ባሕረ ጥበባት ቅዱስ ያሬድ
በቤተክርስቲያናችን ግንቦት ፲፩ ቀን በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት ኢትዮጵያዊው ሊቁ ባሕረ ጥበባት ቅዱስ ያሬድ ይከብራል።
ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን መዓርዒረ ዜማ፤ ማኅሌታይ፤ ርእሰ ሊቃውንት፤ ዓርከ ሊቃውንት፤ ልዑለ ስብከት፤የዜማ አባት፤የኢትዮጵያ ብርሃን፤ የቤተክርስቲያን እንዚራ፤ ወዘተ ብለው ቢጠሩትም ይኽ ኹሉ ስያሜ ቅዱስ ያሬድን ባይገልጥላቸው “አልቦ እምቅድሜኹ ወአልቦ እምኅድሬኹ ለያሬድ ካህን በመኃልይኹ ማኅሌተ ትንሣኤ ዘይደምፅ ጉርዔኹ” ብለው ዘጉ።
በእርግጥም ከምድር ተነጥቆ ከሰማያውያን መላእክት የቅኔ እና የዜማ ጓዳ ምስጢር ቀድቶ ብሉይን ከሐዲስ አሰናኝቶ ያሰማንን፤ ያስተማረንን ታላቅ ሊቅ አባት በቃላት መግለጽ እንደምን ይቻላል!
ቅዱስ ያሬድ ትውልዱ አክሱም ኾኖ፥ የኖረው በንጉሥ ገብረ መስቀል ዘመን ነው። የአክሱም ጽዮን አለቃና መምህር አባ ጌዴዎን ዘመዱ ነበረ። የአባ ጌዴዎን ተማሪ ኾኖ ዳዊት ለመድገም ብዙ ቢሞክር አልኾንልኽ አለው።
በዚኽ ጊዜ አንድ ልጅ ትምህርት አልገባኽ ሲለው አስተማሪዎች የሚያደርጉትን ኹሉ መምህሩ አደረገለት- “ወዘበጦ፡ ብዙኃ” (ለምን አይገባህም ብሎ ብዙ ደበደበው)። ግርፋቱ ስለጎዳው መታገሥ ተስኖት ከወላጆቹ ቤት ወጥቶ ጠፋ። ከአንድ ዛፍ ስር ከፀሓይ ተጠልሎ ቁጭ አለ።
ከዚያ ቍጭ እንዳለ አንድ ትል ከዛፉ ላይ ሊወጣ ሲሞክር በተደጋጋሚ ግማሽ መንገድ እየሄደ ሲወድቅ ቆይቶ ከብዙ ሙከራ በኋላ በ፯ኛው ከጫፍ ደርሶ ሊበላት የፈለጋትን ቅጠል ሲበላ አየና፥ “እንዴት ግርፋትን አትታገሥም፡ ሕመምንስ ለምን አትሸከምም? ትዕግሥት ብታበዛ እኮ እግዚአብሔር (ትምርቱን) ይገልጽልኽ ነበረ” ሲል ራሱን ገሠጸው።(ጌታቸው ኃይሌ:፳፻፲፪ ዓ.ም ገጽ 94).
ይኸንን ብሎ (በጸጸት) አለቀሰና ወደ መምህሩ ወደ አባ ጌዴዎን ተመልሶ፥ “አባት ሆይ፥ ይቅር በለኝና እንደበፊቱ አስተምረኝ” አለው። መምህሩም እንዳልክ ብሎ ተቀበለው። እግዚአብሔር ልቡን አብርቶለት ያንኑ ዕለት ዳዊት ደገመ፤ ከመዝሙረ ዳዊት ጋር አብረው የሚቀዱትንም መኃልየ መኃልይንና ውዳሴ ማርያምን፥የ፹፩ዱን መጻሕፍት ትርጕም፥ ሌሎችንም ተምሮ ጨረሰ። (ዝኒ ከማሁ 95)
ከዚኽ በኋላ ፫ ፀጋዎች ተገለጡለት። ለቅዱስ ያሬድ የተገለጠለት ጸጋ ለአንድ ሰው ይኽ ኹሉ ይሰጠዋልን በማለት የሚያስደምሙ ናቸው። ተዘግቶ(ትምህርት ሳይገባው)በመኖሩ እስከ መገረፍ አድርሶት የነበረው አእምሮው ሲከፈት በመጀመሪያ ትርጓሜ መጻሕፍት ተገለጠለት፡ በመቀጠልም ወንበር ዘርግቶ በማስተማር ላይ ሳለ ” አሮዲዮን” በተባሉ አእዋፍ አማካኝነት ሰማይዊውን ዓለም ጎብኝቶ ሰማያዊ ዜማ ተገለጠለት፣ ሊቃውንት እንደሚመሰክሩት ከዜማው ጎን ለጎን ቅኔ ተገለጠለት።(ፍኖተ ሊቃውንት:፳፻፩፮ ዓ.ም ገጽ 59)
የማሕሌት እና የዝማሬ አፍላግ የኾነው ቅዱስ ያሬድ ገብቶበት ከቆየው ሰማያዊ ዓለም ወደ መሬት ሲወርድ፣ ❝ ሃሌ ሉያ ለአብ፡ ሃሌ ሉያ ለወልድ፡ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ፡ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሣረረ ወበዳግመ አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ በደብተራ፡-ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድም ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ገባል፤ ከጽዮን አስቀድሞ ሰማይን ፈጠረ፤ ዳግመኛም ለሙሴ ድንኳኑን እንዴት መሥራት እንደሚገባው አሳየው” በማለት የዘመረው በሰማይ የተመለከተውን ምሥጢር አምላኩ በልቡናው ሰሌዳ ስለሳለለት ነው። (ዝኒ ከማሁ)
ቅዱስ ያሬድ በአኵሱም ዐደባባይ አዲሱን ዜማ ያሰማበት ስፍራ “ሙራደ ቃል” ተብሎ ይጠራል። በመጀመሪያ የደረሳትን ዜማ ሰማያዊ መኾኗን ለማመልከት “አርያም” ብሏታል።
የቅዱስ ያሬድን የሕይወቱን ፍጻሜ በተመለከተም ኹለት ዓይነት አተያይ አለ።ቅዱስ ያሬድ አርፏል የሚሉ እና ተሰውሯል የሚሉ ናቸው።እንደ ብዙዎች ሊቃውንት ሊቁ ፈጣሪውን ሲያገለግል ኖሮ ግንቦት ፲፩ ቀን ዐርፎ መቀበሩን፣ እና አጽሙ ያረፈበትን ቦታ እግዚአብሔር ከፈቀደላቸው ከአንዳንድ ከበቁ ባሕታውን በቀር ለኹሉ የማይገለጥ መኾኑን፣ ለበቁ ባሕታውያን ግን አጽሙ በረድኤተ እግዚአብሔር እየተገለጠላቸው ብዙ መንፈሳዊ ተግባር እንደሚፈጽሙበት የሚናገሩ ናቸው።
ሰላም እብል ለያሬድ ቀሲስ ምሉዐ መንፈስ፤
ለኢትዮጵያ ነደቀ በሃሌ ሉያ ምድራስ
አስተካልሐ ደቂቃ በዜማ ሠላስ።
የባሕር ጥበባት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በረከት ረድኤት በኹላችን ይደርብን።
