“ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ የውይይት ጥያቄዎች ተነሱ”

አዲስ አበባ | ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
ስ/ወ/ሐ/ተ/መ/ሚዲያ
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ እየተካሄደ
በሚገኘው በ፫ኛው ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን መርሐ ግብር ላይ፣የቅድስት ቤተክርስቲያን የወንጌል አገልግሎትን ወቅታዊ ኹኔታ የሚፈትሹና ለቤተክርስቲያን ቀጣይ ሐዋርያዊ ተልዕኮ መንገድ ጠራጊ የኾኑ አምስት መሠረታዊ ጥያቄዎች ለውይይት ቀረቡ።
ጥያቄዎቹ የቀረቡት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በኩል ሲኾኑ፣ በአኹኑ ሰዓትም ታዳሚው በጥያቄዎቹ ላይ በጥልቀት እየተወያየ ይገኛል።
በዋናነት ጥያቄዎቹ
፩,የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ዘመኑን ከመዋጀት አንጻር ምን ይመስላል?
፪.የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከተደራሽነት አንጻር አንዴት ይታያል? በተለይም
ጠረፉን አካባቢ በቋንቋ ጭምር ከመድረስ እና ከዓለምአቀፍ ነባራዊ ኹኔታ አንጻር ሲታይ ምን ይመስላል?
፫.የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በሠርክ ጉባኤያት ምን ያኽል ውጤታማ ነው?
፬.የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በሚዲያ ከመድረስ አንጻር እንዴት ይታያል? እና
፭.በቅድስት ቤተክርስቲያን በኹሉም የስራ ዘርፍ የምንገኝ ኹላችንም አገልጋዮች የሥነ-ምግባር ጉዳይ እንዴት ይታያል? የሚሉ ናቸው።
ጥያቄዎቹን ለታዳሚው ይፋ ያደረጉት የመመሪያው ኃላፊ ክቡር መላከ ሰላም ዳዊት ያሬድ ፥ በጥያቄዎቹ በሚነሱ የውይይት ነጥቦች ቤተክርስቲያን በአገልግሎቱ ያላትን ተደራሽነት እና ሌሎችም ተግዳሮቶች መንስዔ በማጤን ለቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫ ጠቋሚ ሃሳቦችን ታገኝበታለች ተብሎ እንደሚታሰብ ገልጸዋል።
አኹን ላይ መርሐ ግብሩ ቀጥሎ ከታዳሚው የተለያዩ ሐሳቦችና የመፍትሔ ጥቆማዎች እየቀረቡ ሲኾን፤ ከዚኽ የውይይት መድረክ ለቤተክርስቲያን ቀጣይ ሐዋርያዊ የወንጌል ተልዕኮ ጉዞ እጅግ ጠቃሚ የኾኑ ስልታዊ ነጥቦች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።