንደነበሩና እንደ ሆኑም ነው፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሚያስተዳድራቸው ገዳማትና አድባራት የታወቁ የቅዳሴ፣ ቅኔ፣ የአቋቋም፣ የድጓና የመጽሐፍ መምህራን መድቦ የመማር ማስተማሩ ሂደት በተሳካ ሁኔታ ትምህርትን በመስጠት ላይ ገኛል፡፡

ስብከተ ወንገልና ሐዋርያዊ ተልእኮ

1. ስብከተ ወንጌል

1.1. የወንጌል ምንነት 

ስለ ስብከተ ወንጌል ለመናገር ከተፈለገ አስቀድሞ ስለ ወንጌል መናገር የግድ ይሆናል፤ ወንጌል ዋናው መልእክቱ ስብከተ ወንጌል ደግሞ መልእክቱ የሚተላለፍበት ዘዴ ነውና፡፡ በግእዝና በአማርኛ ወንጌል ተብሎ የተተረጐመው ቃል በግሪክኛ “ዩአንጌሊዮን” የሚለው ቃል ሲሆን ትርጒሙም “የምሥራች” ማለት ነው፡፡ “ወንጌል ብሂል በልሳነ ፅርዕ ወትርጓሜሁ ስብከት” ማለትም “ወንጌል የሚለው ቃል ከፅርዕ ቋንቋ የተገኘ ነው፤ ትርጓሜውም ስብከት ወይም የምሥራች ማለት ነው” የሚለው ቃልም ይህን ያመለክታል፡፡

በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ወንጌል” የሚለው ቃል 101 ጊዜያት ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ በእንግሊዝኛው ደግሞ 96 ጊዜያት ተጠቅሷል፤ ይህን የመሰለ ልዩነት ሊኖር የሚችለው ሐዲስ ኪዳን ከግሪክኛ ቋንቋ ወደ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ሲተረጐም “ዩአንጌሊዮን” የሚለው ቃል ተመሳሳይ በሆኑ አቻ ቃላት ሊተረጐም ስለሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ፡ ወንጌልና የምሥራች ተመሳሳይ መልእክት ያላቸው ቃላት ናቸው፡፡ ስለዚህ ዮአንጌሊዮን የሚለው ቃል ወንጌል ወይም የምሥራች ተብሎ ሊተረጐም ይችላል ማለት ነው፡፡

ሆኖም ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ በልዩ ልዩ መንገድ የሚናገር ወንጌል ነው፤ በሕግ፣ በትንቢት፣ በምሳሌ፣ በታሪክ፣ በመዝሙር፣ በቅኔና በጥበብ፣ እና በመሳሰሉት መልኩ ቢነገርም በአንድም ይሁን በሌላ የሚመራው ወደ ክርስቶስ፣ የሚናገረውም ስለ ክርስቶስ ነው፡፡ ለምሳሌ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ወንጌል የሚለው ቃል አንድ ጊዜ እንኳን ተጠቅሶ አይገኝም፣ ነገር ግን ከዮሐንስ ወንጌል የበለጠ ወንጌል የለም፡፡ ዮሐንስ በመልእክቶቹም ወንጌል የሚለውን ቃል አልጠቀሰም፤ በተመሳሳይ መልኩ በሌሎችም አንዳንድ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ወንጌል የሚለው ቃል አይገኝም፤ ነገር ግን ሙሉ ሐዲስ ኪዳን ወንጌል መሆኑ የታወቀ እውነት ነው፡፡

ወንጌል የሚለው ቃል ከሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት መካከል ለዐራቱ መጠሪያ ቢሆንም ከመልእክት አንጻር ሲታይ በመክብባቸው በወንጌል ሁሉም የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ወንጌል ናቸው፡፡ ወንጌል ትምህርትና እምነት ስለሆነ አንድ ነው፤ ዐራት ወንጌላት ተብለው የሚጠሩ መጻሕፍት ቢኖሩንም ወንጌል አንድ ብቻ ነው፡፡ በተለያዩ ዘመናት፣ በተለያየ ዘዴ፣ ለተለያዩ ሰዎች፣ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የሚሰበከው የዘለዓለም ሕይወት የሚገኝበት ወንጌል አንድ ነው፡፡

ስብከተ ወንጌል በቤተ ክርስቲያን አንድ የሥራ ዘርፍ አይደልም፡፡ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን ሥራዎች ሁሉ መሠረት ስብከተ ወንጌል ነው፡፡ ሁላችንም ሰባክያነ ወንጌል ነን፤ ስብከተ ወንጌል እምነትና እውቀትን እንጂ ሹመትን አይጠይቅም፡፡ የስብከተ ወንጌል ኀላፊነት እንደሌሎች የሥራ ኀላፊነቶች በደብዳቤ የሚሰጥና በደብዳቤ የሚነሣ ተግባር አይደለም፡፡ ክርስቶስ “ሂዱ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” ብሎ የተናገረው ቃል እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለክርስያኖችና ወንጌልን መስበክ ለሚፈልጉ ሁሉ መመሪያ ሆኖ ይኖራል፡፡ ይህ ማለት ግን በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ሥርዐትና ሕግን ሳይከተሉ እንደፈለጉ መስበክ ይቻላል ማለት አይደለም፡፡ ወንጌልን የመስበክ ኀላፊነት አምላካዊ ትእዛዝ መሆኑን ለመናገር ነው እንጂ፡፡ ይህን የተረዳው ሐዋርያ “ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ” (1ቆሮ.9÷6) ሲል የጻፈውም በዚህ ምክንያት መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡

ወንጌል የቅኔ፣ የዜማ፣ የትርጓሜ መጻሕፍት፣ የሊቃውንት ምሥጢር፣ የቅዱሳን ገድል፣ የጻድቃን ጽድቅ፣ የሰማእታት ጽንአት የፈለቀበት የጥበባት ሁሉ መገኛ ነው፡፡ የልዩ ልዩ ጥበባትና ዕውቀቶች ሁሉ ምንጭ ወንጌል ነው፡፡ ወንጌል ውቅያኖስ (ባሕር) ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ሙያዎች (ትምህርቶች) ደግሞ ከወንጌል የተቀዱና በልዩ ልዩ መንገድ የሚፈስሱ ወንዞች ናቸው፡፡ የምናጠምቃቸው፣ የምናቆርባቸው፣ ቢሞቱ ፈትተን የምሸኛቸው፣ በተክሊል በቁርባን የምናጋባቸው፣ ምእመናን ሁሉ የወንጌል ፍሬዎች ናቸው፡፡ ወንጌል የሚሰበክባት ዐውደ ምሕረትም እንደ ስሟ ምሕረት የሚታወጅባት የወንጌል መድረክ ናት፡፡

1.2. የስብከተ ወንጌል አስፈላጊነት

የቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ዓላማና ተግባር ምንድን ነው ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ወንጌልን መስበክ እንደሆነ ከማንም ክርስቲያን አእምሮ የተሠወረ አይደለም፡፡ ስለዚህ ስብከተ ወንጌል ለቤተ ክርስቲያን ህልውና እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡

ስብከተ ወንጌል ለምን አስፈለገ?

ስብከተ ወንጌል ያስፈለገባቸውን ምክንያቶች በሮሜ 10÷13-17 የሐዋርያው ቃል እንዲህ ይላል፤ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና፤እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ? ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና። እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።” ይህ ቃል የስብከተ ወንጌል ዐቢይ ተልእኮ ሰዎች የወንጌልን ቃል ሰምተው በማመን የእግዚአብሔርን ስም ጠርተው እንዲድኑ ወይም የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኙ ማስቻል ነው፡፡

2. ሐዋርያዊ ተልእኮ

2.1. ሐዋርያ ማለት ምን ማለት ነው? (የሐዋርያነት ትርጒም)

“ሐዋርያ” የሚለው ቃል “ሖረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን “መንገደኛ፣ መልእክተኛ፣ ቀላጤ” የሚል ትርጒም አለው፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱን ተከትለን ስንተረጒመው “ሐዋርያ” የሚለው ቃል በአማርኛም በቁሙ ሐዋርያ ተበሎ ከመተርጐሙ በተጨማሪ “መንፈሳዊ ሹም፣ መምህር፣ ዙሮ የሚሰብክና የሚያስተምር፣ ባለምሥራች፣ ዐዋጅ ነጋሪ” የሚል ፍቺ አለው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ 1948 ዓ.ም. ገጽ. 437)፡፡ መልእክቱም የጌታ ወንጌል ነው፤ ስለዚህ የሐዋርያነት መሠረቱ ወንጌልን መስበክ ይሆናል ማለት ነው፤ለሰው ልጆች ሁሉ ይደርስ ዘንድ የተላከው የጌታ መልእክት ወንጌል ስለሆነ ወንጌልን ሳይይዙ ወይም ሳይሰብኩ ሐዋርያ መሆን አይቻልም፡፡
በላቲንና በእግሊዝኛ ቋንቋዎች “apostle” የሚለው ቃል ከግሪክኛው “Apostolos” ከሚለው ቃል የተወሰደ ነው፤ ግሪክኛውም ከሁለት የግሪክ ቃላት ማለትም “apo” እና “stellen” የተገኘ ጥምር ቃል ነው፤ “apo” የሚለው “ወዲያ” ወይም “ሩቅ” ማለት ሲሆን “stellen” ደግሞ የተላከ የሚል ትርጒም አለው፤ አንድ ላይ “ወደ ሩቅ ቦታ መልእክተኛ ሆኖ የተላከ” የሚለውን ዐሳብ ይገልጣል፡፡ (ምጭ፡ Dictionary of Word Origins)

ሐዋርያነት ስልጣን ነው፡፡

ሐዋርያ መልእክተኛ ቢሆንም በላኪው ስለሚመረጥና ስልጣንን ተቀብሎ የላኪውን ትእዛዝ ስለሚፈጽም ባለሟል ወይም እንደራሴ ነው፤ “ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲያወጡአቸው፣ በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ስልጣን ሰጣቸው” የሚለው የወንጌል ቃልም ይህን ያረጋግጣል (ማቴ.10፥1) ፡፡ የማቴዎስ ወንጌል ትይዩ ንባብ የሆነውና በማርቆስ ወንጌል የተጻፈው የሐዋርያትን ጥሪና መመረጥ የሚናገረው የወንጌል ቃል ደግሞ እንዲህ ይላል፤ “ራሱም የወደዳቸውን ወደ እሱ ጠራ፤ ወደ እርሱም ሄዱ፤ ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፣ ድውዮችንም ሊፈውሱ፣ አጋንንትንም ሊያወጡ ስልጣን ይሆንላቸው ዘንድ ዐሥራ ሁለት አደረገ” (ማር.3፥13-15) ፡፡
በዚህ ቃል ውስጥ ስለ ሐዋርያነት ብዙ ነገሮች ተገልጠዋል፤ እነዚህም፣ በራሱ በጌታ መወደድ፣ መመረጥና መጠራት፣ ወደ እርሱ መሄድና ከእርሱ ጋር መኖር፣ ወንጌልን ለመስበክ መላክ፣ ድውዮችን ለመፈወስና አጋንንትን ለማውጣት ስልጣንን መቀበል ናቸው፤ ሐዋርያነት አንድ ነገርን ብቻ ወይም ጥቂት ነገሮችን ብቻ የያዘ ኀላፊነት እንዳልሆነ ከዚህ ቃል በግልጽ እንመለከታለን፡፡

ሐዋርያነት መሠረትነትና ቀዳሚነት ነው፡፡

በዕብራውያን መልእክት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሐዋርያ” ተብሎ ተጠርቷል፤ ይህም ሐዋርያነት መሠረትነት፣ ጀማሪነት፣ ጥንትነት፣ ፊታውራሪነት፣ አበጋዝነት፣ አስታራቂነት መሆኑን ያስረዳል፤ ኢትዮጵያውያን የአንድምታ ትርጓሜ ሊቃውንት “ርእይዎ ለዝንቱ ሐዋርያክሙ” ያለውን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል ሲተረጒሙ “ፊታውራሪያችሁ፣ አበጋዛችሁ፣ አስታራቂያችሁ ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርጉት” ብለውታል (የዕብ. 3፥1 አንድምታ ትርጓሜን ተልከት)፤ የነቢያትና የሐዋርያት መሠረትነት ቀደምት አማንያንና ለክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የዐይን ምስክሮች መሆናቸው ነው፡፡

በሌላ ስፍራ ቅዱስ ጳውሎስ “እስመ ተሐነጽክሙ ዲበ መሠረተ ሐዋርያት ወነቢያት” ያለውን የሐዋርያ ቃል የአንድምታ ትርጓሜ መምህራን “ነቢያት ሐዋርያት ባመኑበት እምነት ጸንታችኋልና” ብለው መተርጐማቸው ለዚህ ምስክር ነው፤ “አንተ ኰኵሕ ወዲበ ዛቲ ኰኵሕ አሐንጻ ለቤተ ክርስቲያንየ” ያለውን የወንጌል ቃልም “እኔ መሠረት ነህ ብዬ መሠረት እንደሆንህ እናገርልሃአለሁ” በማለት ይፈቱትና “መሠረትነቱ የሃይማኖት የሹመት ነው” ይላሉ፤ ግእዝ በግእዝ ትርጓሜ ወንጌልም “ወኰኵሕሰ ዘተብህለ በአፈ ጴጥሮስ ሃይማኖተ ጴጥሮስ፤ እስመ ይቤ ወዲበ ዛቲ ኰኵሕ አሐንጻ ለቤተ ክርስቲያንየ ከመ ዘይቤ ወዲበ ዛቲ ሃይማኖትከ” ብሎ ይተረጒመዋል፤ በአማርኛ “ዐለት የተባለው በጴጥሮስ አንደበት የተነገረው ሃይማኖት ነው፤በዚህች ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ ብሏልና፤ ይህም በዚህች ሃይማኖትህ ላይ እንደማለት ነው” የሚል ነው፤ የሃይማኖትና የሹመት መሠረት የመሆን ሐዋርያዊ እምነትና ትምህርትም ይህ ነው፡፡
ሐዋርያት የሰበኩት መሠረት ክርስቶስ ነው፤ እነርሱ ከሰበኩት ክርስቶስ የተለየ ሐሰተኛ ክርስቶስን የሚሰብክ ቢኖር ከእውነተኛው እምነት የወጣና በፍርድ ቀን የሚቀጣ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ በሚከተለው መልእክቱ ያስጠነቀቀውም በዚህ ምክንያት ነው፤ “የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል” (1ቆሮ.3፥10-12) ፡፡

ሐዋርያነት አብነት/አባትነት ነው፡፡

አብነት የሚለው ቃል “አብ” ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም “አባትነት፣ ጌትነት፣ ባለቤትነት፣ አርአያ፣ ምሳሌ፣ መድኃኒት፣ ነባር፣ ጥልቅና ትልቅ ዕውቀት ያለው፣ ምስክር ፣ተጠያቂ፣ አዋቂ፣ ሊቅ፣ አባት፣ ወይም ለምስክርነትና ለተጠያቂነት የበቃ ሊቅ አዋቂ” ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አብነት የሚለው ቃል ለተጠያቂነት ከመብቃት፤ለአንድ ሙያ (ዕውቀት) በቂ ትምህርትን ከመያዝና ምስክር ሆኖ ከመገኘት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያይቱ የቆሮንቶስ መልእክቱ “በክርስቶስ ብዙ ሞግዚቶች ቢኖሩአችሁም ብዙ አባቶች የሉአችሁም፤ እኔ በክርስቶሰ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና” (1ቆሮ.4፥15) ይላል፡፡ ከዚህም በመነሣት “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” ብሎ ልጆቹን ይመክራል (1ቆሮ.11፥1) ፡፡ ዛሬም የሚያስፈልገን ሐዋርያዊ አባት እንዲህ ክርስቶስን መስሎ እኔን ምሰሉ የሚልና በወንጌል ለወለዳቸው ልጆች አባት የሚሆን፣ አብነት/አርኣያ የሆነ ሕይወት ያለው ሊሆን ይገባዋል፡፡

2.2. ሐዋርያዊ (የሐዋርያት) ተልእኮ ማለትስ ምን ማለት ነው? የሐዋርያት ተልእኮ ምን ነበር?

ሐዋርያዊ ተልእኮ ዘርፈ-ብዙ፣ እግዚአብሔርንና ሰውን ማገልገልን የሚያካትት ሰፊ ኀላፊነት ነው፤ ሐዋርያት በቤተ ክርስቲያን ያላቸው ኀላፊነት ሁለንተናዊ እንጂ በአንድ ወይም በጥቂት ጉዳዮች ላይ የሚያተኵር ብቻ አይደለም፤ ሆኖም ግን ለዚህ አጭር ጽሑፍ በሚሆን መልኩ ዋና ዋና ነገሮችን እንጠቅሳለን፡፡

ወንጌልን መስበክ

የአንድ ሐዋርያ ወይም የሐዋርያትን መንበር የወረሰና በእግራቸው ተተክቶ ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግል አባት ዋና ተልእኮ ወንጌልን መስበክ ነው፤“ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው፤… ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” የሚለው የወንጌል ቃል ይህን ታላቅና የከበረ ተልእኮ የሚያስረዳ ነው (ማር.16፥8፡15) ፡፡

ሐዋርያት የተመረጡት፣ ከዓለም የተለዩት፣ ክርስቶስ ከዋለበት ውለውና ካደረበት አድረው ትምህርትና ተአምራት ሳይከፈልባቸው ሁሉን ያዩትና የተማሩት፣በመጨረሻም ሰማያዊ ኀይልን የተቀበሉትና በጸጋ መንፈስ ቅዱስ የተሞሉት ለዚህ ታላቅና ክቡር ተልእኮ መሳካት ነው፤ በዚህ መልክ የክርስቶስ ምስክሮች ሆነው የወንጌሉን ቃል ከኢየሩሳሌም ጀምሮ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ሰበኩ፤ “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም፣ በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም፣ እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” (የሐዋ.1፥8) ብሎ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርት ያዘዘው ትእዛዝ መዳረሻውም መላውን ዓለም በወንጌል መድረስና በዕርፈ መስቀል ማረስ እንደ ሆነ ያሳያል፤ ለዚህም አስቀድሞ “ውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ፤ ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ” ማለትም “ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ፣ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ” የሚል ትንቢት አስቀድሞ ተነግሮ ነበር (መዝ.18፥4፤ሮሜ 10፥18) ፡፡

ይህን ተልእኮ 12 ሐዋርያት ብቻ ሊፈጽሙት እንደማይችሉ፣ተልእኮውም ለነርሱ ዘመን ብቻ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤ በሐዋርያት መንበር የተተኩ አባቶች በየዘመኑ ይህን ሐዋርያዊ ተልእኮ ተረድተውና ሐዋርያዊ ቅብብሎሽን ጠብቀው እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ድረስ በትጋት ሊፈጽሙት ይገባል፤“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ.28÷19) በሚለው የክርስቶስ ቃል ውስጥ “እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” የሚለው የወንጌል ቃል ተልእኮው እስከ ዓለም ፍጻሜ እንደሆነ ያሳያል፤ስለዚህ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በቀዳሚነት፣ ካህናትና ምእመናን ደግሞ በአበው መሪነት በዚህ ታሪካዊና መንፈሳዊ ሂደት ውስጥ ዛሬ ላይ ይህን ታላቅና ክቡር ኀላፊነት እየተወጡ ነው፡፡

ጥሙቃንን በትምህረተ ወንጌል ማጽናትና መጠበቅ

“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” (የሐዋ.20፥28) የሚለው የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ጥሙቃንን የመጠበቅ ኀላፊነት ለጳጳሳት የተሰጠ ሐዋርያዊ ተልእኮ መሆኑን ያስረዳል፤ ቅዱስ ጳውሎስ “አኔ ተከልሁ፤ አጵሎስ አጠጣ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር” (1ቆሮ.3፥6) እንዳለ መትከል ዐዳዲስ አማንያንን አስተምሮ ማጥመቅና ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ማስገባት ነው፤ ማጠጣት ደግሞ አማንያንን በትምህርተ ወንጌል ማጽናትና ማሳደግ ነው፤ የሚተክልና የሚያጠጣ ሁለቱም አገልጋዮች ናቸው፤ ባለቤቱ እግዚአብሔር ሕይወትን ይሰጣል፤ ያሳድጋልም፡፡ ጥሙቃንን (አማንያንን) የመጠበቅና የማሳደግ ሐዋርያዊ ተልእኮ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ በዘመነ ሊቃውንትና በዚህም ዘመን ቤተ ክርስቲያን ያለምንም መቋረጥ እየፈጸመችው የኖረና ያለ ሐዋርያዊ ተግባር ነው፡፡

የሐሰት (የስሕተት) ትምህርቶችን መቃወምና እውነተኛውን ትምሀርት መጠበቅ

ሐሰተኛ ትምህርት /ምንፍቅና/ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ደዌ ነው፤ ከአባላት መካከል በአንዱ ወይም በብዙ አባላት ላይ የሚታይና ሌላውን ጤነኛ አባል/የአካል ክፍል/ በቅርበት የሚጐዳ ይሆናል፤ ከዘመነ ሐዋርያት ቀጥሎ በነበረው ዘመነ ሰማእታት ቤተ ክርስቲያን ከዓላውያን ነገሥታት በሚመጣ ከፍተኛ ስደትና መከራ ውስጥ አልፋለች፤ እንደ አውሮፓውያን አቈጣጠር ከ312 ዓ.ም. በኋላ ሰላም ሲገኝ ደግሞ ቀድሞም በመጠኑ የነበረ ቢሆንም የመናፍቃን መነሣትና የስሕተት ትምህርቶች መስፋፋት ቤተ ክርስቲያንን ከውስጥ ፈተናት፤ ወደ ውጭ መዘርጋትና ያላመነውን ዓለም በወንጌል የማሳመን ተልእኮዋን በማደናቀፍ የውስጥ ችግሮችን በመፍታት ላይ እንድትጠመድ አደረጋት፤ በመስፋፋት ፈንታ ተሰበሰበች ወይም መስፋፋትዋ ተገታ፤ማውገዝና መናፍቃንን ከቤተ ክርሰቲያን መለየት የግድ ስለሆነ በክርስቲያኖች መካከል መለያየቱ እየሰፋ ሄደ፤ቤተ ክርስቲያን በዚህ ችግር ለ300 ዓመታት ስትፈተን ከቆየች በኋላ ችግሯን የበለጠ የሚያባብስ የእስልምና መነሣት ተከሠተ፤ ይህ ሁሉ ታሪካዊ ሁኔታ የሚነግረን የሐሰት ትምህርትን መከላከልና እውነተኛውን ትምህርት ማስተማር በሐዋርያዊ ተልእኮ የግድ መሆኑን ለማሳየትና ይህን ኀላፊነት በትክክል አለመወጣት ሁለንተናዊ ጥፋት የሚያመጣ መሆኑን ለማመላከት ነው፤ ስለዚህ ብፁዓን አባቶች፣ ካህናትና ምእመናን ከቅዱሳን ሐዋርያት የተቀበልነውን እምነትና ትምህርት መጠበቅና ሳይበረዝ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባቸዋል፡፡

ሐዋርያዊ ቅብብሎሽንና የቤተ ክርስቲያንን ቅዱስ ትውፊት በመጠበቅ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ማጽናት

ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ የሚባለው ቃል የ12ቱ ሐዋርያት ስልጣን በተለይ በኤጲስ ቆጶሳት (ጳጳሳት) በኩል እስከ ዛሬ የቀጠለበት፣ ወደፊትም የሚቀጥልበት ክህነታዊ ሰንሰለት ነው፤ ዋናው ዐሳብ የዛሬዋ ኦርቶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ሐዋርያት ከሰበሰቧትና ከመሯት ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር በእምነትና በትምህርት አንድ መሆንዋን የሚያረጋግጥ ቅብብሎሽ ነው፤ ከጥንት ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ቀሌምንጦስ ዘሮምና አግናጥዮስ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ምን እንደሆነ አስተምረዋል፤ ግኖስቲካውያን ስዉር እንቅስቃሴ በመፍጠርና ይህን ስዉር እንቅስቃሴ ትክክለኛው የሐዋርያት ትምህርትና እምነት ወራሽ እንደሆነ በማስተማር ክርስቲያኖችን ማሳት ሲጀምሩ ቀሌምንጦስና አግናጥዮስ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያትን ተልእኮ በስዉር ሳይሆን በዐደባባይ እየሰበከች ጠብቃ ያለች መሆንዋንና ስዉር እንቅስቃሴ ያደረጉ መናፍቃን ከእውነተኛው ሐዋርያዊ ሰንሰለት ራሳቸውን እንደለዩ በማስተማር የሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ትምህርት ምን እንደሆነ የሚያሳይ መሠረት ጥለዋል፤ ከትምህርትና እምነት ይዘት በተጨማሪም ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ እጅ በመጫን የሚገለጥ ክርስቲያናዊ የሢመተ ክህነት መስመርም ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚገለጠው በእምነትና በትምህርት ኦርቶክሳዊነት (ርቱዕነት)፣ በሐዋርያዊ ቅብብሎሽ፣ በቀኖና ወጥነትና በመዋቅር አንድነት መጽናት ሲቻል ነው፤ የትምህርት ትክክለኛነት የእምነትን ትክክለኛነት ያመጣል፤ በትምህርት የተከፋፈለች ወይም ሐሰተኛ ትምህርትን የማትቃወምና የማታወግዝ ቤተ ክርሰቲያን ውስጣዊ ጥንካሬዋና አንድነትዋ ይዳከማል፤ እንዲህ ባለ ሁኔታ ያለች ቤተ ክርስቲያን በቀኖና እና በመዋቅር አንድነት ሊኖራት አይችልም፤ከሐዋርያዊ ቅብብሎሹ ያፈነገጠና ቀኖናን የጣሰ አሠራር ሊስፋፋባት ይችላል፤ ሐሰተኛ ትምህርትን መከላከልና እውነተኛውን ትምህርት መጠበቅ የሐዋርያት ትልቅ ተልእኮ እንደሆነም አስቀድመን ተመልክተናል፤ የቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ትውፊትንና ሐዋርያዊ ቅብብሎሽን (Apostolic succession) መጠበቅ የቀኖና አንድነት መሠረት ይሆናል፤ የትምህርት፣ የእምነትና የቀኖና አንድነት ካለ የቤተ ክርስቲያን ሕጎች ወጥና ተፈጻሚነታቸው ከፍተኛ፣ የቤተ ክርስቲያን መዋቅርም አንድነቱ የጸና ይሆናል፤ ሐዋርያነት ይህ ነው! የዛሬ ዘመን አባቶች ኀላፊነትም ይህን ጠብቆ ማስጠበቅ ነው፡፡

በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙትን መፈወስ

ሕማምና ደዌ ልዩ ልዩ ዐይነት ነው፤ አካላዊ፣ ሥነ ልቡናዊ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ መልክ ያላቸው ልዩ ልዩ ደዌያት አሉ፤ደዌ ነፍስ በትምህርት፣ ደዌ ሥጋ ደግሞ በተአምራት ይርቃል፤ የነፍስ ደዌ ለሥጋ እንደሚተርፈው ሁሉ የነፍስ በትምህርተ ሃይማኖት መፈወስም የሥጋዊ ጤንነትን ያስገኛል፤ ደዌያት እርስ በእሳቸው የተሳሰሩ ናቸውና፤ አባቶች ሐኪሞች ናቸው፤ የሰው ልጆችም በኀጢአት በሽታ ከተያዙ ዘመናት ተቈጥረዋል፤ በሽታው እያስከተለ ያለው ሁለንተናዊ ሥቃይም ለአንድ መንፈሳዊ ሐኪም የተገለጠ ነው፡፡

እንግዲህ ሐኪሞች ምን ያህል ለሕዝቡ ሥቃይ ያዝናሉ? ለማከም ምን ያህል ይተጋሉ? ምን ያህል የሙያ ብቃትና ዝግጅት አላቸው? የሚሉት ጥያቄዎች አሁንም መልስ ይፈልጋሉ፤ ደዌ ነፍሱ በስብከተ ወንጌልና በትምህርተ ሃይማኖት ይርቃል ብለናል፤ መንፈሳዊ ጤንነቱ ለሥጋዊ ጤንነት መሠረት እንደሚሆነውም ዐይተናል፤ ከዚህ ቀጥሎም በጸሎትና በጸበል ሕሙማንን መርዳት፣ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት፣ የሕፃናት ማሳደጊያዎችንና የአረጋውያን መደገፊያ ተቋማትን መመሥረት፣ የጤና ተቋማትን መገንባትና ባለሙያዎችን በሳይንስና በመንፈሳዊ ሥነ ምግባር ማሰልጠንና ማብቃት፣ ወጣቶችን በእውነተኛ ትምህርተ ሃይማኖት ማሳደግ፣ የማኅበረሰብ ፈውስ መሠረት ናቸው፤ ዘርፈ ብዙ ሕማምና ሥቃይ እየደረሰበት ያለውን የሰውን ልጅ ለመርዳት ዘርፈ ብዙ ዐቅምና ችሎታ ያለው አገልጋይ ያስፈልጋል፡፡

ስብከተ ወንጌል

“ሑሩ ውስተ ኩሉ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት” ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንግልንም ለፈጥረት ሁሉ ስበኩ

ወንጌል፡- ወንጌል የሚለው ቃል “ዩአንጌሊዎን” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው በግእዙ ቋንቋ ብሥራት ይባላል፡፡ የግሪኩም ይሁን የግእዙ ትርጉም የምሥራች ማለት ነው፡፡

ወንጌል በሚል ቃል የተጠራው የመድኃኔታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዜና ልደቱና ትምህርቱ ነው ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት የሠራው የአድኅኖት ሥራ ሁሉ ወንጌል ተብሏል፡፡
ወንጌል ከላይ እንዳየነው የምሥራች ሲሆን የልዑል አምላክ ከቅድስት ድንግል ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ መወለዱን ስለሚያበሥር ነው፡፡ “እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” (ሉቃ.2፡፥10)

በዚህም የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ጸጋ ወደ ቀደመ የልጅነት ክብሩ እንደተመለሰ ሲያስረዳ እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች በማለት መልአኩ ለኖሎት አበሰራቸው ከዚህ የበለጠ የምሥራች የሚባል ምን አለ? የተወለደው የሁሉ መድኃኒት ነውና ሰውን ሁሉ አዳነ ይህ ለእኛ ከደስታ ሁሉ በላይ ደስታ ነው በምንም ዋጋ የማይተመን እግዚአብሔር ለእኛ የተሰጠበት የምስራች ቃል ነው፡፡

እንግዲህ ስብከተ ወንጌል ሲባል የወንጌል ትምህርት ሲሆን ይህም የምስራችን ቃል ላለተበሠሩ ማብሠር፣ ላልተሰበኩ መስበክ፣ ላልሰሙ ማሰማት ፣ማስተማር ፣ማስረዳት ፣ማሳማን ፣በቃለ ወንጌል አምነው ጸንተው እንዲኖሩ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ከተሰጣት የአገልግሎት ሥራ ሁሉ ቀዳሚም ደኃሪም የምስራቹን ቃል መስበክ ነው፡፡ ቀጥሎ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በማስተዋል እንመልከት፡፡
“እንዲህም አላቸው ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ ያመነ የተጠመቀም ይድናል” ማር 16፡15
“ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላዓለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው” ማር 16፡8
“የወንጌል ሰበኪነትን ሥራ አድርግ አገልግሎትህን ፈጽሞ” 2ጢሞ4፡5 “በጊዜውም አለጊዜውም ወንጌልን ስበክ”

የስብከተ ወንጌል ዓላማ

ወንጌልን የማስተማር ዓላማው ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት ወራሾች እንዲሆኑ ለማድረግ ነው፡፡ ወንጌል በመጀመሪያ የተሰበከው በባለቤቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው /ማቴ.4፥17 ሉቃ.8፥1/ በመቀጠልም ከላይ እንደተገለጸው የቃሉን ትምህርት እየሰሙ የሚሰራውን የማዳን ሥራ እያዩ ያስተማራቸውን ደቀመዛሙርቱን ለዚህ ምስክሮች እንደሆኑ በአንደበታቸውም የምስራቹን ቃል እንዲሰብኩ በሕይወታቸው ሁሉ የሚመሰክሩበትን የዕውቀትና ጥንካሬ መንፈስ አጎናጸፋቸው (ሉቃ.24፥ 47-53)እነሱም እንዲህ እያሉ መሰከሩ፡፡

ስለሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን” 1ዮሐ 1፡1 እንዳሉትም፡-
• ጆሮአቸው የሰማውን ቃለ ወንጌል ሰበኩ፤
• ዓይናቸው ያየውን የማዳኑን ሥራ መሰከሩ፤
• በእጆቻቸው የዳሰሱትን ሁሉ አረጋግጠው ተናገሩ፡፡
በዚህ የወንጌል ስብከታቸው ልባቸው የተነካ ሰማዕያን ወንድሞች ሆይ እንድንድን ምን እናድርግ አሉአቸው (የሐዋ.ሥራ 2፥37፣16፥30)

ከጨለማ ወደ ሚደነቀው ብርሃን የሚያወጣውን የምስራቹን ቃል ከሰሙ በኋላ ሐዋርያትን ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ ምንስ መሥራት ይገባናል ብለው ሰሚዎቹ መጠየቃቸው የቃሉ ባለቤት እግዚአብሔር ከሐዋርያቱ ጋር አብሮአቸው ይሠራ እንደነበር ማስረጃ ነው፡፡ ወንጌላዊው ቅ/ማርቆስ “እነሱ ወጥተው በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ ጌታም ከእነሱ ጋር አብሮአቸው ይሠራ ነበር በሚከተሉትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር” በማለት እንደጻፊው /ማር.16፥20/።

በዚሁ ሁኔታ የቃሉ ባለቤት የተናጋረውን ልበ አእምሮ እያበራ የሰሚውን እዝነ ህሊና እየከፈተ የምስራቹ ቃለ ወንጌል ለሁሉም ደረሰ በዘባነ ኪሩብ የሚመሰገነው ልዑል አምላክ በጎል የተወለደው ሰዎችን ለማዳን በመሆኑ ታላቅ ደስታን አጎናጸፈ“ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና” (ቲቶ.2፥11ስለሆነም ሐዋርያቱም ከነሱ ቀጥለው በወንጌል አገልግሎት ላይ የተሾሙ ሁሉ በቃለ ወንጌል እያሳመኑ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወራሾች እንዲሆኑ አገለገሉ፡፡

ስብከተ ወንጌል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶዶ ቤተክርስቲያን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ወንጌልን በሁለት መንገድ ትሰብካለች፤ እነዚህ የስብከተ ወንጌል ዓይነቶች ሕይወትና ዕውቀት ናቸው፡፡

1. በዕውቀት
ከአበው ሐዋርያት ጀምሮ የተምሮ ማስተማርን ፈለግ በመከተል የወንጌሉን ሙሉ ዘርዓ ቃል በአእምሮአቸው ሰሌዳ በመጻፍ ትርጓሜውን በርቱዕ አንደበታቸው የሚተነትኑ ምሁራንን በማፍራት የዕውቀት ማኅደር መሆኗ ይታወቃል ፡፡ እነዚህ ምሁራኖቿ የሚናገሩ መጻሕፍት ናቸው ፡፡ ከእነዚህ የሚቀዳው የትርጓሜ ወንጌል ምሥጢር ሌላውን የወንጌል ደቀመዝሙር ይወልዳል ይህ አንዱ ትልቁ የወንጌልን ምሥጢር በከፍተኛ ትርጓሜ ደረጃ የመተንተን የማስረዳት መንገድ ነው፡፡
ሌላው ደግሞ ቀለል ባለ አገላለጽ ለሰሚዕ አእምሮ በሚመጥን ደረጃ ሆኖ ከሕይወታቸው ጋር እያዛመዱ የምስራቹን ቃል መስበክ ነው ለዚህ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ምሁራኖቿ የበለጠ የክህሎት ማበልጸጊያ መንፈሳዊ ከሌጆችን በማቋቋም አሠልጥና የክህሎት ምስክር ሰጥታ የሰለጠኑትን በመላው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በዓለም ዓቀፍ ሁሉ አሰማርታ እየሠራች ትገኛለች፡፡

2.የሕይወት ስብከት
በሕይወት መስበክ በዕውቀት ከሚሰበከው በላይ ሌላውንም ያሳምናል የሕይወት ስብከት ስንል ጾረ መስቀሉን በሕይወት ትክሻ ተሸክሞ ክርስቶስ ለሁሉም የተቀበለውን መከራ ማሳየት ነው፡፡ ሐዋርያው “የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁል ጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራልን”
እንዳለው /2ቆሮ4፥11፣ ቁላ.1፥24/ የዓለምን የሞቀ የደመቀ ካባ ከመልበስ የጣመ የላመ ከመጉረስ የሕይወትን መስቀል ተሸክሞ እንደ ወንጌል ቃል በእግዚአብሔር መንግሥት ከፀሐይ ሰባት እጅ በርቶ ለሌላው ማብራት /ማቴ 13፥43/ ነው፡፡

እንግዲህ በዚህ የሕይወት ሰብከት ወንጌሉን በቃል ሳይሆን በሕይወት የረተጎሙ ብዙ ቅዱሳንና ቅዱሳት በማህጸኗ ተጸንሰው ተወልደው ፍሬአቸውን አበርክተዋል፡፡ ለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንንና ኢትዮጵያን በደንብ አድርጎ መመልከት በጆሮ ከሚሰሙት በላይ ዕፁብ ድንቅ ነው፡፡

በወርቃማ የሃይማኖታዊ ቀለም የተጻፉ ገዳማቶቿ ሕያዋን ምስክሮቿ ናቸው፡፡ ዓለም ያለውንና የነበረውን በዘመንዮሽ ቁሳዊነት እየለወጠ የራሱን ማንነት እያጣ ባለበት በአሁኑ ዘመን እንኳ የእስዋ ገዳማት የወንጌል ቃል የሕይወት ትርጉም አንባዎቿ ናቸው፤ ስለሆነም ኢትዮጵያዊቷ /ብሔራዊቷ/ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን በወንጌል የተመሰረተች ቃለ ወንጌልን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር /በሕይወት/ የምትሰብክ ሕያዊት ቤተክርስቲያን ናት፡፡

ስብከተ ወንጌል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት

አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚመራቸው ከ160 በላይ የሆኑ ታላላቅ ካቴድራሎች፣ ገዳማትና አድባራት ያሉት ሲሆን ሀገረ ስብከቱ የሀገሪቷ ዋና ርዕሰ ከተማ በሆነችው ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሥራውም እጅግ ሰፌ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ የቤተክርስቲያኗን መሠረታዊ የወንጌል ስብከት አገልግሎት ለማከናውን እንዲቻል ካሉት ትላልቅ መምሪ ያዎች አንዱ የስብከት ወንጌል መምሪያ ነው በዚህ መምሪያ አስተባባሪነት ደግሞ በ160 አብያተ ክርስቲያናት የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ እጅግ ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል በተለይ ባለፉት ዓመታት የስብከተ ወንጌል የኅብረት ጉባኤ በመባል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መስራችነት በሀገረ ስብከቱ ሙሉ አስተተባባሪነት በመላዋ አዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት መርሐግብሮች
• የየዕለት ጉባኤያት ዘወትር ከ11 – 1፡00 የሚካሄዱ
• የወርኃዊያን ልዩ ጉባኤያት በልዩ ዝግጅት የሚካሄዱ
• የወርኀዊያን ጉባኤ በዓላት በልዩ ዝግጅት የሚካሄዱ
• የዓመታውያን  ጉባኤያት በዓላት በልዩ ዝግጀት የሚካሄዱ  ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ሌሎችንም የተለያዩ የስብከተ ወንጌል ልዩ ጉባኤያት በማዘጋጀት ሀገረ ስብከቱ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እያስተባበረ፣ እየመራና እያሠራ ይገኛል፡፡

ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ምን መደረግ አለበት?

የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋትና ማጠናከር መሆኑ የታወቀ ነው፤ በተለይ ለአገልግሎት መቃናት በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት አገልግሎቱ በሚጠይቀው የሙያ ብቃት መምህራንን በመመደብ፤ አቅምን ያገናዘበ በቂ በጀት በመበጀት፤ ለሥራው አስፈላጊ ማቴሪያሎችን በማሟላት፤ አገልግሎቱ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ እንዲሰጠው ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

የደረስንበት ዘመንና እየተቀበልነው ያለው ጊዜ በሁሉም ዘርፍ በግሎበላይዜሽን አስተሳሰብ ጥላ ውስጥ እያስባገን ስለሆነ ሰዎች በማዕበሉ አቅጣጫቸውን እንዳይስቱ የወንጌሉን ቃል በምልዓት መስበክ አእምሮአዊ ሚዛናቸው ወዳልሆነ አካሄድ እንዳያጋድል ማድረግ የቤተክርስቲያኒቱ እና የሀገረ ስብከቱ ሃይማኖታዊ ኃላፊነት ነው፡፡

ሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን

ምሥጢር ማለት ቃሉ የግሪክ ቋንቋ ሆኖ ቃሉ ከግዕዝና ከአማርኛ በቀጥታ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም ድብቅ ፣ ስውር፣ ሽሽግ፣ ረቂቅ ፣ለቅርብ ዘመድ ካልሆነ በቀር የማይገለጥ ማለት ነው፡፡ ለሁለት የሚከፈል ሲሆን ይኸውም የፍጡር ሚሥጢርና የፈጣሪ ሚስጥር በመባል ይታወቃል፡፡

የፍጡር ምስጢር ሁለት ይዘት አለው፡፡ የሰውና የመላዕክት ምስጢር ይባላል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው የፈጣሪ የእግዚአብሔር ሚስጥር ይህ የከበረ የተወደደ የሚናፈቅ የበረከት ስጦታ ነው፡፡ ብርሃነ አለም ሀዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል በከበረ ቃሉ ገልፆታል፡፡“እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ /በክርስቶስ/ አምናችሁ የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱን የነብሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ በማይናገርና ክብር በሞላበት ሀሴት ደስ ይበላችሁ”፡፡ በማለት ስውር ረቂቅ ከሆነው ጸጋ እግዚአብሔር የምንሰጠው ሀብት መሆኑን በማብራራት ገልፆታል፡፡

በዚህ መሰረት በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ከሚፈጸሙት ሚስጥራት በቁጥር 7 ተወስነው ተቀምጠዋል፡፡ ውሳኔነታቸው ለሰባቱ ሰማያት ስብዐተ እግዚአብሔር ለማይከፈልባቸው ከተሞች ገላጭ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰባት ሚስጥራት ቤተክርስቲያን የሚስጥርነታቸው ምክንያት በአይናችን ልናያቸው በእጃችን ልንዳስሳቸው የማንችል ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በእነዚህ ሚስጥራት አማካኝነት የሚሰጡን ስለሆነ ነው፡፡ አበው ሲናገሩ በንባብ የተሰወረ ብሂል ምስጢር ይባላል ብለው ስውርነቱን ረቂቅነቱን ይናገራሉ፡፡ ሰባቱ ሚስጥራተ ቤተክርስቲያን የሚባሉት እንደሚከተለው ይዘረዘራሉ፡፡
• ጥምቀት
• ሜሮን
• ቁርባን
• ክህነት
• ንስሀ
• ቀንዲል
• ተክሊል ናቸው፡፡

1. ምስጢረ ጥምቀት

ይህ ምሥጢረ ጥምቀት ከኃጢያት ነፃ የምንሆንበት ከዲያቢሎስ አገዛዝ አርነት የምንወጣበት ከእግዚአብሔር በጸጋ የምንወለድበት የምስጢር ዓይነት ነው፤ በቅሰዱሳት መጻህፍት እንደተገለጸው በነብየ እግዚአብሔር በቅዱስ ሕዝቅሌል /ት.ሕዝ 36፡25 “ጥሩ ውሀንም ጥምቀትን እረጫችኋለሁ፤ እናንትም ትጠራላችሁ ከርኩስነታችሁም ሁሉ ከጣኦቶቻችሁ ሁሉ አጠራችኋለሁ አዲስ ልብ እሰጣችኋለው” በማለት የዚህን ምስጢር ክብርነት በረከትነት አምልቶ አስፍቶ ተናገሯል፡፡
በዚህ ሐሳብ ሌሎች ንፁሐን አበው ሐዋርያት ተባብረውታል፤ በምልዓት ሰብከውታል፤ /የሐዋ.2፡38 ፣ 1ቆሮ.6፥11፣ ዮሐ.3፥5 ፣ኤፌ.5፥26 ፣ገላ.3፥27፣ቲቶ 3፥5/ ጥምቀት ዳግመኛ ተወልደን ወደ እግዚአብሔር መንግስት የምንገባበት ምስጢር ነው፡፡
ከመጸሕፍ ቅዱስ ውስጥ ጥምቀት ብዙ ምሳሌዎች ይኖሩታል፡፡ እነሆ ከማየአይኅ የዳነበትን መርከብ ቅዱስ ጴጥሮስ የጥምቀት ምሳሌ እንደሆነ ገልጾታል፤ /1ጴጥ.3፥21 ምዕመናን ከሐጢያት ከጥፋት የሚድኑት በጥምቀት ነውና ቅዱስ ጳውሎስም እስራኤል ከግብጽ የባርነት ቀንበር ተላቀው የኤርትራን ባህር ተሻግረው ወደምድረ ርስት ያደረጉትን ጉዞ የጥምቀትን ምሳሌ አድርጎ አመስጥሮታል፤1ቆሮ 10፡1-2/

ምዕመናን ባሕረ ኃጢአትን ተሻግረው ምድረ ርስተ መንግሥተ ሰማያትን  የሚወርሱት በጥምቀት ነውና፡፡ ዳግመኛም ይህ ብርሃናዊ ሐዋርያ ጥምቀትን በሞትና በመቃብር ይመስለዋል፡፡ /ሮሜ 6፡3-4፤ ቆላ.2፡12/ በሞት ጊዜ ነፍስና ስጋ እንደሚለያዩ በጥምቀትም አሮጌው ሰውነት ይሞታል ይቀበራል አዲስ ሰውነት አዲስ ሕልውናን ይጀምራልና፡፡

2. ምስጢረ ሜሮን

ይህ ቃል የጽርዕ ቋንቋ ነው ትርጉሙም መአዛ ያለው የሚያውድ ፣ የሚጣፍጥ፣ ልብ የሚመስጥ ፣ ጣዕም ያለው መልኩ ጽርየቱ ዘይት ነው፡፡ በግዕዝ ቅብዕ፣ ቅብዐ ሜሮን ይባላል፡፡ ከብዙ እጽዋት ተቀምሞ የሚሰራ ነው፡፡ ሕዝበ እስራኤልን የሚያስተዳድሩ የእግዚያብሔር እንደራሴዎች ነገስታትን መሲሀን የሚባሉት ለዚህ ቅብ ተቀብተው ስለሚነግሱ ነው፡፡ ዘፍ.20፥23 1ሳሙ. 10፥1 ዘዳ. 28፥41 1ሳሙ. 9፡6 1ነገ 1፥34 ይህ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር የሚገለገልባቸው የቤተመቅደስ ነዋያተ ቅድሳትን አስቀድሞ በዚህ መታተም አለባቸው፡፡
ከተቀቡ በኋላ ለቤተ መቅደስ እንጂ ለተራ አገልግሎት አይውሉም ስለ ቅብዐ ሜሮን ቅዱስ መጽሐፍን የፃፉ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ቅብዐት ይሉታል፡፡ 2 ቆሮ.1፥21 ዮሐ.2፡20 ቅብዕን በመንፈስ ቅዱስ ማህተምን ይሉታል፡፡ ኤፌ. 1፥13 ፣4፥30 ይህ ቅብዓ ማህተመ ሕይወት በመሆኑ ለአገልግሎት ይውላል፡፡

3. ምሥጢረ ቁረባን

ይህ ቃል የሱርስት ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም አምኃ ስጦታ ማለት ነው፡፡ ሥጋውና ደሙ የተሰጠን በነፃ ያለ ዋጋ ሳይገባን በችሮታ ነውና፡፡ በቤተክርስቲያን ምሥጢራት ሁሉ መደምደሚ ቅዱስ ቁርባን ነው፡፡ መስዋዕት ማቅረብ የተጀመረው በአዳም ጊዜ ሲሆን ከአዳም እስከ ሙሴ የተነሱ አበው ሁሉ በህገ ልቦና ለእግዚአብሔር መስዋት ይሰው ቁርባን ያቀርቡ ነበር፡፡ መስዋዕታቸው ከእንሰሳ ቁርባናቸው ከእህልና ከአትክልት ማለት ከስንዴ እህል፣ ከወይን ፍሬ የሚቀርብ ነው፡፡
ዘመነ ኦሪት በብሉይ ኪዳን በሙክራብ የተሰዋ እንሰሳት ሁሉ በአዲስ ኪዳን በቤተክርስቲያን ለሚሰዋው ሁሉ የክርስቶስ ሥጋና ደም ምሳሌ ነበር፡፡ መልከ ጼዴቅ ያበረከተው ኅብስተ አኮቴት ጽዋዐ በረከት ለአምላክ የሥጋውና የደሙ ምሳ ሆነው አልፈዋል፡፡ ከምሥጢራት አንዱ መሆኑ ሕብስቱ ተለውጦ የክርስቶስ ሥጋ ጽዋው ተለውጦ የክርስቶስ ደም ሲሆን አይታይም፡፡ ነገር ግን እምነት ያለው ሁሉ በእምነት መነጽር ይመለከተዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ሳይታይ የሚወደድን ሕይወት ለማግኘት ከቁርባን በፊት ንስሐ መግባት ለአስራ ስምንት ሰዓት መጾም አለበት፡፡ ንጽሕናውን በጠበቅ አለበት፡፡ መምክረ ካህን ጸንቶ መገኘት ያስፈልጋል፡፡

4. ምሥጢረ ክህነት

ይህ ቋንቋ የግዕዝ ቋንቋ ነው፡፡ ተክህነ አገልገለ ከሚለው ግስ የወጣ ነው፡፡ ክህነት የተጀመረው በአባታች አዳም ነው፡፡ ክህነት የአገልግሎት ስም ሆኖ የቤተክርስቲያን ከፍተኛ መንፈሳዊ ማዕረግ ነው፡፡

እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ በልጅነት አክብሮ ነብይና ካህን አድርጎ ሾሞ በኦሪት በወንጌል ሥርዓት እስኪወሰን ድረስ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ የነበሩ አበው በበረከት አበው ከእግዚአብሔር እየተሾሙ ትንቢትን ክህነት ከቅዱሱ መንፈስ እየተቀበሉ (እየተሾሙ) በነብይነታቸው ያለውን የሚመጣውን ሲገልጽ ሲያስተምሩ በሀብተ ክህነታቸው መስዋዕት ሲቀርቡ ነበር፡፡ ክህነት በዘመነ ኦሪት ለሌዊ ነገድ ከተሰጠ በኋላ ሲወርድ ሲወራረድ እስከ ክርስቶስ ደርሷል፡፡ ታላቁ ሊቀ ካህናት እየሱስ ክርስቶስ እንደ ብሉይ ኪዳን መስዋዕት እንሰሳ ሳሆን እራሱን መስዋዕት፣ እርሱ ሰዋዒ ሆኖ ወደ መቅደስ ገብቷል፡፡ ዮሐ. 20፡22 ማቴ. 18፥18  1ቆሮ 4፥1 ማቴ.28፡20

5. ምሥጢረ ንስሐ

ይህ ቃል የግዕዝ ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም በሰሩት ኃጢያት መጸጸት ምነው ባልሰራሁት ባላደረኩት ብሎ ማልቀስ ወደ ኃጢያት ላለመመለስ መወሰን፣ በሕጉ ጸንቶ ለመኖር ቃል መግባት፡፡ ክርስቲያን በጥምቀት ከአለም ክፉ ስራዎች ሁሉ የተለየ ነው፡፡
ሕይወቱ ለክርስቶስ የተሰጠ ነው፤ /ሮሜ 12፥1/ የመጨረሻው ግቡና ዓላማው ሥርየተ ኃጢያትን ማግኘት እና የዘላለም ሕይወት መወረስ ነው፡፡ አካሉ የመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ /1ቆሮ 6-19/

6. ምሥጢረ ቀንዲል

ይህ ቃል የላቲን ቋንቋ ነው ትርጉሙም ፍፁም መብራት ማለት ነው፡፡ ከሰባቱ ሚስራት አንዱ ቀንዲል ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘይት የፈውስ ምልክት ነው፡፡ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዘው የሚሰቃዩ ህሙማን ወይም በድንገተኛ አጋጣሚ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ቁስለኞች እየተቀቡ ይፈወሱ ነበር፡፡ ኢሳ 1፡6፤ ሉቃ.10፥34 ራዕ.3፥18 ማር. 6፥13  ይህ ቅብዓተ በሐዲስ ኪዳን ለሚጠመቁ ከሚደረግ ቅብዐ ሜሮን ጋር ግንኙነት የለውም ራሱን የቻለ ሕሙማነ ሥጋ ብቻ ሳይሆን ሕሙማነ ነፍስ ኃጥአን የሚቀቡት ፈውስ የሚያገኙበት ነው፡፡ /ማር.6፥13 ያዕ.5፥13-15 ራዕ 1፥17፡፡

7. ምሥጢረ ተክሊል

ይህ ማለት “ተከለለ” ተቀናጀ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ በሥርዓተ ጋብቻ ቅደም ተከተል መሰረት በመተጫጨት እና በቃል ኪዳን የተመሰረተ ጋብቻ በተክሊል ይፈጸማል፡፡ ቤተክርስቲያን ምስክርነት የሚፈጸመው ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የሚያሰጥ ስለሆነ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ጋብቻ ትክክለኛነቱም የሚታወቀው በተክሊል ሥጋወ ደሙ ሲፈጸም ነው፡፡

ክርስቲያናዊ ጋብቻ ትክክለኛነቱም የሚታወቀው በትክሊል ሥጋወ ደሙ ሲፈጸም ነው፡፡ ዘፍ.1፥27-28 ፣ 2-18 ማቴ 19-4 እነዚህን ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን አውቀን ተረድተን የእምነታችን ፍጻሜ የሆነውን አምላካችንን ለተፈጠርንለት ዓላማ በመገዛት የነፍሳችንን መዳን ልናረጋግጥ ይገባል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ምንድንነው?

፩. ሥርዓት ቤተ ክርስቲያን  ምንድን ነው?

ሥርዓት “ሠርዐ” ሠራ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ደንብ፣ አሠራር፣ መርሐ ግብር ማለት ነው። ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ስንልም የቤተ ክርስቲያን ዕቅድ፣ የቤተ ክርስቲያን አሠራር መርሐ ግብር ወይንም ደንብ ማለታችን ነው። ሥርዓት የሚከተሉት ጥቅሞች አሉት፦
ሥራን ወጥ በሆነ መልኩ ለመፈጸም
ማንኛውንም ነገር ወጥና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመሥራት ከየት ተጀምሮ በየት በኩል ሄዶ በየት በኩል እንደሚጠናቀቅ ወጥ የሆነ የአሠራር ሥርዓት ይዘጋጅለታል። የአንድ ሥራ አሠራር በትክክል ካልተነደፈና አካሄዱ ካልተስተካከለ፤ ሥራው የተዘበራረቀ ይሆናል ፍጻሜውም አያምርም።
ማኅበረ ምዕመናንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ አንድ ዓይነት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያስፈልገናል። ብዙ ስንሆን አንድ ልቡና አንድ ሃሳብ የሚያደርገን ሥርዓት ነውና። /ኤፌ. ፬፥፫፤ የሐዋ. ፬፥፴፪፤ ሮሜ. ፲፭፥፮
የሃይማኖትን ምሥጢራት ለመጠበቅ
ሥርዓት የሃይማኖት መገለጫ ነው። ጥምቀት፣ ቁርባን፣ ጾም፣ ጸሎት፣ ሥግደት፣ ወዘተ በማመን ብቻ የሚያበቁ ሳይሆን የአፈጻጸምና አተገባበር መንገድ /ሥርዓት/ ያስፈልጋቸዋል። የእነዚህ ሁሉ ዝርዝር አፈጻጸም በሥርዓት ውስጥ ይካተታል። ስለዚህ በአንዲት ርትዕትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እምነት ሥር ያሉ ሁሉ ያቺን አንዲት እምነት የሚገልጹት አንድ ዓይነት በሆነ ሥርዓት ነው። ሥርዓት በመሠረተ እምነት /ዶግማ/ የምናምናቸውን በተግባር የምንገልጽበትና ተግባራዊ የምናደርግበት መንገድ ስለሆነ ሥርዓቱ ሲሠራና ሲፈጸም ሃይማኖታዊ አንድምታና ነጸብራቅ ይኖረዋል።

፪. ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን

ቤተክርስቲያን ማለት ሕንፃው፣ የክርስቲያኖች አንድነት ጉባኤ እና የምዕመኑ ሰውነት በመሆኑ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የምንለውም በእነዚህ በሦስቱ ላይ የተሠራውን ሥርዓት ነው። አንዳንዶቻችን ቤተ ክርስቲያንን ከራሳችን አርቀን ሌላ አካል አድርገን ስለምንመለከት ሥርዓቱ እኛን የሚመለከት አይመስለንም፤ ሥርዓቱ ግን የተሠራው ለሦስቱም የቤተ ክርስቲያን ትርጓሜዎች መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው።

ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ምንጩ ወይንም መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የቅዱሳን አባቶቻችን ጉባኤያት ውሳኔ /ሲኖዶስ/ እና አባቶቻችን ሊቃውንት በተለያዩ ጊዜ ያደረጓቸው ጉባኤያት ውሳኔዎች ናቸው፤ሰንበትን ማክበር፣በጻድቃን ስም አብያተ ክርስቲያናትን ማነጽ፣ የቁርባን ሥርዓት፣ የመሳሰሉት ከመጽሕፍ ቅዱስ የተገኙ ሥርዓቶች ናቸው። /ዘፍ. ፳፰፥፳-፳፪፤ ዘጸ. ፲፮፥፳፱፤ (የሐዋ. ፩፥፲፪/)

ወደ ቤተክርስቲያን የገባውንና የተቀደሰውን ንዋየ ቅድሳት እንደገና ወደውጭ አውጥቶ ለሥጋዊ ጥቅም ማዋል እንደማይገባ /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፩ ረስጣ ፳፰/፣ጥምቀት በፈሳሽ ውኃ መፈጸም እንዳለበት፣ ወንዶች ሴቶችን ሴቶች ደግሞ ወንዶችን ክርስትና እንዳያነሱ፣ ሥጋ ወደሙ ለመቀበል ፲፰ ሰዓት መጾም እንደሚገባሥጋ ወደሙ በምድር ላይ እንዳይወድቅ /እንዳይነጥብ/፣ ያላመኑ ሰዎች ሥጋ ወደሙን መቀበል እንደሌለባቸው፣ ወዘተ ያሉት ደግሞ በሲኖዶስ የቅዱሳን አባቶቻችን ጉባኤያት/ የተገኙ ሥርዓቶች ናቸው።

ከእናቱ፣ ከእህቱ፣ ከአክስቱ ወይንም እንደዚህ ባለ ሁኔታ ከምትታሰብ ሴት ጋር ካልሆነ በቀር አንድ ኤጲስ ቆጶስ፣ አንድ ቄስ፣ አንድ ዲያቆን፣ ወይንም ሌላ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ከማንኛውም ሴት ጋር አብሮ እንዳይኖር፤ ስለ መናፍቃን ጥምቀት፣ ስለ ትንሣኤ በዓል አከባበር፣ ስለ ድንግልና ኑሮ፣ ወዘተ ደግሞ በተለያዩ ጉባኤያት አባቶቻችን ያስተላለፏቸው ውሳኔዎችና ቀኖናዎች የተገኙ ሥርዓቶች ናቸው።

የቤተ ክርስቲያን አመሠራረትና የቅዳሴ አገልግሎት ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን አንጻር
መቼም በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን እየሰፋች ከሀገር ቤት አልፋ በውጭ ሀገርም አብያተ ክርስቲያናት እየታነጹ ስለሆነና ሁላችንም የቻልን ዘወትር ቅዳሴ በሚቀደስባቸው ዕለታት፣ ያልቻልን ደግሞ በዕለተ ሰንበት ለቅዳሴ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስለምንሄድ ስለ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አመሠራረት፣ አሠራርና ቡራኬ፣ እንዲሁም ስለ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር እንዴት መሆን እንዳለበት እንገነዘባለን። ለዚህም እንዲረዳን እንደሚከተለው እናያለን።
ቤተክርስቲያን ሲሠራ
ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ ቃሉ ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል /ቤቴሰ ቤተጸሎት ትሰመይ/ የሚለው /ኢሳ. ፶፮፥፮-፯፤ ኤር. ፯፥፲፩፤ ማቴ. ፳፩፥፲፫፤ ማር.  ፲፩፥፲፯፤ ሉቃ. ፲፱፥፵፮፤ ዮሐ. ፪፥፲፮-፲፯/ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን የዋዛ የፈዛዛ፣ የሳቅ የስላቅ፣ የጨዋታ፣ የመብል፣ የመጠጥ ቤት ሳትሆን፤ ምዕመናን ኃጢአት ቢሠሩ ሰለ ኃጢአታቸው የሚያዝኑባት የሚያለቅሱባት ንጹሕ የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ካህናት የሚያስተምሩባት ነው።

ምዕመናንም የሚማሩባት የግል ጸሎት፣ የማኅበር ጸሎት የሚጸልዩባት፣ በኅብረት የሚያስቀድሱባት ሥጋ  ወደሙ የሚቀበሉባት፣ የኃጢአት ሥርየት የሚያገኙባት፣ ሕፃናት በአርባ ቀንና በሰማንያ ቀን በጥምቀተ ክርስትና አማካኝነት ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት የሚቀበሉባት፣ ኢአማንያን የነበሩ በመምህራን ትምህርት አምነው ክርስቲያን የሚሆኑባት፣ ለክህነትም ሆነ ለአባልነት የዘር ሐረግ የማይቆጠርባት ዓለም አቀፋዊት የእግዚአብሔር ቤት ናት፡፡

አንዲት ቤተ ክርስቲያን ስትመሠረት ጀምሮ ሥርዓት አላት። የምትመሠረተው ባንድ ግለሰብ ስም ሳይሆን በካህናትና በምዕመናን ጥያቄ በሀገረ ስብከቱ ኤጲስ ቆጶስ ፈቃድና ትእዛዝ ነው፤ ካለኤጲስ ቆጶስ ፈቃድ ከመጽሐፉ ትዕዛዝ ወጥቶ አንዱ ቢያቋቁም ወይም ቢሠራ ቤተ ክርስቲያን ናት ብለው ለዘለዓለሙ በዛች ቤተ ክርስቲያን አይቁረቡባት፤ እንደገበያ፣ እንደእንስሳት በረት ፈት ሆና ትኑር ይላል።/ፍትሐነገሥት አንቀጽ ፩-፫/፤

ቤተክርስቲያን ለመሥራት ፈቃድ ከተገኘ በኋላ ስለ አሠራሯ የሚከተለው ሥርዓት ተሠርቶላታል። ቤተ ክርስቲያኗ ስትሠራ ደጆችና መስኮቶች አውጡላት ዛፍ ቅረጹላት ሐረግ ሳቡላት እንደሚል በተቻለ መጠን ሊያስጌጧት ይገባል የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናትና።  በሰማይ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት እንዲያበሩ፣ ሰባቱ ሰማያት ብሩሃን እንዲሆኑ ቤተ ክርስቲያንም ብርህት ትሁን፤ ይልቁንም ክቡራት መጻሕፍት ሐዲሳት፣ የጳውሎስ መልእክታት፣ የሐዋርያት መልእክታት፣ ግብረ ሐዋርያት በሚነበቡበት ጊዜ የበራች ትሁን፣ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ ያለውም ይህንኑ ያመለክታል። ማቴ. ፭፥፲፬/። ቅዱስ ወንጌል በሚነበብበት ጊዜ ግን ፈጽማ የበራች ትሁን፤ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ያለው ይሻል። /ዮሐ. ፱፥፭/።
ቤተክርስቲያን ሲባረክ
ቤተክርስቲያን ሕንፃዋ ተፈጽሞ በምትባረክበትና በምትቀደስበት ጊዜ ከኤጲስ ቆጶሱ ጋር ሰባት ቀሳውስት አብረውት ሊኖሩ ይገባል፣ ታቦቱም በሚባረክበት እንደዚሁ ሊሆን ይገባል፣ ኤጲስ ቆጶሱ እግዚአብሔር ሰውን የሚያከብርበት ራሱን የሚያስመስልበት ነውና ደስ በሚያሰኝ በቅብዐ ቅዱስ በሜሮን ያክብራት ያትማት፣ ታቦቱንም በመቅደስ ውስጥ በመንበር ያስቀምጡባት ከታቦቱ ጋራ የዮሐንስን ወንጌል ያኑሩ ከደቀ መዛሙርቱም በጌታ ኢየሱስ አጠገብ የሚቀመጥ ጌታ የሚወደው ቅዱስ ዮሐንስን ነበርና። /ዮሐ. ፲፫፥፳፫/ ።

ታቦቱም ሲቀረጽ ከላይ አልፋ፣ ቤጣ፣ የውጣ፣ ወኦ/ወዖ/ ይቀረጻል። ቀጥሎ እመቤታችንን፣ ከእመቤታችን ቀጥሎ ዮሐንስን፣ ቀጥሎ ቤተ ክርስቲያኑ የሚተከለው ታቦት መልአክም ቢሆን፣ ሰማዕትም ቢሆን፣ ጻድቅም ቢሆን ይቀረጻል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ካልተሟሉ ታቦቱን ሊቀድሱበት አይገባም።

ከቤተ ክርስቲያን የገባ ዕቃ የወርቅ፣ የብር፣ ፃሕል ጽዋእ እርፈ መስቀል ቢሆን ንዋየ ቅድሳት ነው ተብሎ አቡነ ዘበሰማያት ከተደገመበት በኋላ ከቤታቸው ወስደው በፃሕሉ ፈትፍተው ሊበሉበት በጽዋው ቀድተው ሊጠጡበት አይገባም። ደፍረው ቢያደርጉ ሥርዓት ማፍረስ ነውና ይህን ያደረገ ቢኖር በአንድ ሁለት ተቀጥቶ ንሰሐውን እሰኪፈጽም ከምዕመናን ይለይ። /ዳን. ፭፥፩-፴፩/።

በቤተ ክርስቲያንም ኤጲስ ቆጶሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናትና ምዕመናን እንዴት መቆም እንዳለባቸው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚከተለው ይገልጻል። ኤጲስ ቆጶሳት የቤተ ክርስቲያን አዛዚያን እንደመሆናቸው በታቦቱ ፊት ይቁሙ፣ ቀሳውስትም መምህራን እንደመሆናቸው ከኤጲስ ቆጶሳት ቀጥለው ይቁሙ፣ ሊቀዲያቆናትም ከኤጲስ ቆጶስ አጠገብ ይቁሙ፣ ዲያቆናትም አገልጋዮች እንደመሆናቸው ከቀሳውስት ቀጥለው ይቁሙ፣ ከዲያቆናት ቀጥለው ሕዝቡ ሁሉ ባንድ ቦታ ይቁሙ፣ የሚበቃ ቦታ ቢኖር ሕፃናት በአንድ ወገን ለብቻቸው ይቁሙ።

የሚበቃ ቦታ ከሌለ ግን ከአባቶቻቸው ጋራ ተስገው ይቁሙ፣ እንደዚሁም ሴቶች ባንድ ወገን /ቦታ/ ለብቻቸው ይቁሙ፣ ቦታ ቢገኝ ሕፃናት ሴቶች ባንድ ወገን ለብቻቸው ይቁሙ፣ ቦታ ባይኖር ግን ሕፃናቱ በፊት እናቶች በኋላ ይቁሙ፣ ደናግላን ሴቶችና ባልቴቶች ግን ከሴቶች በላይ ይቀመጡ ። /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፪ ድስቅ ፲፪ ኒቅያ ፷፩/።

ሥርዓተ ቅዳሴ

በቅዳሴ ጊዜ ስለሚደረጉና ሰለማይደረጉ ነገሮች ደግሞ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚከተለው ያዝዛል፦
በቅዳሴ ጊዜ የሚስቅ ሰው ቅዱስ ባስልዮስ በጻፈው በ፸፪ኛው አንቀጽ ካህን ቢሆን የሚያቀብል ነውና ሥጋ ወደሙን ከተቀበለና ካቀበለ በኋላ ወጥቶ አንድ ሱባዔ ይቀጣ ይጹም ይስገድ፣ የሳቀው ሕዝባዊ ቢሆን ግን ሥጋ ወደሙን ሳይቀበል ያን ጊዜ ፈጥኖ ይውጣ ይላል።

ምነው ፍርድ አበላለጠ ካህኑን ተቀብሎ ወጥቶ ይቀጣ አለ፤ ሕዝባዊውን ሳይቀበል ወጥቶ ይሂድ አለ ቢሉ ካህኑ የሚቆመው ከውስጥ ነው ሲስቅ የሚያየው የለም። ካህኑ በቅዳሴ ጊዜ ቅዳሴውን ጥሎ ወጥቶ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ቄስ እገሌ አባ እገሌ በመሥዋዕቱ ምን አይተውበታል ብለው መሥዋዕቱን ሳይቀር ይጠራጠሩታል፤ ስለዚህ ነው። ምዕመኑ ግን ሲስቅ ሁሉ ያየዋልና ለሌላ መቀጣጫ እንዲሆን፤ በቤተ መቅደስ የማይወደድ ሌላ ነገር አይናገር፤ በቤተ መቅደስ ጭንቅ፣ ደዌ ሳያገኘው አንዱን ስንኳ ምራቁን እንትፍ አይበል። ነገር ግን ደዌ ቢያስጨንቀው ድምፅ ሳያሰማ ምራቁን በመሐረቡ ተቀብሎ ያሽሸው።

በቤተ ክርስቲያንና በቅዳሴ ጊዜ ማንም ማን ዋዛ ፈዛዛ ነገር የሚናገር አይኑር፣ ቤተ ክርስቲያን በፈሪሃ እግዚአብሔር ሆነው የሚጸልዩባት የጸሎት ቦታ ናትና ቅዳሴው ሳይፈጸም አቋርጦ መውጣት አይቻልም፣ አይፈቀድም፣ በጣም ጭንቅ ምክንያት ወይም በሕመም ምክንያት ከሆን ግን ክቡር ወንጌል ከተነበበ በኋላ ሊወጣ ይችላል። በቅዳሴ ጊዜ ካህናት የሚቀድሱባቸው አልባሳት ነጫጭ ይሁን ነጭ ልብስ ደስ እንዲያሰኝ በሥጋ ወደሙ የተገኘ ክብርም ደስ ያሰኛልና፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ባህርየ መለኮቱን በገለጸ ጊዜ ልብሱ እንደበረድ ነጭ ሆኗል። መላእክትም ወርኃ ሰላም ወርኃ ፍስሐ ነው ሲሉ የልደት፣ የትንሣኤ፣ የዕርገት ነጫጭ ልብስ ለብሰው ታይተዋል።

አንድ ሰው እንኳ ጫማ አድርጎ ከቤተ መቅደስ አይግባ ልዑል እግዚአብሔር የምትቆምባት ደብረ ሲና የከበረች ናትና ጫማህን አውልቅ ብሎ ለሙሴ ተነግሮታልና። /ዘጸአት ፫-፭/ ።

በቅዳሴ ጊዜ ተሰጥዖውን የማያውቅ ደግሞ በአንክሮ፣ በተዘክሮ፣ በአንቃእድዎ፣ በንጹሕ ልቡና፣ በሰቂለ ሕሊና ሆኖ ሕሊናው ወደ ዓለማዊ እንዳይወስደው መቆጣጠር አለበት።

ቅዱስ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ካህኑ ለሕዝቡ ተርጉሞ ይንገራቸው ያስተምራቸው እጁንም በሚታጠብበት ጊዜ የተጣላችሁ ሳትታረቁ፣ የሰው ገንዘብ የወሰዳችሁትን ሳትመልሱ ሥጋ ወደሙን ብትቀበሉ ሥጋው እሳት ሆኖ ይፈጃችኋል ደሙ ባህር ሆኖ ያሰጥማችኋል። ነገር ግን የወሰዳችሁትን የሰው ገንዘብ መልሳችሁ፣ ከተጣላችሁት ታርቃችሁ ኃጢአት ብትሰሩ ንስሐ ገብታችሁ ብትቀበሉት ግን መድኃኒተ ሥጋ መድኃኒተ ነፍስ ይሆናችኋል። በረከተ ሥጋውን በረከተ ነፍሱን ያድላችኋል ብሎ ይንገራቸው ያስተምራቸው ይላል።

በቅዱስ ቁርባን ጊዜም አስቀድሞ ሊቃነጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ በቁምስና መዓርግ ያሉ መነኮሳት፣ ቀጥሎ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ ወንዶች በአርባ ቀን የሚጠመቁ ሕፃናት ከሁሉ አስቀድመው ይቀበሉ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይእ መላእክትን ይመስላሉና። ከነዚህ ቀጥሎ ከአርባ ቀን በኋላ እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉት ሕፃናት ትንሾቹ በፊት እየሆኑ እንደየዕድሜያቸው ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው /ክህነት የሌላቸው/ በድንግልና ኑረው የመነኮሱ ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው ሃያ፣ ሃያ ሁለት ዓመት የሆናቸው ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው በሹመት ያሉ ናቸውና ንፍቀ ዲያቆናት፣ አናጉንስጢሳውያን፣ መዘምራን ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው የንስሐ ሕዝባውያን በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።

በሴቶችም በኩል ከሁሉ አስቀድሞ የተጠመቁ የሰማንያ ቀን ሕፃናት ይቀበላሉ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይእ መላእክትን ይመስላሉና፤ ከነዚያ ቀጥሎ ከሰማንያ ቀን እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉ ሕፃናት እንደየዕድሜያቸው ሕፃናቱ አስቀድመው ታላላቆች ቀጥለው ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው አሥራ ሁለት፣ አሥራ አምስት የሆናቸው ደናግል ይቀበላሉ።

ከነዚያ ቀጥለው የቀሳውስት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በሕግ ኑረው የመነኮሱ እናቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያው ቀጥለው የዲያቆናት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በንሰሐ ተመልሰው የመነኮሱ መነኮሳት እና መነኮሳይያትይቀበላሉ፤ ከነዚያ በኋላ የንፍቀ ዲያቆናት፣ የአናጉንስጢሳውያን፣ የመዘምራን ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በሕግ ጸንተው ያሉ ሕጋውያን እናቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው የንስሐ ሕዝባውያን ሚስቶች በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።

ከዚህ በኋላ ካህኑ ሥጋ ወደሙን በፈተተበት እጁ ሕዝቡን ፊታቸውን ይባርካቸው። ቀሳውስት ግን እጅ በእጅ ተያይዘው እርስ በርሳቸው ይባረኩ። ቀዳሹ ካህን ቀሳውስትን ሲያሳልም “የጴጥሮስን ሥልጣን ባንተ አለ” ይበል፣ ተሳላሚው ቄስም “መንግሥተ ሰማያት ያውርስህ ከሾመ አይሻርህ” ይበል። ለዲያቆናትም “ልዑል እግዚአብሔር ያክብርህ ይባርክህ፣ ለማስተማር ዓይነ ልቡናህን ያብራልህ፣ ምሥጢሩን ይግለጥልህ” እያለ ይባርካቸው። ለምዕመናንም “ልዑል እግዚአብሔር ያክብርህ፣ ይባርክህ፣ ገጸ ረድኤቱን ይግለጽልህ” እያለ ይባርካቸው። ለሴቶችም “ልዑል እግዚአብሔር ይባርክሽ፣ ያክብርሽ ገጸ ረድኤቱን ይግለጽልሽ” ብሎ በእጁ ይባርክ።