“የአበው ሥርዓት ለቤተ ክርስቲያን አንድነት” በሚል ርዕስ ለሁለት ቀናት ሲከናወን የነበረው ሥልጠና እና ምክክር ባለ 8 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ!!
በመንበረ ፓትርያርክ ገዳማት መምሪያ አዘጋጅነት የአበው ሥርዓት ለቤተ ክርስቲያን አንድነት በሚል መሪ ቃል ከገዳማውያኑ ጋር ሲደረግ የነበረው ምክክርና ውይይት ተጠናቋል።
የአቋም መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል።
፩. መንፈሳዊ ተጋድሎን ስለማጽናት፦
ጌታችን ወደ ገዳም ፈቀቅ ብሎ እንደጸለየ እኛም አርአያነቱን በመከተል፣ ገዳማቶቻችን የጾምና የጸሎት ማዕከልነታቸው ጸንቶ እንዲኖር፣ ስለ ዓለም ሰላምና ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ያለማቋረጥ ለመጋደል ቃል እንገባለን።
፪. የአብነት ትምህርትንና ሊቃውንትን ስለማፍራት፦
ገዳማት የጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን የዕውቀት መፍለቂያ እንደመሆናቸው መጠን፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በማጠናከርና መምህራንን በመደገፍ፣ ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተተኪ ሊቃውንትንና መምህራንን ለማፍራት ቃል እንገባለን።
፫. ትውልድን በሥነ ምግባር ስለመቅረጽ፦
በዘመኑ የዓለማዊነት ተግዳሮት ውስጥ ለወደቀው ትውልድ ገዳማቶቻችን የመንፈሳዊነትና የሥነ ምግባር ተምሳሌት እንዲሆኑ በማድረግ፣ በፍቅረ ቤተ ክርስቲያን የታነጸ ዜጋን ለመቅረጽ ቃል እንገባለን።
፬. በልማት ሥራ ራስን ስለመቻል፦
በገዳማቶቻችን ያለውን ሰፊ መሬትና የተፈጥሮ ጸጋ በመጠቀም፣ በግብርናና በልዩ ልዩ የልማት ዘርፎች ተሰማርተን፣ ገዳማችንን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት አላቀን ለሌሎችም ተርፈን ለመገኘት ቃል እንገባለን።
፭. የገዳማውያንን ፍልሰት ስለመግታት፦
አስፈላጊውን የኑሮና የሥራ ሁኔታ በገዳማት ውስጥ በማመቻቸት፣ ገዳማውያን በአካላዊና በመንፈሳዊ ምክንያት ወደ ከተማ የሚያደርጉትን ፍልሰት በማቆም በገዳማቸው እንዲጸኑ ለማድረግ ቃል እንገባለን።
፮. የሥነ ጥበብና የታሪክ ቅርሶችን ስለመጠበቅ፦
አባቶቻችን በደምና በአጥንታቸው ጠብቀው ያቆዩልንን የብራና መጻሕፍት፣ የጥበብ ሥራዎችና የኪነ ሕንጻ ቅርሶች እንዳይጠፉና እንዳይዘረፉ በንቃት ለመጠበቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ ቃል እንገባለን።
፯. ተቋማዊ አንድነትንና ታዛዥነትን ስለማጽናት፦
ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ጋር በመተባበርና በጋራ በመመካከር፣ የገዳማትን አንድነትና ተቋማዊ አሠራር ለማጠናከርና ለበላይ አካል መመሪያዎች ተገዢ ለመሆን ቃል እንገባለን።
፰. የምጽዋትና የርኅራኄ ማዕከል ስለመሆን፦
ጌታችን የተራቡትን እንዳበላ ሁሉ፣ እኛም በልማታችን በረከት የታመሙትን ለመጠየቅ፣ የተራቡትን ለመመገብና ለተቸገሩት ሁሉ የርኅራኄ መጠጊያ ሆነን ለመገኘት ቃል እንገባለን።
ሚያዝያ 23 ቀን 2018 ዓ.ም
መንበረ ፓትርያርክ
አዲስ አበባ ፦ኢትዮጵያ
