ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ በ፵ ዓመት ጉዞው
መግቢያ
ሀገራችን ኢትዮጵያ በሕገ ልቡና፤ በሕገ ኦሪት እና በሕገ ወንጌል ከአምልኮተ እግዚአብሔር ሳትለይ የኖረች ሀገረ እግዚአብሔር መኾንዋን ብዙ ሊቃውንት ተናግረዋል፤ ጽፈዋልም። በተለይም፤ ኹለቱ ኪዳናት ወደ ሀገራችን መግባታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈ እውነት ነው፡፡ ጥንቱንም በሕገ ልቡና እግዚአብሔርን ታመልክ የነበረች ሀገራችን፤ ወዳና ፈቅዳ የስሎሞንን ጥበብ ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም በሔ ደችው ንግሥቷ አማካይነት ሃይማኖተ ኦሪትንና ሥርዓተ ኦሪትን የተቀበለች መኾኗ በመጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ምዕራፍ ፲˖ ፩-፲፫ተጠቅሷል፡፡በዚኽም የኢየሩሳሌም ጉዞ ንግሥተ ሳባ ከስሎሞን ቀዳማዊ ምኒልክን ፀንሳ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ወለደች፤ ልጁም አድጎ የአባቱን ሀገር ኢየሩሳሌምን ጎብኝቶ ሲመለስ የሙሴን ጽላት እና ካህናተ ኦሪትን፣ እንዲሁም አያሌ የብሉይ መጻሕፍትን ከሊቆቻቸው ጋራ ይዞ መጣ:: ይህ ፈቃደ እግዚአብሔር የነበረበት አጋጣሚ፣ ሥርዓተ ኦሪት ወደ ሀገራችን እንዲገባ ምክንያት ኾኗል፡፡
ነቢዩ ዳዊት “ኢትዮጵያውያን በፊቱ ይሰግዳሉ፤ ጠላቶቹም ዐመድ ይቅማሉ፤ የጠረሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታ ያመጣሉ፤ የሳባና የዐረብ ነገሥታትም እጅ መንሻ ያቀርባሉ፤ ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል፤” ብሎ (መዝ. ፸፩፥ ፱-፲) በተናገረው ትንቢት መሠረት፣ ሄሮድስ በነገሠበት ዘመን ይሁዳ ክፍል በምትኾን በቤተልሔም፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ፣ ወርቅ ዕጣን ከርቤ ከገበሩለት ሦስት ነገሥታት አንዱ፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ ባዜን እንደ ነበረ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ፣ የግመሎች ብዛት፣ የምድያም እና የጌፌር ግመሎች ይሸፍኑሻል፤ ኹሉ ከሳባ ይመጣሉ፤ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ፤” (ኢሳ.፰፥፮) ብሎ የተናገረውን ትንቢት መሠረት በማድረግ፣ ኹሉም ከሳባ ይመጣሉ ብሏልና፣ “ሰብአ ሰገል ሁሉምም ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ብለውም የሚሞግቱ ሊቃውንት አሉ፡፡ በዚኽም መሠረት ኢትዮጵያ ክርስቶስን ያወቀችውና መባ በማቅረብ ልደቱን ያከበረችው ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቀዳማዊት ቤተ ክርስቲያን መሆኗ አጠያያቂ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ እስከ ቤተልሔም ድረስ ተጉዛ ልደቱን በማክበር ሳትወሰን በ34 ዓ.ም ሐዋርያ ሳይጓደልባት እና ደም ሳይፈስባት በራሷ ሐዋርያ ተሰብካ ትጠብቀው የበረውን የክርስቶስን መምጣት እና ዓለምን ማዳን አምና ሃይማኖተ ወጌልንና ሥርዓተ ወንጌልን የተቀበለች ሀገር ናት፡፡ “የጌታም መልአክ ፊልጶስን ተነሥተኽ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደ ሚያወርድው ምድረ በዳ ወደ ኾነው መንገድ ሒድ አለው፤ ተነሥቶም ሔደ፤ እነኾም ሕንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥ እና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ኹሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ መጥቶ ነበር፤ ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያ መጽሐፍ ያነብ ነበር፡፡ መንፈስም ፊልጶስን፣ ወደዚኽ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው፤ ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና፣ በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለኽን? አለው፡፡ እርሱም የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው፤ ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፣ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል? ፊልጰስም መልሶ፣ እባክህ፥ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል ስለ ሌላ? አለው፡፡ ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት፡፡ በመንገድም ሲሔዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፣ እነኾ በውኃ፤እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምምንድር ነው አለው፤ ፊልጶስም፣ በፍጹም ልብኽ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው፤መልሶም ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ኾነ አምናለሁ አለ፤ ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስ እና ጃንደረባው ኹለቱዎ ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም:: ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፤ ደስ ብሎት መንገዱን ይሔድ ነበርና፤ ”(የሐዋ. 8፡26-39) በማለት አገራችን ኢትዮጵያ ሐዋርያ ሳይላክላት በራሷ ሐዋርያ ክርስትናን የተቀበለች የመጀመሪያዋ ሀገር መኾንዋን መጽሐፍ ቅዱስ ይመሠክራል፡፡ ምንም እንኳን ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ሀገራችን መጥቶ ማስተማሩን፣ ኢትዮጵያም መንበረ ማቴዎስ መኾኗን የሚጠቁሙ፣ ባልታወቀ ምክንያት ብዙም ጎልቶ የማይነገር ታሪክ ቢኖርም፣ ኢትዮጵያ በራሷ ሐዋርያ መሰበኳ ግን ጥርጥር የሌለው ሐቅ ነው፡፡ ከላይ በሐዋርያት ሥራ የተጠቀሰው ታሪክ፣ ኢትዮጵያውያን እንደ ኦሪት ሥርዓት በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ይሔዱ የነበረ መኾኑን ኢትዮጵያ ውስጥ ከንግሥተ ሳባ ጊዜ ጀምሮ ወደ አገራችን የገቡ መጻሕፍተ ነቢያት እንደነበሩ፣ ኢትዮጵያውያን በመጻሕፍተ ብሉያት ጠቋሚነት የኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚኽ ዓለም መምጣት በተስፋ ይጠብቁ እንደነበር፤ ለኢትዮጵያ መምህር የላከላት መንፈስ ቅዱስ መኾኑን፣ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በራሳቸው በኢትዮጵያውያን መሆኑን፣ ክርስትና ከምድረ እስራኤል ውጭ መጀመሪያ የተሰበከው ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ መሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡
ቅዱስ ሄሬኔዎስ ጳጳስ ዘሊዮ “ጃንደረባው ለወገኖቹ ሐዋርያ ሆነ፡፡” በማለት ይህንኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ መነሻ ያደረገ ታሪክ ጽፏል፡፡ እንደዚሁም አውሳብዮስ ዘቂሣርያ “ከቤተ እስራኤል ውጭ የአካላዊ ቃልን ምሥጢር በመቀበልና በመጠመቅ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ነው፤ በዓለም የወንጌል ፍሬ በመሆንና ወደ አገሩም ተመልሶ በማስተማር በዓለም ላይ የመጀመሪያው ነው፡፡ በዚህም “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ተብሎ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን አገኘ፤ በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ከላይ እንደ ተገለጸው ቋሚ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ እንዳለ ሆኖ ከሐዋርያት መካከል ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ማስተማሩን ሩፊኖስ፣ ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ መምጣቱን ደግሞ ጄሮም፣ እነደዚሁ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ኢትዮጵያንም ጭምር ማተማሩን ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ መስክረዋል፡፡
ስብከተ ወንጌልን ለማፋጠን የተገኙ እድሎች
መንበረ ጵጵስና ማግኘቷ
በኢትጵያዊው ጃንደረባ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ አስቀድሞ የገባ የክርስትና ሃይማኖት ወደ መንበረ ጵጵስና ከፍ ያለው በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፍሬምናጦስ የጵጵስና ሢመት አማካኝነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደ ተጻፈው በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲያስመጣላት ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማን ወደ እስክንድርያ ላከች፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ የእስክንድርያ ፓትርያርክም ራሱኑ ሾሞ ላከው፤ ከኢትዮጵያ ተልኮ ሔዶ ከእስክንድርያው ፓትርያርክ ከቅዱስ አትናቴዎስ ዘንድ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሾሞ በመጣው በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መምህርነት በአብርሃና በአጽብሐ ዘመነ መንግሥት ክርስትና የግዛቱ ይፋዊ ሃማኖት ሆነ፡፡ አባ ሰላማም መንበረ ጵጵስናውን አክሱም ላይ አድርጎ በሀገራችን እየተዘዋወረ የወንጌልን ብርሃን በሰፊው ስለገለጠ በኢትዮጵያ «አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን» በመባል በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀች ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ለመሆን መብቃቷን ታሪክ ያስረዳል፡፡
የቅዱስ ያሬድ መነሣት
በ፭፻፶፭/555 ዓ.ም በአክሱም ከተማ የተወለደው ቅዱስ ያሬድ የቤተ ክርስቲያናች የዜማ አባት ብቻ ሳይኾን፣ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት የነበረው አስተዋፅኦ እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ዜማዊ ይሁኑ እንጂ በውስጣቸው ያለው ትምህርትና ምሥጢር እጅግ ከፍተኛ ነው፤ ዜማው ለጆሮ ምሥጢሩ ለአእምሮ የሚስማማ አድርጎ ስላዘጋጀው ከመደበኛው ስብከተ ወንጌል ባልተናነሰ ለብዙ ዘመናት ምእመናን ሲመከሩበትና ሲመሰጡበት ተምረውበትና ተጠብቀውበት ኖረዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ዜማን ከማበርከቱም በተጨማሪ በዘመኑ ከነበረው ንጉሥ ከአጼ ገብረ መስቀል ጋር በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተዘዋውሮ በማስተማር ዜማውን እንደ አንድ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ተጠቅሞበታል፡፡
ዘጠኙ ቅዱሳን
ዘጠኙ ቅዱሳን በኬልቄዶን ጉባኤ ምክንያት በተዋሕዶዎች ላይ በአውሮፓ በእስና በመከላከለኛው ምሥራቅ በተነሣው ፈተናና መገፋት ምክንያት ከሮም፣ ከእስያ፣ ከአንጾኪያ፣ ከቁስጥንጥንያ፣ ከቂሳርያና ከኪልቂያ በስደት የመጡ ናቸው፤ ለቤተ ርስቲያን ባበረከቱት ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ በቤተ ክርስቲያናችን የቅድስና ማዕረግተሰጥቷቸው ዘጠኙ ቅዱሳን በመባል የሚታወቁት እነዚህ ቅዱሳን ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን ወንጌልን ዞረው የሚያስተምሩ መምህራንን የሚያፈሩ ገዳማትን በመመስረት ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለውለታ ናቸው። በተለይም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በማጽናት የተለያዩ መጽሐፍትን በመተርጎም ስብከተ ወንጌልን አስፋፍተዋል፡፡ በርካታ ገዳማትን መስርተዋል፤ ሥርዓተ ምንኩስናን አደራጅተዋል፡፡ ይህም በሀገራችን ክርስትናው እንዲሰፋና እንዲጸና የነበረው አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡
የጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት መነሣት
ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት በኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፣ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ በመመለስ “ሐዲስ ሐዋርያ” የተባሉ በተለይም በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ለነበረው የስብከተ ወንጌል መስፋፋት የመሪነቱን ድርሻ የተወጡ ታላቅ ሐዋርያና ጻድቅ ናቸው፡፡ ጻድቁ ሕይወታቸውን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው፣ በብሕትውና ከመኖራቸውም በተጨማ እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ፣ ሐዋርያ ናቸው፡፡ በተለይም የአባቶቻቸውን ፈለግ የተከተሉ፣ 12ቱ የጻድቁ ደቀ መዛሙርት በ12ቱ ሐዋርያት አምሳል ከፍተኛ የሐዋርያዊ ተልእኮን ተግባር ፈጽመዋል፡፡
መንበረ ፕትርክናን ማግኘት
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከመንበረ ጵጵስና ወደ መንበረ ፕትርክና በመሸጋገር ይልቁንም የራሷን ኢትዮጵያውያን ጳጳሳትን መሾም ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ “ሑሩ ውስተ ኵሉ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኵሉ ፍጥረት /ወደ ዓለም ኹሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ኹሉ ስበኩ” ተብሎ በታዘዘው አምላካዊ ትእዛዝ መሠረት የእግዚአብሔርን ወንጌለ መንግሥተ ሰማያት ለአማንያንና ለኢአማንያን በማዳረስና የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትዕዛዝ በመፈጸም ከተመሰረተችት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በስብከተ ወንጌል ዙሪያ ከፍተኛ ሥራ ሠርታለች፡፡ ለስብከተ ወንጌል የተለየ ትኩረት በመስጠት ክርስቲያናችንን ሐዋርያዊ ተልእኮን ሊያፋጥኑ የሚችሉ አንዳንድ ተግባራት እንደ ተሞከሩ ይታወቃል። ቤተ ክርስቲያናችን ከግብጻውያን አገዛዝ ተላቃ የራሷን ፓትርያርክ ካገኘችበት ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ዘመን የቤተ ክህነት የዕለት ተዕለት አጀንዳ ስብከተ ወንጌል እንደ ነበር ይነገራል፡፡ በተለይም በ1952 ዓ.ም የተመሠረተውና በቤተ ክርስቲያናችን ተግባር ከፍተኛ ውጤት ያመጣል ተብሎ ግምት ተሰጥቶት የነበረው “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ምክር ቤትን” መቋቋሙ ትልቅ እርምጃ ነበር፡፡ ምክር ቤቱ በንጉሠ ነገሥቱ የበላይ ጠባቂነት፣ በብዑፅ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፓትርያርክ ሊቀ መንበርነት፣ በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የጉባኤ መሪነት፤ 14 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቋሚ አባልነት፣ ከምእመናንና ከካህናት በተመረጡ የጉባኤ አባላት የተዋቀረ ሆኖ መዋቅሩን እስከ መንበረ ጵጵስና በመዘርጋ ወንጌልን በጥራትና በስፋት ይሰጥ እንደ ነበር መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ እንደ መልአከ ታቦር ተሾመ ዘርይሁን አገላለጽ በዚያ ወቅት በተለይም የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ደቀ መዛሙርትም አብዛኛዎቹ በአብነት ትምህርቱ የበሰሉ ስለነበሩ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ምቹ ሁኔታን ፈጥሮ ነበር፡፡ የዚያን ጊዜው መመሪያ ‹‹እየተማሩ ማስተማር፣ እያስተማሩ መማር›› ሲኾን ይኽንን መመሪያ መሠረት በማድረግ ለስብከተ ወንጌል ተግባር ብቻ በተዘጋጀች ድምፅ ማጉያ ባላት መኪና በየበዓላቱና በየዕረፍት ጊዜው በዐራቱም ማዕዘን ከገጠር እስከ ከተማ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ ከፍተኛ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሰጥ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት የስብከተ ወንጌልና የሰንበት ትምህርት ቤት አስተምህሮ ሐዋርያዊ ጉዞዎች ዋና አድራሻዎች ነበሩ፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ የሐዋሪያዊ ጉዞ መኪናዋና ድምፅ ሲሰማ በመደሰት ወደ የቤተ ክርስቲያኑ የስብከት መድረክ ዙሪያ ስለሚሰበሰብ ወንጌልን ቃል ለተሰበሰበው ሕዝብ በማሰማት ከፍተኛ ሐዋርያዊ ተግባር ይፈጸም ነበር፡፡ በወቅቱ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የነበረው ተነሳሽነት እጅግ ከፍተኛ ስለነበረ የስብከተ ወንጌል ማኅበር ተቋቁሞ ነበር፡፡ የማኅበሩ ሊቀ መንበርም የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ሠራዊት አዛዥ የነበሩት ጀኔራል ታደሰ ብሩ ስለነበሩ ሰባክያነ ወንጌል ለስበከተ ወንጌል በኢትዮጵያ ምድር ሲዞሩ ችግር ቢደርስባቸው በየአካባቢው የፖሊስ ሠራዊት አባላት ትብብር እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ተላልፎ ነበር፡፡ ይህም የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት በነጻነት በሁሉም አቅጫ ዞረው እንዲየያስተምሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ ነበር፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ለስብከተ ወንጌል የነበራቸ ቦታ ከፍተኛ ስለነበር በአንድ ወቅት ስብሰባ በማድረግ ለደቀ መዛሙርት መመሪ ሲሰጡ “እናንተን ከየአቅጣጫው አሰባስበን በዚኽ ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርት እንድትማሩ ያደረግነው፤ ዓለሙ በአሁኑ ጊዜ በዘመናዊ ትምህርት እየመጠቀ በመሔድ ላይ ስለኾነ፤ እናንተም ካላችሁ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር ዓለሙ የሚያውቀውን ዐውቃችሁ ካላስተማራችሁ በቋንቋም፣ በንግግርም ልዩነት ትምህርታችሁን ላይቀበለው ስለሚችል ነው” በማለት ከዘመኑ እድገት ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል የወንጌል ሠራዊት በብቃት ለማዘጋጀት አስበውና ትኩረት ስጥተው ይሠሩ እንደ ነበር የሚያመላክት ንግግር ተናግረዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስም በእንደራሴነትና በፓትርያርክነት ቤተ ክርስቲያናችንን ባገለገሉበት ዘመን ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን ችግር አስቀድሞ በመረዳት በዘመኑ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ ከማድረግም ባለፈ ስብከተ ወንጌልና የቤተ ክስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይቋረጥ ሰበካ ጉባኤን በማቋቋምና ለወንጌል አገልግሎቱ ድጋፍ ሰጪ የሁኑ ገቢ የሚያስገኙ ሕንጻዎችን በማሳነጽ ለቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ ከደርግ ዘመነ መንግሥት በፊት ትምህርተ ወንጌል በሬድዮና በልዩ ልዩ የሕትመት ውጤቶች ጭምር እንዲሰጥ በማድረግ ስብከተ ወንጌል በስፋትና በተለያዩ አማራጮች ለመስጠት ይደረግ የነበረው ሙከራ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ሆኖም በደርግ ዘመነ መንግሥት የነበረው የሥርዓቱና የርእዮተ ዓለሙ ጫና እንዳለ ሆኖ ከሥርዓት ለውጡ በኋላ ቢሆን አስቀድሞ የነበረውን ስብከተ ወንጌልን የማስፋፋት ጥረትና ትኩርት በሚፈለገው ልክ ማስቀጠልና ማስፋፋት ተችሏል ማለት አያስደፍርም፡፡
የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ በዘመነ ደርግ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለፕትርክና የተመረጡበት ዘመን በሥርዓት ለውጥ ምክንያት ቤተ ክርስቲያናችን በፈተና ውስጥ የነበረችበትና ፓትርያርኳንም በግፍ ያጣችበት ወቅት የነበረ ቢሆንም በዚያ በፈተና ወቅት በዘርና በገንዘብ የማይታሙ የፖለቲካም ወገንተኝነት የሌላቸው ፍጹም መናኝ የነበሩት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለፓትርያርክነት መመረጥ በፈቃደ እግዚአብሔር የሆነ እንደ ነበር ምንም አጠያያቂ ይደለም፡፡ በደርግ ዘመነ መንግሥት የነበረው ርእዮተ ዓለም ለቤተ ክርስቲያን የተመቸ ባይሆንም ያንን የመከራ ዘመን ቤተ ክርስተያን በጥበብ እንድትሻገር በማድረግ ረገድ ቅዱስነታቸው የነበራቸው ሚና ቀላል አልነበረም፡፡ በወቅቱ የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሓፊ የነበሩት መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን ዝክረ ነገር በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደ መሰከሩት በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም፣ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በምስካየ ኀዙናን መድኃኔ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት ላይ ውርስ ለማድረግ የታሰበና የተደረገ ሙከራ የነበረ ቢሆንም እኚህ ታላቅ አባት እኖር ባይነት፤ እከብር ባይ ልቡና፣ የዓለም ግርማ የሀብት ፍትወት በእርሳቸው ዘንድ ቦታ አልነበረውምና “እኔ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዳደር እንጂ የሕዝበ ክርስቲያኑን የአምልኮ መፈጸሚያ ቤተ እግዚያብሔር ንብረት ወደ ሌላ ባለቤትነት ለማስተላለፍ ሥልጣን የለኝም የሚል ምላሽ በመስጠት የታስበው እንዳይፈጸም ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ ሥርዓቱን የሚተች ንግግርም ሆነ ስብከት ከእስራት እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት ሊያስከፍል እንደ ሚችል የታወቀ ቢሆንም ቅዱስነታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ያመኑበት እኩይ ተግባርን ከማውገዝ ወደ ኋላ የማይሉ አባትም ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት “በአንድ ቤተ ክርስቲያን ክብረ በዓል ላይ ሲያስተምሩ በሌላው አገር አንድ ዛፍ መቁረጥ ሰውን የመግደል ያህል ወንጀል እንደ ሆነ ሰምቻለሁ በእኛ አገር ግን ዛፍ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ እየተገደለ በየመንገዱ ይጣላል” በማለት ሲናገሩ ሕዝብ ዕንባ በዕንባ እንደ ኾነ መስማታቸውንም ጭምር መሥክረዋል፡፡ በአስቸጋሪ ዘመንና ሁኔታ ውስጥም ሆነው አስፈላጊነቱን ባመኑበት ቦታና ጊዜ “መምህር ወመገሥጽ ዘኢያደሉ ለገጽ” በመሆን ወንጌልን ይሰብኩ እንደ ነበር ይህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
በአርሲ የተደረገው የወንጌል አርበኝነት ተግባር
በደርግ ዘመነ መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች ወንጌል እንዳይሰበክ የደርግ ካድሬዎች የተለያዩ ጫናዎች ያደርሱ የነበረ ቢሆንም በዚያው ልክ ብዙ አባቶች ያንን እየተቋቋሙ በአርበኝነት ወንጌልን ይሰብኩ እንደነበር የታወቀ ሀቅ ነው፡፡ አንዱ ማሳያም በአርሲ የተደረገው የወንጌል አርበኝነት ተግባር መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን እንደሚከተለው ተርከውታል፡፡ በወቅቱ በአርሲ ይነገር የነበረው የካድሬዎች መፈክር አርሲን ሌኒን ግራንድ እናደርጋለን የሚል ስለ ነበር የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ እና በቦታቸው የተተኩት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በሀገረ ስብከቱ የከፈሉት መሥዋዕትነትና ያሳዩት የሥራ ውጤት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ለስብሰባና ቡራኬ ተግባር በሀገረ ስብከቱ ሥር ወደ ሚገኙ ወረዳዎች ሲሄዱ በስብሰባው ቦታ ተገኝተው እንዳያስተምሩና ጠንከር ያለ መልእክት እንዳያስተላልፉ በየኬላው የቆሙ ዘቦች የይለፍ ፈቃድ ካልያዙ አይሄዱም ብለው አግተው ያውሏቸው ነበር። ሆኖም እርሳቸውም ሆነ ሕዝቡ የሚበገሩ ስላልነበሩ ጊዜው አልፎ ዘግይተው ቢደርሱም ለስብሰባው ተጨማሪ ጊዜ በመስጠትና የሚፈለገውንም ተልእኮ በታስበው መሠረት በመፈጸም የተንኮሉን ዓላማ ውጤት አልባ ያደርጉት ነበር። በአንድ ወቅት በዚሁ ሀገረ ስብከት በአሰላ ከተማ ላይ ሕዝቡ በጥምቀት በዓል ማግስት የሚውለውን የቃና ዘገሊላን በዓል ለማክበር እንዳይወጣ የከተማው የደርግ ካድሬ በአሰላ ከተማ የጽዳት ዘመቻ በማወጅ ሕዝቡ ሁሉ ለዚያ የጽዳት ዘመቻ እንዲወጣ በመደረጉ የቃና ዘገሊላ በዓል ዕለት የታቦት ማደሪያ ቦታ ሰው አልባ ይሆናል፡፡ በዚህ በዓል ላይ ለአስተማሪነት ተጋብዘው በቦታው ላይ የተገኙት የያኔው ሊቀ ኅሩያን መርሐ ጽድቅ የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከቤተ ክህነት በተላከውና የድምጽ ማጉያ ማይክራፎን ባለው መኪና ላይ ሆነው ወደ ከተማው ሕዝብ ጆሮ በማነጣጠር “ወይቤሎ እግዚአብሔር ለፈርዖን ፈንዎሙኣ ለሕዝብየ ይግበሩ በዓልየ /እግዚአብሔር ፈርዖንን አለው ሕዝቤን ልቀቅ በዓሌን ያከብር ዘንድ” (ዘፀ.5÷1) የሚለውን ቃል በማስተጋባት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ለፖለቲካው ክፍል አስቸኳይ ጥሪ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ሲያደርጉ ሕዝቡም የያዘውን የጽዳት መሣሪያ እያስቀመጠ ልብሱን እየለወጠ ወደ ታቦት ማደሪያው በመሄዱ በዓሉ በተለመደው መሠረት ሊከበር ችሏል። ይህም በወቅቱ የነበረው የወንጌል እንቅፋት ብቻ ሳይሆን ለስብከተ ወንጌል በጥብአት የተሰለፉ አባቶችም እንደነበሩ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በአጠቃላይ በዘመነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ትልቅ የዕለት ተዕለት አጀንዳ የስብከተ ወንጌልና የሰንበት ትምህርት፣ የሰበካ ጉባኤ ጉዳይ ስለ ነበር፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደርና መምሪያዎች የዕለት ተዕለት ተግባርም በየከተማውና በየገጠሩ፣ በየአህጉረ ስብከቱ፣ በየወረዳውና በየአጥቢያው ለዚኽ ተግባር ጥንካሬና ዕድገት በሙሉ ኃይል መንቀሳቀስ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ለስብከተ ወንጌል መምሪያ ብቻ ለአገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማስፈጸሚያ የተመደቡ ዐራት መኪናዎች ነበሩት፡፡ ከእነዚኽም አንዱ የቤቱ ሲኾን ኹለቱ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጥያቄ ከውጭ አብያተ ክርስቲያናት በእርዳታ የተገኙ፤ አንዱ ደግሞ ከአገር ውስጥ በጎ አድራጊ ድርጅት የተሰጠ ነበር፡፡ ስለኾነም የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንቅስቃሴ በዚያው መጠን የሰፋ ነበር፡፡ ይህም በጣም ውስን ሀብት በነበረበት በዚያ ወቅት ለስብከተ ወንጌል የተሰጠው ትኩረት ምን ያህል ከፍተኛ እንደነበር ያሳያል፡፡ ያ ትኩረት በዚያው መጠን ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የተሻለ ሀብት ባለበትና የበለጠ መሥራት በሚቻልበት በዚህ ዘመን ምን ያህል ለውጥ ማምጣት በተቻለ፣ ስንቱ ከመንጋው የኮበለለው ምእመን በቤቱ እንዲጸና ማድረግ በተቻለ ነበር፡፡
የስብከት እንቅስቃሴ ከደርግ ዘመነ መንግሥት በኋላ
ከደርግ ዘመነ መንግሥት በኋላ ለሁሉም ቤተ እምነቶች ሃማኖታቸው በነጻነት የማስፈፋት ዕድል ሁሉም በእኩልነት ያገኙ ቢሆንም ሌሎች ቤተ እምነቶች ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋት በተጠቀሙበት ልክ ተጠቅመንበታል ማለት ግን የሚቻል አይደለም፡፡ ሆኖም ስብከተ ወንጌልን ለማጠናከርና ለማስፋፋት የተደረጉ ሙከራዎች አልነበሩም ማለት ግን አይቻልም፡፡ በ1990ዎቹ መጨረሻ ላይ የስብከተ ወንጌልን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በሚመለከት አንድ ከፍተኛ የስብከተ ወንጌል ማኅበር በዐዲስ መልክ ተቋቁሞ ሥራ ጀምሮ ነበር፡፡ ማኅበሩ፡-
- በዐሥራ ኹለቱ ሐዋርያት፣ በሰብአ አርድዕት፣ በሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት፤ በጠቅላላ በመቶ ሃያው የክርስቶስ ቤተ ሰብእ አንጻር የተዋቀረ ማድረግ፣
- ዓላማው ስብከተ ወንጌልን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ከጠረፍ እስከ ጠረፍ በማዳረስና አገልግሎቱን በቋሚነት እንዲቀጥል ማድረግ፤
- የገቢ ምንጭን በሚመለከት የዐዲስ አበባ ካህናትና ከቤተ ክህነት አገር አቀፍ የቢሮ ሠራተኛ እስከ ሲኖዶስ አባላት ድረስ ያለው ኃይል ከወርኃዊ ገቢው /ክፍያ ላይ/ ከመቶ ኹለት ብር እንዲከፍል የየአህጉረ ስብከቱ ሠራተኛም እንዲኹ እንዲያደርግ፤
- ለዚኽ ክፍያ ገቢና ወጭ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ብቃት ያላቸው የሒሳብ ሠራተኞ እንዲመደቡ ማድረግ፣
- በጠቅላይ ቤተ ክህነት የዚህን እንቅስቃሴ ገቢና ወጭ ሕጋዊነት በቅርብ እንዲከታተል ማድረግ፤ የሚሉ በማኅበሩ የሚሠሩ ዝርዝር ሥራዎች ተለይተው ሥራ ጀምሮ ነበር፡፡ 9
ከዚህም በተጨማሪ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የሥራ እንቅስቃሴና የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር በቅንጅት እንዲካሄድ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ የስብከተ ወንጌል ማስፋፋያና ማጠናከሪያ ደንብ በ1991 ዓ.ም እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ የደንቡም ዋና ዓላማ የእግዚአብሔርን መንግሥት መስበክ፣ ትምህርተ ወንጌልን ማስፋፋት፣ መሆኑ በወጣው ደንብ አንቀጽ 1 ንዑስ አንቀጽ 2.2 ተራ ቁጥር “ሀ” ላይ ተቀምጧል፡፡ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያና ማጠናከሪያ ጉባኤ መዋቅር በጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ በሀገረ ስብከት፣ በወረዳና በአጥቢያ ተዘርግቶ እንደ የደረጃው በቅደም ተከተል በ120፣ በ72፤ በ36፣ እና በ24 አባላት ተመሥርቶ ዓላማውን ሲፈጽምና ሲያስፈጽም የነበረ ቢሆንም ጉባኤው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ ሄዶ በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ቆሟል፡፡
የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ከሀገር ውጪ
- በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም
የኢትዮጵያና የእስራኤል ግንኙነት በዘመነ ብሉይ ንግሥተ ሳባ ወደ ሰሎሞን ባደረገችው የኢየሩሳሌም ጉዞ የተጀመረ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ለበዓል ሊሠግዱ ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዙ ኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ከእስራኤል ጋር ባላት ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ትስስር ንጉሥ ሰሎሞን ለንግሥተ ሳባ ከሰጣት ከጋዛ ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም የራሷ አድባራት እና ገዳማት እንዲኖራት ምክንያት ሆኗል፡፡ እነርሱም፡- ሀ. ዴር ሱልጣን፡- ከጎልጎታ አጠገብ የሚገኘው ዴር ስልጣን (ደብረ ሥልጣን) ገዳም ከልደተ ክርስቶስ በፊት በ1013 ዓመተ ዓለም ገደማ ንግሥተ ሳባ ኢየሩሳሌም ስትሄድ ሠራዊቷን እና ጓዟን ያሳረፈችበት ቦታ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ለ. ቅዱስ ፊልጶስ፡- የኢትዮጵያ መንበረ ጵጵስና የሚገኝበት ሲሆን ኢትዮጵያዊውን ጀንደረባ ባጠመቀው በቅዱስ ፊልጶስ ስም የተሠራ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በአፄ ዮሐንስ ትእዛዝ መ/ር ወልደ ሰማዕት በ1883 ዓ.ም የገዙት ቦታ ነው፡፡ ሐ. ደብረ ገነት ኪዳነ ምህረት፡- በነቢያት መንገድ አጠገብ የምትገኝ የመነኮሳት መኖሪያ የእንግዶች መቀበያ እና አዳራሽ ያላት ሰፋ ያለ ይዞታችን ስትሆን ቦታው በ1882 ዓ.ም በአፄ ዮሐንስ ዘመን ተጀምሮ ሕንጻውን ያስፈጸሙት በ1885 ዓ.ም. አፄ ምኒልክ ናቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ይዞታቸው በኢሩሳሌም ከተማ የሚገኙ ናቸው፡፡ መ. አቡነ ተክለ ሃይማኖት /አልአዛር/፡- በኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ 12 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ ላይ በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም የታነጸ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን መካነ መቃብር በዚህ ይገኛል፡፡ አፄ ኃ/ሥላሴ ያስገዙት ቦታ ሲሆን በአቡነ ፊልጶስ ጊዜ በ1953 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡ በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ያገልግሎት ዘመን ዘመናዊ ሕንፃ ታንፆ ለአረጋውያን መጦሪያነት ያገለግላል፡፡ ሠ. ቅድስት ሥላሴ፦ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ በሚገኘው ከሩብ ጋሻ በማያንስ ቦታ ላይ የታነጸ ቤተ ክርስቲያን ሲኾን፣ በአረቦችና በእሥራኤል ጦርነት ምክንያት በአካባቢ ሰው ሊኖር ባለመቻሉ ታቦቱም መነኮሳቱም ተዘዋውረው በኢያሪኮ ይኖራሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ በ1925 ዓ.ም. በእቴጌ መነን የተሠራ እንደ ነበረ ይነገራል፡፡ ረ. ቅዱስ ገብርኤል፡- በኢያሪኮ ከተማ ለብዙ ጊዜያት የአትክልት ቦታ ሆኖ በቆየው የኢትዮጵያ ይዞታ ላይ የተሠራ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ቦታው ወ/ሮ አማረች ዋለሉ በኋላ እማሆይ አማረች የተባሉ እናት በ1928 ዓ.ም ገዝተውት ለገዳሙ የሠጡት ነው፡፡ ሰ. ቤተልሔም፡- በምድረ ፍልስጥኤም ጌታችን ከተወለደበት ቦታ አጠገብ የሚገኝ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን ቦታው ልዑል ራስ ካሣና ልዑል መኮንን ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ ያስገዙት ነው፡፡ በአጠቃላይ በሀገረ እስራኤል የሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት ሀገራችን ከጥንት ጀምሮ የነበራት ጠንካራ ግንኙነትና የኢዮጵያ ቀደምት ነገሥታት ሃማኖተኞች የመሆናቸው ውጤቶች ሲሆኑ ከሐዋርያዊ ተልእኮም አንጻር ገዳማትና አድባራቱ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
- በምድረ ጅቡቲ
በደርግ ዘመነ መንግሥት በፖለቲካዊ ወይም በኢኮኖሚያዊ ምክንያት ወደ ጅቡቲ የፈለሱት ኦርቶዶክሳውያን ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጽሙበት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ቀድሰው የሚያቆርቡ ካህናት ስላልነበሩአቸው በጣም ይቸገሩ ነበር። በተለይም በየዓመቱ የስቅለት ዓርብ በአንድ አዳራሽ ተስብስበው ሲያለቅሱ ነበር የሚውሉት፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የስዊድን ሊቀ ጳጳስ ለስደት እንደተዳረጉ ወዲያው በዚሁ ሕዝብ መካከል በመገኘት ለቤተ ክርስቲያናቸው ቅዱስ ሲኖዶስም ለኢትዮጵያ መንግሥትም ለሕዝቡም ጥሪ አደርገው ከሁሉም አቅጣጫ አዎንታዊ መልስ ስላገኙ አሁን በጂቡቲ የሚገኘውን ታሪካዊ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ታንጾ ስደተኛውን ሕዝብ ከችግር ለመታደግ ተችሏል፡፡ ይህ ሐዋርያዊ ተግባር በምድረ ጅቡቲ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የሌላ ሀገር ዜግነት ላላቸው ኦርቶዶክሳውያን ትምህርተ ወንጌል ለማዳረስ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
- በምድረ ኬንያ
በምድረ ኬንያ የተመሠረተው ዛሬ የኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የብዙ ኦርቶዶክሳውያን መጠጊያ ለመሆን የበቃው በኬንያ ናይሮቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጅቡቲው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መመሥረት በኋላ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት የተመሠረተ ነው፡፡ እኒህ ብፅዕ ሊቀ ጳጳስ በግሪክም በስዊድንም ሀገር በስደት የሚገኘውን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አማኝ ሕዝብን በማደራጀትና የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ባለቤትም በማድረግ የፈጸሙት ገድል እጅግ የሚያስመሰግን ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ዓላማ ከሆነው ሐዋርያዊ የስብከተ ወንጌል ተልእኮ አንጻር የቤተ ክርስቲያን በምድረ ኬንያ መመሥረት እጅግ አስፈላጊ ነበር፡፡ በመመሥረቱም አያሌ ምእመናንን በወንጌል ማጽናናት ተችሏል፡፡ በተለይም በአሁን ሰዓት በሰሜን አሜሪካ በካሊፎርኒያ ግዛት የሳክራሜንቶ ቅዱስ ሚካኤልና ቅድስት ማርያም አስተዳዳሪ የሆኑት መልአከ ሰላም አባ ገ/ሚካኤል ገ/ኪዳን በኬንያ በነበሩበት ወቅት የናይሮቢ መድኃኔ ዓለም አስተዳዳሪ በመሆን ከፍተኛ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አበርክተዋል፡፡
- በምድረ ሊባኖስና በአረብ ኤምሬትስ
በምድረ ሊባኖስና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተለያየ ምክንያት ከሀገራቸው የተስደዱ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ይታወቃል። እነዚህ በተለያዩ የአረብ ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው ሴቶች ሲሆኑ በስደት የሚያጋጥማቸው ፈተና ደግሞ እጅግ ከባድ በመሆኑ የሚጽናኑበትና የሚረጋጉበት ሥፍራ ደግሞ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህን የተረዱት የሊባኖስና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ በሀገረ ሊባኖስ፣ በዮርዳቦስ፣ በኳታር ወዘተ ለቤተክርስቲያን የሚሆን ቦታን ይዞ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን በማስገንባት በሌሎችም የአረብ ሀገራት የሌሎችን ሕንጻ በመጠቀም ምእመና ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡርደሙ እንዳይርቁ በቋሚና በየጊዜው በሚጋበዙ መምህራን ትምህርተ ወንጌል እያገኙ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጠንካራ እንዲሆኑ እያደረጉት ያለው ጥረት እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ በዚህም ሐዋርያዊ ተግባር በርካታ ኦርቶዶክሳውያን በወንጌል ተጽናንተው የስደቱ መከራ ተስፋ እንዳያስቆርጣቸው ይልቁንም ብርቱዎች ሆነው ከቅዱስ ምሥጢር የማይርቁ ጠንካራ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ እውነተኛው የወንጌል ተልዕኮ ምቹ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ላሉት ብቻ ሳይሆን በእንዲህ ያለ ችግር ውስጥ ላሉት የክርስቶስን ወንጌል ማድረስ ስለሆነ በአረብ ሀገራት ውስጥ የሚታየው እጅግ አስደናቂ የሆነ ሐዋርያዊ ተግባርሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው፡፡
- በምድረ ደቡብ አፍሪካ
በደቡብ አፍሪካ የምትገኝ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አመሠራረት ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ለመሆን ከመፈለግ የመነጨ ሲሆን ነጻ የመውጣት ንቅናቄ (Ethiopianism አንቅስቃሴም movement) የሚል ነበር፡፡ ኢትዮጵያን የነጻነት ምልክት በማድረግ ከቅኝ ነዢዎች ቀንበር ለመላቀቅ ያደረጉት ትግል ፍሬ አፍርቶ በመጨረሻም ነጻ ወጥተዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያን የነጻነት ተምሳሌት አድርገው እንደታገሉ ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወሕዶ ሃይማኖትም በቅኝ ገዢዎች ለቅኝ ግዛት ዓላማ የተሰበከች ሳትሆን ቅኝ ያልተገዛች ነጻ ሀገር አምና በፈቃዷ የተቀበለችው እውነተኛ የአፍሪካ ሃይማኖት የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ናት በሚል በራሳቸው በደቡብ አፍሪካውያን ፍላጎት የተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን ናት የደቡብ አፍሪካ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፡፡ ይች ቤተ ክርስቲያን እንድትሰፋና እንድትጸና በካሪቢን ሀገሮች ሰፊ ሓዋርያዊ ተግባር የፈጸሙት ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ በደቡብ አፍሪካም ሰፊ ሐዋርያዊ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ ከአንግሊካል ቤተ ክርስቲያን (Angelical Church) ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመመለስ ባለፈ ከመሠረተ እምነትና ሥርዓት አንጻር ሰፊ ክፍተት ስለነበረበት ያንን ክፍተት በመጠኑም ቢሆን ለመሙላት መልአከ ሰላም ዳኛቸውም የፈጸሙት ሐዋርያዊ ተግባር ደቡብ አፍሪጋውያኑም በአድናቆት የሚጠቅሱት ተግባርነው፡፡ በረከታቸው ይድረሰንና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስም ወደ ደቡብ አፍሪካ በሄዱባቸው አጋጣሚዎች በመምከርና በማበረታታት ተስፋ እንዳይቆርጡ የማድረግ ሥራን ይሠሩ አንደ ነበር ይጠቀሳል፡፡ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ጊዜ ለበርካታ ደቡብ አፍሪካውያን ማዕርገ ቅስናን በመስጠት ከመካከላቸውም ሊቀ ካህናት በመሾም ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዳትዳከም ያደረጉት አስተዋጽኦ የሚያስመሰግን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ብፁዕነታቸው በስደት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ትምርተ ወንጌል እንዲያገኙ ቋሚ ካህናትንና መምህራንን በመቅጠር በየጊዜውም መምህራነ ወንጌል ከኢትዮጵያ በመጋበዝ ሰፊ ሐዋርያዊ ተግባር የፈጸሙ ሲሆን በርካታ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን በማሳነጽ መእመናን ከቅዱስ ምሥጢር እንዳይርቁና ትምህርተ ወንጌል እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡ ይህ ሐዋርያዊ ተግባር አሁንም በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ እዚህ ላይ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ደቡብ አፍሪካውያኑ እዚያው ባሉበት ሠልጥነው ማስተማር እንዲችሉ ታስቦ ብሉምፎንቴን በተባለች የደቡብ አፍሪካ ከተማ ውስጥ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ገዳምና ቅዱስ ያሬድ ካህናት ማሠልጠኛ ተቋቁሞ የነበረ ቢሆንም ገዳሙ በስደት ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ትልቅ አገልግሎት እየስጠ ቢሆንም ለደቡብ አፍሪካውያኑ ታስቦ የነበረውን አገልግሎት ግን እየሰጠ አይደለም፡፡ በመሆኑም በተለይደቡብ አፍሪካውያኑ ኦርቶዶክሳውያን ጠንክረው ለሌሎች አፍሪካውያንም ጭምር መትረፍ እንዲችሉ እነሱን መሠረት ያደረገ ሥራ በሚገባ ታቅዶና ታስቦበት ሊሠራ ይገባል፡፡
- በካሪቢያን ሀገሮች
ወደ ካሪቢያን ሀገሮች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የገባችው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሲሆን በዚያው ዘመን በተለይም በጃማይካ ውስጥ የሚገኙ ራስተፈሪያን ማለትም አፄ ኃይለ ሥላሴን እንደ መሲህ የሚያዩ ጃማይካውያንን አስተምሮ በማጥመቅ ትልቅ ሥራ የሠሩት አድዋ የተወለዱትና እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቅጣጠርበ 1970 ዓ.ም ከኒውዮርክ ወደ ጃማይካ የሄዱት አባ ማንደፍሮ ናቸው፡፡ እኚህ አባት አፄ ኃይለ ሥላሴን ለ2ኛ ጊዜ ተመልሶ እንደ መጣ ክርስቶስ የሚቆጥሩ ብዙ ጃማይካውያንን ከማጥመቃቸውም በተጨማሪ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን በካሪቢያን ሀገሮች መሥርተዋል፡፡ እንደ አውሮፓውን ዘመን አቆጣጠር በ1979 ዓ.ም የምዕራባዊ ንፍቀ ክበብና የደቡብ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ ሆነው አቡነ ይስሐቅ ተብለው ተሾመው በርካታ ሐዋርያዊ ተግባር በካሪቢያን ሀገሮችና በደቡብ አፍሪካ የፈጸሙ ሲሆን ጃማይካዊው ታወቂው የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ ቦምባርሊንም ያጠመቁት እኚህ አባት ናቸው፡፡ ይህ ተግባር ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፋዊት መሆንዋን በሚገባ የሚገልጽና የስብከተ ወንጌል ተልእኮን በአካባቢ ሳይገደብ ለሁሉ መድረስ እንዳለበት የተረዳ ሐዋርያዊ ተግባር ነው፡፡
- በአሜሪካ ፣ በአውሮፓና በኤዥያ
በሀገረ አሜሪካና በአውሮፓ በስደት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምክንያት በርካታ አብያተ ክርስቲያናት የተመሠረቱ ሲሆን በርካታ ሊቃነ ጳጳሳትና አህጉረ ስብከትም ይገኛሉ፡፡ አብያተ ክርስቲያናትና ጳጳሳት በዚያ የመገኘታቸው ዋነኛው ምክንያት ስደት ቢሆንም በእግዚአብሔር ፈቃድ ስደቱ ለመልካም ሆኖ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ትልቅ በር ከፍቷል፡፡ በአጠቃላይ ከሀገር ውጪ የሚገኘው የአብያተ ክርስቲያናት ምሥረታና አንቅስቃሴ በጠንካራ ብፁዓን አባቶች፣ ካህናትና ምእመናን ብርታት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ዓላማ የሆነው የስብከተ ወንጌል ተልእኮን ከማሳካት አንጻር ከፍተኛ ሚናን መጫወት ችሏል፡፡
የስብከተ ወንጌል አሁናዊ እንቅስቃሴ
በአሁን ሰዓት በአትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የፋይናስ አቅም መጠናከር፣ የጳጳሳት ቁጥር መጨመር፤ የአብያተ ክርስቲያናት ቁጥር መጨመር፣ በውጭ ሀገር የቤተ ክርስቲያናች አገልግሎት በስፋት መከናወን በበጎነት የሚጠቀሱ መልካም እድገቶች ቢሆኑም የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ አሁናዊ ሁኔታ ዘመኑ ከሚጠይቀው አገልግሎት አንጻር ሲታይ የስብከተ ወንጌሉን ሥራ በተጠና፤ በታቀደና በተቀናጀ መልክ ስልትን ቀይሶ የማደራጀት፣ የመከታተል፣ አፈጻጸሙን እየገመገሙ የእርምት እርምጃ የመውሰድ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው ለማለት አስደፍርም፡፡
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያም ትምህርተ ወንጌልን ለዓለም ሁሉ ለማዳረስ፣ የቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና ሳይበረዝና ሳይከለስ በየትኛውም ቦታ ትምህርተ ወንጌል መሰጠቱን የማረጋገጥ፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበትና ለዚሁ ዓላማ የተዋቀረ መምሪያ ቢሆንም በሰው ኃይል፤ በፋይናንስና በሎጂስቲክስ ያልተጠናከረ ከመሆኑም በላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶች መሻሻልና ማደግ ሲገባው በንጉሡ ዘመንም ሆነ በዘመነ ደርግ ከነበረው እንቀስቃሴ በእጅጉ ተዳክሞ ይታያል፡፡ በመሆኑ በተሰጠው ኃላፊነት ልክ በሀገራችንም ሆነ በመላው ዓለም ያለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴን የመከታተል፣ የመቆጣጠርና የማጠናከር ሥራ መሥራት በሚችልበት ደረጃ ላይ አይገኝም፡፡ በተለይም መምሪያው በውጭ አገር ያሉትን አብያተ ክርስቲያናትና ምእመናንን በተመለከተ በትምህርተ ወንገል ዙሪያ ምን እየተሠራ እንደሆነ የሚከታተልበትም ሆነ የሚቆጣጠርበት የግንኙነት መስመር የለውም፡፡ በመምሪያው ውስጥ የሚዘጋጁ የሕትመት ሥራዎችም ቢሆኑ ከሐዋርያዊ ተልእኮ አንጻር ሚናቸው ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም የአደረጃጀት፣ የሰው ኃይልና የማቴሪያል ችግር ስላለባቸውና አደረጃጀታቸውና የሥራ ሂደታቸው በአግባቡ ተፈትሾ መፍትሔ ስላልተሰጠው ዘመኑን በዋጀና በሚፈለገው ደረጃ ይገኛሉ ማለት አይቻልም፡፡ ይህም ሲባል እንደ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ እድገት የለውም ማለት ሳይሆን ከስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልኮ መምሪያ አንጻር እድገት አለ ለማለት የሚያስደፈር አለመሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ሆኖም እንደ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምረያ መዋቅር የተዳከሙና መጠናከር ያለባቸው ነገሮች ቢኖሩም ከስብከተ ወንጌል እድገትና ማስፋፋት አንጻር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተሠሩ በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም ሥራዎች ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
- የተዘጉ መንፈሳዊ ኮሌጆች መከፈትና መስፋፋት
- የማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤ ት/ት መጠናከር
- የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መከፈት
የዚህ ዘመን ስብከተ ወንጌል ፈተናዎች
ባለንበት በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ዓላማን እንዳታሳካና ተልእኮዋም በሚፈለገው ደረጃ እንዳይፋጠን እንቅፋት የሆኑባትና እየገጠሟት ያሉ ፈተናዎች የውጭና የውስጥ ብሎ በሁለት ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡
ሀ. ውጫዊ ፈተናዎች
በዚህ ዘመን የቤተ ክርስቲያናች ሐዋርያዊ ተልእኮን እየተገዳደሩ ያሉ ውጫዊ ፈተናዎች በዋናነት በፕሮቴስታንቱ በኩል የሚደረግ የምእመናን ዝርፊያ (ቅሰጣ)፣ በአክራሪዎች የሚፈጸም የኃይል ጥቃት፣ የርዕዮተ ዓለም ፈተና እና የዘውግ ፖለቲካ ፈተና ናቸው፡፡
- የመንጋ ቅሰጣ
በቤተ ክርስቲያናችን የ40 ዓመት ጉዞ ውስጥ በተለይም ባለፉት 30 ዓመታት ቤተ ክርስቲያናችን የገጠማት ከባዱ ፈተና የምዕራባውያን ሥውር ሴራና የፖለቲካ ዓላማን መሠረት ያደረገው ከፕሮቴስታንቱ ዓለም የገጠማት ፈተና ነው፡፡ ይህ ኃይል የክርስቶስን ወንጌል ለዓለም የመስበክ ዓላማ ቢኖረው ኖሮ ፈጽሞ ወንጌልን ያልሰሙትንና የክርስቶስን አዳኝነት የማያውቁትን ሕዝቦች ለማዳን ክርስትናው ያልደረሰባቸው አካባቢዎችን የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ በሠራ ነበር፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ለሁለት ሺህ ዓመታት የክርስትናን እውነት ጠብቃ የኖረችውን ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም በብርቱ ሠርቷል፡፡ የኢትዮጵያ አንድነትን አስጠብቃ በመቆየቷ በምዕራባውያን ቂም የተያዘባት የኢትየጵያን ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከምና ከተቻለም ለምጥፋት አሁንም በብርቱ ይሠራል፡፡ይህ ኃይል ከክርስትናው ዓላማ ባፈነገጠ መልኩ የዘውግ የፖሎቲካውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዓለም አቀፋዊቷን ቤተ ክርስቲያን ስም የአንድ ብሔርና የተወሰነ ሀገራዊ ክልል ሃይማኖት እንደ ሆነ አድርጎ በውሸትና በማጥፋት የዋሃን ምእመናንን በመዝረፍ ቁጥሩን ከፍ አድርጓል፡፡ አንዳንድ ፍቅረ ንዋይ የጸናባቸውና በተለያየ ምክንያት ያኮረፉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ተጠቅሞ ወደ ውስጥ ስርጎ በመግባት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ያስፈልጋታል የሚል እንቅስቃሴን በመፍጠርና በመምራት ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮን ለመቀየርና ለምዕራባውያን ርዕዮተ ዓለም በሚመቸው ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮ ለመተካት በብዙ ሠርቷል፡፡
- የአክራሪዎች የኃይል ጥቃት
ቤተ ክርስቲያን በ40 ዓመት ጉዞዋ ከገጠሟት ፈተናዎች ሌላው የአክራሪ ሙስሊሞች እንቅስቃሴ ነው፡፡ የአክራሪ እስልምና መሪዎች በውሸትና በፈጠራ ታሪክ ኢትዮጵያ እስላማዊት ሀገር እንደ ነበረች እየተረኩና ኢትዮጵያም እስልምና የከሸፈባት ሀገር መሆኗን በመቆጨት እየተናገሩ የዋሃን ሙስሊሞችን ለዓላማቸው እንዲሰለፉ በማድረግ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይም ጥቃት እንዲፈጽሙ በብርቱ ይሠራሉ፡፡ ይህ ኃይል የኢኮኖሚ አቅሙን ከፍ በማድረግ በገንዘብ ኃይል ምእመናንን እያታለለ በመውስድ፣ እንደዚሁም ደግሞ ጋብቻን እንደ መሳሪያ በመጠቀም ሆን ብሎ ኦርቶዶክሳውያን ሴቶችን በጋብቻ ስም በማታለል፣ ይህም ካልተቻለ ምእመናንን እየገደለ ወንጌልን ለምእመናን የሚያስተምሩ ካህናትን እያረደ ከፍተኛ ፍርሐትን በምእመናን ላይ በመፍጠር ያለ ፍላጎታቸው ከመንጋው እንዲለዩ ያደርጋል፡፡
- የዘውግ ፖለቲካው ችግር
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሀገርን በመገንባት የመጀመርያና ዋነኛ ድርሻው ያላትና የኢትዮጵያ አንድነትን አስጠብቆ በመቆየት ትልቁ ሚና የተወጣች አንጋፋና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ ልትመሰገንና ልትከበር የሚገባት ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህች ቤተክርስቲያን “የአንድ ወገንና አካባቢ ሃይማኖት “እንደ ሆነች አድርገው በሚያቀነቅኑ ኃይሎችና “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቤተክርስቲያኒቱን ቀድሞ ማዳከምና ማፈረስ “የሚለውን ሴራ እንደ መርህ ባነገቡ የዘውግ ፖለቲከኞች ምክንያት ከባድ ፈተና እየገጠማት ትገኛለች፡፡ በዚህም ምክንያት በአንዳንድ የክልልና የዞን መስተዳደድሮች ጣልቃ ገብነት የቤተክርስቲያኒቱን መዘረፍና የማምልኪያ መቅደሶቿ መቃጠል፤ ነባር ይዞታዎቿ መነጠቅ ወይም ሕጋዊ እንዳይሆኑ ማድረግ፤ የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ማክበሪያዎችን ለልማት ብሎ መቀማት አልፎም ተርፎም ለሌሎች ቤተ እምነቶች ቦታውን መስጠት ወይም እንዲጋሩ ማድረግ፣ ምእመናንን ማሸማቀቅና ማዋከብ፣ የፖለቲካ ሐሳባቸውን በምእመናን ላይ ለመጫን ከፍተኛ ግፊት ማድረግ፣ አንዳንዴም ጥቃት አድራሾችን አሰልጥኖ በመሰማራት አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠልና ማውደም የዘውግ ፖለቲካው ያመጣቸው የወቅቱ የቤተ ክርስቲያን ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያናችን በነጻነት ወንጌልን ሰብካ የጠፍትን እንዳትመልስና ያሉትንም እንዳታጸና የዘውግ ፖለቲካው ፈተና ሆኖባታል፡፡
- የርዕዮተ ዓለምተጽእኖ
የካፒታሊዝም ርዕዮተ ዓለም በነገሠበትና ሰው የሚፈልገውንና የተመቸውን ይመርጣል እንጂ ቋሚ የሥነ ምግባር መስመር የለም ተብሎ በሚታሰብበት በዚህ ዘመንዋናው ስኬትህ ነው እንጂ ወደ ስኬት የምትሄድበት መንገድ ትክክል መሆንና አለመሆን ወሳኝ ነገር አይደለም የሚለው እጅግ አደገኛ የሆነ አስተሳሰብ ሰውን ቁሳዊ እንዲሆን ስላደረገው በክርስትና ውስጥም ሳይቀር የብልጽግና ወንጌል እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡
የዘመናችን ርዕዮተ ዓለም በፈጠረው ተጽእኖ በክርስትናው ሽፋን ድኃውን እየበዘበዙ እራሳቸውን የሚያበለጽጉ ከመበለቲቱና ከድኃው የተሰበሰበውን መባዕ ዘርፈው በድኃው ላይ ጌቶች የሚሆኑና ለመንጋው የማይራሩ የነፍሳትም መጥፋት ግድ የማይሰጣቸው አገልጋዮች የመብዛታቸው ምስጢር ገንዘብን የሚያመልከው የዘመናችን ርዕዮተ ዓለም ውጤት ነው፡፡ በአጠቃላይ የተዛባ ርዕዮተ ዓለም በወለደው ድኅረ ዘመናዊነት ተጽእኖ ምክንያት ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እየተዘነጋ ቅድስናና እራስን ለእግዚአብሔር ማስገዛት የሞኝነት ያህል እንዲቆጠር አድርጎታል፡፡ ከዚህም የተነሳ ድኅረ ዘመናዊነት የቅድስናና የርኩሰት ድንበር እንዲጠፋ፣ ግለኝነትና ራስን መውደድ እንዲስፋፋ፣ አርአያ የሚሆን አገልጋይም እንዲጠፋ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህም አገልጋዩን በእጅጉ የሚጎዳ አስተሳሰብ ለስብከተ ወንጌል ትልቅ ፈተና ሆኗል፡፡
ሊውስጣዊ ፈተናዎች
በቤተ ክርስቲያናች ዘርፈ ብዙ ውስጣዊ ፈተናዎች ቢኖሩም መንጋውን እንዲጠብቁ አደራ የተሠጣቸው ካህናትን የተመለከቱ የተወሰኑትን ወቅታዊ ፈተናዎች እንመለከታለን፡፡
- አርአያ ማጣት
በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያናችን ከገጠማት ውስጣዊ ፈተኛዎች አንዱና ዋነኛው አርአያን ማጣት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ተዘከሩ መኳንንቲክሙ ዘነገሩክሙ ቃለ እግዚአብሔር እንዘ ትሬእዩ ሠናየ ግእዞሙ ወተመሰሉ በሃይማኖቶሙ የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁ ዋኖቻችሁን አስቡ የኑሯቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በሃይማኖት ምሰሏቸው፡፡'(ዕብ. 13፡7) በማለት ምእመናን መልካም አርአያ የሚሆኗቸው መምህራንን በሃይማኖት እንዲመስሏቸው አስተምሯል፡፡ ይህም ምእመናን አርአያ የሚያደርጉት መምህር እንደሚያስፈልጋቸው መምህራንም ለምእመናን አርአያ መሆን እንዳለባቸው የሚጠቁም መለኮታዊ ሐሳብ ነው፡፡ ባለንበት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በየደረጃው ያለ አገልጋይ እስከ ሕይወት መሥዋዕትነትም ቢሆን ዋጋ እከፍላለሁ፤ ከዓለም ርኩሰት ተጠብቄ ለአልጫው ዓለም ጨው እሆናለሁ፤ የሚል ሳይሆን በከፍተኛ የርኩስት ተግባር ውስጥ የሚዘፈቅ፣ ክብረ ክህነትን በሚያቀሉ ተግባራት የሚሰማራ፣ አንዳንዱ በገንዘብ ዘረፋና በማጨበርበር የሚታሰር፣ አንዳንዱም በሟርትና ጥንቆላ ሥራዎች የሚሳተፍ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን የሚንቅ ትውልድ እንዲፈጠርና ሃይማኖት አይጠቅምም የሚል ትውልድ እንዲበራከት ያደርጋል፡፡ ሁሉም አገልጋዮች አርአያ የሚሆኑ አይደሉም ባይባልም ቁጥራቸው በመቀነሱና በአርአያነት ይልቅ መሰናክል የሚሆኑ አገልጋች በመብዛታቸው በስብከተ ወንጌል ሚፈለገው ለውጥ እንዳይመጣ ምክንያት ሆኗል፡፡
- የአመራር ዕጦት
በዕቅድ የሚመራ ስብከተ ወንጌል ተልዕኮ አላማን ግብ ያለው የቤተ ክርስቲያንዋነኛ ተልእኮ እንጂ በግምት ወይም በዘፈቀደ የሚደረግ ተራ ተግባር አይደለም፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱ ጠካራ አመራርን ይፈልጋል፡፡ ነገርግን በአመራር እጦት ምክንያት ያለ ጸጋውና ያለ ጥሪው ለእንጀራ ብቻ የሚያገለግል ከመብዘቱም በተጨማሪ ጸጋው ያለውም ቢሆን የወንጌል ዓላማ የዘነጋ በዘር፣ በፖለቲካ፣ ወይም በገንዘብ ፍቅር የተጠመደ ሆኖ ይገኛል፡፡ በቤተ ክርስቲያን አመራር በኩል ከመሪነት ጋር የሚመጣ ኃላፊነትንና ተጠያቂነት ስለሌለ በመሪውና በተመሪው መካከል ያለ ስፊ የፍላጎት ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ በተለይ የመሪነት ዓላማ ያልተረዱ ለማገልገል ሳይሆን ለመገልገል የተሠየሙ አመራሮች ቁጥር መብዛት ዋነኛ የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ የሆነውን ስብከተ ወንጌል እንዲዘነጋ ገንዘብ በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ መጠመድ ዋነኛ የቤተ ክርስቲያን አመራሮች ተግባር ሆኗል፡፡ ይህም በስብከተ ወንጌል ላይ የራሱ ተጽእኖ ፈጥሯል፡፡
- የፖለቲካ ወገን ተኝነት
ስብከተ ወንጌል ከዘር ከፖለቲ ነጻ በመሆን የወንጌልን እውነት የሚነገርበት ሰውን የሚጎዳ ነውርም የሆነ ተግባር ሲፈጸምና ፍርድ ሲጓደል ፍርድ ጎደለ ድኃ ተበደለ በማለት ለእውነትና ለፍትሕ ዘር ሳይለዩ ለሁሉ የሚጮሁነትና ማንንም ሳይፈሩ ሁሉንም ገሥጹበት አገልግሎት እንጂ የፖለቲካ ወገንተኛ በመሆን የምንደግፈው አካል ሲበድል ዝም የምንልበት የምንቃወመው አካል ቢበደል እንኳን እንዳላየና እንዳልሰማ ዝም የምንልበት አገልግሎት አይደለም፡፡ ነገር ግን በዘመናችን ያለው አገልግሎት ፖለቲካው እየተጫነው ለእውነትና ለፍትሕ መቆም እያቃተን የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌለን ሁሉም በእኩልነት የሚሰማው አገልጋይ ቁጥሩ በእጅጉ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ይህም የዘመናችን የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን በእጅጉ ጎድቶታል፡፡
ማጠቃለያ
በሦስቱ ሕግጋት ከአምልኮ እግዚአብሔር ሳትለይ ጸንታ የኖረችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሳለፈችው የረጅም ዘመን ታሪክ ብዙ የጨለማም ወርቃማም ጊዜያትን አሳልፋለች፡፡ በተለይም በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ እጅግ ውጤታማ ከነበረችባቸው ዘመናት ቅዱስ ያሬድ የተነሳበት፤ ቤተ ክርስቲያናችን እስከ ዛሬ ድረስ የምትገለገልበት ሰማያዊ ዜማን ያገኘችበት ዘመንና ምናኔን ከስብከተ ወንጌል ጋር አስተባብረው የያዙ ጻድቁ አባታች አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተነሱበት ዘመን በተለየ መልኩ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ በተለይም ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት የፈጸሙት ሐዋርያዊ ተግባርና የጻድቁ ደቀ መዛሙርት የሆኑት 12 ንቡራነ እድ አህጉረ ስብከት ተከፋፍለው አንደ አባታቸው እነርሱም የፈጸሙት ሐዋርያዊ ተግባር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ ሆኖም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተከሠተው ቤተ ክርስቲያንን በከፍተኛ ደረጃ የጎዳው የአሕመድ ግራኝ ወረራ በከፍተኛ ደረጃ ተነቃቅቶ የነበረው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ አጥፍቶታል፡፡ ወረራው ያስከተለው ጉዳት ከፍተኛ ስለነበር ሙሉ በሙሉ ወደ ነበረበት ለመመለስ እጅግ አዳጋች የነበረ ቢሆንም ከአህመድ ግራኝ ሞት መኋላ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ሊያንሰራራ ችሏል፡፡ ከዘመናት በኋላም ዘመነ መሳፍንት አልፎ ሀገራችን በማዕከላዊ መንግሥት መመራት ስትጀምር አብያተ ክርስቲያናት እየበዙ የስብከተ ወንጌል አገልግሎትም ከገዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ እንደ መጣና በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከግብፅ አገዛዝ ተለይታ በራሷ ፓትርያርክና በራሷ ቅዱስ ሲኖዶስ ሲኖዶስ ስትጀምር በስብከተ ወንጌልም ረገድ ከፍተኛ መሻሻልና መነቃቃት ተፈጥሮ እንደነበረ ተመልክተናል፡፡ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮን የበለጠ ማስፋፋት ይቻል ዘንድ ሰበካ ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላም ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ የነበረው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ምን ይመስል እንደነበረና በስብከተ ወንጌል ዙሪያ የነበሩና አሁንም ያሉ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን በዝርዝርተመልክተናል፡፡ በመሆኑም ዘመኑን ዋጅተን ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋትና በዚህ ዘመን እየገጠሙን ያሉ ተግዳሮቶችን በመሻገር ታሪካችንን፣ ባሕላችንንና ሃይማኖታችንን ጠብቀን ለቀጣይ ትውልድ ማስረከብ እንችል ዘንድ፡-
– በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅሮችን በማጠናከር በየመዋቅሩ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ድረስ ኦርቶዶክሳውያን የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ባለሞያዎችን በየዘርፍ ዘርፉ በማቋቋም አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ በሚያስፈልግ ጊዜና ሰዓት እንዲሰጡ ማድረግ፣
– ካህናት የዋጁና በከፍተኛ ፍጥነት እየተለዋወጠ በሚገኘው ዓለም ውስጥ ቀድመው ተገኝተው መምራት የሚችሉባቸው ወቅታዊ ሥልጠናዎች ከማዕከል እስከ አጥብያ ቀጣይነት ባለው መልኩ በመስጠት የማብቃት ሥራን መሥራት፤
-የቤተክርስቲያኒቱ ተተኪ ትውልድ የሆነው ወጣቱ በእምነቱ እንዳያፍርና እንዳይፈራ የተጠናና የታቀደ ኦርቶዶክሳዊ ማንነቱ የሚያስገነዝብ ስልጠናን በየደረጀው መስጠት፣
-ከተለያዩ ቤተ እምነቶች በቃልም ሆነ በጽሑፍ መልክ የሚመጡ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ያነጣጠሩ እንቅስቃሴዎችን መመከት ይቻል ዘንድ የዕቅበተ እምነት ሥራን የሚሠሩ የተመረጡ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንትን፤ የኮሌጅ መምህራንንና ሰባክያነ ወንጌልን በግብረ ኃያል መልክ በማደረጀት ከሊቃውንት ጉባኤ ጋር በጥምረት እንዲሠሩና ተገቢውን መልስ በተገቢው ጊዜ እንዲሰጡ ማድረግ፤
-በተጠናና በታቀደ መልኩ ባህልን ታሪክንና ቋንቋን መሠረት ያደረጉ የወንጌል አገልግሎቶችን በተጠናከረ መልኩ መተግበር፣
-የሥልጠና ተቋሞቻችን የማስተማር ካሪኩለማቸውን ከነባሩና ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ካቆዩልን ሥርዓተ ትምህርትና የትርጓሜ ስልት ጋር በማገናዘብ ዘመኑንና ሁኔታውን የተረዱ ችግር ፈቺ የሆኑ ሊቃውንት በብዛትና በጥራት የሚፈሩባቸው ተቋማት እንዲሆኑ ማድረግ፣ -ውሳጣዊ ችግሮችን በጥንቃቄ በመፍታትና ለኢአማንያን መሳለቂያ ከመሆን በመቆጠብ የቤተ ክርስቲያን ዋና ተልእኮዋ ወደ ሆነው ስብከተ ወንጌል መመለስ፣ በዚህ ዘመን ልተገብራቸው የሚገቡን ዐበይት ተግባራት ናቸው፡፡
በመሆኑም ዘመኑ ቀድሞ በማሰብ በእምነት፣ በዕውቀትና በጥበብ እየተጓዝን የወንጌልን ተልእኮ የምንፈጽምበት እንጂ ተዘናግተን የምንቀመጥበት አይደለምና ነቅተን አገልግሎታችንን በትጋት ልንፈጽም ይገባናል፡፡
በመጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወ/ትንሣኤ
