ፍልሰተ ዐፅሙ ለአቡነ ተክለ ይማኖት
ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በምድራዊ ሕይወታቸው እጅግ ጽኑዕ የኾነ መንፈሳዊ ተጋድሎ ካደረጉና በመላው ኢትዮጵያ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ከፈጸሙ በኋላ፣ነሐሴ ፳፪ ቀን በክብር ዐርፈው ተቀበሩ።
ጻድቁ አባታችን ከዚኽ ዓለም ድካም ከተለዩከ፶፯ ዓመታት በኋላ ለመንፈስ ልጃቸው ለአባ ሕዝቅያስ በሕልም «ጌታዬ ሥጋህን ያፈልሳሉ ያለኝ ዘመን ደርሷልና ልጆቼን ዅሉ ቅጠራቸው፤ እኔና ቅዱስ ሚካኤል ከወዳጄ አባ ፊልጶስ ጋር ስለ እኔ ፍቅር የተሰበሰበውን ሕዝብ ልንባርክ እንመጣለን» አሏቸው።
በጥሪውም መሠረት አባ ሕዝቅያስ፤ ታላላቅ መምህራን እና ቊጥሩ የበዛ ምእመናን ከአራቱም አቅጣጫ ግንቦት ፲፪ ቀን በደብረ ሊባኖስ በመሰባሰብ የተቀደሰ ዐፅማቸውን በሣጥን አክብረው በመንበሩ ፊት ሦስት ጊዜ አዙረው በቤተክርስቲያን በክብር አሳረፉ።
ጻድቁ አባታችንም አስቀድመው በገቡት ቃል መሠረት ከሊቀ መላእክት ከቅዱስ ሚካኤልና ከአባ ፊልጶስ ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በረድኤት ገቡ፣ዐፅማቸው ካረፈ በኋላም የተሰበሰበውን ሕዝብ ባረኩ።
በዚኽ አብነት በቤተክርስቲያናችን ፍልሰተ ዐጽሙ ለተክለ ሃይማኖት በየዓመቱ ግንቦት ፲፪ ቀን በታላቅ ድምቀት እና መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት ታከብራለች።
በተጨማሪም በቅድስት ቤተክርስቲያናችን በዛሬው እለት ብዙ ዓመታዊ እና ወርኃዊ በዓላት በደባልነት የሚከብሩ ሲኾን ለአብነትም፦
1.ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ (ቃል ኪዳን የተቀበለችበት)
2.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እና ሌሎችም ዓመታዊ በዓላት ያሉ ሲኾን እንዲኹም በወርኃዊ በዓላት በዋናነት ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል እና ሌሎችም ታላላቅ በዓላት ይከብራሉ።
ከእሊኽ ኹሉ ቅዱሳን ጻድቃን እና
ቅዱሳን ሰማዕታት በረከት ረድኤት ያሳትፈን፤
መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል በክንፈ ረድኤቱ ከክፉ ኹሉ ይከልለን
