፫ኛው ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን የመክፈቻ መርሐ ግብር በየረር ጎሮ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል እጅግ ደስ በሚል መንፈሳዊ ድምቀት ተከናውኗል

“በወንጌል ኮነ ሕይወትነ – በወንጌል ሕይወታችን ሆነ” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው ፫ኛው ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ቀን የመክፈቻ መርሐ ግብር ሚያዝያ ፲፰ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ አማካኝነት የተዘጋጀ ሲሆን
በዕለቱ የወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስና መካነ ጎልጎታ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ ሊቀ ሊቃውንት ሥሙር አላምረው “ወቦአ ከመ ይኅድር ምስሌሆሙ፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ” ሉቃ. ፳፬፥፳፱ የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ እንዲሁም የዘመነ ትንሣኤ ሦስተኛ ሳምንት በሆነችው በዚህች ሰንበት ዘመነ ፋሲካን የዋጀ ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲሆን፤
“ይህ የወንጌል ቀን መዘከር ያስፈለገውም በጨለማ ውስጥ ያለነውን ወደ ብርሃን ለማውጣት፣ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ ለመመለስና ሌሊት የሆነውን ሕይወታችንን ወደ ቀን በንስሐ ለመመለስ ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው አስተምረዋል።
በመቀጠልም የመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ጸሐፊ መ/ር ሽፈራው እንዳሻው መምርያው ያለበትን አሁናዊ ሁኔታና ይህ የስብከተ ወንጌል ቀን ክብረ በዓል ያስፈለገበት፣ ተደራሽነትና አላማ ምን እንደ ሆነ ገልጸው ማኅበረ ምእመናኑ የመምርያውን ድኅረ ገጽና በebs tv በየሣምንቱ የሚያቀርበውን እየተከታተሉ እንዲማሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።