ዳግሚት ሔዋን (ኹለተኛዪቱ ሔዋን) Second Eve

በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

ሐሰተኛ የኾነ የእባብ ክፉ ምክርን በመስማቷ በመቀበሏ ለሰው ልጆች ኹሉ የውድቀትና የሞት ምክንያት ከኾነችው ከሔዋን ተለይታ፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ለእግዚአብሔር ታዛዥ በመኾን ፲፪ት ዓመት በቤተ መቅደስ ኖራ፤ እውነተኛ መልእክት የያዘውን የቅዱስ ገብርኤል ብሥራትን በእምነት ተቀብላ፤ የሰው ልጆችን ወደ ቀደመ ክብራቸው ወደ ቀደመ ቦታቸው የመለሰ ክርስቶስን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ወልዳ ያስገኘችልን የተስፋ ምንጭ ናትና፤ የቤተ ክርስቲያን ታላላቅ የነገረ እግዚአብሔር ምሁራን ሔዋንና ቅድስት ድንግል ማርያምን በማነጻጸር ድንግል ማርያምን “ዳግሚት ሔዋን” (Second Eve) ወይም “ዐዲሲቱ ሔዋን” (New Eve) የሚል ሥያሜን ሰጥተዋታል፡፡

ለሊቃውንት መነሻ ኾኖ ያለፋቸው (በዘፍ ፫፥፩-፯) ያለው ቅዱስ ቃል ሲኾን፤ በታሪኩ እንደተጠቀሰው አዳምና ሔዋን በገነት የጌታን ሕግ ጠብቀው ሰባት ዓመት ከቆዩ በኋላ፤ ዲያብሎስ ሔዋንን አካለ ከይሲን ማደሪያ ልሳነ ከይሲን መናገሪያ በማድረግ፤ ዕፀ በለስን ብትበሉ የባሕርይ አምላክ ትኾናላችኊ፤ ቢላት የእባብ የሐሰት ምክሩን በመቀበል አምላክነትን ሽታ የእግዚአብሔርን ሕግ በማፍረስ፤ የተከለከሉት ዕፀ በለስን በልታ ለባሏ ለአዳም አብልታ ለባሏና ባጠቃላይ ለሰው ዘር ኹሉ መውደቅ ምክንያት ኾናለች (ዘፍ ፫፥፩-፮)፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያም ግን የአምላኳን ሕግ ካፈረሰችው ከሔዋን ግብር ተለይታ፣ በሃይማኖት፣ በምግባር፣ በንጽሕና፣ በቅድስና ጸንታ ከእግዚአብሔር ተልኮ የመጣ፤ የጨለማ መልአክ ያይደለ የብርሃን መልአክ ቅዱስ ገብርኤል የነገራትን የእውነት የብሥራት ቃልን በታላቅ እምነት ተቀብላ፤ ለአምላክ ቃል ታዛዥ በመኾን እንደቃልኽ ይደረግልኝ (ሉቃ ፩፥፴፰) በማለት ታማኝነቷን በማሳየቷ ቅድስት ድንግል ማርያም (ኹለተኛዪቱ ወይም ዐዲስቱ ሔዋን) ተብላ ተጠርታበታለች፡፡
ይኽነን በሔዋንና በድንግል ማርያም መኻከል ያለውን ታላቅ የታማኝነት ልዩነት ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በጥልቀት ሲገልጽ ፡-

“እስመ ቀዳሚኒ ሔዋን ኮነት ድንግል ወአስሐታ ዲያብሎስ ለማርያምሂ ድንግል አብሠራ ገብርኤል ወባሕቱ ለሔዋንሰ አስሐታ ዲያብሎስ ወወለደት ቃየልሀ ዘውእቱ ምክንያተ ሞት ወማርያምሰ ሶበ አብሠራ መልአክ ወለደት ቃለ በሥጋ ዘውእቱ መራሔ ኲሉ ኀበ ሕይወት ዘለዓለም”
(ቀድሞም ሔዋን ድንግልን ነበረችና ዲያብሎስ አሳታት እንጂ፤ ድንግል ማርያምን ግን ገብርኤል አበሠራት፤ ነገር ግን ሔዋንን ዲያብሎስ አሳታት፤ የሞት ምክንያት የሚኾን ቃየልን ወለደች፤ ማርያም ግን መልአክ ባበሠራት ጊዜ ኹሉን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ አካላዊ ቃልን በሥጋ ወለደች) በማለት ሔዋንና ድንግል ማርያም ያላቸውን ልዩነት በማነጻጸር ገልጾታል፡፡

ዳግመኛም ይኸው ሊቅ ሔዋን አምላክነትን ሽታ እንብላ ያለችው ቃሏ ለኹሉ ምክንያተ ሞት የኾነ ዕፀ በለስን አስገኝቶ፤ በዚኹ ምክንያት አዳም ከገነት ቢባረር እንኳን፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተገኘ አካላዊ ቃል ግን ዕፀ ሕይወት መስቀልን አስገኝቶ፤ በዕፀ በለስ ምክንያት ከገነት የወጣውን አዳምን በዕፀ ሕይወት በመስቀሉ ወደጥንት ቦታው ገነት እንደመልሰው በትምህርቱ፡-

“ቃላ ለሔዋን ከሠተ ዕፀ ወበውእቱ ዕፅ ወፅአ አዳም እምገነተ ተድላ ወቃልሰ ዘተወልደ እምድንግል ከሠተ መስቀለ ወቦቱ ቦአ ፈያታዊ ውስተ ገነተ ተድላ ዘምስለ አቡሁ አዳም ወኲሎሙ አበው ቀደምት”

(የሔዋን ልብላ ልብላ ማለቷ ዕፀ በለስ የሞት ምክንያት እንደኾነ አስረዳ፤ በዚያም ዕፅ አዳም ተድላ ደስታ ካለበት ከገነት ወጣ፤ ከድንግል የተወለደ አካላዊ ቃል ግን መስቀል የድኅነት ምክንያት እንደኾነ ገለጠ፤ በዚያም መስቀል ቀማኛ ወንበዴ የነበረው ሰው ከአባቱ ከአዳምና ከቀደሙ አባቶች ኹሉ ጋር ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት ገባ) በማለት እያነጻጸረ አስተምሯል (ዘፍ ፫፥፳፬፤ ሉቃ ፳፫፥፵፩-፵፬፤ ፩ኛ ቆሮ ፩፥፲፰)፡፡

ሔዋንንና ድንግል ማርያምን እያነጻጸሩ ሊቃውንት ያስተማሩትን ጥልቅ ትምህርት ኹሉ በዚኽ ማጠቃለል ባይቻልም ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ድንግል ማርያም ዳግሚት ሔዋን የመባሏን ምስጢር በስፋትና በጥልቀት ያስተማረውን ትምህርት ለማየት እንሞክራለን፡፡

ይኽ ሊቅ የሐሰትንና የሞት መልእክትን የያዘውን እባብንና፤ የእውነትና የሕይወት መልእክትን የያዘውን ቅዱስ ገብርኤልን፤ የሐሰት የዲያብሎስን መልእክት በደስታ በመቀበል ለሰው ኹሉ ውድቀት መነሻ የኾነችውን ሔዋንንና፤ ከእግዚአብሔር ተልኮ የመጣውን መልእክት በፍጹም እምነት ተቀብላ ሕይወት የሰጠን ጌታን የወለደችው ድንግል ማርያምን ሲያነጻጽር፡- “The evil time which had killed Adam was changed, another good time came…” (አዳምን እንዲሞት ያደረገች ያቺ ክፉ ቀን ተለወጠች፤ ርሱም ከሞት የሚድንባት ሌላ ቀን መጣች፤ እባቧ ሳትኾን ገብርኤል ሊናገር ተነሣ፤ ሔዋን ሳትኾን ድንግል ማርያም ቃሉን ልትቀበል ተዘጋጀች፤ በተንኰል ቃል የሚያሳስተው ሳይኾን ሕይወትን የሚያውጅ እውነተኛ ቃል ወጣ፤ በሞት ዛፍ መኻከል የሞት ዕዳዋን በጻፈችው እናት (ሔዋን) ፈንታ፤ ልጇ (እመቤታችን) የአባቷን ዕዳ ኹሉ ከፈለች፤ ሔዋንና እባቡ በመልአኩና በድንግል ማርያም ተተኩ፤ ያ ከመዠመሪያው የተበላሸውም ጉዳይ እንደገና ተስተካከለ፤ የሔዋን ዦሮና ቀልብ አታላዩ በሚናገርበት ጊዜ ምን ያኽል እንዳዘነበለ አስተውል፤ ነገር ግን ያ በገነት ሲመለከታቸው የነበረ መልአክ አኹን በማርያም ዦሮ የድኅነት የተስፋ ቃል ሲያሠርጽ የእባቡን ክፉና መርዛማ ቃል ሲያጠፋ ርሷንም ሲያጽናና ተመልከት፤ ያነን እባብ ያፈረሰውን ሕንጻ ገብርኤል ገነባው፤ በዔደን ሔዋን ያፈረሰችውን ድንግል ማርያም መሠረቱን ገነባች፤ ከኹለት መልእክተኞች መልእክት የተቀበሉ ኹለት ደናግል ኹለት ኹለት ኾነው ትውልዶችን ቀጠሉ፤ አንዱ የአንዱ ተቃራኒ ኾነ፤ በእባብ አማካኝነት ሰይጣን ምስጢርን ለሔዋን ላከ፤ በመልአክ አማካኝነት ደግሞ ጌታ የምሥራቹን ወደ እመቤታችን ማርያም ላከ፤ እባብ የሐሰትን ቃል ለሔዋን ስትናገር ገብርኤል ግን የእውነትን ቃል ለድንግል ማርያም ተናገረ፤ እውነትን በሚናገር አንደበቱ መልአኩ ቃሉን አደሰው፤ እውነትን ተናገረ በዚኽም ሐሰትን ኹሉ አስወገደው፤ ተንኰልን ከራሱ ባወጣ በሰይጣን በዔዴን ገነት ድንግሊቷ ተታለለች፤ ታላቁ ስሕተት በዦሮዋ ዐልፎ እንዲሰማት ዐደረገች፤ በመዠመሪያዋ ድንግል ፈንታ ሌላ ድንግል ተመረጠች፤ በዚኽችም ድንግል ዦሮ ከአርያም የመጣ የእውነት ቃል ገባ፤ ሞት በገባበት በዚያው በር ደግሞ ሕይወት ገባ፤ ክፉው ያጠበቀውን ጽኑዕ የሞት ማሰሪያ ፈታ፤ ኀጢአትና ሞት ከመዠመሪያው እጅግ እንደሰለጠኑ ኹሉ፤ እንዲኹ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በዝቶ በአዳም ታየ፤ እባብ ከሔዋን ጋር ስትነጋገር ሔዋን አልተንበረከከችም አልሰገደችም፤ ሞት በመላበት ጐዳና ሰላምና ትሕትና አይገኙምና፤ እባብ የስሕተትን ዜማ ለሔዋን ዘመረ ሐሰትን ረጨባት፤ በተፈጥሮዋ ገና ድንግል በኾነች ሔዋን ላይ ክፉ ምክርና ስሕተት ፈሰሱ፤ ለመግደል የኾነ ጠላትነትና ክፉ ምክር ደምን የተጠማ መርዙን በንግግሩ ውስጥ በአዳም ቤት ውስት አስገባ፤ በወልድ የተላከው መልአክ እነዚኽን የክፋት ሰይፎች ለመቋቋም ኼደ፤ ለድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር የኾነውን የመዳን ብሥራትን ነገረ፤ ሰገደላት፣ ሕይወትን በውስጧ አሠረጸ፤ ሰላምን ዐወጀላት፤ በፍቅር ቀረባት የቀደመውን የሞት ዳባ በጣጠሰ፤ እባብ የገነባው የማታለል ግንብ ዳግመኛ ላይገነባ በእግዚአብሔር ልጅ በወልድ ተናደ፤ በእባብ የታጠረው የሞት ቅጥር በወልድ መውረድ ተሰባበረ፤ በሰማያትና በምድር በሚኖሩ ኀይላት መኻከል ሰላም ይወርድ ዘንድ) በማለት ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የቀደመችቱ ሔዋን ሐሰተኛ የኾነውን የእባቡን መርዝ የመላበት ንግግሩን ተቀብላ ባሏን በአጠቃላይ የሰው ልጆችን በዲያብሎስ የክሕደት መርዝ እንዲወጉ ስታደርግ፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ግን የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል የእውነት ብሥራትን በእምነት በመቀበሏ፤ ዲያብሎስ የተከለውን የኀጢአት መርዝን ነቃቅሎ ያጠፋ ወሀቤ ሕይወት ጌታን ያስገኘችልን መኾኗን አስረድቷል፡፡

በዚኽ ትምህርቱም ሔዋን ለታማኝነት የማትበቃ ተወቃሽ ስትኾን፤ ድንግል ማርያም ግን አስተዋይ የአባቷን ዕዳ የከፈለች ፍጹም እምነትን የተመላች መኾኗን ሳያስተምር አላለፈም፤ ይኽነንም በጥልቀት ስናየው ሔዋን የሐሰት መልእክትን ከሐሰተኛው በሰማች ጊዜ ከመጠየቅ ይልቅ ዝምታን በመምረጥ የሚያባብል የተንኰልና የክፋት ቃሉን በደስታ ተቀብላ፤ አምላክ መኾንን ፈልጋ በስሕተት ስትወድቅ፤ በተቃራኒው ግን ቅድስት ድንግል ማርያምን የአምላክ እናት እንደምትኾን ቅዱስ ገብርኤል ሲያበሥራት፤ ይኽነን ልዩና ከኅሊናት ኹሉ በላይ የኾነውን ምስጢር ለመረዳት አጥብቃ የጠየቀች አስተዋይ ናት፡፡

ይኸውም በድንግል ማርያም መናገር ሕይወት፣ ብርሃን ሲኾን በሔዋን ዝምታ ግን ኀጢአት፣ ውርደት፣ ሞት መምጣቱንና ዳግመኛ የሔዋን ዦሮ የሞትና የውድቀት መልእክትን ሲሰማ የድንግል ማርያም ዦሮ ግን ታላቅ የኾነ የሕይወትና የድኅነት መልእክትን መስማቱን ይኽ ቅዱስ ያዕቆብ ሲመሰክር፡-
“On this account, the watcher had saluted Mary as a pledge of great peace for the whole world…”

(በዚኽም መልአኩ ድንግል ማርያምን አከበራት፤ ለዓለም ኹሉ ሰላም ታላቅ ቃል ኪዳን ነውና፤ “ማርያም ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ በድንግልና ትፀንሻለሽ በድንግልናም ወንድ ልጅን ትወልጃለሽ” አላት፤ ድንግል ማርያም መለሰች እንዴት ይኽ ሊኾን ይችላል? እኔ ድንግል ነኝ እንዴት እፀንሳለኍ? በዚኽ ቅጽበት መጠየቋ እጅግ ግድ ነበር፤ የወልድ በእርሷ ማሕፀን የማደር ምስጢርን መልአኩ ይገልጥላት ዘንድ፤ እመቤታችን ማርያም ጠየቀች ከመልአኩ መልስ እንማር ዘንድ፤ ስለመፅነሷ እንድትረዳ ዐደረጋት፤ ትርፋ የርሷንና ርሷን ለሚሰሙ ኹሉ ነውና) ሲል እመቤታችን ከመልአኩ ጋር ያደረገችው ምልልስ እንደ ዘካርያስ በመጠራጠር እንደ ኒቆዲሞስ በመከራከር ሳይኾን፤ ብልኅ ደቀ መዝሙር ምስጢር ለመረዳት ሲል ከመምህሩ ጋር ክርክር እንደሚያነሣ ኹሉ ድንግል ማርያም በማስተዋል እየጠየቀች መልአኩ እየመለሰ ብዙ ምስጢር በመገለጹ፤ በጥያቄዋ ለስዉሩ ምስጢር መታወቅ ምክንያት የኾነች መኾኗን አስተምሯል፡፡

ሔዋን ግን የሐሰትና የሞት መልእክትን ስትሰማ ለምን? እንዴት? ብላ ሳትጠይቅ ሐሰትን በማመኗ ፈጽማ ተወቃሽ መኾኗን ሊቁ ሲያነጻጽር፡- “Eve had not questioned the serpent when he led her astray…” ሔዋን እባብ ወደሞት ሲመራት ለምን? አላለችም ነበር፤ ነገር ግን በፈቃዷ ዝምታን መረጠች፤ የሚያባብል የተንኰል ቃልንም ሳትጠራጠር አመነች፤ ኹለተኛዋ ሴት (እመቤታችን) ግን የእውነት ቃል ከሚታመነው ሰማች፤ ቢኾንም ነገሩ የተረዳ እንዲኾንላት አጥብቃ ጠየቀች፤ የቀደመችው ሴት ሔዋን የዛፍን ፍሬ በመብላት አምላክ እንደምትኾን ሰማች፤ እንዴት ይኽ ሊኾን ይችላል? ብላ ግን አልጠየቀችም፤ ድንግል ማርያም ግን መልአኩ የእግዚአብሔር ልጅን እንደምትፀንስ በነገራት ጊዜ ግን የበለጠ እስክትረዳው ድረስ አልተቀበለችውም፡፡ አምላክ እንደምትኾን የአዳም ሚስት የኾነችው ድንግሊቷ ሔዋን ሳትጠራጠር የሐሰተኛውን ቃል ተቀበለች፤ የእግዚአብሔርን ልጅ ትፀንሳለች የተባለላት ግን መረመረች፣ ጠየቀች፣ ተማረች ግን ዝም አለች፤ ኹለተኛዋ ከመዠመሪያዋ ሴት እጅግ ውብ እንደነበረች አስተውሉ፤ ስለውበቷ ምክንያትም ጌታ መረጣት እናቱ እንድትኾን ዐደረጋት፤ ለእርሷ ዝም ማለት ቀላል ነበር ጥያቄ ማቅረብም እንዲኹ፤ ግን በማስተዋሏ ከመልአኩ የሰማችውን እውነት ዐወቀች ተረዳች፤ ሔዋን በምርጫዋ ተወቃሽ እንደኾነች፤ እንዲኹ ድንግል ማርያም በምርጫዋ የከበረች ኾነች፤ እንደመዠመሪያዋ ጥበብ ማነስ ኹሉ የኹለተኛዋ ጥበብ ተገለጠ፤ የመዠመሪያዋ ሴት ክፉን በፈቃዷ ስታመጣ እንዳላፈረችበት የኹለተኛዋ ስለ ወልድ በማሕፀኗ በግብረ መንፈስ ቅዱስ መፀነስ አላፈረችበትም፤ የቀደመችው ጥበብ እንደጐደላት ኹሉ ኹለተኛዋ ለሚያስተውል እጅግ ጥበብ የመላባት ኾነች፤ በቀደመችው የነበረባትን ዕዳ ኹሉ ይኽቺ ከፍላለችና፤ በቀደመችው ውድቀት፤ በኹለተኛዋ ትንሣኤ ለዘራችን ኹሉ ደረሰ፤ ኀጢአት በሔዋን ቢመጣም ጽድቅ ግን ከድንግል ማርያም ተገኘ፤ በሔዋን ዝምታ ኀጢአትና ውርደት፤ በእመቤታችን ማርያም መናገር ሕይወትና ብርሃን ከድል መንሣት ጋር ኾነ፤ እንዲኽ ብላ ለመልአኩ መለሰች “እንዴት የምትለው ይኾናል?” የወልድን ከሰማያት መውረድ በእርሷም የማደሩን አሠራር ገለጠላት፤ “የተባረክሽ ሆይ መንፈስ ቅዱስ ወደ አንቺ በክብር ይመጣል፤ የልዑል ኀይልም ይጸልልሻል” አኹን የምላስ ንግግር ኹሉ የማያስፈልግ ትርፍ ነገር ነው ስለሚያስደንቅ እምነቷ ካልኾነ በቀር ማንም አይናገርም) በማለት የመዠመሪያዪቱ ሔዋንና ዳግሚት ሔዋን የተባለች ቅድስት ድንግል ማርያምን በማነጻጸር ያስተማረው ትምህርት እጅግ አድርጐ የሚረቅ የሚያስደንቅ መኾኑን ከልብ እናስተውለዋለን፡፡