በዓለ ጰራቅሊጦስ
በቤተክርስቲያናችን ትልቅ ስፍራ ከሚሰጣቸው ዓበይት በዓላት አንዱ በዓለ ጰራቅሊጦስ ነው። ይኽ በዓል ከጌታችን ትንሣኤ በዓል በኋላ በ፶\50ኛው ቀን፣ ከበዓለ ዕርገት ደግሞ በ፲ኛው ቀን ይከበራል።
“ጰራቅሊጦስ” የሚለው ቃል (Parákletos / Παράκλητος) ከሚለው የግሪክ ቃል በቀጥታ የተወሰደ ሲኾን፤
ትርጉሙም መንጽሒ (የሚያነጻ)፣ ናዛዚ (የሚያጽናና፣ የሚያረጋጋ)፤ ከሣቲ (ምስጢር ገላጭ)፣ መስተሥርዪ (ይቅር ባይ) እና መስተፍሥሒ (ደስታን የሚሰጥ) ማለት ነው።ይኽም በአንድነት ሦስትነት ከከበሩ ከሥላሴ አካላት አንዱን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን የሚገልጥ ነው።
ጰራቅሊጦስ በብሉይ ኪዳን ፤ ካህናተ ኦሪት ዓሥራቱን፤ በኩራቱን፣ቀዳምያቱን ይቀበሉበት ነበርና ይኽ በዓል በዘመነ ኦሪት በዓለ ሠዊት ይባል ነበር፡፡ማለትም እስራኤል ዘሥጋ በዓለ ፋሲካን ካከበሩ በኋላ ሰባት ሣምንታትን ቆጥረው በ፶ኛው ቀን በዓለ ሠዊት (የእሸት በዓል) ያከብሩ ነበር (ዘሌ.፳፫፥፲፭ -፳፪፣ዘኁ.፳፰፥፳፮)፡፡ይኽ የብሉይ ዘመን ታሪክ ሊመጣ ላለው ለክርስቶስ ቤዛነት ምሣሌ ነበር፡፡
የቤተክርስቲያን ሊቃውንት በትርጓሜ ምስጢር በበዓለ ጰራቅሊጦስ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለውበታልና ከዘመነ ሐዋርያት ወዲኽ በበዓለ ሠዊት በዓለ ጰራቅሊጦስ ገብቶበታል ሲሉ ያስተምራሉ።
(ማሕቶተ ዘመን: ፪፻፲፩ ዓ.ም: ገጽ 195).
ከአይሁድ ፍርኻት ሙሉ በሙሉ መላቀቅ ያልቻሉት ደቀመዛሙርቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነርሱ ተለይቶ እንደሚያርግ ሲነግራቸው አዘኑ፤ ተከዙ፤ ሰብሳቢ፣ ጠባቂ እንደሌላቸው የሙት ልጆች የሚኾኑ መስሏቸው ነበርና “የሙት ልጆች ትኾኑ ዘንድ አልተዋችኹም” አላቸው። (ዮሐ.፲፬፥፲፰).
ስለ ስሙ መከራን ለመቀበል እንዲጸኑ መንጽኢ (የሚያጸና)ያስፈልጋቸው ነበርና “እኔ የአባቴን ተስፋ ለእናንተ እልካለኹ፤ እናንተ ግን ከአርያም ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀመጡ፡፡” ሉቃስ ፳፬፥፵፱) በማለት ተስፋ ሰጣቸው፡፡
እንደተናገረውም ጌታችን ካረገ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ አርድእትና ቅዱሳት አንስት ከእመቤታችን ጋር በአንድነት ለጸሎት ለምስጋና ተሰብስበው እያለ መጽሐፍ እንደሚል፦ “በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ኹሉም በአንድ ልብ ኾነው አብረው ሳሉ፥ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ኹሉ ሞላው።
እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በእያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በኹሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።
ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ኹሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤ይኽም ድምፅ በኾነ ጊዜ ሕዝብ ኹሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ።ተገርመውም ተደንቀውም እንዲኽ አሉ፡— እነኾ፥ እነዚኽ የሚናገሩት ኹሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? “(ሐዋ. ፪፥ ፩-፯)
ታላቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ግብረ ሐዋርያትን በተረጎመበት በ፬ኛው ድርሳኑ “…በብሉይ ኪዳን በበዓለ ሠዊት መከር እንደሚሰበሰብበት ኹሉ፣ በአዲስ ኪዳን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ እንደ ስለታም ማጨጃ ወርዶ የሰዎችን ነፍስ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሰበሰበበት እውነተኛው የመከር ቀን ነው።
“. . . ” እንደ እሳት” የተባለበት ምስጢር
በጌታችን ጥምቀት ወቅት ” በእርግብ አምሳል ” ወረደ እንጂ እርሱ ” እርግብ ” እንዳልኾነ ኹሉ እዚኽም ” በአምሳል” እንጂ እርሱ ግዙፍ እሳት አለመኾኑን ለማጠየቅ ነው።ኾኖም “እሳቱ” የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ሲያሳይ፣ በእያንዳንዳቸው ላይ “መቀመጡ” ደግሞ ጸጋው በሐዋርያት ላይ ጸንቶ መኖሩን ያመለክታል።”
(St.John Chrysostom, Homily 4 on the Acts of the Apostles)
ዛሬም በነቢያትና በሐዋርያት መሰረትነት የቆመች ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በዓለ ጰራቅሊጦስን በሐዋርያት ዘመን እንደነበረው ኹሉ ከጌታችን ትንሣኤ በኋላ በ፶ኛው ቀን ታከብራለች፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በዓለ ጰራቅሊጦስን “የቤተክርስቲያን የልደት ቀን” ሲል ይጠራዋል፡፡ ምክንያቱም ቤተክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተመልታ ለሰው ልጆች ኹሉ እውነተኛ የክርስቶስን ወንጌል መስበክ የጀመረችበት ቀን ነውና፡፡
በዚኹ ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ሦስት ሺህ ያኽል ሰዎች በስመ ሥላሴ አምነው ተጠምቀዋል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን
