❞ ጻድቃን ❞
መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት ጽድቃንን ለምን በሊባኖስ ዝግባና በዘንባባ ዛፍ መስሎ የተናገረ ይመስላችኋል?
” ጻድቅሰ ከመ በቀልት ይፈሪ፤ ወይበዝኅ ከመ ዘግባ ዘሊባኖስ፤ ትኵላን እሙንቱ ውስተ ቤተ እግዚአብሔር” /ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፥ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል፤ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል፥ በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ።
(መዝ. ፺፪፣፲፪)
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እንዲኽ ብሎ የመዘመሩ ምስጢር ታላቅ ነው። የዘንባባ ዛፍ በባሕሪው በበጋም ኾነ በክረምት ቅጠሉ አይረግፍም፣ አይጠወልግም፤ ዘወትር አረንጓዴ ነው።
ጻድቃንም በደስታም ኾነ በመከራ ጊዜ ከፈጣሪያቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት አይቋረጥም፣ ተስፋቸውም አይጠወልግም።
የዘንባባ ዛፍ ሌላኛው ባሕሪ፤ አሸዋማና የዝናብ እጥረት ባለበት በረሃ ውስጥ መኖር መቻሉ ነው።ሥሩ በጣም ጥልቅ ስለኾነ ከመሬት በታች ያለውን የውኃ ምንጭ አግኝቶ ይኖራል።
ጻድቃንም በዚህ ዓለም “የፈተና በረሃ” ውስጥ ቢኖሩም፣ ሥሮቻቸው (እምነታቸው) ከእግዚአብሔር የሕይወት ውኃ ጋር ስለተያያዙ አይደርቁም።
አብዛኞቹ ዛፎች ከታች ወደ ጎን በቅርንጫፍ ይሰፋሉ፤ ዘንባባ ግን እድገቱና ቅጠሉ በሙሉ ወደ ላይ ነው። ይኽም የጻድቃን ልባቸውና ሃሳባቸው ኹሉ ዘወትር ወደ ሰማያዊው ዓለም መኾኑን ያመለክታል።
የሊባኖስ ዝግባ ባሕርይ ደግሞ፤ በቀላሉ የማይበሰብስና ደስ የሚል መዓዛ ያለው ነው። የጻድቃንም የቅድስና መዓዛቸው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነው።
የዝግባ ዛፍ ሳይበሰብስ ብዙ ዓመታትን ይኖራል።“ የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል።” መዝ. 112፥6 እንደ ተባለ ጻድቃንም በዚኽ ዓለም በሥጋ ቢለዩ እንኳ መታሰቢያቸውና ሥራቸው ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
እንኳን ለጻድቁ አባታችን አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ወርኃዊ መታሰቢያ በዓል አደረሰን።
