“ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ የውይይት ጥያቄዎች ተነሱ”

አዲስ አበባ | ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
ስ/ወ/ሐ/ተ/መ/ሚዲያ
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ እየተካሄደ
በሚገኘው በ፫ኛው ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን መርሐ ግብር ላይ፣የቅድስት ቤተክርስቲያን የወንጌል አገልግሎትን ወቅታዊ ኹኔታ የሚፈትሹና ለቤተክርስቲያን ቀጣይ ሐዋርያዊ ተልዕኮ መንገድ ጠራጊ የኾኑ አምስት መሠረታዊ ጥያቄዎች ለውይይት ቀረቡ።
ጥያቄዎቹ የቀረቡት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በኩል ሲኾኑ፣ በአኹኑ ሰዓትም ታዳሚው በጥያቄዎቹ ላይ በጥልቀት እየተወያየ ይገኛል።
በዋናነት ጥያቄዎቹ
፩,የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ዘመኑን ከመዋጀት አንጻር ምን ይመስላል?
፪.የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከተደራሽነት አንጻር አንዴት ይታያል? በተለይም
ጠረፉን አካባቢ በቋንቋ ጭምር ከመድረስ እና ከዓለምአቀፍ ነባራዊ ኹኔታ አንጻር ሲታይ ምን ይመስላል?
፫.የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በሠርክ ጉባኤያት ምን ያኽል ውጤታማ ነው?
፬.የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በሚዲያ ከመድረስ አንጻር እንዴት ይታያል? እና
፭.በቅድስት ቤተክርስቲያን በኹሉም የስራ ዘርፍ የምንገኝ ኹላችንም አገልጋዮች የሥነ-ምግባር ጉዳይ እንዴት ይታያል? የሚሉ ናቸው።
ጥያቄዎቹን ለታዳሚው ይፋ ያደረጉት የመመሪያው ኃላፊ ክቡር መላከ ሰላም ዳዊት ያሬድ ፥ በጥያቄዎቹ በሚነሱ የውይይት ነጥቦች ቤተክርስቲያን በአገልግሎቱ ያላትን ተደራሽነት እና ሌሎችም ተግዳሮቶች መንስዔ በማጤን ለቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫ ጠቋሚ ሃሳቦችን ታገኝበታለች ተብሎ እንደሚታሰብ ገልጸዋል።
አኹን ላይ መርሐ ግብሩ ቀጥሎ ከታዳሚው የተለያዩ ሐሳቦችና የመፍትሔ ጥቆማዎች እየቀረቡ ሲኾን፤ ከዚኽ የውይይት መድረክ ለቤተክርስቲያን ቀጣይ ሐዋርያዊ የወንጌል ተልዕኮ ጉዞ እጅግ ጠቃሚ የኾኑ ስልታዊ ነጥቦች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

“ሰባኪው ተዋኝ ሳይኾን ፈዋሽ ሐኪም ሊኾን ይገባል” መ/ታ ኢንጂነር ባሕረጥበብ ሙጬ

አዲስ አበባ | ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
ስ/ወ/ሐ/ተ/መ/ሚዲያ
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ እየተከናወነ በሚገኘው ፫ኛው ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን መርሐ-ግብር አኹንም በልዩ ልዩ ክንውኖች እየተካሄደ የሚገኝ ሲኾን፤ ከክንዉኑ መካከልም በመ/ታ ኢንጂነር ባሕረጥበብ ሙጬ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል።
ጥናቱን “የስብከተ ወንጌል ተግዳሮቶ እና መፍትሔው” በሚል ርዕስ ያቀረቡ ሲኾን፤ በጥናት ዳሰሳቸውም ተልዕኮ አልባ ዕውቀት፤ ወንጌልን በአውደ ምሕረት ላይ ብቻ መወሰን፤ ትውልዱን ከመገንባት ይልቅ ለውበትና ለህንጻ ግንባታ ብቻ ትኩረት መሰጠቱ፤ እና ዘመኑን የዋጀ አግልግሎት አለመኖር በጥናታዊ ጽሑፉ የስብከተ ወንጌል ተግዳሮቶች መኾናቸውን ጠቅሰው፤ የሥርዓተ ትምህርት (Curriculum) ማሻሻያ ማድረግ እንደ መፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
መርጌታ ኢንጂነር ባሕረጥበብ ሙጬ በጥናታዊ ዳሰሳቸው ወቅት “ሰባኪ ፈዋሽ ሐኪም እንጂ ተዋኝ አርቲስት መኾን የለበትም ያሉ ሲኾን፤አክለውም፣ ቤተክርስቲያንን እንደ ኩባንያ፣ ሰባኪውን እንደ ማርኬቲንግ ባለሙያ እና ምእመናንን እንደ ደንበኛ የማየት አደገኛ አካኼድ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።
በአኹኑ ሰዓት ጥናቱን አስመልክቶ ከመድረክና ከታዳሚው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው በመወያየት ላይ የሚገኙ ሲኾን፤ በውይይቱም
ቤተክርስቲያን በስብከተ ወንጌል አገልግሎቷ ላይ ስትራቴጂያዊ ለውጥ ማድረግ እንዳለባት የሚያመላክቱ ኾነው ተገኝተዋል።
መርሐ-ግቡሩ አኹንም የቀጠለ ሲኾን በቀጣይም የሚኖሩትን ልዩ ልዩ ክንውኖች በመከታተል የምናቀርብ ይኾናል።

የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ አሁናዊ ገጾች!

“ፈነወኒ እስብክ ዐመተ እግዚአብሔር ኀሪተ
ወዘኮነ መዋዕለ”
የተወደደችው የጌታ ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል” /ሉቃ 4፡14/
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ መዳረሻውን ቤተልሔም ሁለተኛ መዳረሻውን ደግሞ ቀራንዮ አድርጐ ወደ ምድራችን የመጣበትን ዓላማ ሲገልጽ “የጌታ
መንፈስ በእኔ ላይ ነው ለድሆች ወንጌልን እስብክ ዘንድ ቀብቶኛል፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፣ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታ ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል” በማለት ተናግሯል፤ ይህ ንግግር መጀመሪያ በነቢዩ ኢሳይያስ አንደበት የተነገረ ሲሆን ቀጥሎ ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ የራሱን አገልግሎትና የመጣበትን ዓላማ ለማስተዋወቅ የተጠቀመበት ጥልቅ መንፈሳዊ ኃይለ ቃል ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን ሕግ (ዘሌዋ. 25) በየሃምሳ ዓመቱ በሚከበረው የኢዮቢልዩ ወይም የነፃነት በዓል ላይ በባርነት የተያዙ ባሪያዎች ነፃ የሚወጡበት ነበር፤ ዕዳም የሚሰረዝበትና የተያዘ መሬት ወደ ባለቤቱ የሚመለስበት እንዲሁም ለምድሪቱም ጭምር ብሔራዊ ዕረፍትም የሚደረግበት ነበረ የተወደደችውን የጌታን ዓመት የሚለው ሐሳብ በቀደመው ኪዳን ይደረግ የነበረውን የአካልና የቁሳቁስ ነፃነት ወደ መንፈሳዊ ልኬት ከፍ ያደረገ
ነው፡፡
የተወደደችውን የጌታ ዓመት እሰብክ ዘንድ ሲል በጥላነት መልኩ የአካልና የቁሳቁስ ነፃነት በመስጠት ሲከበር የነበረው የኢዮቤልዮ /የነፃነት በዓል/ አልፎ የኃጢያት ዕዳ
የሚሰረዝበት የሰይጣን ባርያዎች ነፃ የሚወጡበት እና ከእግዚአብሔር ጋር የታረቁበት የምሕረትና የይቅርታ የመንፈሳዊ ነፃነትና የድህነት ዘመን እንዲሁም እውነተኛና
ዘለዓለማዊ የነፃነትና የጸጋ ዘመን መምጣቱን ለማብሰር የተነገረ መንፈሳዊ አዋጅ ነው፡፡
ብፅዕ ወቅዱስ አባታችን፤
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፤
ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ፤
ብፁዕ የመምሪያችን ሊቀጳጳስ፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፤
የተከበራችሁ የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች
በዛሬው ዕለት ለሦስተኛ ጊዜ “በወንጌል ኮነ ሕይወትነ” በሚል መሪ ቃል በቅድስት ሥላሴ ዩንቨርስቲ ሁለገብ አዳራሽ እየተከበረ የሚገኘው ሦስተኛው ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልዩ ልዩ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ችግሮች ውስጥ የነበሩትን ነፃ ለማውጣት እንደተላከ የተናገረውን መንፈሳዊ አዋጅ መነሻ በማድረግ ስለኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረውን የመዳን መልዕክት፤ የሐዲስ ኪዳን የምስራች ቃል፤ የሕይወት መንገድና የተስፋ ቃል እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን በዚህ ምድር ላይ የመኖር ምስጢርና ዋና ተልዕኮ ስለሆነ ቅዱስ ወንጌል በሰፊው እንነጋገርበታለን፤በልዩ ልዩ መንገድም አስበነው እንውላለን፡፡
የበዓሉ/ጉባኤው ዋና ዓላማ፡-
የቅዱስ ወንጌሉን መልዕክት ማስታወስ፤ በተግባር መኖርን ማሳየት፤ እንዲሁም በጨለማ ሕይወት ላሉት ሁሉ የሕይወት ብርሃንን ለማካፈል ይሆን ዘንድ በክህነት ጥሪ
የተሰጠንን የአገልግሎት ቃል ኪዳን በድጋሚ ማደስ ሲሆን፡-
ግቡም፡- የምሥራች ዜናውን ማዳረስ፤ የአማኞችን መንፈሳዊ ሕይወት ማነቃቃት /ማነሳሳት/፤የቤተክርቲያንን አንድነት ማጠናከርና ቀጣዩን ትውልድ ማስተማር ነውና ለዚህ ቀንና ዕለት እንኳን በሰላም በጤና አደረሰን፤ አደረሳችሁ!!
ከዚህም በተጨማሪ ሦስተኛውን ሀገር ዓቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀንን በዚህ መልኩ ተገናኝተንና ተሰባስበን ስናከብር የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያው
የቅዱስ ወንጌልን አገልግሎት ለማዳረስ ከቢሮ ጀምሮ በየደረጃው ያከናወናቸውን የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የሥራ ክንውን ሪፖርት በማቅረብ እና በቀጣይ በመምሪያው ሊሠሩ
የታሰቡትን በመግለፅ ጭምር ይሆናል፡፡
ስለሆነም የበጀት ዓመቱን የ10 ወራት ዋና ዋና የሥራ ክንውን ሪፖርት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
1.የቢሮ አደረጃጀትና ዕድሳትን በተመለከተ ቀደም ሲል መምሪያው የነበረበት ቢሮ ለሥራ ተነሳሽነት የማይመች ከመሆኑም ባሻገር በመምሪው ሥር ያሉትን የየዘርፍ ኃላፊዎች ለማስተናገድ የማይበቃ _ ስለነበር፤ ስፓንሰርሽፕ በማፈላለግና በተገኘው ድጋፍ በፓርትሽን በመከፋፈል እንዲሁም ያለሥራ የተቀመጡ ቢሮዎችን በማስፈቀድ ቢሮውን ለሥራ ምቹ በሆነ መልኩ ከማድረግም
ባሻገር ቀድሞ ከነበሩት በቁጥር 5 ቢሮዎች ወደ 9 በማሳደግ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
ለዚህም ስፖንሰር በማድረግ ለተባበሩን ሁሉ ከልብ የሆነ ምሥጋናችንን እናቀርባለን፡፡
2.የመምሪውን አዲስ አደረጃጀትና የሥራ አፈጻጸም መመሪያ ማዘጋጀትና ማጽደቅን አስመልክቶ፣ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ ያለው የመምሪያው መተዳደሪያ ደንብና የክፍሎች አደረጃጀት በጊዜው ቢሠራበትም በአሁኑ ወቅት ግን የትውልዱን ጥያቄ የማይመልስና ዘመኑን የማይዋጅ በመሆኑ መምሪያው ዘመኑን ያገናዘበ አዲስ አደረጃጀትና የሥራ አፈጻጸም መመሪያ ማዘጋጅት አስፈላጊ መሆኑን አምኖበት ክርስቲያናዊ የምክክር አገልግሎት ዋና ማስተባበሪያ የአጫጭር ሥልጠናዎች ዋና ማስተባበሪያ ዘርፍ፤ የሚዲያና ሕትመት ዋና ማስተባበሪያ ዘርፍ፤ የጥናትና ምርምር ዋና ማስተባበሪ ዘርፍ ወዘተ የሚሉ 10 ዋና ዋና ማስተባበሪያ ዘርፎች እና 36 ንዑሳን ዘርፎች ያሉት
የአፈጻጸም መመሪያ /ደንብ/ አዘጋጅቶ በማቅረብ በጠቅላይ ቤተክህነት አስተዳደር ጉባኤ ጸድቆ የመጨረሻውን ዕውቅና ለማግኘት የግንቦት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡
3.መጠነኛ ቤተመጻሕፍት ማደራጃትን በተመለከተ
የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሰፊ ዝግጅት እና በየጊዜው ራስን ማሻሻልን የሚጠይቅ የአግልግሎት ዘርፍ በመሆኑና መምሪያው በሥሩ ከ30 በላይ ተዘዋዋሪ ሰባክያነ ወንጌል
ያሉት መምሪያ ስለሆነ ለአገልግሎት ዝግጅ የሚጠቅሙና የአመለካከት ከፍታን የሚጨምሩ መንፈሳዊ ሥነ ልቦናዊ፧ ማህበራዊና ፍልስፍናዊ ይዘት ያላቸውን መጻሐፍት በማሰባሰብና መጠነኛ ቤተመጻሕፍት በመምሪያው ቢሮ በማደራጀት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፤ በዚህ ሂደት መጻሕፍቱን ሂደት መጻሕፍቱን በመለገስ አስተዋጽኦ
ላደረጉልን ሁሉ በዚሁ ጉባኤ ፊት ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
4.የ120ው ቤተሰብ ፕሮጀክት የ1% ወርኃዊ የስብከተ ወንጌል መዋጮ አሰባሰብን በተመለከተ
ቀደም ሲል የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን ከከተማ እስከ ገጠሪቱ ቤተክርስቲያን ለማዳረስ ታሳቢ በማድረግና በበጀት ዕጥረት ችግር
እንዳይገጥመው የ120 ቤተሰብን ከመመሥረትና ወርኃዊ መዋጮ እንዲደረግ ከማዘዝ ጀምሮ በየትኛውም የቤተክርስቲያን መዋቅር የሚያገለግል አገልጋይ ወይም ሠራተኛ ከሚከፈለው ወርኃዊ ደመወዝ ላይ _ 1% ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲያበረክት በተወሰነው መሠረት የ1% ወርኃዊ መዋጮው ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጅምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲናት ድረስ መምሪያው በከፍተኛ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ውሳኔው ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፤ በሚገኘው ገቢም የስብከተ ወንጌል ተደራሽነት በእጅጉ እየሰፋ መሆኑን ሁሉም የሚረዳው ሐቅ ነው፤
የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ከሀገረ ስብከቱ እስከ ገዳማትና አድባራቱ ድረስ እንዲወርድ እና ተግባራዊ እንዲደረግ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ
ከልብ የሆነ ምሥጋና እናቀርባለን፤ጉባኤውም ከፍተኛውን ድርሻ ስለተወጡልን ከልብ ያመስግንልን፤
4.የመምሪያውን ሚዲያ አጠቃቀም በተመለከተ
መምሪያው ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጅ ምህበራዊ ሚዲያና ልዩ ልዩ መተግበሪያዎች ተጠቅሞ የቅዱስ ወንጌሉን አገልግሎት ለዓለም ሁሉ ማዳረስ ዋና ተግባሩ በመሆኑ
ለዚህ አገልግሎት የሚበጁ አስፈላጊ መሳሪዎችን ከማሟላት ጀምሮ በመምሪያው ስም ልዩ ልዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመክፈት ስብከተ ወንጌል ነክ ዜናዎችንና ልዩ ልዩ ትምህርቶችን እያስተላለፈ ይገኛል፤ ከፍተኛ የሚባል እምርታም አግኝቶበታል፡፡
በሕትመት ሚዲያው ረገድም ቀደም ሲል በመምሪያው እየታተሙ ሲሰራጩ የቆዩትን የመጽሔትና የጋዜጣ ሕትመት በተሻለ ይዘትና አቀራረብ በድጋሚ ለመጀመርና በዲጅታል መልኩም ለማዳረስ የሚያስችል ጥናት ቀርቦ በዝግጅት ላይ ይገኛል፤
ዓመታዊ በዓላችንን ታሳቢ ተደርጎ የታተመውን ብሥራት መጽሔት ጨምሮ ለበዓለ ጥምቀትም በርካታ መምህራንን ያሳተፈ ልዩ እትም መጽሔት በማዘጋጀት በነፃ
ለምዕመናን እንዲሰራጭ ተደርጓል፡፡
በመደበኛ ሚዲያውም ከኢቢኤስ ቴሌቭዥን ጣቢያ በተገኘው ሳምንታዊ ነጻ የአየር ስዓት መምሪያው ትምህርትና ስብከቶችን እያዘጋጀ፡- ረቡዕ ከቀኑ 9 ስዓት እና እሁድ ከጠዋቱ
4 ስዓት ላይ ቅዱስ ወንጌልን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፤ በዚህም አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገልን ላለው ኢቢኤስ ቴሌቭዥን ጣቢያ ከልብ የሆነ ምሥጋናችንን
እናቀርባለን፤በቅርቡ በዕረፍተ ሥጋ የተለዩንን የድርጅቱ ባለቤት የአቶ አማኑኤልን ነፍስ በቅዱሳኑ ዕቅፍ እንዲያሳርፍልንም እንጸልያለን ፡፡
በተጨማሪም መቀመጫውን በሀገረ ኖርዌ ካደረገው አጥቢያ ዶትኮም የተባለ የቴክኖሎጅ ድርጅት ጋር መምሪያው በኢንተርኔቱ ዓለም ሰርበር ላይ የራሱ አድራሻ እንዲኖረው በመነጋገር በመምሪያው ስም ድህረ ገጽ የማበልጸጉ ሥራ ተጠናቅቆ በዛሬው ዕለት በይፋ
የሚመረቅ ይሆናልና እንኳን ደስ አላችሁ::
5.መስከረም 6 ቀን 2018 ዓ.ም በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የተደረገውን ምክክርና ውይይት በተመለከተ
መምሪያው ከሁሉም አህጉረ ስብከት ጋር ያለውን መዋቅራዊ ግንኙነትና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተደራሽነት ዙሪያ መሪነትና ተልእኳችን በሚል መሪቃል ምክክርና ውይይት ለማድረግ መስከረም 6 ቀን 2018 ዓ.ም ባዘጋጀው ጉባኤ ከየአህጉረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች ጋር በቀረቡት ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች መነሻነት ምክክርና ውይይት ተደርጓል፤ መምሪውም ለቀጣይ ሥራዎቹ የሚጠቅሙ የሐሳብ ግብዓቶችን አግኝቶ በሥራ ላይ እያዋለው ይገኛል፡፡
6.ስምሪትን በተመለከተ የስብከተ ወንጌል፣ ስምሪት ወይም ተልእኮ የቅድስት ቤተክርስቲያን ዋና ተልዕኮ ማስፈጸሚያ መንገድ በመሆኑ ላለፉት ሦስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን ስምሪት በድጋሚ በማስጀመር ዓመታዊ ክብረ በዓላት ተጠብቆ ከሚደረገው ስምሪት በተለየ መልኩ የስብከተ ወንጌል ተደራሽነትና የምዕመናን ቁጥር አነስተኛ በሆነባቸው ጠረፋማና አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው 34 አህጉረ ስብከቶች የመምሪውን ሰባክያን ከድጋፍ ሰጭ ሰባክያነ ወንጌል ጋር በማቀናጀትና የአሰልጣኞች ሥልጠና በመስጠት ባደረገው ስምሪት የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ፤ ዕቅበተ እምነትና የቤተክርስቲያን ታሪክ በሚል በተመረጡ
ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ለአገልጋይ ካህናት ሥልጠና ተሰጥቷል፤ ጉባኤያትም ተከናውነዋል፡፡ በስምሪቱም ልዩ ልዩ ድጋፍ ላደረጉልን ሁሉ ምሥጋናችን ላቅ ያለ ነው፡፡
7.ሚያዝያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም በተመረጡ 12 አብያተ ክርስቲያናት የተደረገውን ሕዝባዊ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ በተመለከተ ሦስተኛውን ሀገረ አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን ከሚያዝያ 18 -19 ቀን 2018 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት ለማክበር በመምሪያው በተያዘው ዕቅድ መሠረት በዓሉ
ምዕመናንንም እንዲሳትፍ በማሰብ ሚያዝያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም የዋናው ጉባኤ ማብሰሪያ ሆኖ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተመረጡ 9 ገዳማትና አድባራት እንዲሁም
በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት በተመረጡ 3 አብያተ ክርስቲያናት በድምሩ በ12 ቦታዎች በመምሪያው አስተባባሪነትና አስፈላጊውን ወጪ ሁሉ በመሸፈን ወጥ የሆነ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በተመሳሳይ ስዓት ተከናውኗል፤ እግዚአብሔረም በህብረ ዝማሬ ተመስግኗል፡፡
8.ለደቡብ ኦሞ ኮሚቴ የተደረገውን የገንዘብ ድጋፍ በተመለከተ፣
የደቡብ ኦሞ የስብከተ ወንጌል ማስፋፋትና ሕንጻ ቤተክርስቲያን አሠሪ ኮሚቴ ባኮስ ሚዲያ) በደቡብ ኢትዮጵያ በተለይም በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመተባበር ያላመኑትን በማሳመንና የሥላሴ ልጅነት በማሰጠት ያመኑትን በማጽናትና ተተኪ ደቀመዛሙርት በማፍራት እያደረገ ለሚገኘው ከፍተኛ አገልግሎት መምሪያው የዕውቀትና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርግለት በተደጋጋሚ ጥያቄ ባቀረበው መሠረት መምሪያው ምንም እንኳን የራሱ የሆነ በቂ በጀት ባይኖረውም ሥራው መደገፍ
እንዳለበት በመምሪያው ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ታምኖበት መምሪያው ከሚሰበስበው አንድ ፐርሰንት ገቢ ላይ 259,000 ብር ድጋፍ እንዲደረግ ተፈቅዷል፡፡
በቀጣይም ከሀገረ ስብከቱና ከኮሚቴው ጋር በመተባበር በጋራ ለመሥራት ዕቅድ ተይዟል፡፡
በቀጣይ በመምሪያው የሚሠሩ ዋና ዋና ሥራዎችን ለማመላከት ያክል
1. በመምሪው የተዘጋጀውን የሰባክያነ ወንጌልና የዘማሪያን አጠቃላይ የአገልግሎትና የሥነ ምግባር ደንብ በቅዱስ ሲኖዶስ አጸድቆ ሥራ ላይ ማዋል ፣
2. ከጽርሐ ጽዮን አንድነት ኑሮ የካህናት ማሠልጠኛ ጋር በመተባበር ከአህጉረ ስብከቱ ተተኪ የቋንቋ አገልጋዮችን በመመልመል አሰልጥኖ ማሰማራት፣
3. ሳምንታዊ የረቡዕ ተከታታይ የዮሐንስ ወንጌል ጥናት ላይ በተጨማሪነት የሚሰጡ አጫጭር ኮርሶችን በማከልና ልዩ ድጋፍ በመስጠትና ቋሚ የሥልጠና ቦታ በማዘጋጀት
ማስቀጠል፣
4. ልዩ ድጋፍና ክብካቤ የሚሹ ወገኖችን ማለትም
ማውታ ማዕከላት በሆስፒታልና በማረሚያ ቤት ያሉ
ጋር በመቀናጀት ቀሚ አገልግሎት መስጠት፣ በአረጋውያን መጦሪያ እና በእጓለ ወገኖችን በትኩረት ከሚመለከተው
5. የስብከተ ወንጌል በሚዲያ ተደራሽነት ዙሪ አሁን ካለው አጠቃቀም በተሻለ መልኩ ራሱን የቻለ የባለሙያ ቡድን በማደራጀትና ሱቱድዮ በማዘጋጀት ሥራውን መጀመር፧
6. 4ኛውን ሀገረ አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን ከቀናት ስያሜ ከፍ በማለት የሰብከተ ወንጌል ሳምንት በማለት በተመረጡ የክልል ከተሞች ለማክብር ዝግጅት ማድረግ፤
7. ወጥ የሆነ የሥልጠና ማንዋል በማዘጋጀት በየአህጉረ ስብከቱ ውጤት ተኮር ተደጋጋሚ ሥልጠናዎችን መስጠት፣
8. መምሪያው የራሱ የሆነ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት እና ለተለያዩ ሁነቶች የሚሆነ ሳውንድ ሲስተም መግዛት፣
9. ከመዋቅር ውጭ የሚያገለግሉ አገልጋዮችን በሚመለከት የራሱ የሆነ ወጥ መመሪያ በማዘጋጀት በመምሪያው መሠረት እንዲመሩ ማድረግ፣
10.ከተለያዩ ኮሌጆች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በስብከት አገልግሎት ዙሪያ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሳለጥኑ ማድረግ፣ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
11የመምሪያውን የሰው ኃይል አደረጃጀት በተሻለና ሙያውና ብቃቱ ባላቸው አገልጋዮች በድጋሚ ማደራጀት የሚሉት ይገኙበታል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፡

ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ በ፵ ዓመት ጉዞው

መግቢያ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በሕገ ልቡና፤ በሕገ ኦሪት እና በሕገ ወንጌል ከአምልኮተ እግዚአብሔር ሳትለይ የኖረች ሀገረ እግዚአብሔር መኾንዋን ብዙ ሊቃውንት ተናግረዋል፤ ጽፈዋልም። በተለይም፤ ኹለቱ ኪዳናት ወደ ሀገራችን መግባታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈ እውነት ነው፡፡ ጥንቱንም በሕገ ልቡና እግዚአብሔርን ታመልክ የነበረች ሀገራችን፤ ወዳና ፈቅዳ የስሎሞንን ጥበብ ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም በሔ ደችው ንግሥቷ አማካይነት ሃይማኖተ ኦሪትንና ሥርዓተ ኦሪትን የተቀበለች መኾኗ በመጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ምዕራፍ ፲˖ ፩-፲፫ተጠቅሷል፡፡በዚኽም የኢየሩሳሌም ጉዞ ንግሥተ ሳባ ከስሎሞን ቀዳማዊ ምኒልክን ፀንሳ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ወለደች፤ ልጁም አድጎ የአባቱን ሀገር ኢየሩሳሌምን ጎብኝቶ ሲመለስ የሙሴን ጽላት እና ካህናተ ኦሪትን፣ እንዲሁም አያሌ የብሉይ መጻሕፍትን ከሊቆቻቸው ጋራ ይዞ መጣ:: ይህ ፈቃደ እግዚአብሔር የነበረበት አጋጣሚ፣ ሥርዓተ ኦሪት ወደ ሀገራችን እንዲገባ ምክንያት ኾኗል፡፡

ነቢዩ ዳዊት “ኢትዮጵያውያን በፊቱ ይሰግዳሉ፤ ጠላቶቹም ዐመድ ይቅማሉ፤ የጠረሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታ ያመጣሉ፤ የሳባና የዐረብ ነገሥታትም እጅ መንሻ ያቀርባሉ፤ ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል፤” ብሎ (መዝ. ፸፩፥ ፱-፲) በተናገረው ትንቢት መሠረት፣ ሄሮድስ በነገሠበት ዘመን ይሁዳ ክፍል በምትኾን በቤተልሔም፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ፣ ወርቅ ዕጣን ከርቤ ከገበሩለት ሦስት ነገሥታት አንዱ፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ ባዜን እንደ ነበረ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ፣ የግመሎች ብዛት፣ የምድያም እና የጌፌር ግመሎች ይሸፍኑሻል፤ ኹሉ ከሳባ ይመጣሉ፤ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ፤” (ኢሳ.፰፥፮) ብሎ የተናገረውን ትንቢት መሠረት በማድረግ፣ ኹሉም ከሳባ ይመጣሉ ብሏልና፣ “ሰብአ ሰገል ሁሉምም ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ብለውም የሚሞግቱ ሊቃውንት አሉ፡፡ በዚኽም መሠረት ኢትዮጵያ ክርስቶስን ያወቀችውና መባ በማቅረብ ልደቱን ያከበረችው ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቀዳማዊት ቤተ ክርስቲያን መሆኗ አጠያያቂ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ እስከ ቤተልሔም ድረስ ተጉዛ ልደቱን በማክበር ሳትወሰን በ34 ዓ.ም ሐዋርያ ሳይጓደልባት እና ደም ሳይፈስባት በራሷ ሐዋርያ ተሰብካ ትጠብቀው የበረውን የክርስቶስን መምጣት እና ዓለምን ማዳን አምና ሃይማኖተ ወጌልንና ሥርዓተ ወንጌልን የተቀበለች ሀገር ናት፡፡ “የጌታም መልአክ ፊልጶስን ተነሥተኽ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደ ሚያወርድው ምድረ በዳ ወደ ኾነው መንገድ ሒድ አለው፤ ተነሥቶም ሔደ፤ እነኾም ሕንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥ እና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ኹሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ መጥቶ ነበር፤ ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያ መጽሐፍ ያነብ ነበር፡፡ መንፈስም ፊልጶስን፣ ወደዚኽ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው፤  ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና፣ በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለኽን? አለው፡፡ እርሱም የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው፤ ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፣ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል? ፊልጰስም መልሶ፣ እባክህ፥ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል ስለ ሌላ? አለው፡፡ ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት፡፡ በመንገድም ሲሔዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፣ እነኾ በውኃ፤እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምምንድር ነው አለው፤ ፊልጶስም፣ በፍጹም ልብኽ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው፤መልሶም ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ኾነ አምናለሁ አለ፤ ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስ እና ጃንደረባው ኹለቱዎ ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም:: ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፤ ደስ ብሎት መንገዱን ይሔድ ነበርና፤ ”(የሐዋ. 8፡26-39) በማለት አገራችን ኢትዮጵያ ሐዋርያ ሳይላክላት በራሷ ሐዋርያ ክርስትናን የተቀበለች የመጀመሪያዋ ሀገር መኾንዋን መጽሐፍ ቅዱስ ይመሠክራል፡፡ ምንም እንኳን ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ሀገራችን መጥቶ ማስተማሩን፣ ኢትዮጵያም መንበረ ማቴዎስ መኾኗን የሚጠቁሙ፣ ባልታወቀ ምክንያት ብዙም ጎልቶ የማይነገር ታሪክ ቢኖርም፣ ኢትዮጵያ በራሷ ሐዋርያ መሰበኳ ግን ጥርጥር የሌለው ሐቅ ነው፡፡ ከላይ በሐዋርያት ሥራ የተጠቀሰው ታሪክ፣ ኢትዮጵያውያን እንደ ኦሪት ሥርዓት በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ይሔዱ የነበረ መኾኑን ኢትዮጵያ ውስጥ ከንግሥተ ሳባ ጊዜ ጀምሮ ወደ አገራችን የገቡ መጻሕፍተ ነቢያት እንደነበሩ፣ ኢትዮጵያውያን በመጻሕፍተ ብሉያት ጠቋሚነት የኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚኽ ዓለም መምጣት በተስፋ ይጠብቁ እንደነበር፤ ለኢትዮጵያ መምህር የላከላት መንፈስ ቅዱስ መኾኑን፣ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በራሳቸው በኢትዮጵያውያን መሆኑን፣ ክርስትና ከምድረ እስራኤል ውጭ መጀመሪያ የተሰበከው ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ መሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡

ቅዱስ ሄሬኔዎስ ጳጳስ ዘሊዮ “ጃንደረባው ለወገኖቹ ሐዋርያ ሆነ፡፡” በማለት ይህንኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ መነሻ ያደረገ ታሪክ ጽፏል፡፡ እንደዚሁም አውሳብዮስ ዘቂሣርያ “ከቤተ እስራኤል ውጭ የአካላዊ ቃልን ምሥጢር በመቀበልና በመጠመቅ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ነው፤ በዓለም የወንጌል ፍሬ በመሆንና ወደ አገሩም ተመልሶ በማስተማር በዓለም ላይ የመጀመሪያው ነው፡፡ በዚህም “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ተብሎ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን አገኘ፤ በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ከላይ እንደ ተገለጸው ቋሚ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ እንዳለ ሆኖ ከሐዋርያት መካከል ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ማስተማሩን ሩፊኖስ፣ ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ መምጣቱን ደግሞ ጄሮም፣ እነደዚሁ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ኢትዮጵያንም ጭምር ማተማሩን ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ መስክረዋል፡፡

ስብከተ ወንጌልን ለማፋጠን የተገኙ እድሎች

መንበረ ጵጵስና ማግኘቷ

በኢትጵያዊው ጃንደረባ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ አስቀድሞ የገባ የክርስትና ሃይማኖት ወደ መንበረ ጵጵስና ከፍ ያለው በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፍሬምናጦስ የጵጵስና ሢመት አማካኝነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደ ተጻፈው በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲያስመጣላት ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማን ወደ እስክንድርያ ላከች፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ የእስክንድርያ ፓትርያርክም ራሱኑ ሾሞ ላከው፤ ከኢትዮጵያ ተልኮ ሔዶ ከእስክንድርያው ፓትርያርክ ከቅዱስ አትናቴዎስ ዘንድ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሾሞ በመጣው በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መምህርነት በአብርሃና በአጽብሐ ዘመነ መንግሥት ክርስትና የግዛቱ ይፋዊ ሃማኖት ሆነ፡፡ አባ ሰላማም መንበረ ጵጵስናውን አክሱም ላይ አድርጎ በሀገራችን እየተዘዋወረ የወንጌልን ብርሃን በሰፊው ስለገለጠ በኢትዮጵያ «አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን» በመባል በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀች ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ለመሆን መብቃቷን ታሪክ ያስረዳል፡፡

የቅዱስ ያሬድ መነሣት

በ፭፻፶፭/555 ዓ.ም በአክሱም ከተማ የተወለደው ቅዱስ ያሬድ የቤተ ክርስቲያናች የዜማ አባት ብቻ ሳይኾን፣ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት የነበረው አስተዋፅኦ እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ዜማዊ ይሁኑ እንጂ በውስጣቸው ያለው ትምህርትና ምሥጢር እጅግ ከፍተኛ ነው፤ ዜማው ለጆሮ ምሥጢሩ ለአእምሮ የሚስማማ አድርጎ ስላዘጋጀው ከመደበኛው ስብከተ ወንጌል ባልተናነሰ ለብዙ ዘመናት ምእመናን ሲመከሩበትና ሲመሰጡበት ተምረውበትና ተጠብቀውበት ኖረዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ዜማን ከማበርከቱም በተጨማሪ በዘመኑ ከነበረው ንጉሥ ከአጼ ገብረ መስቀል ጋር በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተዘዋውሮ በማስተማር ዜማውን እንደ አንድ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ተጠቅሞበታል፡፡

ዘጠኙ ቅዱሳን

ዘጠኙ ቅዱሳን በኬልቄዶን ጉባኤ ምክንያት በተዋሕዶዎች ላይ በአውሮፓ በእስና በመከላከለኛው ምሥራቅ በተነሣው ፈተናና መገፋት ምክንያት ከሮም፣ ከእስያ፣ ከአንጾኪያ፣ ከቁስጥንጥንያ፣ ከቂሳርያና ከኪልቂያ በስደት የመጡ ናቸው፤ ለቤተ ርስቲያን ባበረከቱት ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ በቤተ ክርስቲያናችን የቅድስና ማዕረግተሰጥቷቸው ዘጠኙ ቅዱሳን በመባል የሚታወቁት እነዚህ ቅዱሳን ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን ወንጌልን ዞረው የሚያስተምሩ መምህራንን የሚያፈሩ ገዳማትን በመመስረት ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለውለታ ናቸው። በተለይም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በማጽናት የተለያዩ መጽሐፍትን በመተርጎም ስብከተ ወንጌልን አስፋፍተዋል፡፡ በርካታ ገዳማትን መስርተዋል፤ ሥርዓተ ምንኩስናን አደራጅተዋል፡፡ ይህም በሀገራችን ክርስትናው እንዲሰፋና እንዲጸና የነበረው አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡

የጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት መነሣት

ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት በኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፣ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ በመመለስ “ሐዲስ ሐዋርያ” የተባሉ በተለይም በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ለነበረው የስብከተ ወንጌል መስፋፋት የመሪነቱን ድርሻ የተወጡ ታላቅ ሐዋርያና ጻድቅ ናቸው፡፡ ጻድቁ ሕይወታቸውን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው፣ በብሕትውና ከመኖራቸውም በተጨማ እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ፣ ሐዋርያ ናቸው፡፡ በተለይም የአባቶቻቸውን ፈለግ የተከተሉ፣ 12ቱ የጻድቁ ደቀ መዛሙርት በ12ቱ ሐዋርያት አምሳል ከፍተኛ የሐዋርያዊ ተልእኮን ተግባር ፈጽመዋል፡፡

መንበረ ፕትርክናን ማግኘት

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከመንበረ ጵጵስና ወደ መንበረ ፕትርክና በመሸጋገር ይልቁንም የራሷን ኢትዮጵያውያን ጳጳሳትን መሾም ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ “ሑሩ ውስተ ኵሉ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኵሉ ፍጥረት /ወደ ዓለም ኹሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ኹሉ ስበኩ” ተብሎ በታዘዘው አምላካዊ ትእዛዝ መሠረት የእግዚአብሔርን ወንጌለ መንግሥተ ሰማያት ለአማንያንና ለኢአማንያን በማዳረስና የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትዕዛዝ በመፈጸም ከተመሰረተችት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በስብከተ ወንጌል ዙሪያ ከፍተኛ ሥራ ሠርታለች፡፡ ለስብከተ ወንጌል የተለየ ትኩረት በመስጠት ክርስቲያናችንን ሐዋርያዊ ተልእኮን ሊያፋጥኑ የሚችሉ አንዳንድ ተግባራት እንደ ተሞከሩ ይታወቃል። ቤተ ክርስቲያናችን ከግብጻውያን አገዛዝ ተላቃ የራሷን ፓትርያርክ ካገኘችበት ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ዘመን የቤተ ክህነት የዕለት ተዕለት አጀንዳ ስብከተ ወንጌል እንደ ነበር ይነገራል፡፡ በተለይም በ1952 ዓ.ም የተመሠረተውና በቤተ ክርስቲያናችን ተግባር ከፍተኛ ውጤት ያመጣል ተብሎ ግምት ተሰጥቶት የነበረው “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ምክር ቤትን” መቋቋሙ ትልቅ እርምጃ ነበር፡፡ ምክር ቤቱ በንጉሠ ነገሥቱ የበላይ ጠባቂነት፣ በብዑፅ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፓትርያርክ ሊቀ መንበርነት፣ በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የጉባኤ መሪነት፤ 14 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቋሚ አባልነት፣ ከምእመናንና ከካህናት በተመረጡ የጉባኤ አባላት የተዋቀረ ሆኖ መዋቅሩን እስከ መንበረ ጵጵስና በመዘርጋ ወንጌልን በጥራትና በስፋት ይሰጥ እንደ ነበር መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ እንደ መልአከ ታቦር ተሾመ ዘርይሁን አገላለጽ በዚያ ወቅት በተለይም የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ደቀ መዛሙርትም አብዛኛዎቹ በአብነት ትምህርቱ የበሰሉ ስለነበሩ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ምቹ ሁኔታን ፈጥሮ ነበር፡፡ የዚያን ጊዜው መመሪያ ‹‹እየተማሩ ማስተማር፣ እያስተማሩ መማር›› ሲኾን ይኽንን መመሪያ መሠረት በማድረግ ለስብከተ ወንጌል ተግባር ብቻ በተዘጋጀች ድምፅ ማጉያ ባላት መኪና በየበዓላቱና በየዕረፍት ጊዜው በዐራቱም ማዕዘን ከገጠር እስከ ከተማ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ ከፍተኛ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሰጥ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት የስብከተ ወንጌልና የሰንበት ትምህርት ቤት አስተምህሮ ሐዋርያዊ ጉዞዎች ዋና አድራሻዎች ነበሩ፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ የሐዋሪያዊ ጉዞ መኪናዋና ድምፅ ሲሰማ በመደሰት ወደ የቤተ ክርስቲያኑ የስብከት መድረክ ዙሪያ ስለሚሰበሰብ ወንጌልን ቃል ለተሰበሰበው ሕዝብ በማሰማት ከፍተኛ ሐዋርያዊ ተግባር ይፈጸም ነበር፡፡ በወቅቱ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የነበረው ተነሳሽነት እጅግ ከፍተኛ ስለነበረ የስብከተ ወንጌል ማኅበር ተቋቁሞ ነበር፡፡ የማኅበሩ ሊቀ መንበርም የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ሠራዊት አዛዥ የነበሩት ጀኔራል ታደሰ ብሩ ስለነበሩ ሰባክያነ ወንጌል ለስበከተ ወንጌል በኢትዮጵያ ምድር ሲዞሩ ችግር ቢደርስባቸው በየአካባቢው የፖሊስ ሠራዊት አባላት ትብብር እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ተላልፎ ነበር፡፡ ይህም የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት በነጻነት በሁሉም አቅጫ ዞረው እንዲየያስተምሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ ነበር፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ለስብከተ ወንጌል የነበራቸ ቦታ ከፍተኛ ስለነበር በአንድ ወቅት ስብሰባ በማድረግ ለደቀ መዛሙርት መመሪ ሲሰጡ “እናንተን ከየአቅጣጫው አሰባስበን በዚኽ ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርት እንድትማሩ ያደረግነው፤ ዓለሙ በአሁኑ ጊዜ በዘመናዊ ትምህርት እየመጠቀ በመሔድ ላይ ስለኾነ፤ እናንተም ካላችሁ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር ዓለሙ የሚያውቀውን ዐውቃችሁ ካላስተማራችሁ በቋንቋም፣ በንግግርም ልዩነት ትምህርታችሁን ላይቀበለው ስለሚችል ነው” በማለት ከዘመኑ እድገት ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል የወንጌል ሠራዊት በብቃት ለማዘጋጀት አስበውና ትኩረት ስጥተው ይሠሩ እንደ ነበር የሚያመላክት ንግግር ተናግረዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስም በእንደራሴነትና በፓትርያርክነት ቤተ ክርስቲያናችንን ባገለገሉበት ዘመን ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን ችግር አስቀድሞ በመረዳት በዘመኑ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ ከማድረግም ባለፈ ስብከተ ወንጌልና የቤተ ክስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይቋረጥ ሰበካ ጉባኤን በማቋቋምና ለወንጌል አገልግሎቱ ድጋፍ ሰጪ የሁኑ ገቢ የሚያስገኙ ሕንጻዎችን በማሳነጽ ለቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ ከደርግ ዘመነ መንግሥት በፊት ትምህርተ ወንጌል በሬድዮና በልዩ ልዩ የሕትመት ውጤቶች ጭምር እንዲሰጥ በማድረግ ስብከተ ወንጌል በስፋትና በተለያዩ አማራጮች ለመስጠት ይደረግ የነበረው ሙከራ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ሆኖም በደርግ ዘመነ መንግሥት የነበረው የሥርዓቱና የርእዮተ ዓለሙ ጫና እንዳለ ሆኖ ከሥርዓት ለውጡ በኋላ ቢሆን አስቀድሞ የነበረውን ስብከተ ወንጌልን የማስፋፋት ጥረትና ትኩርት በሚፈለገው ልክ ማስቀጠልና ማስፋፋት ተችሏል ማለት አያስደፍርም፡፡

የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ በዘመነ ደርግ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለፕትርክና የተመረጡበት ዘመን በሥርዓት ለውጥ ምክንያት ቤተ ክርስቲያናችን በፈተና ውስጥ የነበረችበትና ፓትርያርኳንም በግፍ ያጣችበት ወቅት የነበረ ቢሆንም በዚያ በፈተና ወቅት በዘርና በገንዘብ የማይታሙ የፖለቲካም ወገንተኝነት የሌላቸው ፍጹም መናኝ የነበሩት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለፓትርያርክነት መመረጥ በፈቃደ እግዚአብሔር የሆነ  እንደ ነበር ምንም አጠያያቂ ይደለም፡፡ በደርግ ዘመነ መንግሥት የነበረው ርእዮተ ዓለም ለቤተ ክርስቲያን የተመቸ ባይሆንም ያንን የመከራ ዘመን ቤተ ክርስተያን በጥበብ እንድትሻገር በማድረግ ረገድ ቅዱስነታቸው የነበራቸው ሚና ቀላል አልነበረም፡፡ በወቅቱ የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሓፊ የነበሩት መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን ዝክረ ነገር በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደ መሰከሩት በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም፣ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በምስካየ ኀዙናን መድኃኔ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት ላይ ውርስ ለማድረግ የታሰበና የተደረገ ሙከራ የነበረ ቢሆንም እኚህ ታላቅ አባት እኖር ባይነት፤ እከብር ባይ ልቡና፣ የዓለም ግርማ የሀብት ፍትወት በእርሳቸው ዘንድ ቦታ አልነበረውምና “እኔ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዳደር እንጂ የሕዝበ ክርስቲያኑን የአምልኮ መፈጸሚያ ቤተ እግዚያብሔር ንብረት ወደ ሌላ ባለቤትነት ለማስተላለፍ ሥልጣን የለኝም የሚል ምላሽ በመስጠት የታስበው እንዳይፈጸም ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡                       በወቅቱ ሥርዓቱን የሚተች ንግግርም ሆነ ስብከት ከእስራት እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት ሊያስከፍል እንደ ሚችል የታወቀ ቢሆንም ቅዱስነታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ያመኑበት እኩይ ተግባርን ከማውገዝ ወደ ኋላ የማይሉ አባትም ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት “በአንድ ቤተ ክርስቲያን ክብረ በዓል ላይ ሲያስተምሩ በሌላው አገር አንድ ዛፍ መቁረጥ ሰውን የመግደል ያህል ወንጀል እንደ ሆነ ሰምቻለሁ በእኛ አገር ግን ዛፍ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ እየተገደለ በየመንገዱ ይጣላል” በማለት ሲናገሩ ሕዝብ ዕንባ በዕንባ እንደ ኾነ መስማታቸውንም ጭምር መሥክረዋል፡፡ በአስቸጋሪ ዘመንና ሁኔታ ውስጥም ሆነው አስፈላጊነቱን ባመኑበት ቦታና ጊዜ “መምህር ወመገሥጽ ዘኢያደሉ ለገጽ” በመሆን ወንጌልን ይሰብኩ እንደ ነበር ይህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

በአርሲ የተደረገው የወንጌል አርበኝነት ተግባር

በደርግ ዘመነ መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች ወንጌል እንዳይሰበክ የደርግ ካድሬዎች የተለያዩ ጫናዎች ያደርሱ የነበረ ቢሆንም በዚያው ልክ ብዙ አባቶች ያንን እየተቋቋሙ በአርበኝነት ወንጌልን ይሰብኩ እንደነበር የታወቀ ሀቅ ነው፡፡ አንዱ ማሳያም በአርሲ የተደረገው የወንጌል አርበኝነት ተግባር መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን እንደሚከተለው ተርከውታል፡፡ በወቅቱ በአርሲ ይነገር የነበረው የካድሬዎች መፈክር አርሲን ሌኒን ግራንድ እናደርጋለን የሚል ስለ ነበር የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ እና በቦታቸው የተተኩት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በሀገረ ስብከቱ የከፈሉት መሥዋዕትነትና ያሳዩት የሥራ ውጤት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ለስብሰባና ቡራኬ ተግባር በሀገረ ስብከቱ ሥር ወደ ሚገኙ ወረዳዎች ሲሄዱ በስብሰባው ቦታ ተገኝተው እንዳያስተምሩና ጠንከር ያለ መልእክት እንዳያስተላልፉ በየኬላው የቆሙ ዘቦች የይለፍ ፈቃድ ካልያዙ አይሄዱም ብለው አግተው ያውሏቸው ነበር። ሆኖም እርሳቸውም ሆነ ሕዝቡ የሚበገሩ ስላልነበሩ ጊዜው አልፎ ዘግይተው ቢደርሱም ለስብሰባው ተጨማሪ ጊዜ በመስጠትና የሚፈለገውንም ተልእኮ በታስበው መሠረት በመፈጸም የተንኮሉን ዓላማ ውጤት አልባ ያደርጉት ነበር።                                                   በአንድ ወቅት በዚሁ ሀገረ ስብከት በአሰላ ከተማ ላይ ሕዝቡ በጥምቀት በዓል ማግስት የሚውለውን የቃና ዘገሊላን በዓል ለማክበር እንዳይወጣ የከተማው የደርግ ካድሬ በአሰላ ከተማ የጽዳት ዘመቻ በማወጅ ሕዝቡ ሁሉ ለዚያ የጽዳት ዘመቻ እንዲወጣ በመደረጉ የቃና ዘገሊላ በዓል ዕለት የታቦት ማደሪያ ቦታ ሰው አልባ ይሆናል፡፡ በዚህ በዓል ላይ ለአስተማሪነት ተጋብዘው በቦታው ላይ የተገኙት የያኔው ሊቀ ኅሩያን መርሐ ጽድቅ የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከቤተ ክህነት በተላከውና የድምጽ ማጉያ ማይክራፎን ባለው መኪና ላይ ሆነው ወደ ከተማው ሕዝብ ጆሮ በማነጣጠር “ወይቤሎ እግዚአብሔር ለፈርዖን ፈንዎሙኣ ለሕዝብየ ይግበሩ በዓልየ /እግዚአብሔር ፈርዖንን አለው ሕዝቤን ልቀቅ በዓሌን ያከብር ዘንድ” (ዘፀ.5÷1) የሚለውን ቃል በማስተጋባት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ለፖለቲካው ክፍል አስቸኳይ ጥሪ ለሕዝበ  ክርስቲያኑ ሲያደርጉ ሕዝቡም የያዘውን የጽዳት መሣሪያ እያስቀመጠ ልብሱን እየለወጠ ወደ ታቦት ማደሪያው በመሄዱ በዓሉ በተለመደው መሠረት ሊከበር ችሏል። ይህም በወቅቱ የነበረው የወንጌል እንቅፋት ብቻ ሳይሆን ለስብከተ ወንጌል በጥብአት የተሰለፉ አባቶችም እንደነበሩ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡                                 በአጠቃላይ በዘመነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ትልቅ የዕለት ተዕለት አጀንዳ የስብከተ ወንጌልና የሰንበት ትምህርት፣ የሰበካ ጉባኤ ጉዳይ ስለ ነበር፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደርና መምሪያዎች የዕለት ተዕለት ተግባርም በየከተማውና በየገጠሩ፣ በየአህጉረ ስብከቱ፣ በየወረዳውና በየአጥቢያው ለዚኽ ተግባር ጥንካሬና ዕድገት በሙሉ ኃይል መንቀሳቀስ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ለስብከተ ወንጌል መምሪያ ብቻ ለአገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማስፈጸሚያ የተመደቡ ዐራት መኪናዎች ነበሩት፡፡ ከእነዚኽም አንዱ የቤቱ ሲኾን ኹለቱ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጥያቄ ከውጭ አብያተ ክርስቲያናት በእርዳታ የተገኙ፤ አንዱ ደግሞ ከአገር ውስጥ በጎ አድራጊ ድርጅት የተሰጠ ነበር፡፡ ስለኾነም የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንቅስቃሴ በዚያው መጠን የሰፋ ነበር፡፡ ይህም በጣም ውስን ሀብት በነበረበት በዚያ ወቅት ለስብከተ ወንጌል የተሰጠው ትኩረት ምን ያህል ከፍተኛ እንደነበር ያሳያል፡፡ ያ ትኩረት በዚያው መጠን ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የተሻለ ሀብት ባለበትና የበለጠ መሥራት በሚቻልበት በዚህ ዘመን ምን ያህል ለውጥ ማምጣት በተቻለ፣ ስንቱ ከመንጋው የኮበለለው ምእመን በቤቱ እንዲጸና ማድረግ በተቻለ ነበር፡፡

የስብከት እንቅስቃሴ ከደርግ ዘመነ መንግሥት በኋላ

ከደርግ ዘመነ መንግሥት በኋላ ለሁሉም ቤተ እምነቶች ሃማኖታቸው በነጻነት የማስፈፋት ዕድል ሁሉም በእኩልነት ያገኙ ቢሆንም ሌሎች ቤተ እምነቶች ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋት በተጠቀሙበት ልክ ተጠቅመንበታል ማለት ግን የሚቻል አይደለም፡፡ ሆኖም ስብከተ ወንጌልን ለማጠናከርና ለማስፋፋት የተደረጉ ሙከራዎች አልነበሩም ማለት ግን አይቻልም፡፡             በ1990ዎቹ መጨረሻ ላይ የስብከተ ወንጌልን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በሚመለከት አንድ ከፍተኛ የስብከተ ወንጌል ማኅበር በዐዲስ መልክ ተቋቁሞ ሥራ ጀምሮ ነበር፡፡                                 ማኅበሩ፡-

  1. በዐሥራ ኹለቱ ሐዋርያት፣ በሰብአ አርድዕት፣ በሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት፤ በጠቅላላ በመቶ ሃያው የክርስቶስ ቤተ ሰብእ አንጻር የተዋቀረ ማድረግ፣
  2. ዓላማው ስብከተ ወንጌልን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ከጠረፍ እስከ ጠረፍ በማዳረስና አገልግሎቱን በቋሚነት እንዲቀጥል ማድረግ፤
  3. የገቢ ምንጭን በሚመለከት የዐዲስ አበባ ካህናትና ከቤተ ክህነት አገር አቀፍ የቢሮ ሠራተኛ እስከ ሲኖዶስ አባላት ድረስ ያለው ኃይል ከወርኃዊ ገቢው /ክፍያ ላይ/ ከመቶ ኹለት ብር እንዲከፍል የየአህጉረ ስብከቱ ሠራተኛም እንዲኹ እንዲያደርግ፤
  4. ለዚኽ ክፍያ ገቢና ወጭ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ብቃት ያላቸው የሒሳብ ሠራተኞ እንዲመደቡ ማድረግ፣
  5. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የዚህን እንቅስቃሴ ገቢና ወጭ ሕጋዊነት በቅርብ እንዲከታተል ማድረግ፤ የሚሉ በማኅበሩ የሚሠሩ ዝርዝር ሥራዎች ተለይተው ሥራ ጀምሮ ነበር፡፡ 9

ከዚህም በተጨማሪ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የሥራ እንቅስቃሴና የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር በቅንጅት እንዲካሄድ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ የስብከተ ወንጌል ማስፋፋያና ማጠናከሪያ ደንብ በ1991 ዓ.ም እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ የደንቡም ዋና ዓላማ የእግዚአብሔርን መንግሥት መስበክ፣ ትምህርተ ወንጌልን ማስፋፋት፣ መሆኑ በወጣው ደንብ አንቀጽ 1 ንዑስ አንቀጽ 2.2 ተራ ቁጥር “ሀ” ላይ ተቀምጧል፡፡ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያና ማጠናከሪያ ጉባኤ መዋቅር በጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ በሀገረ ስብከት፣ በወረዳና በአጥቢያ ተዘርግቶ እንደ የደረጃው በቅደም ተከተል በ120፣ በ72፤ በ36፣ እና በ24 አባላት ተመሥርቶ ዓላማውን ሲፈጽምና ሲያስፈጽም የነበረ ቢሆንም ጉባኤው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ ሄዶ በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ቆሟል፡፡

የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ከሀገር ውጪ

  1. በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም

የኢትዮጵያና የእስራኤል ግንኙነት በዘመነ ብሉይ ንግሥተ ሳባ ወደ ሰሎሞን ባደረገችው የኢየሩሳሌም ጉዞ የተጀመረ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ለበዓል ሊሠግዱ ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዙ ኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ከእስራኤል ጋር ባላት ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ትስስር ንጉሥ ሰሎሞን ለንግሥተ ሳባ ከሰጣት ከጋዛ ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም የራሷ አድባራት እና ገዳማት እንዲኖራት ምክንያት ሆኗል፡፡                                                                                 እነርሱም፡-                                                                              ሀ. ዴር ሱልጣን፡- ከጎልጎታ አጠገብ የሚገኘው ዴር ስልጣን (ደብረ ሥልጣን) ገዳም ከልደተ ክርስቶስ በፊት በ1013 ዓመተ ዓለም ገደማ ንግሥተ ሳባ ኢየሩሳሌም ስትሄድ ሠራዊቷን እና ጓዟን ያሳረፈችበት ቦታ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡                                                             ለ. ቅዱስ ፊልጶስ፡- የኢትዮጵያ መንበረ ጵጵስና የሚገኝበት ሲሆን ኢትዮጵያዊውን ጀንደረባ ባጠመቀው በቅዱስ ፊልጶስ ስም የተሠራ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በአፄ ዮሐንስ ትእዛዝ መ/ር ወልደ ሰማዕት በ1883 ዓ.ም የገዙት ቦታ ነው፡፡                                                            ሐ. ደብረ ገነት ኪዳነ ምህረት፡- በነቢያት መንገድ አጠገብ የምትገኝ የመነኮሳት መኖሪያ የእንግዶች መቀበያ እና አዳራሽ ያላት ሰፋ ያለ ይዞታችን ስትሆን ቦታው በ1882 ዓ.ም በአፄ ዮሐንስ ዘመን ተጀምሮ ሕንጻውን ያስፈጸሙት በ1885 ዓ.ም. አፄ ምኒልክ ናቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ይዞታቸው በኢሩሳሌም ከተማ የሚገኙ ናቸው፡፡                                               መ. አቡነ ተክለ ሃይማኖት /አልአዛር/፡- በኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ 12 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ ላይ በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም የታነጸ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን መካነ መቃብር በዚህ ይገኛል፡፡ አፄ ኃ/ሥላሴ ያስገዙት ቦታ ሲሆን በአቡነ ፊልጶስ ጊዜ በ1953 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡ በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ያገልግሎት ዘመን ዘመናዊ ሕንፃ ታንፆ ለአረጋውያን መጦሪያነት ያገለግላል፡፡                                                                                               ሠ. ቅድስት ሥላሴ፦ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ በሚገኘው ከሩብ ጋሻ በማያንስ ቦታ ላይ የታነጸ ቤተ ክርስቲያን ሲኾን፣ በአረቦችና በእሥራኤል ጦርነት ምክንያት በአካባቢ ሰው ሊኖር ባለመቻሉ ታቦቱም መነኮሳቱም ተዘዋውረው በኢያሪኮ ይኖራሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ በ1925 ዓ.ም. በእቴጌ መነን የተሠራ እንደ ነበረ ይነገራል፡፡                                                                    ረ. ቅዱስ ገብርኤል፡- በኢያሪኮ ከተማ ለብዙ ጊዜያት የአትክልት ቦታ ሆኖ በቆየው የኢትዮጵያ ይዞታ ላይ የተሠራ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ቦታው ወ/ሮ አማረች ዋለሉ በኋላ እማሆይ አማረች የተባሉ እናት በ1928 ዓ.ም ገዝተውት ለገዳሙ የሠጡት ነው፡፡                                                       ሰ. ቤተልሔም፡- በምድረ ፍልስጥኤም ጌታችን ከተወለደበት ቦታ አጠገብ የሚገኝ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን ቦታው ልዑል ራስ ካሣና ልዑል መኮንን ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ ያስገዙት ነው፡፡                                                                                 በአጠቃላይ በሀገረ እስራኤል የሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት ሀገራችን ከጥንት ጀምሮ የነበራት ጠንካራ ግንኙነትና የኢዮጵያ ቀደምት ነገሥታት ሃማኖተኞች የመሆናቸው ውጤቶች ሲሆኑ ከሐዋርያዊ ተልእኮም አንጻር ገዳማትና አድባራቱ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

  1. በምድረ ጅቡቲ

በደርግ ዘመነ መንግሥት በፖለቲካዊ ወይም በኢኮኖሚያዊ ምክንያት ወደ ጅቡቲ የፈለሱት ኦርቶዶክሳውያን ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጽሙበት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ቀድሰው የሚያቆርቡ ካህናት ስላልነበሩአቸው በጣም ይቸገሩ ነበር። በተለይም በየዓመቱ የስቅለት ዓርብ በአንድ አዳራሽ ተስብስበው ሲያለቅሱ ነበር የሚውሉት፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የስዊድን ሊቀ ጳጳስ ለስደት እንደተዳረጉ ወዲያው በዚሁ ሕዝብ መካከል በመገኘት ለቤተ ክርስቲያናቸው ቅዱስ ሲኖዶስም ለኢትዮጵያ መንግሥትም ለሕዝቡም ጥሪ አደርገው ከሁሉም አቅጣጫ አዎንታዊ መልስ ስላገኙ አሁን በጂቡቲ የሚገኘውን ታሪካዊ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ታንጾ ስደተኛውን ሕዝብ ከችግር ለመታደግ ተችሏል፡፡ ይህ ሐዋርያዊ ተግባር በምድረ ጅቡቲ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የሌላ ሀገር ዜግነት ላላቸው ኦርቶዶክሳውያን ትምህርተ ወንጌል ለማዳረስ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

  1. በምድረ ኬንያ

በምድረ ኬንያ የተመሠረተው ዛሬ የኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የብዙ ኦርቶዶክሳውያን መጠጊያ ለመሆን የበቃው በኬንያ ናይሮቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጅቡቲው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መመሥረት በኋላ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት የተመሠረተ ነው፡፡                                                   እኒህ ብፅዕ ሊቀ ጳጳስ በግሪክም በስዊድንም ሀገር በስደት የሚገኘውን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አማኝ ሕዝብን በማደራጀትና የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ባለቤትም በማድረግ የፈጸሙት ገድል እጅግ የሚያስመሰግን ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ዓላማ ከሆነው ሐዋርያዊ የስብከተ ወንጌል ተልእኮ አንጻር የቤተ ክርስቲያን በምድረ ኬንያ መመሥረት እጅግ አስፈላጊ ነበር፡፡ በመመሥረቱም አያሌ ምእመናንን በወንጌል ማጽናናት ተችሏል፡፡ በተለይም በአሁን ሰዓት በሰሜን አሜሪካ በካሊፎርኒያ ግዛት የሳክራሜንቶ ቅዱስ ሚካኤልና ቅድስት ማርያም አስተዳዳሪ የሆኑት መልአከ ሰላም አባ ገ/ሚካኤል ገ/ኪዳን በኬንያ በነበሩበት ወቅት የናይሮቢ መድኃኔ ዓለም አስተዳዳሪ በመሆን ከፍተኛ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አበርክተዋል፡፡

  1. በምድረ ሊባኖስና በአረብ ኤምሬትስ

በምድረ ሊባኖስና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተለያየ ምክንያት ከሀገራቸው የተስደዱ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ይታወቃል። እነዚህ በተለያዩ የአረብ ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው ሴቶች ሲሆኑ በስደት የሚያጋጥማቸው ፈተና ደግሞ እጅግ ከባድ በመሆኑ የሚጽናኑበትና የሚረጋጉበት ሥፍራ ደግሞ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህን የተረዱት የሊባኖስና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ በሀገረ ሊባኖስ፣ በዮርዳቦስ፣ በኳታር ወዘተ ለቤተክርስቲያን የሚሆን ቦታን ይዞ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን በማስገንባት በሌሎችም የአረብ ሀገራት የሌሎችን ሕንጻ በመጠቀም ምእመና ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡርደሙ እንዳይርቁ በቋሚና በየጊዜው በሚጋበዙ መምህራን ትምህርተ ወንጌል እያገኙ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጠንካራ እንዲሆኑ እያደረጉት ያለው ጥረት እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ በዚህም ሐዋርያዊ ተግባር በርካታ ኦርቶዶክሳውያን በወንጌል ተጽናንተው የስደቱ መከራ ተስፋ እንዳያስቆርጣቸው ይልቁንም ብርቱዎች ሆነው ከቅዱስ ምሥጢር የማይርቁ ጠንካራ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ እውነተኛው የወንጌል ተልዕኮ ምቹ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ላሉት ብቻ ሳይሆን በእንዲህ ያለ ችግር ውስጥ ላሉት የክርስቶስን ወንጌል ማድረስ ስለሆነ በአረብ ሀገራት ውስጥ የሚታየው እጅግ አስደናቂ የሆነ ሐዋርያዊ ተግባርሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው፡፡

  1. በምድረ ደቡብ አፍሪካ

በደቡብ አፍሪካ የምትገኝ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አመሠራረት ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ለመሆን ከመፈለግ የመነጨ ሲሆን ነጻ የመውጣት ንቅናቄ (Ethiopianism አንቅስቃሴም movement) የሚል ነበር፡፡ ኢትዮጵያን የነጻነት ምልክት በማድረግ ከቅኝ ነዢዎች ቀንበር ለመላቀቅ ያደረጉት ትግል ፍሬ አፍርቶ በመጨረሻም ነጻ ወጥተዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያን የነጻነት ተምሳሌት አድርገው እንደታገሉ ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወሕዶ ሃይማኖትም በቅኝ ገዢዎች ለቅኝ ግዛት ዓላማ የተሰበከች ሳትሆን ቅኝ ያልተገዛች ነጻ ሀገር አምና በፈቃዷ የተቀበለችው እውነተኛ የአፍሪካ ሃይማኖት የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ናት በሚል በራሳቸው በደቡብ አፍሪካውያን ፍላጎት የተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን ናት የደቡብ አፍሪካ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፡፡                                              ይች ቤተ ክርስቲያን እንድትሰፋና እንድትጸና በካሪቢን ሀገሮች ሰፊ ሓዋርያዊ ተግባር የፈጸሙት ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ በደቡብ አፍሪካም ሰፊ ሐዋርያዊ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ ከአንግሊካል ቤተ ክርስቲያን (Angelical Church) ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመመለስ ባለፈ ከመሠረተ እምነትና ሥርዓት አንጻር ሰፊ ክፍተት ስለነበረበት ያንን ክፍተት በመጠኑም ቢሆን ለመሙላት መልአከ ሰላም ዳኛቸውም የፈጸሙት ሐዋርያዊ ተግባር ደቡብ አፍሪጋውያኑም በአድናቆት የሚጠቅሱት ተግባርነው፡፡                                                   በረከታቸው ይድረሰንና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስም ወደ ደቡብ አፍሪካ በሄዱባቸው አጋጣሚዎች በመምከርና በማበረታታት ተስፋ እንዳይቆርጡ የማድረግ ሥራን ይሠሩ አንደ ነበር ይጠቀሳል፡፡ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ጊዜ ለበርካታ ደቡብ አፍሪካውያን ማዕርገ ቅስናን በመስጠት ከመካከላቸውም ሊቀ ካህናት በመሾም ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዳትዳከም ያደረጉት አስተዋጽኦ የሚያስመሰግን ነው፡፡                                                  ከዚህም በተጨማሪ ብፁዕነታቸው በስደት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ትምርተ ወንጌል እንዲያገኙ ቋሚ ካህናትንና መምህራንን በመቅጠር በየጊዜውም መምህራነ ወንጌል ከኢትዮጵያ በመጋበዝ ሰፊ ሐዋርያዊ ተግባር የፈጸሙ ሲሆን በርካታ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን በማሳነጽ መእመናን ከቅዱስ ምሥጢር እንዳይርቁና ትምህርተ ወንጌል እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡ ይህ ሐዋርያዊ ተግባር አሁንም በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡                                                                               እዚህ ላይ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ደቡብ አፍሪካውያኑ እዚያው ባሉበት ሠልጥነው ማስተማር እንዲችሉ ታስቦ ብሉምፎንቴን በተባለች የደቡብ አፍሪካ ከተማ ውስጥ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ገዳምና ቅዱስ ያሬድ ካህናት ማሠልጠኛ ተቋቁሞ የነበረ ቢሆንም ገዳሙ በስደት ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ትልቅ አገልግሎት እየስጠ ቢሆንም ለደቡብ አፍሪካውያኑ ታስቦ የነበረውን አገልግሎት ግን እየሰጠ አይደለም፡፡ በመሆኑም በተለይደቡብ አፍሪካውያኑ ኦርቶዶክሳውያን ጠንክረው ለሌሎች አፍሪካውያንም ጭምር መትረፍ እንዲችሉ እነሱን መሠረት ያደረገ ሥራ በሚገባ ታቅዶና ታስቦበት ሊሠራ ይገባል፡፡

  1. በካሪቢያን ሀገሮች

ወደ ካሪቢያን ሀገሮች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የገባችው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሲሆን በዚያው ዘመን በተለይም በጃማይካ ውስጥ የሚገኙ ራስተፈሪያን ማለትም አፄ ኃይለ ሥላሴን እንደ መሲህ የሚያዩ ጃማይካውያንን አስተምሮ በማጥመቅ ትልቅ ሥራ የሠሩት አድዋ የተወለዱትና እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቅጣጠርበ 1970 ዓ.ም ከኒውዮርክ ወደ ጃማይካ የሄዱት አባ ማንደፍሮ ናቸው፡፡                                  እኚህ አባት አፄ ኃይለ ሥላሴን ለ2ኛ ጊዜ ተመልሶ እንደ መጣ ክርስቶስ የሚቆጥሩ ብዙ ጃማይካውያንን ከማጥመቃቸውም በተጨማሪ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን በካሪቢያን ሀገሮች መሥርተዋል፡፡ እንደ አውሮፓውን ዘመን አቆጣጠር በ1979 ዓ.ም የምዕራባዊ ንፍቀ ክበብና የደቡብ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ ሆነው አቡነ ይስሐቅ ተብለው ተሾመው በርካታ ሐዋርያዊ ተግባር በካሪቢያን ሀገሮችና በደቡብ አፍሪካ የፈጸሙ ሲሆን ጃማይካዊው ታወቂው የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ ቦምባርሊንም ያጠመቁት እኚህ አባት ናቸው፡፡ ይህ ተግባር ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፋዊት መሆንዋን በሚገባ የሚገልጽና የስብከተ ወንጌል ተልእኮን በአካባቢ ሳይገደብ ለሁሉ መድረስ እንዳለበት የተረዳ ሐዋርያዊ ተግባር ነው፡፡

  1. በአሜሪካ በአውሮፓና በኤዥያ

በሀገረ አሜሪካና በአውሮፓ በስደት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምክንያት በርካታ አብያተ ክርስቲያናት የተመሠረቱ ሲሆን በርካታ ሊቃነ ጳጳሳትና አህጉረ ስብከትም ይገኛሉ፡፡ አብያተ ክርስቲያናትና ጳጳሳት በዚያ የመገኘታቸው ዋነኛው ምክንያት ስደት ቢሆንም በእግዚአብሔር ፈቃድ ስደቱ ለመልካም ሆኖ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ትልቅ በር ከፍቷል፡፡                     በአጠቃላይ ከሀገር ውጪ የሚገኘው የአብያተ ክርስቲያናት ምሥረታና አንቅስቃሴ በጠንካራ ብፁዓን አባቶች፣ ካህናትና ምእመናን ብርታት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ዓላማ የሆነው የስብከተ ወንጌል ተልእኮን ከማሳካት አንጻር ከፍተኛ ሚናን መጫወት ችሏል፡፡

የስብከተ ወንጌል አሁናዊ እንቅስቃሴ

በአሁን ሰዓት በአትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የፋይናስ አቅም መጠናከር፣ የጳጳሳት ቁጥር መጨመር፤ የአብያተ ክርስቲያናት ቁጥር መጨመር፣ በውጭ ሀገር የቤተ ክርስቲያናች አገልግሎት በስፋት መከናወን በበጎነት የሚጠቀሱ መልካም እድገቶች ቢሆኑም የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ አሁናዊ ሁኔታ ዘመኑ ከሚጠይቀው አገልግሎት አንጻር ሲታይ የስብከተ ወንጌሉን ሥራ በተጠና፤ በታቀደና በተቀናጀ መልክ ስልትን ቀይሶ የማደራጀት፣ የመከታተል፣ አፈጻጸሙን እየገመገሙ የእርምት እርምጃ የመውሰድ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው ለማለት አስደፍርም፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያም ትምህርተ ወንጌልን ለዓለም ሁሉ ለማዳረስ፣ የቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና ሳይበረዝና ሳይከለስ በየትኛውም ቦታ ትምህርተ ወንጌል መሰጠቱን የማረጋገጥ፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበትና ለዚሁ ዓላማ የተዋቀረ መምሪያ ቢሆንም በሰው ኃይል፤ በፋይናንስና በሎጂስቲክስ ያልተጠናከረ ከመሆኑም በላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶች መሻሻልና ማደግ ሲገባው በንጉሡ ዘመንም ሆነ በዘመነ ደርግ ከነበረው እንቀስቃሴ በእጅጉ ተዳክሞ ይታያል፡፡ በመሆኑ በተሰጠው ኃላፊነት ልክ በሀገራችንም ሆነ በመላው ዓለም ያለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴን የመከታተል፣ የመቆጣጠርና የማጠናከር ሥራ መሥራት በሚችልበት ደረጃ ላይ አይገኝም፡፡ በተለይም መምሪያው በውጭ አገር ያሉትን አብያተ ክርስቲያናትና ምእመናንን በተመለከተ በትምህርተ ወንገል ዙሪያ ምን እየተሠራ እንደሆነ የሚከታተልበትም ሆነ የሚቆጣጠርበት የግንኙነት መስመር የለውም፡፡                                                                           በመምሪያው ውስጥ የሚዘጋጁ የሕትመት ሥራዎችም ቢሆኑ ከሐዋርያዊ ተልእኮ አንጻር ሚናቸው ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም የአደረጃጀት፣ የሰው ኃይልና የማቴሪያል ችግር ስላለባቸውና አደረጃጀታቸውና የሥራ ሂደታቸው በአግባቡ ተፈትሾ መፍትሔ ስላልተሰጠው ዘመኑን በዋጀና በሚፈለገው ደረጃ ይገኛሉ ማለት አይቻልም፡፡ ይህም ሲባል እንደ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ እድገት የለውም ማለት ሳይሆን ከስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልኮ መምሪያ አንጻር እድገት አለ ለማለት የሚያስደፈር አለመሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡                                                                           ሆኖም እንደ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምረያ መዋቅር የተዳከሙና መጠናከር ያለባቸው ነገሮች ቢኖሩም ከስብከተ ወንጌል እድገትና ማስፋፋት አንጻር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተሠሩ በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም ሥራዎች ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

  1. የተዘጉ መንፈሳዊ ኮሌጆች መከፈትና መስፋፋት
  2. የማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤ ት/ት መጠናከር
  3. የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መከፈት

 

የዚህ ዘመን ስብከተ ወንጌል ፈተናዎች

ባለንበት በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ዓላማን እንዳታሳካና ተልእኮዋም በሚፈለገው ደረጃ እንዳይፋጠን እንቅፋት የሆኑባትና እየገጠሟት ያሉ ፈተናዎች የውጭና የውስጥ ብሎ በሁለት ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡

. ውጫዊ ፈተናዎች

በዚህ ዘመን የቤተ ክርስቲያናች ሐዋርያዊ ተልእኮን እየተገዳደሩ ያሉ ውጫዊ ፈተናዎች በዋናነት በፕሮቴስታንቱ በኩል የሚደረግ የምእመናን ዝርፊያ (ቅሰጣ)፣ በአክራሪዎች የሚፈጸም የኃይል ጥቃት፣ የርዕዮተ ዓለም ፈተና እና የዘውግ ፖለቲካ ፈተና ናቸው፡፡

  1. የመንጋ ቅሰጣ

በቤተ ክርስቲያናችን የ40 ዓመት ጉዞ ውስጥ በተለይም ባለፉት 30 ዓመታት ቤተ ክርስቲያናችን የገጠማት ከባዱ ፈተና የምዕራባውያን ሥውር ሴራና የፖለቲካ ዓላማን መሠረት ያደረገው ከፕሮቴስታንቱ ዓለም የገጠማት ፈተና ነው፡፡ ይህ ኃይል የክርስቶስን ወንጌል ለዓለም የመስበክ ዓላማ ቢኖረው ኖሮ ፈጽሞ ወንጌልን ያልሰሙትንና የክርስቶስን አዳኝነት የማያውቁትን ሕዝቦች ለማዳን ክርስትናው ያልደረሰባቸው አካባቢዎችን የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ በሠራ ነበር፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ለሁለት ሺህ ዓመታት የክርስትናን እውነት ጠብቃ የኖረችውን ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም በብርቱ ሠርቷል፡፡ የኢትዮጵያ አንድነትን አስጠብቃ በመቆየቷ በምዕራባውያን ቂም የተያዘባት የኢትየጵያን ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከምና ከተቻለም ለምጥፋት አሁንም በብርቱ ይሠራል፡፡ይህ ኃይል ከክርስትናው ዓላማ ባፈነገጠ መልኩ የዘውግ የፖሎቲካውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዓለም አቀፋዊቷን ቤተ ክርስቲያን ስም የአንድ ብሔርና የተወሰነ ሀገራዊ ክልል ሃይማኖት እንደ ሆነ አድርጎ በውሸትና በማጥፋት የዋሃን ምእመናንን በመዝረፍ ቁጥሩን ከፍ አድርጓል፡፡ አንዳንድ ፍቅረ ንዋይ የጸናባቸውና በተለያየ ምክንያት ያኮረፉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ተጠቅሞ ወደ ውስጥ ስርጎ በመግባት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ያስፈልጋታል የሚል እንቅስቃሴን በመፍጠርና በመምራት ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮን ለመቀየርና ለምዕራባውያን ርዕዮተ ዓለም በሚመቸው ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮ ለመተካት በብዙ ሠርቷል፡፡

  1. የአክራሪዎች የኃይል ጥቃት

ቤተ ክርስቲያን በ40 ዓመት ጉዞዋ ከገጠሟት ፈተናዎች ሌላው የአክራሪ ሙስሊሞች እንቅስቃሴ ነው፡፡ የአክራሪ እስልምና መሪዎች በውሸትና በፈጠራ ታሪክ ኢትዮጵያ እስላማዊት ሀገር እንደ ነበረች እየተረኩና ኢትዮጵያም እስልምና የከሸፈባት ሀገር መሆኗን በመቆጨት እየተናገሩ የዋሃን ሙስሊሞችን ለዓላማቸው እንዲሰለፉ በማድረግ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይም ጥቃት እንዲፈጽሙ በብርቱ ይሠራሉ፡፡                                    ይህ ኃይል የኢኮኖሚ አቅሙን ከፍ በማድረግ በገንዘብ ኃይል ምእመናንን እያታለለ በመውስድ፣ እንደዚሁም ደግሞ ጋብቻን እንደ መሳሪያ በመጠቀም ሆን ብሎ ኦርቶዶክሳውያን ሴቶችን በጋብቻ ስም በማታለል፣ ይህም ካልተቻለ ምእመናንን እየገደለ ወንጌልን ለምእመናን የሚያስተምሩ ካህናትን እያረደ ከፍተኛ ፍርሐትን በምእመናን ላይ በመፍጠር ያለ ፍላጎታቸው ከመንጋው እንዲለዩ ያደርጋል፡፡

  1. የዘውግ ፖለቲካው ችግር

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሀገርን በመገንባት የመጀመርያና ዋነኛ ድርሻው ያላትና የኢትዮጵያ አንድነትን አስጠብቆ በመቆየት ትልቁ ሚና የተወጣች አንጋፋና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ ልትመሰገንና ልትከበር የሚገባት ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህች ቤተክርስቲያን “የአንድ ወገንና አካባቢ ሃይማኖት “እንደ ሆነች አድርገው በሚያቀነቅኑ ኃይሎችና “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቤተክርስቲያኒቱን ቀድሞ ማዳከምና ማፈረስ “የሚለውን ሴራ እንደ መርህ ባነገቡ የዘውግ ፖለቲከኞች ምክንያት ከባድ ፈተና እየገጠማት ትገኛለች፡፡ በዚህም ምክንያት በአንዳንድ የክልልና የዞን መስተዳደድሮች ጣልቃ ገብነት የቤተክርስቲያኒቱን መዘረፍና የማምልኪያ መቅደሶቿ መቃጠል፤ ነባር ይዞታዎቿ መነጠቅ ወይም ሕጋዊ እንዳይሆኑ ማድረግ፤ የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ማክበሪያዎችን ለልማት ብሎ መቀማት አልፎም ተርፎም ለሌሎች ቤተ እምነቶች ቦታውን መስጠት ወይም እንዲጋሩ ማድረግ፣ ምእመናንን ማሸማቀቅና ማዋከብ፣ የፖለቲካ ሐሳባቸውን በምእመናን ላይ ለመጫን ከፍተኛ ግፊት ማድረግ፣ አንዳንዴም ጥቃት አድራሾችን አሰልጥኖ በመሰማራት አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠልና ማውደም የዘውግ ፖለቲካው ያመጣቸው የወቅቱ የቤተ ክርስቲያን ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያናችን በነጻነት ወንጌልን ሰብካ የጠፍትን እንዳትመልስና ያሉትንም እንዳታጸና የዘውግ ፖለቲካው ፈተና ሆኖባታል፡፡

  1. የርዕዮተ ዓለምተጽእኖ

የካፒታሊዝም ርዕዮተ ዓለም በነገሠበትና ሰው የሚፈልገውንና የተመቸውን ይመርጣል እንጂ ቋሚ የሥነ ምግባር መስመር የለም ተብሎ በሚታሰብበት በዚህ ዘመንዋናው ስኬትህ ነው እንጂ ወደ ስኬት የምትሄድበት መንገድ ትክክል መሆንና አለመሆን ወሳኝ ነገር አይደለም የሚለው እጅግ አደገኛ የሆነ አስተሳሰብ ሰውን ቁሳዊ እንዲሆን ስላደረገው በክርስትና ውስጥም ሳይቀር የብልጽግና ወንጌል እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡

 

የዘመናችን ርዕዮተ ዓለም በፈጠረው ተጽእኖ በክርስትናው ሽፋን ድኃውን እየበዘበዙ እራሳቸውን የሚያበለጽጉ ከመበለቲቱና ከድኃው የተሰበሰበውን መባዕ ዘርፈው በድኃው ላይ ጌቶች የሚሆኑና ለመንጋው የማይራሩ የነፍሳትም መጥፋት ግድ የማይሰጣቸው አገልጋዮች የመብዛታቸው ምስጢር ገንዘብን የሚያመልከው የዘመናችን ርዕዮተ ዓለም ውጤት ነው፡፡ በአጠቃላይ የተዛባ ርዕዮተ ዓለም በወለደው ድኅረ ዘመናዊነት ተጽእኖ ምክንያት ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እየተዘነጋ ቅድስናና እራስን ለእግዚአብሔር ማስገዛት የሞኝነት ያህል እንዲቆጠር አድርጎታል፡፡ ከዚህም የተነሳ ድኅረ ዘመናዊነት የቅድስናና የርኩሰት ድንበር እንዲጠፋ፣ ግለኝነትና ራስን መውደድ እንዲስፋፋ፣ አርአያ የሚሆን አገልጋይም እንዲጠፋ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህም አገልጋዩን በእጅጉ የሚጎዳ አስተሳሰብ ለስብከተ ወንጌል ትልቅ ፈተና ሆኗል፡፡

ሊውስጣዊ ፈተናዎች

በቤተ ክርስቲያናች ዘርፈ ብዙ ውስጣዊ ፈተናዎች ቢኖሩም መንጋውን እንዲጠብቁ አደራ የተሠጣቸው ካህናትን የተመለከቱ የተወሰኑትን ወቅታዊ ፈተናዎች እንመለከታለን፡፡

  1. አርአያ ማጣት

በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያናችን ከገጠማት ውስጣዊ ፈተኛዎች አንዱና ዋነኛው አርአያን ማጣት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ተዘከሩ መኳንንቲክሙ ዘነገሩክሙ ቃለ እግዚአብሔር እንዘ ትሬእዩ ሠናየ ግእዞሙ ወተመሰሉ በሃይማኖቶሙ የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁ ዋኖቻችሁን አስቡ የኑሯቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በሃይማኖት ምሰሏቸው፡፡'(ዕብ. 13፡7) በማለት ምእመናን መልካም አርአያ የሚሆኗቸው መምህራንን በሃይማኖት እንዲመስሏቸው አስተምሯል፡፡ ይህም ምእመናን አርአያ የሚያደርጉት መምህር እንደሚያስፈልጋቸው መምህራንም ለምእመናን አርአያ መሆን እንዳለባቸው የሚጠቁም መለኮታዊ ሐሳብ ነው፡፡ ባለንበት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በየደረጃው ያለ አገልጋይ እስከ ሕይወት መሥዋዕትነትም ቢሆን ዋጋ እከፍላለሁ፤ ከዓለም ርኩሰት ተጠብቄ ለአልጫው ዓለም ጨው እሆናለሁ፤ የሚል ሳይሆን በከፍተኛ የርኩስት ተግባር ውስጥ የሚዘፈቅ፣ ክብረ ክህነትን በሚያቀሉ ተግባራት የሚሰማራ፣ አንዳንዱ በገንዘብ ዘረፋና በማጨበርበር የሚታሰር፣ አንዳንዱም በሟርትና ጥንቆላ ሥራዎች የሚሳተፍ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን የሚንቅ ትውልድ እንዲፈጠርና ሃይማኖት አይጠቅምም የሚል ትውልድ እንዲበራከት ያደርጋል፡፡                          ሁሉም አገልጋዮች አርአያ የሚሆኑ አይደሉም ባይባልም ቁጥራቸው በመቀነሱና በአርአያነት ይልቅ መሰናክል የሚሆኑ አገልጋች በመብዛታቸው በስብከተ ወንጌል ሚፈለገው ለውጥ እንዳይመጣ ምክንያት ሆኗል፡፡

  1. የአመራር ዕጦት

በዕቅድ የሚመራ ስብከተ ወንጌል ተልዕኮ አላማን ግብ ያለው የቤተ ክርስቲያንዋነኛ ተልእኮ እንጂ በግምት ወይም በዘፈቀደ የሚደረግ ተራ ተግባር አይደለም፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱ ጠካራ አመራርን ይፈልጋል፡፡ ነገርግን በአመራር እጦት ምክንያት ያለ ጸጋውና ያለ ጥሪው ለእንጀራ ብቻ የሚያገለግል ከመብዘቱም በተጨማሪ ጸጋው ያለውም ቢሆን የወንጌል ዓላማ የዘነጋ በዘር፣ በፖለቲካ፣ ወይም በገንዘብ ፍቅር የተጠመደ ሆኖ ይገኛል፡፡                                               በቤተ ክርስቲያን አመራር በኩል ከመሪነት ጋር የሚመጣ ኃላፊነትንና ተጠያቂነት ስለሌለ በመሪውና በተመሪው መካከል ያለ ስፊ የፍላጎት ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ በተለይ የመሪነት ዓላማ ያልተረዱ ለማገልገል ሳይሆን ለመገልገል የተሠየሙ አመራሮች ቁጥር መብዛት ዋነኛ የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ የሆነውን ስብከተ ወንጌል እንዲዘነጋ ገንዘብ በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ መጠመድ ዋነኛ የቤተ ክርስቲያን አመራሮች ተግባር ሆኗል፡፡ ይህም በስብከተ ወንጌል ላይ የራሱ ተጽእኖ ፈጥሯል፡፡

  1. የፖለቲካ ወገን ተኝነት

ስብከተ ወንጌል ከዘር ከፖለቲ ነጻ በመሆን የወንጌልን እውነት የሚነገርበት ሰውን የሚጎዳ ነውርም የሆነ ተግባር ሲፈጸምና ፍርድ ሲጓደል ፍርድ ጎደለ ድኃ ተበደለ በማለት ለእውነትና ለፍትሕ ዘር ሳይለዩ ለሁሉ የሚጮሁነትና ማንንም ሳይፈሩ ሁሉንም ገሥጹበት አገልግሎት እንጂ የፖለቲካ ወገንተኛ በመሆን የምንደግፈው አካል ሲበድል ዝም የምንልበት የምንቃወመው አካል ቢበደል እንኳን እንዳላየና እንዳልሰማ ዝም የምንልበት አገልግሎት አይደለም፡፡                          ነገር ግን በዘመናችን ያለው አገልግሎት ፖለቲካው እየተጫነው ለእውነትና ለፍትሕ መቆም እያቃተን የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌለን ሁሉም በእኩልነት የሚሰማው አገልጋይ ቁጥሩ በእጅጉ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ይህም የዘመናችን የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን በእጅጉ ጎድቶታል፡፡

ማጠቃለያ

በሦስቱ ሕግጋት ከአምልኮ እግዚአብሔር ሳትለይ ጸንታ የኖረችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሳለፈችው የረጅም ዘመን ታሪክ ብዙ የጨለማም ወርቃማም ጊዜያትን አሳልፋለች፡፡ በተለይም በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ እጅግ ውጤታማ ከነበረችባቸው ዘመናት ቅዱስ ያሬድ የተነሳበት፤ ቤተ ክርስቲያናችን እስከ ዛሬ ድረስ የምትገለገልበት ሰማያዊ ዜማን ያገኘችበት ዘመንና ምናኔን ከስብከተ ወንጌል ጋር አስተባብረው የያዙ ጻድቁ አባታች አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተነሱበት ዘመን በተለየ መልኩ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ በተለይም ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት የፈጸሙት ሐዋርያዊ ተግባርና የጻድቁ ደቀ መዛሙርት የሆኑት 12 ንቡራነ እድ አህጉረ ስብከት ተከፋፍለው አንደ አባታቸው እነርሱም የፈጸሙት ሐዋርያዊ ተግባር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ ሆኖም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተከሠተው ቤተ ክርስቲያንን በከፍተኛ ደረጃ የጎዳው የአሕመድ ግራኝ ወረራ በከፍተኛ ደረጃ ተነቃቅቶ የነበረው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ አጥፍቶታል፡፡ ወረራው ያስከተለው ጉዳት ከፍተኛ ስለነበር ሙሉ በሙሉ ወደ ነበረበት ለመመለስ እጅግ አዳጋች የነበረ ቢሆንም ከአህመድ ግራኝ ሞት መኋላ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ሊያንሰራራ ችሏል፡፡ ከዘመናት በኋላም ዘመነ መሳፍንት አልፎ ሀገራችን በማዕከላዊ መንግሥት መመራት ስትጀምር አብያተ ክርስቲያናት እየበዙ የስብከተ ወንጌል አገልግሎትም ከገዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ እንደ መጣና በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከግብፅ አገዛዝ ተለይታ በራሷ ፓትርያርክና በራሷ ቅዱስ ሲኖዶስ ሲኖዶስ ስትጀምር በስብከተ ወንጌልም ረገድ ከፍተኛ መሻሻልና መነቃቃት ተፈጥሮ እንደነበረ ተመልክተናል፡፡ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮን የበለጠ ማስፋፋት ይቻል ዘንድ ሰበካ ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላም ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ የነበረው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ምን ይመስል እንደነበረና በስብከተ ወንጌል ዙሪያ የነበሩና አሁንም ያሉ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን በዝርዝርተመልክተናል፡፡ በመሆኑም ዘመኑን ዋጅተን ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋትና በዚህ ዘመን እየገጠሙን ያሉ ተግዳሮቶችን በመሻገር ታሪካችንን፣ ባሕላችንንና ሃይማኖታችንን ጠብቀን ለቀጣይ ትውልድ ማስረከብ እንችል ዘንድ፡-

– በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅሮችን በማጠናከር በየመዋቅሩ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ድረስ ኦርቶዶክሳውያን የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ባለሞያዎችን በየዘርፍ ዘርፉ በማቋቋም አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ በሚያስፈልግ ጊዜና ሰዓት እንዲሰጡ ማድረግ፣

– ካህናት የዋጁና በከፍተኛ ፍጥነት እየተለዋወጠ በሚገኘው ዓለም ውስጥ ቀድመው ተገኝተው መምራት የሚችሉባቸው ወቅታዊ ሥልጠናዎች ከማዕከል እስከ አጥብያ ቀጣይነት ባለው መልኩ በመስጠት የማብቃት ሥራን መሥራት፤

-የቤተክርስቲያኒቱ ተተኪ ትውልድ የሆነው ወጣቱ በእምነቱ እንዳያፍርና እንዳይፈራ የተጠናና የታቀደ ኦርቶዶክሳዊ ማንነቱ የሚያስገነዝብ ስልጠናን በየደረጀው መስጠት፣

-ከተለያዩ ቤተ እምነቶች በቃልም ሆነ በጽሑፍ መልክ የሚመጡ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ያነጣጠሩ እንቅስቃሴዎችን መመከት ይቻል ዘንድ የዕቅበተ እምነት ሥራን የሚሠሩ የተመረጡ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንትን፤ የኮሌጅ መምህራንንና ሰባክያነ ወንጌልን በግብረ ኃያል መልክ በማደረጀት ከሊቃውንት ጉባኤ ጋር በጥምረት እንዲሠሩና ተገቢውን መልስ በተገቢው ጊዜ እንዲሰጡ ማድረግ፤

-በተጠናና በታቀደ መልኩ ባህልን ታሪክንና ቋንቋን መሠረት ያደረጉ የወንጌል አገልግሎቶችን በተጠናከረ መልኩ መተግበር፣

-የሥልጠና ተቋሞቻችን የማስተማር ካሪኩለማቸውን ከነባሩና ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ካቆዩልን ሥርዓተ ትምህርትና የትርጓሜ ስልት ጋር በማገናዘብ ዘመኑንና ሁኔታውን የተረዱ ችግር ፈቺ የሆኑ ሊቃውንት በብዛትና በጥራት የሚፈሩባቸው ተቋማት እንዲሆኑ ማድረግ፣              -ውሳጣዊ ችግሮችን በጥንቃቄ በመፍታትና ለኢአማንያን መሳለቂያ ከመሆን በመቆጠብ የቤተ ክርስቲያን ዋና ተልእኮዋ ወደ ሆነው ስብከተ ወንጌል መመለስ፣ በዚህ ዘመን ልተገብራቸው የሚገቡን ዐበይት ተግባራት ናቸው፡፡

በመሆኑም ዘመኑ ቀድሞ በማሰብ በእምነት፣ በዕውቀትና በጥበብ እየተጓዝን የወንጌልን ተልእኮ የምንፈጽምበት እንጂ ተዘናግተን የምንቀመጥበት አይደለምና ነቅተን አገልግሎታችንን በትጋት ልንፈጽም ይገባናል፡፡

በመጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወ/ትንሣኤ

 

የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ኅትመት አጀማመር ታሪካዊ ዳሰሳ፣

መግቢያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን፣ ትምህርቷን፣ ትውፊቷን፣ ታሪኳን እና መንፈሳዊና ልማታዊ አገልግሎቶችን ለተከታይ ምእመናኖቿ በኅትመት ሚዲያ ስታስተምር መቆየቷን ታሪክ ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኅትመት ሚዲያ ታሪክ ከ፲፱፻፴/1930ዎቹ ጀምሮ የሚጠቀስ ሲኾን በዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ የኅትመት ውጤቶች እየታተሙ ለምእመናን ይሠራጩ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምያ ለመጀመሪያ ጊዜ በትምህርተ ሃይማኖት ላይ ያተኮረ ‹‹ተክለ ሃይማኖት›› የተሠኘ ጋዜጣ ኅዳር ወር ፲፱፻፴፰/1938 ዓ.ም ታትሞ ለንባብ በቃ፡፡
በመቀጠልም በ፲፱፻፵/1940 ዓ.ም ‹‹ዜና ፡ ቤተ ፡ ክርስቲያን ፡ ዘኢትዮጵያ›› ጋዜጣ መታተም ጀመረ ሲኾን ዜና፣ የክብረ በዓላት ታሪክ፣ ወቅታዊ ዘገባዎች፣ እና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚያቀርብ ነበር፡፡ እነዚህ ጋዜጦች በየ፲፭/15 ቀኑ እየታተሙ ይሠራጩ የነበረ ሲኾን በሂደትም ወደ አንድ ጋዜጣነት ተጣምረው በየሳምንቱ እሑድ እንዲወጡ ተደርጎ ነበር፡፡

ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በቤተ ክርስቲያን ኅትመት ሚዲያዎች ዕድሜ ጠገብ እና በታሪክም ትልቅ ሥፍራ የሚይዝ ነው፡፡ ዜና ቤተ ክርስቲያን በረጅም ታሪኩ በርካታ ዓምዶችን በመክፈት የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮችን በስፋት ሲያስተናግድ የቆየና የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን ኾኖ የዘለቀ አንጋፋ የሕትመት ሚዲያ ነው፡፡

ጋዜጣው በዋነኛነት የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ሓላፊዎች የሚያከነወኗቸው ሥራዎችን ፣ ጉባኤዎችንና ስብሰባዎችን ፣ እንዲሁም በአህጉረ ስብከትም ኾነ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚከናወኑ ልማታዊና መንፈሳዊ እንቅስቀሴዎችን በመዘገብ ለአንባብያን ሲያደርስ የቆየ መንፈሳዊ ጋዜጣ ነው ፡፡

ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በሀገራችን እንደ ዛሬው የሚዲያ አማራጭ በሌለበት በዚያ ዘመን የቤተ ክርስቲያኒቱን መልካም ተግባር እየዘገበ በማስነበብ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ክብር ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ አገልግሎት ተደረሽነቷ ፣ በተለይም በድርቁ ዘመን ለተጎዱ ወገኖች ታደርገው የነበረውን ሰብአዊ ድጋፍ በዜና ሽፋን ከትቦ ለመላው ዓለም በማሳወቅ ረገድ ፣ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ያከናወነው ተግባር በወቅቱ ተወዳዳሪ አልባ ጋዜጣ እንዲኾን አስችሎታል ፡፡

ዓምዶች፣

ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በዋነኛነት የሚያተኩረው የዜና ሽፋን በመዘገብ ላይ ቢኾንም የጋዜጣው ወቅታዊ መልእክት ማስተላለፊያ በጥንቱ ርእሰ ነገር በኋላም ርእሰ አንቀጽ የተሰኘ ዓምድ ይዞ ዘልቋል፡፡
በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የሚሻሻልበትን ፣ የገቢ ምንጭ የሚስፋፋበትን ፣ መሪዎቿ የሚመረጡበትንና በተሐድሶ ጎዳና የምትራመድበትን መንገድ በማብራራት እና በማስረዳት የሚቀርቡና የቤተ ክርስቲያንን ታሪክም ኾነ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርት በጠቅላላውም መንፈሳዊውን ፍልስፍና ተተንትነውና ተመሥጥረው ለግንዛቤና ለምርምር የሚቀርቡ ጽሑፎች የሚሠፍርበት፡- ‹‹ተሐድሶ ፡ ዓምድ ፡ ለውይይት›› በኋላም ‹‹የተሐድሶ ፡ ዓምድ ፡ ለውይይትና ፡ ለትምህርት›› የተሰኘ ዓምድ እስከ ፲፱፻፹፩/1981 ዓ.ም ይዞ ዘልቋል፡፡

እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያትም የተለያዩ ዓምዶችን በመክፈት ጽሑፎችን ያሰፍር የነበረ ሲኾን፡-
‹‹ከመንፈሳዊ ፡ ዓለም›› ፣
‹‹የሴቶች ፡ ዓምድ›› ፣
‹‹ምን ፡ ይላሉ ? የአስተያየት ፡ ዓምድ›› ፣
‹‹ኢትዮጵያ ፡ በዘመነ ፡ ኦሪት ፡ የታሪክ ፡ ዓምድ›› ፣
‹‹የሊቃውንት ፡ ዓምድ›› ፣
‹‹ወጣቶችና ፡ ቤተ ፡ ክርስቲያን ፡ የወጣቶች ፡ ዓምድ›› ፣
‹‹ኢትዮጵያ ፡ በዘመነ ፡ ሐዲስ ፡ የታሪክ ፡ ዓምድ››
‹‹ትዝብትና ፡ ምክክር ፡ ዓምድ›› ፣ የመሳሰሉትን ዓምዶች በመክፈት ትምህርትንና ታሪክን ለትውልድ ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡

አዘጋጆች፣

ከጋዜጣው ምሥረታ ጀምሮ በርካታ በቤተ ክርስቲያንንም ኾነ በዘመናዊ ትምህርት አንቱ የተሠኙ አንጋፋ ሊቃውንት የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ፣ ምክትል አዘጋጅ እና የጽሑፍ አዘጋጅ ኾነው ተሳትፈውበታል፡፡
በምሳሌነት ለመጥቀስ ያክል፡-
በ፲፱፻፶/1950ዎቹ ዓ.ም አባ ተፈራ (ገብረ ሕይወት) መልሴ፣ ቀሲስ ክንፈ ገብርኤል አልታየ ናደው (ሊቀ ካህናት) ፣
በ፲፱፻፷/1960ዎቹ ደግሞ የጋዜጣው ዕድገት ጠባቂዎች በሚል ፩ኛ ቀሲስ ሰሎሞን ገብረ ሥላሴ ፣
፪ኛ አቶ ኢሳይያስ ዓለሜ፣
፫ኛ አለቃ ብርሃኑ መኰንን ፣
ዋና አዘጋጅ ፡- ቀሲስ ክንፈ ገብርኤል አልታየ (ሊቀ ካህናት) ቀጥሎም ፡-
፩ኛ ክቡር አቶ መኰንን ዘውዴ ፡- በም/ሚኒስቴር ማዕረግ የጠ/ቤተ ክህነት ም/ሥራ አስኪያጅ ፣
፪ኛ ዶክተር ዕጓለ ገብረ ዮሐንስ፣
፫ኛ አቶ ኢሳይያስ ዓለሜ ፡- የታሪክ፣ ድርሰትና ስብከት ክፍል ሹም ፣
ዋና አዘጋጅ ፡- ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ (መጋቤ ምስጢር) በመቀጠልም ፡-
፩ኛ ክቡር ንቡረ ዕድ ኤርምያስ ከበደ ፡- የጠ/ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ፪ኛ ዶክተር ዕጓለ ገብረ ዮሐንስ ፡- በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪ ፣ ፫ኛ ቀሲስ ሰሎሞን ገብረ ሥላሴ ፡- የታሪክ፣ ድርሰትና ስብከት ክፍል ተ/ሹም ፣ ዋና አዘጋጅ ፡- ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ (መጋቤ ምስጢር) ኾነው የጋዜጣውን ሕትመት ያስቀጠሉ ሲኾን ዋና አዘጋጅ ኃይለ ልዑል ወልደ ገሪማ፣ ተ/ዋና አዘጋጅ ይቁም ግዛው ፣ እንዲኹም ም/አዘጋጅ መልአከ ምሕረት ዓምደ ብርሃን ገብረ ጻድቅ የመሳሰሉት ሊቃውንት በመሪነት ተሳትፈውበታል፡፡

በተለይም መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ለረጅም ዓመታት የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ኾነው በማገልገል የጋዜጣው ምልክት እስከ መኾን የደረሱ ናቸው፡፡

ሥያሜና አርማ፣
የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ኅትመት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የጋዜጣው ስም እና አርማ (ሎጎ) በየጊዜው እየቀያየር መጥቷል፡፡

በጥንቱ፡- ዜና ፡ ቤተ ፡ ክርስቲያን ፡ ዘኢትዮጵያ ፡ በሚል ሥያሜ አርማው (ሎጎው) የእጅ መስቀል የነበረው ሲኾን በሂደትም አርማው (ሎጎው) የቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ፣ ሠናይ ፡ እገሪሆሙ ፡ ለእለ ፡ ይዜንው ፡ ሠናየ ፡ ዜና ፡ ሮሜ ፡ ም፡ ፲ ቍ ፲፬ የሚል መሪ ቃል በክብ ቅርፅ ተጽፎበት ይታተም ጀመረ፡፡

በመጨረሻም፡- አርማው (ሎጎ) የቤተ ክርስቲያን ጉልላት መስቀል ኾኖ ‹‹ሠናይ ፡ እገሪሆሙ ፡ ለእለ ፡ ይዜንው ፡ ሠናየ ፡ ዜና››፡፡ መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ፡፡ የሚል መሪ ቃል ይዞ በተለያየ ቀለም ማለትም በጥቁር ፣ በሰማያዊ ፣ በቀይ ቀለማት ዘመኑን በዋጀ ኅትመት (ወረቀት) ‹‹ይህ ጋዜጣችን የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን እምነትና ትምህርት ፣ ሥርዓትና ባሕል ፣ ታሪክና ዜና የሚያትም ስለሆነ ዜና ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ተሠየመ›› ፡፡ ተብሎ እየታተመ እስከ አሁን ዘልቋል ፡፡ጋዜጣው ዋጋ ተተምኖለት በሽያጭ ለአንባብያን የሚሠራጭ እንደ መኾኑ መጠን በጥንቱ 0.10 የነበረ ሲኾን በየዘመናቱ የዋጋ ክለሳ እየተደረገበት በአሁኑ ወቅት ዋጋ ብር 40 ለውጭ ሀገር እጥፍ ይኾናል በሚል እየታተመ ይገኛል ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልሣን ኾኖ የዘለቀው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በብዙ ውጣ ውረድ አልፎ በአሁኑ ሰዓት 66ኛ ዓመት ቁጥር 167 ደርሷል፡፡ እነሆ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የሚዘጋጀው ይህ አንጋፋ ጋዜጣ ይዘቱን እና ኅትመቱን በማሳደግ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ለትውልዱ ተደራሽ እንዲኾን እየሠራ ይገኛል፡፡

መምህር ማርቆስ ተበቃ ኬሬ
የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ

 

 

 

፫ኛው ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን የመክፈቻ መርሐ ግብር በየረር ጎሮ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል እጅግ ደስ በሚል መንፈሳዊ ድምቀት ተከናውኗል

“በወንጌል ኮነ ሕይወትነ – በወንጌል ሕይወታችን ሆነ” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው ፫ኛው ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን የመክፈቻ መርሐ ግብር ሚያዝያ ፲፰ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ አማካኝነት የተዘጋጀ ሲሆን
በዕለቱ የወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስና መካነ ጎልጎታ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ ሊቀ ሊቃውንት ሥሙር አላምረው “ወቦአ ከመ ይኅድር ምስሌሆሙ፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ” ሉቃ. ፳፬፥፳፱ የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ እንዲሁም የዘመነ ትንሣኤ ሦስተኛ ሳምንት በሆነችው በዚህች ሰንበት ዘመነ ፋሲካን የዋጀ ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲሆን፤
“ይህ የወንጌል ቀን መዘከር ያስፈለገውም በጨለማ ውስጥ ያለነውን ወደ ብርሃን ለማውጣት፣ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ ለመመለስና ሌሊት የሆነውን ሕይወታችንን ወደ ቀን በንስሐ ለመመለስ ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው አስተምረዋል።
በመቀጠልም የመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ጸሐፊ መ/ር ሽፈራው እንዳሻው መምርያው ያለበትን አሁናዊ ሁኔታና ይህ የስብከተ ወንጌል ቀን ክብረ በዓል ያስፈለገበት፣ ተደራሽነትና አላማ ምን እንደ ሆነ ገልጸው ማኅበረ ምእመናኑ የመምርያውን ድኅረ ገጽና በebs tv በየሣምንቱ የሚያቀርበውን እየተከታተሉ እንዲማሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

፫ኛው ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን መክፈቻና ማብሰሪያ መርሐ ግብር በተመረጡ 12 አብያተ ክርስቲያናት ተከናወነ!!

ሚያዝያ ፲፰ ቀን ፪፻፲፰ ዓ.ም.)
ስ/ወ/ሐ /ተልእኮ ሚዲያ /አ/አ/
የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በወንጌል ሕይወታችን ሆነ” በሚል መሪ ቃል ለ፫ኛ ጊዜ ሀገር አቀፍ በሆነ መልኩ በቅድስት ሥላሴ ዩንቨርስቲ ሁለገብ አዳራሽ ሚያዝያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም የሚያከብረውን “የስብከተ ወንጌል ቀን” የማብሰሪያ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት በተመረጡ አድባራትና ገዳማት በተመሳሳይ ሰዓት በስብከተ ወንጌል ጉባኤያት ተከብሮ ውሏል።
በዚህ ፫ኛው የስብከተ ወንጌል ቀን ማብሰሪያ በአዲስ አበባና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ከተማ ሥር በሚገኙ የተመረጡና ከፍተኛ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ በሚደረግባቸው 12 ገዳማትና አድባራት የተደረገ ሲሆን በዕለቱም በመምሪያው ጋባዥነትና የወንጌል መምህራንና ዘማርያን ተጋብዘው ሰፊ አገልግሎት ተሰጥቷል።
በየቦታው በተመደቡ አስተባባሪዎች አማካኝነት የስብከተ ወንጌል ቀንን ዓመታዊ ጉባኤ በማድረግ መዘከር ያስፈለገበት በጨለማ ውስጥ ያለነውን ወደ ብርሃን ለማውጣት፣ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ ለመመለስና ሌሊት የሆነውን ሕይወታችንን ወደ ቀን በንስሐ ለመመለስ
መሆኑ ተወስቷል።
በተጨማሪም መምሪያው ከሁሉም አህጉረ ስብከትና የትምህርት ተቋማት ጋር በመናበብና በመተባበር የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴን ለማጠናከር እያከናወነ ያለውን ተግባር ተስፋ የሚጣልበት መሆኑ በብዙዎች ምስክርነት አግኝቷል።
መርሐ ግብሩ ነገ ሰኞ ሚያዝያ ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፪፻፲፰ ዓ.ም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን፣ “ሀገር አቀፍ ዓመታዊ የወንጌል ቀን እና የምክክር ጉባኤ” በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሁለገብ መሰብሰቢያ አዳራሽ ከረፋዱ 2:30 ጀምሮ እንደሚካሄድ ታውቋል።

በበርካቶች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ድረ-ገጽ አገልግሎት ጀመረ

ሚያዚያ ፲፭ ቀን ፳፻፲ወ፰ዓ.ም.
ኢኦተቤክ ቤሕአልድ
አዲስአበባ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለዘመናት በመኳንንት፣ በወይዛይርትና በግለሰቦች አማካኝነት በውርስ፣ በኑዛዜና በስጦታ መልክ የተሰጧትንና በይዞታ አስከብራ ያቆየቻቸውን ቤቶች፣ ሕንፃዎችና ይዞታዎች ረጅም ዘመናት በድርጅቱ ባሳለፉ ቅን የድርጅቱ ሠራተኞች አእምሮ ከመያዝ ባሻገር የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲያውቁት በሚስችል መልኩ ተሰንዶ አለመቀመጡ ድርጅቱ በሥሩ የሚገኙ ደንበኞችን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚቸገር ከመሆኑም በላይ የሚባክኑ ይዞታዎች መኖራቸውን ይነገራል ።
ይህንን የተረዱት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪጅ ሊቀ ስዩማን እስክንድር ገብረክርስቶስ በድርጅቱ ሥር የሚተዳደሩ ቤቶች ፣ ሕንጻዎችና ይዞታዎች መላ ታሪካቸው ተመዝግቦና ተሰንዶ ለሚመለከታቸው አካላት ከማቅረብ ባሻገር በዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተጫኑ እንዲሰነዱ ለማድረግ ለድርጅቱ የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ክፍል ከማቋቋም ጀምሮ በመላው ዓለም ተዳራሽነቱን ለማስፋት የድርጅቱን ድረ-ገጽ ማበልጸግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ወደ ሥራ ተገብቷል።
በዚህ ሥራ ላይ ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ቆርጠው የተነሱ ቅን የቤተክርስቲያን ልጆችን በማስተባበር የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የሚል ድረ-ገጽ በልፅጎ በዛሬው እለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፤
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብጰት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንና የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣
ክቡር ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ የጠቅላይ ቤተክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ፤
ክቡር ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ባቱ የጠቅላይ ቤተክህነት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ፤ ክቡራን የጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎችና የየድርጅቶች ሥራ አስኪያጆች፤ ክቡራን እና ክቡራት የድርጅቱ ሠራተኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በታላቅ መንፈሳዊ ስነ-ስርዓት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
©የቤቶችና ሕንጻዎች ሚዲያ

በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በተደረገው ስምሪት በጎፋ ሳውላ ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና እና የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ተጠናቀቀ!!

ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም
ስ/ወ/ሐ/ተ ሚዲያ /አዲስ አበባ/
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ካለፈው የካቲት 26 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ በተመረጡ 32 አህጉረ ስብከት ሲያካሂድ የቆየው ስምሪት በአብዛኛው አህጉረ ስብከት እጅግ ስኬታማ በሆነ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን በቀሪዎቹ ደግሞ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ስምሪቱ በዋናነት ትኩረት ያደረገው ምዕመናንን በሃይማኖታቸው ለማጽናት፣ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ለማስፋፋትና ወንጌል በስፋት እንዲደርስ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ቀደም ሲል ተገልጿል።
ከሚያዝያ 12 እስከ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት ቀናትም በጎፋና ባስኬቶ ሳውላ በጋሞና አካባቢው አርባ ምንጭ አህጉረ ስብከቶች ለአህጉረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ ካህናትና ለ/ሰ/ት/ ቤት ወጣት ተወካዮች በመ/ሐ ቃለ ጽድቅድ አሰፋ እና በመ/ር ዘማርያም ጌጡ ፦ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ፣ዕቅበተ እምነት ፣የወንጌል አገልግሎታችንና የቤተክርስቲያን ታሪካዊ ጉዞ በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሥልጠና ተሰጥቷል።
በመጨረሻ በአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በተሰጠው መልእክት ስብከተ ወንጌልን ማጠናከር ሥራ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ባለ ድርሻ አካላት መሆኑን ተገልጾና መመሪያ ተላልፎ ሥልጠናው ተጠናቋል።
©የመረጃው ምንጭ ጎፋ ሳውላ ሀገረ ስብከት

ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ “በወንጌል ሕይወታችን ሆነ” በሚል ሕያው ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ “የስብከተ ወንጌል ቀን” እንዲሚያከብር ገለጸ!!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
«በወንጌል ኮነ ሕይወትን»
በወንጌል ሕይወታችን ሆነ
በመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ቤ/ክ/የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ «የስብከተ ወንጌል ቀንን» አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ፣
የስብከተ ወንጌል ቀን በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት መከበር ከተጀመረ ለ3ኛ ጊዜ ሲሆን በዚህ በጀት ዓመት ከሚያዝያ 18 ቀን እስከ ሚያዝያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የሚከናወን መርሐ ግብር ነው፡፡
በመሆኑም በመጀመሪያው ቀን ማለትም ሚያዝያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ በ8 ክ/ከተማ ቤተክህነት በተመረጡ 9 አድባራትና ገዳማት ማለትም፡-
1.በአራዳ ጉለሌ ጽ/አ/ቅ/ሩፋኤል ቤተክርቲያን
2.በየካ ክ/ከ/በየካ ደ/ሣ/ቅ/ሚካኤል ቤተክርቲያን
3.በአዲስ ከተማ በማህደረ ስብሐት ቅ/ልደታ ቤተክርቲያን
4.በኮልፌ ቀራንዮ በአየር ጤና አንቀጸ ብርሃን ኪዳነ ምሕረት ቤተክርቲያን
5.በለሚ ኩራ በጐሮ ደ/ም/ቅ/ገብርኤል ቤተክርቲያን
6.በቦሌ በገርጂ ደ/ገ/ቅ/ጊዮርጊስ ቤተክርቲያን
7.በአቃቂ ቃሊቲ መ/ብ/ቅ/ገብርኤል ቤተክርቲያን
8.በነፋስ ስልክ በጀሞ ፈ/ዮ/ቅ/ዮሐንስና ማርያም ቤተክርቲያን
9.በሸገር ሀገረ ስብከት አድባራት ማለትም
10.በዓለም ገና ደ/ም/ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል
11.በወይብላ ማ/መ/ቅ/ማርያምና ቅ/ሚካኤል ካቴድራል
12.በካዬ ፈጬ ደጉ ደ/ኃ/ቅ/ገብርኤል ቤተክርቲያን ልዩ መንፈሳዊ ጉባኤያትን በማዘጋጀት በታላላቅ መምህራን ዕለቱን በማስመልከት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥ ሲሆን በተጨማሪም በዘማሪያን አማካኝነት በዝማሬ እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ቀን ይሆናል፡፡
በሁለተኛው ቀን ሚያዝያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱሰ አባታችን ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ የቅዱስ ሊኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዓን አበው ሊቀነ ጳጳሳት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያውና የድርጅት የሥራ ኃላፊዎች ፤ የሁሉም አህጉረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍል ሐላፊዎች፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ዋና ክፍል ኃላፊና ም/ኃላፊ የ8ቱ ክ/ከ/ቤ/ክ/ሥራ አስኪያጆችና የስ/ወ/ኃላፊዎች የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎችና የስ/ወ/ኃላፊዎች እንዲሁም የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና የሀ/ስ/የስ/ወ/ ዋና ክፍልና ም/ኃላፊ የክ/ከተማ ቤ/ክ ሥራ አስኪያጆችና የስ/ወ/ኃላፊዎች እንዲሁ ተጋባዥ እንግዶችና የመምሪያው አጋሮች በተገኙበት የጥናት የውይይትና የምክክር መርሐ ግብር በልዩ ሁኔታ ለሙሉ ቀን የሚካሄድ ሲሆን በመጨረሻም የጋራ የአቋም መግለጫ በማውጣት መርሐ ግብሩ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡
በመሆኑም ይህን መልእክት በመከታተል ላይ የምትገኙ የሚመለከታችሁ ጥሪ የተላለፈላችሁ አካላት በተጠቀሱት ቀናትና ቦታ በሰዓቱ በመገኘት ተሳትፎ እንድታርጉና ለቅ/ቤ/ክ/የሚጠቅመውን ምክረ ሐሳባችሁን እንድትለግሱ በመምሪያው ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በተጨማሪም በቅድስት ቤተክርስቲያን የስ/ወ/ቀን ያልሆነ ዕለት ባይኖርም በተለየ ሁኔታ ቀኑን በማሰብ የስ/ወ/አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት ያመች ዘንድ በሁሉም አገልጋዮችና አማኞች ዘንድ የወንጌልን እውነት ለማስረፅ የተደረገ /የተዘጋጀ/ መርሐ ግብር ነው፡፡
በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ እያስገነዘብን በተለይም በሚዲያ ሥራ ላይ ተስማርታችሁ የምትገኙ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በጉባኤያቱ ቦታዎች ላይ በመገኘት የሚዲያ ሽፋን እንድትሰጡልንና የስ/ወ/ተደራሽነትን አጠናክረን እንድንቀጥል ጥራያችንን በድጋሜ በቤተክርስቲያን ስም እናስተላልፋልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር