ጾመ ሐዋርያት
በቤተክርስቲያናችን ከ፯ቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ” ጾመ ሐዋርያት ” ወይም በተለምዶ አጠራሩ ” የሰኔ ጾም ” ሲኾን፤ የስያሜው መነሻም ቅዱሳን ሐዋርያት በበዓለ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስን ከአርያም ከተቀበሉ በኋላ የጾሙት ጾም በመኾኑ “ጾመ ሐዋርያት ” ተብሏል።
ስያሜውን በተመለከተ አስቀድሞ በመጀመሪያ ‹የጰንጤቆስጤ ጾም›› ይባል እንደነበርና፤በኋላ ግን ” ጾመ ሐዋርያት ” የሚለውን ስያሜ ያገኘው ከኒቅያ ጉባዔ በኋላ መኾኑን የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ።
በመጀመሪያዎቹ ዘመናት የሐዋርያት ጾም የሚጀምረው ከጰራቅሊጦስ አንድ ሳምንት በኋላ እንደነበር አንዳንድ መዛግብት ይናገራሉ። ከዚያም በ258ዓ.ም ከበዓለ ጰራቅሊጦስ እስከ ሐዋርያት በዓል (The Feast of the Holy Apostles) (ሐምሌ 5) ድረስ እንዲኾን አባቶች ደነገጉ በማለት ያስረዳሉ፡፡
ይኽም የተረደገው የቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ በኔሮን ቄሳር በሮም አደባባይ ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ዕለት አብሮ ለማሰብ እንዲረዳ ነው በማለት ያጠናክሩታል።
በእርግጥ ” አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም፤ ወከዐዉ ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር ወተዐገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት”/ ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ፡፡/ እንዳለ ቅዱስ አባ ኤፍሬም፤
ስለ ያዙት እውነት በገዥዎች እና አስጨናቂዎች ሥጋቸው በእሳት ቢቃጠል፤ ለአራዊት ቢጣል እንኳ ስለ ስሙ የተገባ አድርገው ይቆጥሩና ይደሰቱ የነበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት ” አይጾሙም ” ብሎ በአስረጅ ሊሞግት የሚችል አይኖርም። ቢኖር እንኳ በአስተምህሮ እና በታሪክ አስረጅነት ይረታል።
በማቴ 9፥15-16 ላይ “እኛ እና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ የምንጦመው ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለምንድን ነው?” ብለው በጠየቁት ጊዜ “ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወስድበት ወራት ይመጣል በዚያን ጊዜም ይጦማሉ )” በማለት ጌታችን እንዲጾሙ ያዘዛቸው መኾኑን እንረዳለን፡፡
በኋላም ትምህርቱን አብነት በማድረግ ቅዱሳን ሐዋርያት የወንጌልን አገልግሎት ሲጀምሩ፤ ዲያቆናትና ቀሳውስት ሲሾሙ በጾምና በጸሎት ነበር (የሐዋ 13፥3፤4፥25)፡፡
በታሪክም ከኼድን እንደ St. Athanasius the Great, In his letter to Emperor Constance (ቅዱስአትናቴዎስ ለንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በጻፈው መልእክት) St. Ambrose of Milan, St. Leo the Great and Theodoret of Cyrrhus የመሳሰሉ ታላላቅ የጥንት የቤተክርስቲያን አባቶች ድርሳናት ላይ ተሰድሮ ተገኝቷል።
ከዚህ በተጨማሪ በ፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተጻፈው መጽሐፈ ድዲስቅሊያ፣ በ፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተጻፈው መጽሐፈ ቀለሜንጦስ፣ እንዲኹ ተዘግቦ ይገኛል፡፡
❝ ዛሬ ለምን እንጾማለን ❞
ቅድስት ቤተክርስቲያን በነቢያት እና ሐዋርያት መሠረት (አስተምህሮ) ላይ የጸናች እንደመኾኗ ለእነርሱ የተነገረው ቃለ እግዚአብሔር ዛሬም ላለነው ለቤተክርስቲያን ምእመናን ኹሉ የሚሰራ ነው።ይኽም “ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያን ጊዜም ይጾማሉ” (ማቴ 9፥15) ብሏልና ቤተክርስቲያን ይኽንን ቃል በተግባር ትተረጉማለች።
ሌላኛው ምክንያት ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ የወንጌልን ብርሃን ለዓለም ለማብራት ከመውጣታቸው በፊት በጾምና በጸሎት እንደ ተዘጋጁ ኹሉ፤ ዛሬም ቤተክርስቲያን የእነርሱን ፈለግ በመከተል የአገልግሎትና የበረከት ጉዞዋን በጾም ትጀምራለች።
በተጨማሪም ከትንሣኤ እስከ በዓለ ሃምሳ ስንደሰት፣ ስንበላና ስንጠጣ ቆይተናል። ይኹን እንጂ ሥጋችን ከደስታው ብዛት ሰነፍ እንዳይኾንና የተሰጠንን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በፈተና እንዳናጣው፣ ሥጋን በትሕትና ለመግራትና እግዚአብሔርን ለማመስገን ይጾማል።
ስለዚኽ ጾመ ሐዋርያትን ዛሬ የምንጾመው እንዲኹ በልማድ የመጣ ሳይኾን፣ ነፍሳችንን ከሥጋዊ ምኞት የምናነጻበት፣ ከሐዋርያት በረከት የምንሳተፍበት እና በበዓለ ሃምሳ ያገኘነውን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በቅድስና የምንጠብቅበት ታላቅ የመንፈሳዊ ተጋድሎ ጾም መኾኑን አውቀን እንድንጾም ቤተክርስቲያን አደራ ትለናለች።
ጾሙን የበረከት ያድርግልን።

