❝ ልደታ ለማርያም ❞

ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፤ በማርያም ልደት ምክንያት ዛሬ ደስታ ኾነ! (ቅዱስ ያሬድ)
የንጽሕናችን መሠረት፤የመመኪያችን ዘውድ፤ ድንግል ማርያም ግንቦት ፩ ቀን ተወለደች፤ እግዚአብሔር ለአዳም የገባለትን የድኅነት ቃል ኪዳን ለማጽናት፣ ከሰማያት ሰማያት ዝቅ ብሎ የሚያድርባትን ንጽሕት ማደሪያውን በዚኽች ዕለት ከምድር አዘጋጀ።
የእመቤታችን ወላጆቿ ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፤ ይኹን እንጂ ለብዙ ዘመናት ልጅ በማጣት በሰዎች ዘንድ ይነቀፉና ይናቁ ነበር።
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፱ ላይ ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው አይተው ይህ ሰው ዕውር ኾኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ? ብለው መጠየቃቸውን ስናነብ፤ በዚያ ዘመን ዓይን ማጣት ይኽን ያኽል ካስባለ ልጅ ማጣት ደግሞ ምን ሊባል እንደሚችል መገመት አያዳግትም።
እነርሱ ግን እንደ እመ ሳሙኤል ሐና በፊቱ ዘወትር ማልቀስን አላቆሙም፤ እንዲኽ ያለ ነቀፌታ ሲደርስባቸው ከእግዚአብሔር ከእግሩ ስር ዝቅ ብለው በእንባ የሚናገሩ ልቦች እንዴት የታደሉና ያማሩ ናቸው።
በመጽሐፍ “…እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ።
(መዝ. ፴፱፥፱) ተብሎ ተጽፏልና የቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና ኀዘንና ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት መዓዛው እንደማይጠፋ ዕጣን አረገና ለዓለሙ ኹሉ ድኅነት የሚደረግባት ቡርክት ዘርን ሰጣቸወ።
“ሰጣቸው” ያልነው በሕገ ልደት ዘሥጋ እንጂ የተሰጠችውስ ለእኛ ለአዳም ልጆች ኹሉ ነው፤ ያማ ባይኾን እንዴት ያልወለደችውን ዮሐንስን”እናትህ እነኋት” (ዮሐ.፲፱፥፳፯) ይላል ጌታችን።
እመ አምላክ ድንግል ወላዲተ ቃል ከበዓሉ ረድኤት በረከት ታሳትፈን።

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሓዱ ኣምላክ ኣሜን!
ብፁዕ ኣቡነ ሳዊሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ ኣስኪያጅ፤
ብፁዕ ኣቡነ ዲዮስቆሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፤
ብፁዕ ኣቡነ ሕርያቆስ
የኣዲስ ኣበባ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዓን ኣበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት፣
በኣጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልኣተ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ፦
ማሕየዊት በምትሆን ሞቱ ሰማያውያንና ምድራውያንን ያስታረቀ፣ በቅድስት ትንሣኤውም የሙታንን ሕይወት በተስፋ ያለመለመ ጌታችን፣ ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እንኳን ለዓመታዊው የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልኣተ ጉባኤ ኣደረሰን ኣደረሳችሁ!
“እስመ ተዋለጠ እግዚአብሔር ዓለመ በክርስቶስ ኣናኅስዮ ኃጢኣቶሙ ወኢነጺሮ ጌጋዮሙ፤ ወረሰየ ላዕሌነ ቃለ ሥምረቱ፤ ወወሃበነ መልእክተ ሣህሉ፡- እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና በደላቸውን ኣይቈጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል ኣኖረ” (2ቆሮ. 5፥19)።
የእግዚአብሔርም ልጅ፣ የሰውም ልጅ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሰብእነት ሲገለጽ ግልጽ የሆነ ዓላማና ግብ እንደነበረው ቅዱስ መጽሓፍ ይነግረናል፤ እሱም በሰማይም፣ በምድርም ያሉትን በሙሉ ማስታረቅ፣ ማገናኘትና ኣንድ ማድረግ ነበረ፤
ጌታችን ይህንን ሲያደርግ ሰማያውያኑንና ምድራውያኑን የለያየው ምክንያት በማስወገድ ነው፤ የመለያየቱ ምክንያት ክፉ ኅሊና ኣምጦ የወለደው በደልና እሱን ተከትሎ የተከሠተው ኃጢኣት ነበረ፤ በኃጢኣት ምክንያት የገባው ሞት ደግሞ የቅጣቱ ማሳያ ፍርድ ነበረ።
የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በፈጸሙት ስሕተት መነሻነት ምድርንና ምድራውያንን ለከባድ ቅጣትና መርገም የዳረገው ይህ መለያየት ለሰማያውያኑም ተርፎኣል፤
ምክንያቱም መለያየቱ በእግዚአብሔርና በሰው፣ በመላእክትና በሰው፣ በሰውና በሰው፣ በነፍስና በሥጋ ጭምር የጥል ግድግዳን ገንብቶ እስከ ክርስቶስ ዕለተ ስቅለት መዝለቁን በቅዱስ መጽሓፍ የምናውቀው ስለሆነ ማለት ነው።
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት!
ቀዳማዊና ዘላለማዊ የሆነው ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብእናችንን ተዋሕዶ በዚህ ዓለም የተገለጸው ሰማያውያንንና ምድራውያንን የለያየው የጥል ግድግዳን ለማፈራረስ ነው፤
ለመለያየት ምክንያት የሆነችውን ኃጢኣት በሰውነቱ በመቅጣት የሕግን ትእዛዝ ከፈጸመ በኋላ የዕርቁን ተግባር በወሳኝ መልኩ ኣከናውኖታል፤
በክርስቶስ ቤዛነት የሆነው ይህ ዕርቅ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተወደደ ነበረና እሱ ራሱ በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ኣስታረቀ፤
ለዚህም ነው ተበዳይ እሱ፣ ቤዛዊ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው እሱ፣ ኣስታራቂ እሱ፣ ታራቂ እሱ ሆኖ የምናገኘው፤ ለሱ የሚሳነው ነገር የለምና ለኛ ግር የሚል ቢመስልም ለሱ ቀላል ነበረ።
በዚህ የዕርቅ ተግባር ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሰውና ሰው፣ ነፍስና ሥጋ ታርቀው በይፋ ተገናኙ፤ በኅብረትና በኣንድነትም መኖር ቻሉ፤ በቀኙ ለተሰቀለው ሽፍታ “ዛሬውኑ ከኔ ጋር በገነት ትኖራለህ” የሚለው ቃለ ምሕረትና “ኣባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ ኣደራ እሰጣለሁ” የሚለው ቃለ ኣማሕፅኖ የዕርቁ፣ የግንኙነቱና የኣንድነቱ ማሳያ ኣስረጅ ናቸው።
ስቅለተ ክርስቶስ ነፍሶቻችን ወደ ግዞት ቤት ሳይሆን ወደ ገነት እንዲገቡ፣ የሚቀበላቸውም ራሱ እግዚአብሔር እንዲሆን ያስቻለ ታላቅ መለኮታዊ ፍጻሜ ነው፤
እኛ “ክርስቶስ መድኃኒታችን ነው፤ ኣድኖናል” ብለን በልበ ሙሉነት የምንመሰክረው፣ እሱም “ሰላሜን ሰጠኋችሁ” ብሎ የሚያረጋጋን በመሰቀሉ ይህንን ውጤት ስላስገኘልን ነው።
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት!
የድኅነታችንና የሰላማችን መሠረት የሆኑትን የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ለዓለም ማኅበረ ሰብ የማብሰርና የማሥረጽ ተግባር የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቍጥር ኣንድ ተልእኮ ነው፤
ነገረ ሞቱና ነገረ ትንሣኤው በኣስተውሎት፣ በጥልቀትና በተመሥጦ ስናስተምር በውስጡ የምናገኘው የዕርቅ፣ የሰላምና የኣንድነት ምስጢር ነው፤
እንደ እውነቱ ከሆነ እኛ የክርስቶስ መልእክተኞች እንደ ቃሉ ራሳችንን ክደን በሚጠበቀው መጠን ተልእኮኣችንን መወጣት ብንችል ኖሮ፣ ኣሁን በዓለማችን የተፈጠረው መለያየትና ግጭት ኣይኖርም ነበር፤
ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባንችልም በእጅጉ መቀነስና ዓቅሙን ማዳከም እንችል ነበር፤ ነገር ግን ተልእኮኣችንን በኣግባቡ ኣለመወጣት ኣንድ ነገር ሆኖ የዓለሙ መሳሪያ ሆነን መገኘታችን “በዕንቅርት ላይ…” ሆኖ ይስተዋላል።
ይሁንና ኣሁንም ሕዝቡን ወደ ኣንድነት፣ ወደ ፍቅር፣ ወደ ሰላም፣ ወደ ዘላቂ የጋራ ጥቅምና ወደ ፈሪሐ እግዚአብሔር ማምጣት የጉባኤያችን ዓቢይ ተግባር ሊሆን ይገባል፤ እነዚህ ካሉ የምናጣውም ሆነ የሚያመልጠን የለምና ነው፤
ሃገርን በኃላፊነት ተረክባችሁ በላዕላዊ፣ በማእከላዊና በታሕታዊ መዋቅር የምትገኙ፣ እንደዚሁም ኣማራጭ ሓሳብ ኣለን ብላችሁ የምትንቀሳቀሱ ልኂቃነ ሃገር ፣ ሁላችሁም እግዚአብሔርን ከሚያውቅ፣ ከሚያመልክና ከሚፈራ ሕዝብ የተገኛችሁ ናችሁና በልባችሁ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ድምፁንም ስሙ፤ የሱ ገንዘብ በሆኑ ፍጡራንም ኣትጨክኑ፤ ሰውን መያዝ የሚቻለው ኅሊናን በመርታት እንጂ በሌላ ኣይደለምና፣
የሕዝቡን ፍላጎትና የልብ ትርታ በሚገባ ኣዳምጡ፤ ሕዝቡ የሚፈልገው በኣንድነትና በእኩልነት መኖር፣ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ፍትሕን ማስፈን፣ ለኑሮው የሚበቃ ምጣኔ ሃብትን ማግኘት፣ የእምነት ነጻነትና እኩልነት መረጋገጥ የመሳሰሉት ናቸው።
ሕዝቡ እነዚህ ከተሟሉለት ተደመጠ ማለት ነው፤ ከተደመጠ ደግሞ እሱም በበኩሉ ያደምጣል፤ ይከተላልም፤
ስለሆነም ለሁሉም ልጆቻችንና ወገኖቻችን የምናስተላልፈው ወቅታዊ ጥሪ ሁሉንም ችግሮቻችን በሰላምና በሰላም ብቻ ለመፍታት ተባበሩ የሚል ነው፤ ከዚህ ውጭ የሚደረገው ኣማራጭ ሁሉ ለዘላቂ ሰላማችን ኣይበጅም እንላለን።
በመጨረሻም፦
በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ከበዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ ኣምስተኛው ቀን የሚካሄደው ዓመታዊው የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልኣተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተጀመረ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑና ለመላው ኢትዮጵያውያን እናበስራለን!!!
እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሓት ለእግዚአብሔር፤
አሜን!!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘኣኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤
ሚያዝያ 28 ቀን 2018 ዓ.ም
ኣዲስ ኣበባ – ኢትዮጵያ

መድኃኔዓለም

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መድኃኔዓለም”ብላ ስትጠራው ” የዓለም ኹሉ መድኃኒት አንተ ነኽ” እያለች ነው።
ይኽም ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መላውን ዓለም ከዘላለም ሞት፣ ከሲኦል ባርነትና ከሰይጣን አገዛዝ ነፃ ያወጣበትን ታላቅ የማዳን ሥራ የሚገልጽ ስም በመኾኑ ነው።
​ለዚህም ስያሜ መነሻ የሆናት ቅዱሱ መጽሐፍ ሲሆን ይኸውም ክብር ይግባውና እርሱ ገና ​በጽንሰቱ፤ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለቅዱስ ዮሴፍ “ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” (ማቴ ፩፡፳፩) በማለት የመድኃኒትነት ስሙን ከነ ግብሩ አብስሯል።
በዚኽ ያላበቃው ቸርነቱ ​በልደቱም ቀጥሎ እርሱ በተወለደ ጊዜ መላእክት ለእረኞች “ለሕዝቡ ኹሉ የሚኾን ታላቅ ደስታ… መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል” (ሉቃ ፪፡፲) በማለት የዓለም መድኃኒትነቱን መስክረዋል።
ኋላም በመዋዕለ ሥጋዌ ​ትምህርቱ፤ ሳምራዊቷ ሴት ያደረገላትን ነገር ኹሉ ለሴቶቹ ከመሰከረችላቸው በኋላ “አኹን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ኾነ እናውቃለን ይሉአት ነበር።”
(ዮሐ. ፬፥፵፪)
መድኃኔዓለም አባታችን በቤታችን የጎደለውን በምሕረቱ ይሙላልን።
የጎበጠውን ኑሯችንን ያቅናልን።
በእልፍኛችን ተሸሸግን ያነባነውን እንባችንን ያብስልን።
አሜን

ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ

በዘመናት ጉዞ በማዕበል እየተመታች፣ ፈጽሞ ያልሰመጠች መርከብ ብትኖር እርሷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ናት። የዚኽ ኹሉ መሠረት ደግሞ ‟ አናቅጸ ሲኦል ኢይኄይልዋ፤ የገሃነም ደጆች አይችሏትም”(ማቴ.፲፮፥፲፱) በማለት ለቤተክርስቲያን በተነገረላት የአምላክ ቃል ኪዳን ነው።
“You will burn and you will burn out; you will be healed and come back again.” እንዳለ ደራሲው ‘ርግጥም ቤተክርስቲያን ሲያቆስሏት፦ ድና ሌላውን እየፈወሰች፣ ሲቀጥፏት፦ አብባ እልፍ እያፈራች፣ ሲረግሟት፦ መርቃ እየባረከች፤ ሲያነዷት ደምቃ እያበራች፤ከየዘመናቱ ርዕዮተ ዓለም ታግላ፥ ከኑፋቄ ተፋልጣ፤ለሐቅ ተጋድላ ከታሪክ ተጣምራ፤እዚኽ ደርሳለች።
የመድረሷ ምስጢርም ከአምላካዊ የኪዳኑ ጠብቆት ጋር፤ የቅዱሳን አባቶቻችን ነፍሳቸውን እንደ ኢምንት ነገር እንኳ ሳይቆጥሩ ለቤተክርስቲያን ባደረጉት ታላቅ ተጋድሎ ነው።
የእግዚአብሔርን ቃልየተናገሩአችኹን ዋኖቻችኹን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።”(ዕብ. ፲፫፥፯)ይላልና ቃለ እግዚአብሔር፤ በዚኽ አጠር መጠን ባለ ገጸ ንባብ ፤ በዜማ በኩል ከያሬድ በኋላ የተነሣ ❝ ዳግማዊ ያሬድ ❞ የተባለ እና በዘመኑ የነበሩ መናፍቃንን በመከራከርና በመርታቱ ❝ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ ❞ (ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እና ገድለ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል፤ ፳፻፬ ዓ.ም ገጽ 12) ።
በዚህ የሚጠራውና የተሰጠው ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሊቅና ጻድቅ አባት፣ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን ሕይወት እና ሥራዎች እንመለከታለን።
ልደቱ 
በ፲፭ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ የጥበብ ሰማይ ላይ እንደ ንጋት ኮከብ ደምቆ የበራ፣ የእውቀቱ ጥልቀት እንደ ውቅያኖስ የማይመረመር! የመንፈሱ ግርማ እንደ ደብረ ታቦር ብርሃን የሚያንጸባርቅ አንድ ታላቅ ሊቅ ተነሥቶ ነበር እርሱም አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ነው። (በመ/ር በኃይሉ በቀለ:2018 ዓ.ም ገጽ: 162)።
ይኽ ታላቅ አባት የተነሣበት ዘመን በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ወርቃማው ዘመን ተብሎ ከሚጠራበት ጊዜ አንዱ ነው። (ዲ/ን ሰሎሞን ዮሐንስ: 2001 ዓ.ም፡ ገጽ 145 -185)
ምክንያቱም በጨለማው ዘመን ወይም (ከ፯ኛው-፲፩ኛው መ/ክ/ዘ) ተገትቶ የነበረው የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ያንሰራራበት፤ የክርስትና እምነት በአዲስ መልኩየተጠናከረበት፤ከግብፅ ቤተክርስቲያን ጋር የነበረን ግንኙነት እንደገና እየታደሰ የኼደበት፤ የብህትውና እና የምንኩስና ሕይወትም እያደገ የመጣበት፤ በጣና ሐይቅ ዙሪያ ታላላቅ ገዳማት የተተከሉት ..ወዘተ ስለነበር።(ዝኒ ከማሁ፡ገጽ 145 -146)
አባ ጊዮርጊስ ገድል ስለተጻፈላቸው ማን እንደኾኑ ለማወቅ ይቻላል፤(ጌታቸው ኃይሌ 2012፡ገጽ 233).
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ከሕዝበ ጽዮን እና ከእምነ ጽዮን በ1357 ዓ.ም (ግድም ይላሉ ጌታቸው ኃይሌ) ተወለዱ። የአባ ጊዮርጊስ ወላጆች ልጅ ስላልነበራቸው ዘወትር እግዚአብሔርን በጸሎት ሲጠይቁ ኖረው የተሰጣቸው የጸሎት ፍሬ፡ የተማጽኖ ውጤት፣ የስለት ልጅ ነው።​(አሻግሬ አምጤ፣ 2017፣ ገጽ 94).
አባቱ በሸ/ሰግላ ውስጥ በነበረች ደብረ ማህው በተባለች አምላክን በወለደች በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በተሠራች ቤተክርስቲያን ውስጥ በነበረ የመላእክት አለቃ የቅዱስ ዑራኤል ሥዕል ፊት ተንበርክኮ በማልቀስ ያገኘው የስለት ልጅ መኾኑን…ድርሳነ ዑራኤል ዘሰኔ ያስነብበናል ።(ዝኒ ከማሁ: ገጽ 94)
ሸግላ/ሰግላ ማለት በአሁኑ ደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በቦረና አውራጃ በከለላ ወረዳ በወለቃና በበቶ ወንዝ መካከል በምትገኝ ልዩ ስሟ ሸግላ/ሰግላ/ ተብላ የምትጠራ ደብረ ማኅው የተሰኘች አካባቢ ነው፡፡(ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እና ገድለ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል፤ ፳፻፬ ዓ.ም ገጽ, 9)
እናቱ እመነ ጽዮን ልጇ እንደ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ የእውነት ምስክር እንዲኾንላት በመመኘት ጊዮርጊስ ብላ ስም አወጣችለት። ስሙ ብቻ ሳይኾን ግብሩም ጊዮርጊስን ይመስል ዘንድ ፈሪኻ እግዚአብሔርን እያስተማረች፡ በጥበብ እና በዕውቀት አሳደገች።
ጉዞ ወደ ትምህርት ዓለም
አባቱ ሕዝበ ጽዮን ልጁን መጻሕፍትን በማንበብና በመተርጎም ረገድ በጣም ጠቢባንና የተካኑ ወደተባሉ ካህናት መምህራን ወዳሉበትበጊዜው በኢትዮጵያ ታላቅ የትምህርት ማእከል በነበረችው ሐይቅ ደብረ ነጐድጓድ ገዳም ወደምትገኘው ትምህርት ቤት ይዘዋቸው በመሔድ ከታላቁ ሊቅ ዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ጋር እንዲማሩላቸው አድርሰዋቸው መጡ፡፡
ለትምህርት ሐይቅ የገባው በዐፄ ዳዊት /1365-1395 ዓ.ም/ ዘመነ መንግሥት አባ ሠረቀ ብርሃን ገዳሙን በሚያስተዳድርበት ዘመን ነበር። አባ ሠረቀ ብርሃን የተማረ ብቻ ሳይኾን ለቀናች ሃይማኖት ተቆርቋሪና ድጋፍ ነበር። በእርሱ ዘመን እዚያ መማር መታደል ነበር። ጊዮርጊስ በትምህርት ብቻ ሳይኾን በቀናች ሃይማኖትም ለመቀረጽ መልካም አጋጣሚ ኾኖለታል።(ሥርግው ሐብለሥላሴ (ዶ/ር) : 2018:ገጽ, 772)
እንደ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ጥናት ጽሑፍ አባቱ ሕዝበ ጽዮን በቤተ መንግሥት ከነበሩ የንጉሥ ካህናት አንዱ ስለነበር፣ ወጣቱ ጊዮርጊስ የመጀመሪያዎቹን የልጅነት ጊዜያቱን ያሳለፈው በቤተመንግሥት መኾኑን ሲነግረን፤
(Taddesse Tamrat, 1972, p. 437)
ዲ/ን አሻግሬ አምጤ ደግሞ፤ አባቱ ነገሥታት በየኼዱበት አብራ እየኼደች በድንኳን ትኖር በነበረችው ሥዕል ቤት ያገለግሉ ከነበሩ ካህናተ አንዱ እንደነበር ይነግረናል።(አሻግሬ አምጤ፣ 2017፣ ገጽ 95).
❝ ትምህርት ዓለም ፈተና ❞
አባ ጊዮርጊስ ከ1374 – 1407 ዓመተ ምሕረት የኢትዮጵያ ንጉሥ በነበረው በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ለተጨማሪ ትምህርት ከዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ዘንድ ሐይቅ እስጢፋኖስ ከገቡ በኋላ፣ ብዙ መጻሕፍት ከነበሩበት እና ታላላቅ ሊቃውንት ተምረው ከወጡበት ትምህርት አልገባኽ ብሏቸው ለሰባት ዓመታት ተቀመጡ። (ዝኒ ከማሁ:ገጽ 98)
በወቅቱ አብረዋቸው ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ተምረው እየተዋቸው፣ ከእርሳቸው በኋላ ትምህርት ቤት የገቡትም እያለፏቸው ይኼዱ ነበር። ትምህርት አልገባኽ ስላላቸው አብረው ይማሩ የነበሩት ተማሪዎች ብቻ ሳይኾን እኽል እየፈጩ፣ ውኃ እየቀዱ እና እንጨት እየለቀሙ ያገለግሏቸው የነበሩ የገዳሙ መነኰሳት ጭምር ይሳለቁባቸው ነበር።
በዚኹ ምክንያት በሐይቅ እስጢፋኖስ ወንበር ዘርግቶ ያስተምር የነበረው ዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ለአባቱ ” ልጅህ ትምህርት ስለማይገባው የቤተ መንግሥት ሥርዓት አስተምረው” በማለት ወደ ቤት ሲመልለሷቸው የጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ወላጅ አባት ሕዝበ ጽዮን ግን “ አንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር ስለሰጠሁት” እዚያው እየኖረ ገዳሙን ያገልግል በማለት መልሶ ወደ ገዳሙ ላከው።(ዝኒ ከማሁ:ገጽ 98)
❝ ታሪክ ሲቀየር ❞
ከየአቅጣጫው የደረሰባቸው መገፋት ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን ወደ ገዳሙ ተመልስው ከሥዕለ ማርያም ሥር እየተደፉ መማጸን የዘወትር ተግባራቸው ኾነ፡፡እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም የቅዱሱን ከሥዕሏ ሥር እየተደፉ ማልቀስ በከንቱ አላስቀረችም።
ከዕለታት አንድ ቀን ከመልአኩ ከቅዱስ ዑራኤል ጋር ተገልጣ “ልጄ ጊዮርጊስ ኾይ አይዞኽ፣ ዕውቀት የተሰወረብኽ ትምህርት የማይገባኽ ኾነኽ ሳይኾን የእግዚአብሔር ድንቅ ተአምር በአንተ ይገለጥ ዘንድ ነው።” ብላ በተናገረች ከሰባት ቀን በኋላ፤
በግዕዙ እንደሚለው ❝ ወአመ ሰትየ ውእቱ ጽዋዐ አእምሮ እምእደ እግዝእትነ እመ ብርሃን ❞ /ከብርሃን እናት እመቤታችን እጅ የዕውቀት ጽዋን በጠጣ ጊዜ/
“…ወእምይእቲ ሰዓት ተከሥተ አዕይንተ ልቡ ወተመሰጠ ኅሊናሁ በአክናፈ መንፈስ ቅዱስ፡፡
ወበጽሐ ኀበ ኅሊናሁ ለአብ ወበህየ ረከበ ኢየሱስሃ እንዘ ይነብር በየማነ አቡሁ ወጰራቅሊጦስሃ ኅቡረ በህላዌሁ…” (ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እና ገድለ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል፤ ፳፻፬ ዓ.ም ገጽ 42)
ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ የልቡ ዓይን በራለት፡፡ ተከፈተለት ኅሊናወም በመንፈስ ቅዱስ ክንፎች ተመሰጠ፡፡ ወደ አብም ደረሰ፤ በዚያም ኢየሱስን በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ጰራቅሊጦስንም በአንድ አኗኗር አገኘው፡፡
ከዚያችም ቀን ጀምሮ አባታችን ጊዮርጊስ የመጻሕፍትን ንባባቸውንና ትርጓሜያቸውን አስተዋለ፡፡(ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 43)
እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ጽሑፍ አባ ጊዮርጊስ የኋላ ኋላ ትምህርት የቀናላቸው ስለ ኹለት ነገር ነው።
አንደኛው ምክንያት ከላይ እንደጠቀስነው ከእመቤታችን ሲኾን ኹለተኛው ምክንያት ደግሞ “እስመ እንበለ መከራ
ኢይትወሀብ ጸጋ ወእንበለ ተፈትኖ ኢይከውን አፈድፍዶ” (ያለ መከራ ጸጋ አይሰጥም፤ ያለ መፈተን የተገኘውን ማብዛት አይቻልም) ይለዋል።(ጌታቸው ኃይሌ:2012፡ገጽ 233).
ክፍል ፫ ይቀጥላል

“የአበው ሥርዓት ለቤተ ክርስቲያን አንድነት” በሚል ርዕስ ለሁለት ቀናት ሲከናወን የነበረው ሥልጠና እና ምክክር ባለ 8 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ!!

በመንበረ ፓትርያርክ ገዳማት መምሪያ አዘጋጅነት የአበው ሥርዓት ለቤተ ክርስቲያን አንድነት በሚል መሪ ቃል ከገዳማውያኑ ጋር ሲደረግ የነበረው ምክክርና ውይይት ተጠናቋል።
የአቋም መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል።
፩. መንፈሳዊ ተጋድሎን ስለማጽናት፦
ጌታችን ወደ ገዳም ፈቀቅ ብሎ እንደጸለየ እኛም አርአያነቱን በመከተል፣ ገዳማቶቻችን የጾምና የጸሎት ማዕከልነታቸው ጸንቶ እንዲኖር፣ ስለ ዓለም ሰላምና ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ያለማቋረጥ ለመጋደል ቃል እንገባለን።
፪. የአብነት ትምህርትንና ሊቃውንትን ስለማፍራት፦
ገዳማት የጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን የዕውቀት መፍለቂያ እንደመሆናቸው መጠን፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በማጠናከርና መምህራንን በመደገፍ፣ ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተተኪ ሊቃውንትንና መምህራንን ለማፍራት ቃል እንገባለን።
፫. ትውልድን በሥነ ምግባር ስለመቅረጽ፦
በዘመኑ የዓለማዊነት ተግዳሮት ውስጥ ለወደቀው ትውልድ ገዳማቶቻችን የመንፈሳዊነትና የሥነ ምግባር ተምሳሌት እንዲሆኑ በማድረግ፣ በፍቅረ ቤተ ክርስቲያን የታነጸ ዜጋን ለመቅረጽ ቃል እንገባለን።
፬. በልማት ሥራ ራስን ስለመቻል፦
በገዳማቶቻችን ያለውን ሰፊ መሬትና የተፈጥሮ ጸጋ በመጠቀም፣ በግብርናና በልዩ ልዩ የልማት ዘርፎች ተሰማርተን፣ ገዳማችንን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት አላቀን ለሌሎችም ተርፈን ለመገኘት ቃል እንገባለን።
፭. የገዳማውያንን ፍልሰት ስለመግታት፦
አስፈላጊውን የኑሮና የሥራ ሁኔታ በገዳማት ውስጥ በማመቻቸት፣ ገዳማውያን በአካላዊና በመንፈሳዊ ምክንያት ወደ ከተማ የሚያደርጉትን ፍልሰት በማቆም በገዳማቸው እንዲጸኑ ለማድረግ ቃል እንገባለን።
፮. የሥነ ጥበብና የታሪክ ቅርሶችን ስለመጠበቅ፦
አባቶቻችን በደምና በአጥንታቸው ጠብቀው ያቆዩልንን የብራና መጻሕፍት፣ የጥበብ ሥራዎችና የኪነ ሕንጻ ቅርሶች እንዳይጠፉና እንዳይዘረፉ በንቃት ለመጠበቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ ቃል እንገባለን።
፯. ተቋማዊ አንድነትንና ታዛዥነትን ስለማጽናት፦
ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ጋር በመተባበርና በጋራ በመመካከር፣ የገዳማትን አንድነትና ተቋማዊ አሠራር ለማጠናከርና ለበላይ አካል መመሪያዎች ተገዢ ለመሆን ቃል እንገባለን።
፰. የምጽዋትና የርኅራኄ ማዕከል ስለመሆን፦
ጌታችን የተራቡትን እንዳበላ ሁሉ፣ እኛም በልማታችን በረከት የታመሙትን ለመጠየቅ፣ የተራቡትን ለመመገብና ለተቸገሩት ሁሉ የርኅራኄ መጠጊያ ሆነን ለመገኘት ቃል እንገባለን።
ሚያዝያ 23 ቀን 2018 ዓ.ም
መንበረ ፓትርያርክ
አዲስ አበባ ፦ኢትዮጵያ