❝ደብረ ምጥማቅ ❞
በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ግንቦት ፳፩ ቀን ልዩና እጅግ የከበረች ዕለት ናት።
ይኽም ግብጽ በምትገኘው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም በተሠራችው ደብረ ምጥማቅ ቤተክርስቲያን ጉልላት ላይ ድንግል ማርያም ከግንቦት ፳፩ ጀምሮ እስከ ፳፭ ቀናት በተከታታይ በመገለጧ ምክንያት በዓሉ በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት ይከበራል፡፡
ደብረ ምጥማቅ (Deir Al-Maghtas) እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከልጇ ከወዳጇ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከቅዱስ ዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር በስደት ዘመኗ የረገጠቻትና ያረፈችባት ቅዱስ ስፍራ ነው።
ጌታችንም ቦታውን ባርኮ የእናቱ ክብር መገለጫ እንዲኾን ቃል ኪዳን ገብቶላት ስለነበር፣ ጊዜው ሲደርስ ቦታው የቅዱሳን መነኮሳት በዓት ኾነ።
ግንቦት ፳፩ ቀን የሚዘከረው፣ ከስደት ዘመን በኋላ በዚያ ቦታ ላይ በታነጸው ቤተክርስቲያን ውስጥ የተደረገውን ታላቅ ተአምር መነሻ በማድረግ ነው። በወቅቱ የነበሩ አረማውያን ሳይቀሩ በየዓመቱ ከግንቦት ፳፩ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት እመቤታችን በብርሃን ተከባ፣ በደመና ኾና በቤተክርስቲያኑ ጉልላት ተገልጣ በግልጽ ያዩ ነበር።
በእነዚያ አምስት የእመቤታችን መገለጥ ቀናት ደብረ ምጥማቅ የምድር ስፍራ መኾኑ ቀርቶ ሰማያዊ መቅደስ ትመስል ነበር።
ታላቁ አባት አባ ጽጌ ድንግል በደብረ ምጥማቅ በታላቅ ክብር ለምእመናን የታየችው የአምላክ እናት የድንግል ማርያምን መገለጥ በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ እንዲኽ በማለት ገልጾታል፤
አመ ትበርቂ በደብረ ምጥማቅ ኀምሰ ዕለታተ፣ ትእምርተ ገጽኪ ይርአይ እስከ ይትነሣእ ዘሞተ፣ሚ መጠነ ማርያም ታሥተፌሥሒ ትፍሥሕተ፣ ኅድጊሰ ጽጌ ፍቅርኪ በጊዜ ንቃሁ መዓልተ፣ ብፁዕ ዘርእየኪ በሕልሙ ሌሊተ፤ የፊትሽን መልክ ያይ ዘንድ የሞተ ሰው እስኪነሣ ድረስ በደብረ ምጥማቅ ለአምስት ቀናት ያህል በተገለጽሽ ጊዜ ማርያም ምን ያህል ደስ ታሰኚ ኖሯል! በቀን የታየው የፍቅርሽ አበባ ይቅርና ሌሊት በሕልሙ ያየሽ ምስጉን ነው” ይላል።
ይኽንን ተአምር ለመመልከት ክርስቲያኑና አረማዊው ኹሉ በአንድነት ተሰብስቦ ነበር። ኹሉም ሰው የታላቅ ደስታና በረከት ተካፋይ በመሆኑ፣ በዚያ ቅጽበት ከምድር ወጥተው በተለየ ሰማያዊ ዓለም ውስጥ ያሉ ይመስላቸው ነበር።
የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃና ጸሎት ከኹላችን ጋር ይኹን!ከደብረ ምጥማቅ በረከት ረድኤት ያሳትፈን አሜን!
