ባሕረ ሐሳብ ቁጥር ያለው ዘመን
ክፍል አንድ፡- መግቢያ
ባሕረ ሐሳብ የሚለው ቃል ሐሰበ ቆጠረ ከሚለው ግስ የወጣ ዘር ሲሆን ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን (ዓመተ ዓለም) ማለት ነው፡፡ ሐሳበ ባሕር የሚልም አለ፤ የዘመን ቁጥር ማለት ነው፡፡ በባሕር የተመሰለው ዘመን ነው፡፡ ‹‹እስመ በመዳልው ተደለወ ዓለም ወበመስፈርት ሰፈሮ ለባሕር፡፡›› (ዕዝራ ሱቱኤል ፪÷፴፯) (ይኽ ዓለም በሚዛን ተመዝኗልና ባሕሩንም በመስፈሪያ ሰፍሮታልና) እንዲል፡፡ ባሕር በውስጡ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ከጥቃቅን ነፍሳት እሰከ ግዙፋን ዓሣ ነባሪዎች ወስኖ ይይዛል፡፡ ‹‹ዛቲ ባሕር ዐባይ ወረሓብ፤ህየ ዘይትሐወስ ዘአልቦ ኊልቍ፡፡ እንስሳ ዐበይት ምስለ ደቃቅ›› (መዝ ፻፫፥፳፭) (ይኽች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት፡፡ በዚያ ሥፍር ቁጥር የሌለው ተንቀሰቃሽ ታላላቆችና ታናናሾች እንስሳዎች አሉ) እንዲል፡፡ ዘመንም በውስጡ ከዓመቶች እስከ የደቂቃ ክፍልፋዮች ይወስናልና ዘመንን በባሕር ብለውታል፡፡ ባሕረ ሐሳብ በሚለው መርሐ ዕውር የሚሉ አሉ፡፡ የዕውር መመሪያ ዕውርን የሚመራ እንደ ማለት ሲሆን አቡሻኽርም ይባላል፡፡ አቡሻኽር በ13ኛው ምእት ዓመት የነበረና ባሕረ ሐሳብን የመረመረ (ያጠና) የቁጥር ሊቅ ሲሆን ድርሰትን በደራሲው ስም መጥራት አዲስ ነገር አይደለምና ትምህርቱ በደራሲው ስም አበሻኽር ተብሏል፡፡
ባሕረ ሐሳብን በመጀመሪያ ሙሴ፣ በኋላም ሐዋርያት፣ ከሐዋርያት ቀጥሎ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ድሜጥሮስ፣ በመጨረሻም አቡሻኽር እንዳቀነባበሩት የባሕረ ሐሳብ መምህራን ያስተምራሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ አርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀምበትን የጊዜ መቁጠሪያ ያዘጋጀው ከ፪፻ እስከ ፪፻፵ ዓ.ም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ድሜጥሮስ ነው፡፡
ቅዱስ ድሜጥሮስ በዓላት እና አጽዋማት በጥንተ ተርክቧቸው የሚውለሉበትን የቁጥር ሕግ ለማግኘት ተመኝቶ ሱባዔ ቢገባ የመጥቅዕና የአበቅቴ መንገድ እንዴት እንደሆነ ተገለጾለታል፡፡ የኽን ሱባዔ ገብቶ የተገለጸለትን ለሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት ጽፎ ልኮላቸው ተቀብለውታል፤ በአገራችንም ሲሠራበት ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዘመን አቆጣጠር መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈውን መሠረት በማድረግ ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ብሎ ነው የሚጀምረው፡፡ በዚህ መሠረት ዓለም ከተፈጠረበትና ዘመን ከተቆጠረ ከተቆጠረበት ጊዜ ጀምሮ አሁን እስካለንበት 2018 ዓ ም ያለው ዘመን 7518 ሆነ ይሏል በዘመነ ማርቆስ ወንጌላዊ፡፡
ከኢየሰስ ክርስቶስ ልደት በፊት ነበረው ዘመን 5500 ዓመታት ሲሆን ይኽ ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኵነኔ ይባላል፡፡ ከልደተ እግዚእ እስከ አሁን ያለው 2018 ዘመን ዓመተ ምሕረት ዓመተ ሥጋዌ ነው የሚባለው፡፡ መላው 7518 ዘመን ግን ዓመተ ዓለም ይባላል፡፡ ለዚኽም መሥፈሪያ መቁጠሪያ 7 አዕዋዳት (ዐውዶች) አሉት፡፡ እነሱም፡-
(1) ዐውደ ዕለት፣
(2) ዐውደ ወርኅ፣
(3) ዐውደ ዓመት፣
(4) ዐውደ አበቅቴ፣
(5) ዐውደ ፀሐይ፣
(6) ዐውደ ማኅተም እና
(7) ዐውደ ቀመር ናቸው፡፡
ዐውድ ማለት በአማርኛ ዙሪያ ክብ እንደ ቀለበት እንደ አምባር ዙሮ የሚገጥም የጊዜ መቁጠሪያ ማለት ሲሆን ሲበዛ አዕዋድ (አውዶች) ይሆናል፡፡ አዕዋዳት ይፈጸማሉ እንጂ አያልቁም፡፡ አንድ ዐውድ ሲፈጸም እሱን የሚመስል ሌላ ዐውድ የተካበታል፡፡ እንዲህ እያለ አንዱ ሲፈጸም ሌላው እየተተካ ይቀጥላል እንጂ አዕዋድ መለቂያ የላቸውም፡፡
- ዐውደ ዕለት፡- ዐውደ ዕለት ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ያሉት ሰባቱ ዕለታት ናቸው፡፡ እነዚህም ወሮችን ለማስግኜት በ7 በ7 ዕለታት ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡
- ዐውደ ወርኅ፡- ዐውደ ወርኅ በፀሐይ ዘወትር 30 ቀን ነው፡፡ በጨረቃ አንድ ጊዜ 29 አንድ ጊዜ 30 ዕለታት ይሆናል፡፡ እነዚኽም ዓመታትን ለማስገኘት በ30 በ30 ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡
- ዐውደ ዓመት፡- ዐውደ ዓመት በፀሐይ 365 ዕለት ከስድስት ሰዓቶች ሲሆን በጨረቃ 354 ዕለት ከኻያ ሁለት ኬክሮስ ነው፡፡ እነዚህ ሦስቱ ዐውዶች በዕለት ሌሎቹ አራቱ ደግሞ በዓመት ይለካሉ፡፡
- ዐውደ አበቅቴ፡- ዐውደ አብቅቴ 19 ዓመት ሲሆን ዐውደ ንዑስ ቀመር በመባልም ይታወቃል፡፡ በዚህም ፀሐይና ጨረቃ መንገዳቸውን ፈጽመው በተፈጠሩት ኆኅት ተራክበ ያደርጉበታል፡፡ ፀሐይ በየዓመቱ 365 ሰትዞር ጨረቃ ግን በየዓመቱ 354 ዕለታት ብቻ ትዞራለች፡፡ ሁለቱ በየዓመቱ ተለያይተው ሲዞሩ ቆይተው በአሥራ ዘጠነኛው ዓመት አንድ ጊዜ በተፈጠሩበት ኆኅት የገናኛሉ፤ የህም ዐውደ አበቅቴ ይባላል፡፡
- ዐውደ ፀሐይ፡- ዐውደ ፀሐይ ማለት 28 ዓመት ሲሆን በየኻያ ስምንት ዓመቱ ዙሮ የሚመጣ ማለት ነው፡፡ በዚህም ዕለትና ወንጌላዊ ይገናኙበታል፡፡ ዕለቱ ፀሐይ የተፈጠረችበት ረቡዕ ነው፡፡ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ ነው፡፡
- ዐውደ ማኅተም፡- ዐውደ ማኅተም 76 ዓመት ሲሆን ዐውደ ማዕከላዊ ቀመርም ይባላል፡፡ በዚህም አበቅቴና ወንጌላዊ የገናኙበታል፡፡ አበቅቴው 18ት ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው፡፡ ‹‹ጥንቱ ለቀመር ዕለተ ሠሉስ ወወንጌላዊ ማቴዎስ ወፍጻሜሁ ዕለተ ሰኑይ ወወንጌላዊ ዮሐንስ›› (የቀመር መነሻው ማክሰኞ ዕለት ወንጌላዊው ማቴዎስ ሁኖ መጨረሻው ዕለተ ሰኑይ ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው፡፡) ዐውደ ማኅተም መባሉም አበቅቴው ለአበቅቴ ወንጌላዊዉም ለወንጌላውያን ፍጻሜ ስለሆነ ነው፡፡
- ዐውደ ቀመር፡- ዐውደ ቀመር 532 ዓመት ሲሆን ዐውደ ዐቢይ ቀመርም ይባላል፡፡ በዚህም ዕለት፣ ወንጌላዊ እና አበቅቴ ሦስቱም ይገናኙበታል፡፡ ዕለቱ ሠሉስ፣ ወንጌላዊው ማቴዎስ፣ አበቅቴው አልቦ ነው፡፡ ነገረ ግን በዐውደ ፀሐይ ቦታ ዐውደ ማኅተም በዐውደ ማኅተም ቦታ ዐውደ ፀሐይ የሚል አበነት የገኛል፡፡ ከሁለቱ አንዱ የቀረ እንደሆነ ባሕረ ሐሳብ ለማውጣት ከቀመር ገብቶ የቆጠራል፡፡ እስከዚህ መቅድም ነው፡፡
ክፍል ሁለት ፡- መጥቅዕ እና አበቅቴ
በዓላት የሚውሉበትና አጽዋማት የሚገቡበትን ዕለት ለማግኘት ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን 6 መሠረታዊ ነገሮች መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እነሱም፡- (1) መደብ፣ (2) ወንበር፣ (3) አበቅቴ፣ (4) መጥቅዕ፣ (5) መባጃ ሐመር እና (6) ተውሳክ ናቸው፡፡
- መደብ፡- መደብን ለማግኘት ዓመተ ዓለምን (7518) ለ19 በማካፈል እናገኛለን፡፡
- ወንበር፡- ወንበርን ለማገኘት ከመደብ 1ን ለዘመን በመተው ወንበርን እናገኛለን፡፡
- አበቅቴ፡- አበቅቴ ማለት ስፍረ ሌሊት ቁጥረ ሌሊት ተረፈ ዓመት ማለት ነው፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ያሉትን የሌሊቱንና የጨረቃን ኅድረት ከመዓልት ለይቶ ለማወቅ ይጠቅማል፡፡
- መጥቅዕ፡- መጥቅዕ ማለት ደወል ማለት ነው፡፡ ደወል ሲመታ ሕዝብ ይሰበሰባል፡፡ በዓላት የሚውሉበት፣ አጽዋማት የሚገቡበት ዕለት የሚታወቀውም በመጥቅዕ ነውና መጥቅዕ ደወል ይባላል፡፡ በዚህ መሠረት መጥቅዕ ከዕለታት ተውክ ጋር ተደምሮ መባጃ ሐመርን ያስገኝልናል፡፡
- መባጃ ሐመር፡- መባጃ ሐመር ባጀ ቆየ ካለው ግስ የተገኝ ቃል ሲሆን፡፡ ማቆያ ማክረሚያ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል፡፡ መባጃ ሐመር ከመጥቅዕ እና ከዕለታት ተውሳክ ጋር ተደምሮ አጽዋማትና በዐላት የሚውሉበትን ዕለት ያስገኝልናል፡፡ ከሰባቱ አጽዋማት ማካከል በመባጃ ሐመር የሚወጡት አራቱ (ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያትና ጾመ ድኅነት) ብቻ ናቸው፡፡
- ተውሳክ፡- ተውሳክ ማለት ለአንድ ዕለት ወይም በዓል እና ጾም የተሰጠ ልዩ ቁጥር ማለት ነው፡፡ በዓላት የሚውሉበትንና አጽዋማት የሚገቡበትን ዕለት ማወቅ የሚቻለው በተውሳክን ከመባጃ ሐመር ጋር ደምረን በምናገኘው ስሌት ነው፡፡
የዕለታት ተውሳክ
የሳምንቱ ዕለታት እንደ በዓላቱና አጽዋማቱ ሁሉ ተውሳክ አላቸው፡፡ ተውሳክ መባላቸውም ከበዓለ መጥቅዕ ጋር ተደምረው መባጃ ሐመርን ስለሚያስገኙ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ የዕለታት ተውሳክ በቅዳሜ የጀምራሉ፡፡ እነሱም፡-
| ተ.ቁ | ዕለታቱ | ተውሳካቸው |
| 1 | ቅዳሜ | 8 |
| 2 | እሑድ | 7 |
| 3 | ሰኞ | 6 |
| 4 | ማክሰኞ | 5 |
| 5 | ረቡዕ | 4 |
| 6 | ሐሙስ | 3 |
| 7 | ዐርብ | 2 |
ናቸው፡፡ የዕለታት ተውሳክ ከበዓለ መጥቅዕ ጋር ተደምሮ መበጃ ሐመርን ያስገኝልናል፡፡
መባጃ ሐመር= መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ዕለት ተውሳክ ነው፡፡ መባጃ ሐመርን ለማግኘት መጥቅዕን፣ መጥቅዕና አበቅቴን ለማግኘት ወንበረን፣ ወምበርን ለማወቅ ደግሞ የመደብን ዓመታዊ ስሌት ማወቅ አለብን፡፡ በዚህ መሠረት በዘመነ ማርቆስ የ2018 ዓመተ ምሕረትን መባጃ ሐመር ለማግኘት መጀምሪያ መደብን ማግኘት አለብን፡፡
መደብን ለማገኘት፡- መደብ = ዓመተ ፍዳ ዓመተ ከነኔ + ዓመተ ምሕረት ዓመተ ሥጋዌ÷ 19
5500 + 2018 =7518 ÷ 19 = 395 ቀሪ 13፣ በዘመነ ማርቆስ 2018 ዓ ም መደብ 13
ወንበር ለማወቅ፡- ወምበር = መደብ – 1 = 13 -1 = 12 በ2018 ዓ ም ወምበር 12 ወጣ፡፡ ከዚህ በመነሣት መጥቅዕንና አበቅቴን ማግኝት እንችላለን፡፡
መጥቅዕን ለማገኘት፡- መጥቅዕ = ወምበር × ጥንተ መጥቅዕ ÷ 30
12 × 19 = 228 ÷ 30 = 7 ቀሪ 18 ስለዚህ በ2018 ዓ ም መጥቅዕ 18 ሆነ፡፡
አበቅቴን ለማግኘት፡- አበቅቴን ለማግኜት፡- ጥንተ አበቅቴን ከወምበር ጋር ማባዛት ከዚያም በ30 መግደፍና ቀሪውን መያዝ፡፡ አበቅቴ = ጥንተ አበቅቴ × ወምበር ÷ 30 = 11 × 12 = 132 ÷30 = 4 ደርሶ 12 የቀራል፡፡ በ2018 ዓ ም በዘመነ ማርቆስ አበቅቴ 12 ሆነ፡፡
አበቅቴ የሚጠቅመን ከዕለትና ከሕጸጽ ጋር ተደምሮ ሌሊትን ለማሰገኘት ነው፡፡ መጥቅዕ ቢያንስ አበቅቴ ቢበዛ ወይም አበቅቴ ቢያንስ መጥቅዕ ቢበዛ ሁል ጊዜ አበቅቴና መጥቅዕ ተደምረው ከ30 አያንሱም፤ ከ30 አይበልጡም፡፡ ‹‹መጥቅዕ ወአበቅቴ ኢይበዝኁ ወኢይውሕዱ እም ፴ ወትረ ይከውኑ ፴›› (መጥቅዕና አበቅቴ በኅብረታቸው ከ30 አይበዙም ከ30ም አይጎድሉም ዘወትር 30 ይሆናሉ) እንዲል፡፡
መባጃ ሐመር ለማገኘት፡- መባጃ ሐመር = መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ዕለት ተውሳክ
አሁን መጥቅዕ 18 መሆኑን ስላወቅን መባጃ ሐመርን ለማግኘት በዓለ መጥቅዕ የሚውልበትን ዕለት ተውሳክ ማግኘት አለብን፡፡ መጥቅዕ ሲበዛ ከመስከረም ንዛ፤ መጥቅዕ ሲያንስ ጥቅመትን ዳስ (መጥቅዕ ሲበዛ በዓለ መጥቅዕን በመስከረም ዐውል፡፡ መጥቅዕ ሲያንስ በዓለ መጥቅዕን በጥቅምት ዐውል፡፡) በሚለው መርሕ ተመሥርተን በዓለ መጥቅዕ የሚውልበትን ዕለት ማገኘት እንችላለን፡፡ መጥቅዕ በዛ የሚባለው ከ14 በላይ፣ አነሰ የሚባለው ከ14 በታች ሲሆን ነው፡፡ በዚህ ዓመት መጥቅዕ ከ14 በላይ 18 ስለሆነ በዓለ መጥቅዕ መስከረም 18 እሐድ ዕለት ይውላል፡፡ በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ዕለት የእሑድ ተውሳክ 7 + 18 = 25 ይሆናል፡፡ መባጃ ሐመር የሚባለው በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ዕለት ተውሳክ እና የመጥቅዕ ድምር ሰለሆነ፣ በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ዕለት ተውሳክ እና የመጥቅዕ ድምር (7 + 18) ደግሞ 25 በመሆኑ በዘመነ ማርቆስ 2018 ዓ ም መባጃ ሐመር 25 ይሆናል፡፡
መባጃ ሐመር ዋነኛ አገልግሎቱ ከበዓላትና አጽዋማት ተውሳክ ጋር እየተደመረ በዓላትና አጽዋማትን ማስገኘት ነው፡፡ በተለይ ጾመ ነነዌ የራሱ ተውሳክ ስለሌለው የሚወጣው በመባጃ ሐመር ነው፡፡ ጾመ ነነዌ የሚጀምርበትን ቀን ፈለጎ ለማገኘት የሚየገለግለን በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ወር ነው፡፡ ምክንያቱም በዓለ መጥቅዕ በመስከረም በሚውልበት ጊዜ የነነዌ ጾም በጥር ይውላል፡፡ በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት በሚውልበት ጊዜ የነነዌ ጾም በየካቲት የውላልና ነው፡፡ በ2018 ዓ ም በዘመነ ማርቆስ በዓለ መጥቅዕ በመስከረም ስለዋለ የነነዌ ጾም በጥር ወር ይጀምራል፡፡ ጾመ ነነዌ ተውሳክ ስለሌለውና በመባጃ ሐመር የሚወጣ ስለሆነ መባጃ ሐመር ደግሞ 25 በመሆኑ ጥር በባተ በ25 ዘመነ ማርቆስ (2018 ዓ ም) ጾመ ነነዌ ይጀምራል፡፡
ክፍል ሦስት ፡- በመባጃ ሐመር የሚንቀሳቀሱ በዓላትና አጽዋማት
በመባጃ ሐመር የሚወጡ በዓላትና አጽዋማት የሚገኙት አራት ነገሮችን በመደመር ነው፡፡ እነሱም፡- (1) መጥቅዕ፣ (2) መጥቅዕ የሚውልበት ዕለት ተውሳክ፣ (3) የበዓላትና አጽዋማት ተውሳክ እና (4) የነነዌ መባጃ ሐመር ናቸው፡፡ የዐቢይ ጾምን ተውሳክ ለማግኘት ከነነዌ መግቢያ እስከ ዐቢይ ጾም ያሉትን ዕለታት መቁጠር ነው፡፡ ከነነዌ መግቢያ እስከ ዐቢይ ጾመ መግቢያ ያሉት ዕለታት 14 ስለሆኑ የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14 መሀኑን በቃላሉ ማግኘት እንችላለን፡፡
የበዓላትና አጽዋማት ተውሳክ
| በዓላትና አጽዋማት | ተውሰካቸው | ተውሳክ ሲደመር መባጃ ሐመር | በዐላትና አጽዋማት
የመውሉበት ዕለት |
| ጾመ ነነዌ | መባጃ ሐመር | 25 | ጥር 25 ጾመ ነነዌ |
| ዓቢይ ጾም | 14 | 14 + 25 = 39 – 30 = 9 | የካቲት 9 ዓቢይ ጾም |
| ደብረ ዘይት | 11 | 11 + 25 = 36 – 30 = 6 | መጋቢት 6 ደብረ ዘይት |
| ሆሣዕና | 2 | 2 + 25 = 27 = 27 | መጋቢት 27 ሆሣዕና |
| ስቅለት | 7 | 7 + 25 = 32 – 30 = 2 | ሚያዝያ 2 ስቅለት |
| ትንሣኤ | 9 | 9 + 25 = 34 -30 = 4 | ሚያዝያ 4 ትንሣኤ |
| ርክበ ካህናት | 3 | 3 + 25 = 28 | ሚያዝያ 28 ርክበ ካህናት |
| ዕርገት | 18 | 18 + 25 = 43 -30 = 13 | ግንቦት 13 ዕርገት |
| ጰራቅሊጦስ | 28 | 28 + 25 = 53 – 30 = 23 | ግንቦት 23 ጰራቅሊጦስ |
| ጾመ ሐዋርያት | 29 | 29 + 25 = 54 – 30 = 24 | ግንቦት 24 ጾመ ሐዋርያት |
| ጾመ ድኅነት | 1 | 1 + 25 = 26 | ግንቦት 26 ጾመ ድኅነት |
ክፍል አራት፡- ኢየዐርግና ኢይወርድ
- ጾመ ነነዌ ከጥር 17 አትወርድም ከየካቲት 21 አትወጣም፡፡
- ዐቢይ ጾም ከየካቲት አንድ ወደታች አይወርድም ከመጋቢት 5 ወደላይ አይወጣም፡፡:
- ደብረ ዘይት ከየካቲተት 28 ወደታች አይወርድም ከሚያዝያ 2 ወደላይ ፤አይወጣም፡፡
- ሆሣዕና ከመጋቢት 19 ወደ ታች አይወርድም ከሚያዝያ 23 ወደላይ አይወጣም
- በዐለ ስቅለት ከመጋቢት 24 ወደታች አይወርድም ከሚያዝያ 28 ወደላይ አይወጣም፡፡
- ትንሣኤ ከመጋቢት 26 ወደታች አይወርድም ከሚያዝያ 30 ወደላይ አይወጣም፡፡
- ርክበ ካህናት ከሚያዝያ 20 ወደታች አይወርድም ከገንቦት 24 ወደላይ አይወጣም፡፡
- ዕርገት ከግንቦት አመስት ወደታች አይወርድም ከሰኔ 9 ወደላይ አይወጣም፡፡
- ጰራቅሊጦስ ከገንቦት 15 ወደታች አይወርድም ከሰኔ 19 በላይ አይወጣም፡፡
- ጾመ ሐዋርያት ከግንቦት 16 በታች አይወርድም ከሰኔ 20 በላይ አይወጣም፡፡
- ጾመ ድኅነት ከግንቦት 18 ባታች አይወርድም ከሰኔ 22 በላይ አይወጣም፡፡
ክፍል አምስት ፡- ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘመን አቆጣጠር የተሰየመው የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በጻፉ አራቱ ወንጌላውያን ነው፡፡ ስያሜውም ዓመቱ ዘመነ ማቴዎስ፣ ዘመነ ማርቆስ፣ ዘመነ ሉቃስ እና ዘመነ ዮሐንስ እየተባለ የሚሰየም ሲሆን ስያሚው በየ4 ዓመቱ ከአራቱ ወንጌላውያን ለአንዱ የሚደርስ ይሆናል፡፡ በዚህ መሠረት በያዝነው ዓመት 2018 ዓመተ ምሕረት ተሿሚው ወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ በመሆኑ ዘመኑ ዘመነ ማርቆስ ወንጌላዊ ይባላል፡፡ የቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር!!!
በዕውቀቱ ይልማ



