ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ኑሮ
የሰው ልጅ በተፈጥሮው ማኅበራዊ ፍጡር ነው፤ ማኅበራዊነት ከሌለ የዚህ ዓለም ጉዞውን በውጤት መፈጸም አይችልምና በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ታሳቢ በማድረግ የአካልና የአእምሮ ሀብታትን ተቀብሏል ። የሚያየው ነገር ባይኖር ዓይን አስፈላጊ እንዳልሆነ ሁሉ የሚሰጠው ሰው ባይኖርም እጅ አስፈላጊ አይሆንም ነበር ። ሕይወትን በነጻነት፣ ኑሮንም በቀላሉ ለመምራት የሚጠቅመው ማኅበራዊነት በግድ ሳይሆን በውዴታ የሚደረግ በረከት፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ።
ከማኅበረሰቡ የምንቀበለውና የምንሰጠው ነገር በመኖሩ እና የዚህ ዓለም መከራ ለሁሉም በአንድ ጊዜ የማይመጣ በመሆኑ ማኅበራዊነት መገለጫ መንገድ አግኝቷል፤ ሁሉም ሰው በአንድ ቀን ቢያገባ ደስታን የሚካፈል ፣ ሁሉም ሰው በአንድ ቀን ቢያዝን ኀዘንን የሚካፈል ወገን ባልተገኘ ነበር፤ እግዚአብሔር አንዱ ወገን ሌላኛውን ወገን ይረዳው ዘንድ አስጨናቂ ቀኖች በሁሉም ላይ በአንድ ቀን እንዳይወጡ ከልክሎአል፤ የአየር ትራፊክ አውሮፕላኖችን በተለያየ ርቀት ደርድሮ መንገድ እንደሚመራቸው ሁሉ እግዚአብሔር አምላክም እኛ በተለያየ ከፍታ ውስጥ እንድንጓዝ በማድረጉ ሕይወት አንድ ታላቅ እጅ የሚቆጣጠራት እንጂ እንዲሁ የተለቀቀች ስጋት አለመሆንዋን እንረዳለን፡፡
ቤተ ክርስቲያን በምሥጢራዊ ትርጓሜ የተቀደሰችና አንዲት ማኅበር ናት፤ ቤተ ክርስቲያንን ከማኅበራዊ ስብስብ ልዩ የሚያደርጋትም እግዚአብሔርን የበላይ በማድረግዋ ነው፤ ማኅበራዊነት አንድ ጉዳይን የበላይ የሚያደርግ ስብስብ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ግን ርእሷ አምልኮተ እግዚአብሔር ነው፤ የማኅበራዊ ኑሮ መነሻም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ጀማሪ እግዚአብሔር ነው ። ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ያመኑ ምእመናን የተጠለሉባት ጥላ ስትሆን ማኅበራዊነት የቀለም ወሰን ሳይኖርበት ሰው መሆንን ብቻ ማዕከል ያደረገ ነው፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ከሃይማኖት አጥር ውጭ ላሉትም ጭምር የእግዚአብሔርን ፍቅር የመግለጥ ተልእኮ አላት፤ በዚህም ርቀው ላሉት እግዚአብሔር ምን ያህል እንደሚወዳቸው ከቃል እስከ ተግባር ትሰብካለች ።
ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናት፤ እርሱም በአካሉ የሚሠራ አምላክ ነው፤ በቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ተግባራት ፣ መለኮታዊ ተአምራት ፣ ሕይወትን አድራሻ ያደረጉ ምሥጢራት ይፈጸማሉ ። ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻ ግብዋ ሰማይ ስለሆነ ሰማያዊት ተብላ ስትጠራ ስለ ምድርም ግድ ይላታልና የሰው ልጆች እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲቆሙ ትጨነቃለች፤ ስለ ለሰዎች ኅብረት ብቻም ሳይሆን ስለ አፍላጋት ጽኑ ልመና ታቀርባለች፤ እናት እንደመሆኗ ሕዝብ በቀጣይ ዓመት እንዳይራብ ስለ ዝናብ ትማልዳለች፤ በመዝሙራትና በትምህርትዋ አማካኝነትም ገበሬው ዘሩን በምስጋና እንዲዘራ በማነሣሣት ስንፍናን ትዋጋለች ።
የሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የመሠረተልን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ተዋሕዶ ለድኅነተ ዓለም በተገለጠበት ወቅት አንድ መቶ ሃያ ቤተሰብን እያስከተለ ያስተምርና ይመግብ ነበር፤ እርሱ የቤቱ ራስ፣ ሐዋርያት ተተኪ አባቶች፣ ቅዱሳት አንእስት እናቶች፣ ሰባ አርድእትም አጋዥ ልጆች ነበሩ። በዚህም የቤተ ክርስቲያን መነሻ ግላዊነት ሳይሆን ማኅበራዊነት መሆኑን እንረዳለን፡፡ ግላዊነት ሰይጣናዊ ፍልስፍና ሲሆን ማኅበራዊነት ግን የሰው የተፈጥሮውና የመንፈሳዊነት መልክ ነው ።
ዘመናዊው ዓለም ከጎረቤት በፍቅር የሚገኘውን ነገር ከሱቅ በገንዘብ የሚገኝ በማድረግ ሁሉን ነገር ሸቀጥ አድርጎት የሰው ልጆችን ተስፋ አስቆርጧል፤ ማኅበራዊነት ግን ሰው መምሰል ሳይሆን ሰው መሆን ነው፤ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ማዘኑ፣ በሰዎች መጠላቱ፣ የግፍ ፍርድ መቀበሉ እና የመሳሰሉት በኑሮአችን ውስጥ እንደ ገባ ማሳያዎች በመሆናቸው ማኅበራዊነት በክርስቶስ ተቀድሷል፤ ሕይወት ብርቱ ሰልፍ መሆኗም ለጎረቤታችን ያለንን ፍቅር ለመግለጥ መልካም አጋጣሚ ሆኗል ። እግዚአብሔር ከጨለማው ውስጥ ብርሃን ማውጣት እንደሚችል ለማስረዳት ሰዎች ስለ ወዳጆቻቸው ሲናገሩ ‹‹እገሌ እኮ የክፉ ቀኔ ነው›› ይላሉ፤ በዚህ መልኩ የገለጹትን ሰውም አንገታቸውን ለሰይፍ፣ ጀርባቸውን ለጅራፍ እስከ መስጠት ድረስ እንደሚወዱት ግልጽ በመሆኑ፤ በክፉ ቀን መልካሙ ፍቅር ይገለጣልና ማኅበራዊነት መሠረቱ እግዚአብሔር፤ የሚያድገውም በጉድለት ምክንያትነት እንደሆነ እንገነዘባለን ።
ቅዱሳን ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል ተልእኮ ወደ ዓለም በተሠማሩ ጊዜ ለማኅበራዊነት ትልቅ ዋጋ ከፍለዋል፤ ለዚህም ሦስት ነገሮችን መጥቀስ እንችላለን፡-
1- ማኅበረ እስጢፋኖስ
‘ወውእተ አሚረ በዝኁ ሕዝብ ወግዕዝዎሙ እለ እምአረሚ አርድእት ለአይሁድ እስመ ይሬእይዎን ለመበለታቲሆን እንዘ ኢይፀመዳ ኵሎ አሚረ ወያሰትታ ተልእኮቶን፡፡ ወጸውዕዎሙ ፲ወ፪ ለኵሉ ሕዝብ ወይቤልዎሙ ኢይደልወነ ከመ ንኅድግ ቃለ እግዚአብሔር ወንፀመድ ማእዳተ፡፡ ኅረዩ እምውስቴትክሙ ፯ ዕደወ እለ ምሉአን መንፈሰ ቅዱሰ ወጥበበ እለ ንሠይም ዲበ ዝግብር፡፡ ወንሕነሰ ንፀመድ ጸሎተ ወመልእክተ ቃሉ ወኀብሩ ኵሎሙ ሕዝብ፡-
በዚያም ወራት ደቀ መዛሙርት በበዙ ጊዜ ከግሪክ የመጡ ደቀመዛሙርት በአይሁድ ምእመናን ላይ አንጐራጐሩባቸው፥ የዕለት የዕለቱን ምግብ ሲያካፍሉ ባልቴቶቻቸውን ቸል ይሉባቸው ነበርና። ዐሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ሕዝቡን ሁሉ ጠርተው እንዲህ አሉአቸው። የእግዚአብሔር ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ አይደለም። ወንድሞቻችን ሆይ፥ ከእናንተ ወገን በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን ሰባት ሰዎችን ምረጡ፥ ለዚህ ሥራም እንሾማቸዋለን፤ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማስተማር እንተጋለን።” (የሐዋ. 6፡1-6) ።
ሰባት ዲያቆናት እንዲመረጡ ምክንያት የሆነው ፣ ሊቀ ዲያቆናት እስጢፋኖስንም በታላቅ ጸጋና በቀዳሜ ሰማዕትነት እንዲገኝ ያደረገው ማኅበራዊ ክስተት ነው ፡፡ በጊዜው ነዋሪና እንግዳ የሚል ልዩነት ተነሥቶ ፣ በማዕድም አድልኦ ተፈጽሞ ነበርና ሐዋርያት የምእመናንን ቅሬታ ለመስማትና ለመፍታት ዝግጁ ነበሩ፤ ነገር ግን ይህን ተግባር ሥራዬ ብለው ቢያከናውኑት የወንጌሉ ሥራ ሊቆም እንደሆነ ስለገባቸው ሌሎች ሊሠሩት የሚችሉት ተግባር ሆኖ ባገኙት ጊዜ ሰባት ዲያቆናትን ሾሙ ። ማኅበራዊ ደኅንነት የሚባለው ራሳቸውን ለመከላከል አቅም የሌላቸውን ሕፃናትን ፣ ሴቶችንና አረጋውያንን መከላከል ሲሆን የአንድ መንግሥት የመንግሥትነቱ መገለጫ አቅም የሌላቸውን መጠበቅ በመቻሉ ነውና በየትኛውም አገር የሚደራጅ መንግሥታዊ የጸጥታ አካል ለእነዚህ ወገኖች የደኅንነት ዋስትና ይሰጣል፡፡
በመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን አድልኦና ማግለል እንዲሁም መገለል ፈተና ሆኖ በተከሰተ ጊዜም የቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ ተልእኮ ሁሉንም በእኩል ማስተናገድ መሆኑን ተረድተው ዲያቆናትን ሾመዋል፤ ዛሬም ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያሉ ክስተቶች ሲነሡ ፈጥና ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ይገባታል ። የክርስቶስ መስቀል ልዩነትን ፣ በሰውነት ላይ ደረጃ የሚያወጣውን አስተሳሰብ አሸንፎ ሁሉንም በእኩልነት የምንመለከትበት ነው ።
2- የእርዳታ ተቋም
‹‹ወበእንተ አስተጋብኦሰ ለቅዱሳን በከመ ሠራዕክዎሙ ለቤተ ክርስቲያን ዘገላትያ ከማሁ አንትሙሂ ግበሩ፡-
“ለቅዱሳን ስለሚደረገው አስተዋፅኦ፥ በገላትያ ላሉት ምእመናን እንደ ደነገግሁት እናንተም እንዲሁ አድርጉ።” 1ቆሮ. 16፡1 ።
ሐዋርያትና ቅዱስ ጳውሎስ ከተግባራቸው መካከል ዋነኛው ድሆችን መርዳት ስለነበር የመጀመሪያው የእርዳታ ድርጅት ተመሥርቷል፤ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን አባላትም ንብረታቸውን ሸጠው ፣ በጋራ በመጠቀምና በአንድነት በመኖር እስከ ዛሬ ድረስ ለክርስቲያኖችና ለገዳማውያን ምሳሌ ሆነዋል ። የእኔ ንብረት የሁሉም ወገኔ ነው ብሎ ማሰብ ለክርስቶስ ፍጹም መሰጠትን የሚጠይቅ ነው፤ የራሱ ያልሆነውን በሚቀማው ዓለም ዘንድ ይህ ተግባር ሞኝነት ቢመስልም ለሥጋዊነት ብርቱ፣ ለመንፈሳዊነት ግን ቀላል ነውና የእርዳታ ድርጅቱ በችግር ላይ ወድቀው የተገኙትን፣ በስደት ምክንያት የተራቡትን ደጋግ አማንያን በዋናነት በመደገፍ አይሁድንና አሕዛብን ለማያስማማት ይጥር ነበር ። በዚህም ቤተ ክርስቲያን የመደጋገፍን ድልድይ ስትዘረጋ፣ የሚለያየውን ግንብ ደግሞ በእግዚአብሔር ቃል እያፈረሰች ከእኛ ዘመን ደርሳለች።
ሰዎች በትንሽ ነገር እንደሚጣሉ ሁሉ በትንሽ በጎነትም ፍቅርን ይመሠርታሉና ዛሬም የተጣሉትን ለማስታረቅ ፣ የተጎዱትን ለመካስ ፣ ያለቀሱትን ለማበስ እንዲህ ዓይነቱን መንገድ መጠቀም በእጅጉ አስፈላጊ ነው ።
3- ከሰዎች ጋር ያለውን ሰላም መጠበቅ፡-
‹‹ወእመሰ ይትከሀለክሙ ምስለ ኵሉ ሰብእ ተአኀዉ፡- ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።›› ሮሜ. 12፡18 ።
ሰው ከሰውና ከእግዚአብሔር ጋር በኅብረት የሚኖር ፍጡር ነው፤ አእዋፋት በመልካቸው ይበራሉ ፣ ወይም ከሚመስላቸው ጋር ይጓዛሉ፤ ሰውን የሚመስለው ግን ሰው ብቻ ነው፤ ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነትም እንዲሁ በቀላሉ የሚሳለጥ ካለመሆኑ በተጨማሪ ሥጋ፣ ዓለምና ሰይጣን ይረብሹታል ። ሥጋ ‹‹እኔ ብቻ›› ይላል፤ ዓለም ‹‹ብልጥ ሁን›› ትላለች፤ ሰይጣን ‹‹ሰው ጠላትህ›› ነው ይላል ። ከሰው ጋር መኖር ብዙ ዋጋ ቢያስከፍል እንኳ ከሰው ጋር አለመኖር ስለማይቻል እንደቅዱስ ቃሉ ከሰዎች ጋር በሰላም መኖር ብንችል እግዚአብሔር ይደሰታል፤ የአእምሮ ዕረፍትም እናገኛለን ።
ቤተ ክርስቲያን የማኅበራዊነት የጀርባ አጥንት እንደመሆኗ ማኅበራዊ ኑሮ ከተዳከመ ተልእኮዋ ስለሚቀዛቀዝ ከሰው ሁሉ ጋር ማለትም በቀለም፣ በሃይማኖት፣ በጎሣ ከማይመስሉን ጋር በሰላም እንድንኖር ትጥራለች፤ በየዕለቱ የምታስተላልፈው ምክሯም ውሉደ ክህነትና ምእመናን ለሰላም መሣሪያነት ይበቁ ዘንድ ነው ።
ማጠቃለያ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰው ልጆችን ደስታ፣ መከራና ኀዘን እየተካፈለች በዓለም ዘንድ የእግዚአብሔርን ፍቅር የምትገልጥ እንደመሆንዋ ከግላዊ አስተሳሰብ ይልቅ የጋራ የሆነ አመለካከት ለቤተሰብእ እና ለማኅበረሰብ ጠቃሚ መሆኑን ታስተምራለች፤ በክርስቶስ የተገለጠውን የእውነትና የነፃነትን መልእክት፣ የፍትሕና የሰላምን አስፈላጊነት በሰዎች ልቡና ለማስረፅም በስብከተ ወንጌል አገልግሎትዋ ታስተጋባለች፡፡
ዘመኑን በዋጀ አገልግሎት ተደራሽነትን የማስፋት ተስፋን ሰንቆ የሚበረታታ አፈጻጸም እያሳየ በሚገኘው የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በኩልም ኦርቶዶክሳዊ የሕፃናት አስተዳደግ፣ የወጣቶች መንፈሳዊ ሕይወት አጠባበቅ፤ የአረጋውያን እንክብካቤ፣ የመልካም ቤተ ሰብእ ግንባታ እና ምግባረ ሠናይ ላይ በትኩረት እየሠራች፤ ምእመናንንም እያሰናዳች፤ ሙሽራዋን ትጠባበቃለች፡፡
”ትሰግድ ለከ ቤተ ክርስቲያንከ፤ ወታሌዕለከ መርዓትከ፡-
ቤተ ክርስቲያንህ ትሰግድልሃለች፤ ሙሽራህም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፡፡‘
(ቅ.ቄርሎስ)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
አሜን፡፡
መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ (ቆሞስ)
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጸሓፊ
መስከረም 2018 ዓ.ም.
