❝ በዓለ ዕርገተ እግዚእ ❞
በቤተክርስቲያናችን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እጅግ ከከበሩ የጌታችን ዓበይት በዓላት አንዱ ዕርገት ሲኾን፤በዓሉ የሚከበረው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ተቀምጦ እንደምናገኘው ከጌታችን ትንሣኤ በኋላ በ፵ኛው ቀን ነው።
የጌታችን የነገረ ዕርገቱ ትምህርት እንደ እንግዳ ደራሽ ድንገት የመጣ ሳይኾን እንደ ልደቱ፤ሞቱ እና ትንሣኤው ኹሉ አስቀድሞ በዘመነ ብሉይ በአበው ታሪክ ውስጥ በጥላ አምሳያ የተገለጠ፤ በትንቢት የተነገረ እና በዘመነ ሐዲስ በአማናዋነት በእርሱ የተፈጸመ ነው።
ከብሉይ ኪዳን በምሳሌነት ብንመለከት «ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፤ እግዚአብሔርም ወስዶታልና አልተገኘም» (ዘፍ. ፭፥፳፬) የሚለውን እና ነቢዩ ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ወደ ሰማይ የመወሰዱ ታሪክ (፪ ነገ. ፪፥፲፩) በኋላ በዘመነ ሐዲስ ለጌታችን ዕርገት ምሳሌ ኾኖ እናገኛዋለን።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ግብረ ሐዋርያትን በተረጉመበት በ፪ኛው ድርሳኑ በኤልያስና በጌታችን ዕርገት መካከል ያለውን ሰማያዊ ልዩነትና ተመሳሳይነት ሲያብራራ፣ ሐዋርያቱ በዕርገቱ ጊዜ እንዳያዝኑ መላእክት መላካቸውን ይገልጽና ኤልያስ ወደ ሰማይ በኼደ ጊዜ ደቀ መዝሙሩ ኤልሳዕ በኃዘን ልብሱን እንደቀደደ ያስታውሳል።
በዚኽም ሐዋርያቱ በመላእክት መጽናናታቸውን ይናገራል በተጨማሪም ኤልያስ ፍጡር በመኾኑ ወደ ሰማይ ለመወሰድ «የእሳት ሰረገላ» ያስፈለገው ሲኾን ፣ ክርስቶስ ግን የሰማይና የምድር ጌታ ስለኾነ ሰረገላ ሳያሻው በራሱ ሥልጣን ማረጉን ይናገራል።( St.John Chrysostom, Homily 2 on the Acts of the Apostles)
ጌታችን በሥጋ ሳይገለጥ ገና ከ፩ ሺኽ ዓመታት በፊት ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በትንቢት መነጽር ❝ ዓርገ እግዚአብሔር በይባቤ፤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን፣ ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ፤ ዘምሩ ለንጉሥነ ዘምሩ።/አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ፤ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ።/❞መዝ ፵፮/፵፯፥፭
እንዲኹም ❝ዐርገ ውስተ አርያም ጼዊወከ ጼዋ ወወሀብከ ጸጋከ ለእጓለመህያው “ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ።”። መዝ. ፷፰፥፲፬ የሚሉት ግልጽ ሃሳቦችን ስናገኝ እንደ ልደቱ፤ሞቱ እና ትንሣኤው ኹሉ ዕርገቱም የሰውን ልጅ ከማዳን ሥራው ጋር የተያያዘ መኾኑን እንረዳለን።
በዘመነ ሐዲስም ስለ ዕርገቱ ታሪክና አስተምህሮ በሰፊዉ በዝርዝር የተዘገበ ሲኾን በዋናነት ማርቆስ ፲፮ ፥ ፲፱፤ ሉቃስ ፳፬ ፥ ፶ – ፶፩ ሐዋርያት ሥራ ፩ ፥ ፱ – ፲፩፤ ኤፌ.፬ ፥ ፰ -፲ ፊል. ፪ ፥ ፱…ወዘተ ዋነኛ ተጠቃሾች ሲኾኑ በዚኽ ክፍል በሐዋርያት ሥራ ፩ ፥ ፱ – ፲፩ የተጠቀሰውን ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትርጓሜ ጋር በማመሳጠር እንመለከተዋለን።
❝ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓ@ይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።
እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፡— የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።❞ በሐዋርያት ሥራ ፩ ፥ ፱-፲፩
ከላይ የተጠቀሰውን ክፍል ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ ሲተነትን እያዩት ማረጉ ደቀ መዛሙርቱ ትኩረት ሰጥተው እየሰሙት ባሉበትና አእምሯቸው ሙሉ በሙሉ በነቃበት ቅጽበት፣ እያዩት ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ብሏል። ይኽም እይታ የተሰጣቸው ወደ ሰማይ መሄዱን በዓይናቸው አይተው እንዲያረጋግጡ ነው።
በትንሣኤው ወቅት ደቀ መዛሙርቱ መጨረሻውን (የተነሣውን ክርስቶስንና ባዶውን መቃብር) አዩ እንጂ መጀመሪያውን (ሲነሣ) አላዩም። በዕርገቱ ግን መጀመሪያውን (ወደ ሰማይ ማረጉን) አዩ እንጂ መጨረሻውን (ደመና ሰውራው ሰማይ መግባቱን) በዓይናቸው ማየት ስላልቻሉ የመላእክት ምስክርነት አስፈልጓቸዋል።
መላእክቱ «ወደ ሰማይ ሲሄድ (ሲያርግ)» አሉ እንጂ «ተወሰደ» አላሉም።ይኽ ራሱ በሥልጣኑ ማረጉን ሲያሳይ፣ «ከፍ ከፍ አለ» የሚለው አገላለጽ ግን ስለ ሥጋ ባሕርይ የተነገረ ነው።(St.John Chrysostom, Homily 2 on the Acts of the Apostles)
ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ “ወልድ በባሕርይው ከአብ ጋር በባሕርይ አንድ ኾኖ ሳለ፤ በተለየ አካሉ ሥጋችንን ተዋሕዶ ወደ ሰማይ አሳረገው፤ ይኽም እኛም እርሱን ተከትለን፤ ወደዚያ ክብር እንደምንደርስ የሚያሳይ ነው” በማለት የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ኅብረትና ክብር ያሳያል።
ዳግመኛም ጌታችን ለሐዋርያቱ “እኔ ካልሄድኹ አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ወደ እናንተ አይመጣም፤ እኔ ብኼድ ግን እርሱን እልክላችኋለኹ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ ፲፮፡፯) ስለዚኽ ዕርገቱ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ (የበዓለ ጰራቅሊጦስን) የገለጠ ነው።
በአጠቃላይ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት የክርስትና እምነት መሠረት ሲኾን፤ በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ በግልጽ እንደተመዘገበውና በብሉይ ኪዳን ትንቢቶችና ምሳሌዎች አስቀድሞ እንደተበሰረው፣ ዕርገቱ የእርሱን ፍጹም መለኮታዊ ሥልጣንና ድል አድራጊነት ያሳያል።
ጌታችን በከበረው ሥጋ ማረጉ፣ ለሰው ልጆች ኹሉ አካላዊ ትንሣኤ እና ሰማያዊ መኖሪያን የማግኘት ተስፋ ዋስትናን ከመስጠቱ በተጨማሪ መላእክቱ «ሲኼድ እንዳያችኹት እንዲኹ ይመጣል» በማለት የመሰከሩት ምስክርነት ፣ የክርስቶስ ዕርገት ፍጻሜ ሳይኾን በዓለም መጨረሻ ለፍርድ በግርማና በደመና የመመለሱ ታላቅ ተስፋ ማረጋገጫ ነው።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
