መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል
“እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ።”
(ሉቃስ ፩፥፲፱)
መልክዐ ቅዱስ ገብርኤል ላይ “ሰላም ለዝክረ ስምከ ዘኢይተረጐም ምሥጢር ባሕቱ ይመስል ብሂለ እግዚእ ወገብር፤ ገብርኤል ኾይ ተመራምሮ ለማይደረስበት ስም አጠራርኽ ሰላም እላለኹ፤ ነገር ግን አምላክ ሰው ኾነ፤ ሰው አምላክ ኾነ ማለት ይመስላል›› እንዲል፤ የስሙ ትርጓሜ “እግዚእ ወገብር፤ አምላክ ሰው ኾነ ሰው አምላክ ኾነ” ማለት ነው።
ሳጥናኤል ሥላሴን በካደ ጊዜ፤ መላእክትን በቃሉ ያጸናቸው ቅዱስ ገብርኤል ነው። የጌታችንን ልደት ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በማብሰር የነቢያት ትንቢት መፈጸሙን ያረጋገጠ እርሱ ነው። ወደ ካህኑ ዘካርያስ ተልኮ የቅዱስ ዮሐንስን ልደት ያበሰረ፤ነቢዩ ዳንኤልን ከአናብስት አፍ ያዳነው እርሱ ቅዱስ ገብርኤል ነው።
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር “በመንገድህ ኹሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል።”
መዝሙር ፺፩፥፲፩ ብሎ እንደተናገረ ፈጣሪ እኛን ከክፉ ነገር ኹሉ ለመጠበቅ መላእክቱን በዙሪያችን ያቆማል።
በሕይወታችን ውስጥ የሚገጥሙንን ልዩ ልዩ ማዕበሎች፣ የፈተናና የጭንቀት እሳቶችን በድል እንድንሻገር፣ ከውስጥ ስብራት እንድንፈወስና ወደ አዲስ የብስራት ምዕራፍ እንድንሻገር ይራዱናል።
የሊቀ መላዕክት የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነትና ጥበቃ አይለየን! የልባችንን ሐዘን ወደ ደስታ፣ ጭንቀታችንን ወደ እረፍት የሚለውጥ የምሥራች የሰላም አምላክ ለኹላችንም ያሰማን!
