“ሰባኪው ተዋኝ ሳይኾን ፈዋሽ ሐኪም ሊኾን ይገባል” መ/ታ ኢንጂነር ባሕረጥበብ ሙጬ
አዲስ አበባ | ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
ስ/ወ/ሐ/ተ/መ/ሚዲያ
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ እየተከናወነ በሚገኘው ፫ኛው ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን መርሐ-ግብር አኹንም በልዩ ልዩ ክንውኖች እየተካሄደ የሚገኝ ሲኾን፤ ከክንዉኑ መካከልም በመ/ታ ኢንጂነር ባሕረጥበብ ሙጬ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል።
ጥናቱን “የስብከተ ወንጌል ተግዳሮቶ እና መፍትሔው” በሚል ርዕስ ያቀረቡ ሲኾን፤ በጥናት ዳሰሳቸውም ተልዕኮ አልባ ዕውቀት፤ ወንጌልን በአውደ ምሕረት ላይ ብቻ መወሰን፤ ትውልዱን ከመገንባት ይልቅ ለውበትና ለህንጻ ግንባታ ብቻ ትኩረት መሰጠቱ፤ እና ዘመኑን የዋጀ አግልግሎት አለመኖር በጥናታዊ ጽሑፉ የስብከተ ወንጌል ተግዳሮቶች መኾናቸውን ጠቅሰው፤ የሥርዓተ ትምህርት (Curriculum) ማሻሻያ ማድረግ እንደ መፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
መርጌታ ኢንጂነር ባሕረጥበብ ሙጬ በጥናታዊ ዳሰሳቸው ወቅት “ሰባኪ ፈዋሽ ሐኪም እንጂ ተዋኝ አርቲስት መኾን የለበትም ያሉ ሲኾን፤አክለውም፣ ቤተክርስቲያንን እንደ ኩባንያ፣ ሰባኪውን እንደ ማርኬቲንግ ባለሙያ እና ምእመናንን እንደ ደንበኛ የማየት አደገኛ አካኼድ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።
በአኹኑ ሰዓት ጥናቱን አስመልክቶ ከመድረክና ከታዳሚው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው በመወያየት ላይ የሚገኙ ሲኾን፤ በውይይቱም
ቤተክርስቲያን በስብከተ ወንጌል አገልግሎቷ ላይ ስትራቴጂያዊ ለውጥ ማድረግ እንዳለባት የሚያመላክቱ ኾነው ተገኝተዋል።
መርሐ-ግቡሩ አኹንም የቀጠለ ሲኾን በቀጣይም የሚኖሩትን ልዩ ልዩ ክንውኖች በመከታተል የምናቀርብ ይኾናል።
