ከግንቦት እስከ ግንቦት
አምና በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የግንቦቱን ርክበ ካህናት ጉባኤውን በሚያካሒድበት ወቅት አንዱ አጀንዳ አድርጎ የያዘው የጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ምርጫን ነበር።
በምርጫውም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በማድረግ በከፍተኛ ድምጽ መርጦ ሾማቸው።
ወዲያውኑም ሁለቱ ብፁዓን አባቶች ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አባታዊ ቡራኬና መመሪያን በመቀበል፣አስፈላጊና ውሳኔ የሚሹ ሥራዎችን በቋሚ ሲኖዶስ በማስወሰንና ውሳኔዎችን በጽኑ በማስፈጸም ሥራዎቻቸውን በውጤታማነት ለማከናወን ጥረት ማድረግ ሲጀምሩ አንድነታቸውንና ወንድማማችነታቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ ማጽናት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በማመን ተናበውና ተመካክረው ዘመነ ሢመታቸውን በስኬት ለመፈጸም ቆርጠው ተነሱ።
ይህንንም ለማድረግ በዕቅድ ላይ የተመሠረተ የትኩረት አቅጣጫን ነድፈው ዕቅዳቸውን ለማሳካት የሚያስችል የሥራ ኃላፋዎች ዝውውርና ምደባን በማድረግ የሚከተሉትን ጉዳዮች ለማሳካት በሙሉ ኃላፊነት ወደ ሥራ ሲገቡ መንፈሳዊ፣አስተዳደራዊና ልማታዊ የሥራ ዘርፎችን በውጤታማነት ለማከናወን የረጅም ጊዜ ልምዳቸው፣የመሪነት አቅማቸውና የማስፈጸም ብቃታቸውን በሚገባ ተጠቅመዋል።
በዚህም መሰረት ባሳለፍነው አንድ ዓመት ውስጥ በቤተክርስቲያናችን ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ውጤት ማስመዝገብ ቻሉ።
በመሆኑም በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አመራር ሰጪነትና ከፍተኛ ክትትል ከግንቦት እስከ ግንቦት ምን ውጤቶች ተመዘገቡ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እንችል ዘንድ ጥቂቶቹን ለማሳያነት ያህል እንደሚከተለው እናቀርባለን ።
1ኛ.ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋትና ለማጠናከር የሚያስችሉ በርካታ የውይይት መድረኮች ፣የሰባኪያነ ወንጌልን አቅም ሊገነቡ የሚችሉ ሥልጠናዎች፣የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ አገልግሎትን በማኅበራዊ ሚዲያ የማስፋፋት ሥራዎች ፣ለበርካታ ዓመታት ሳይሰበሰብ የቀረውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አንድ ፐረሰንት ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብም የመምሪያውን ገቢ የማሳደግና በበጀት ዕጥረት ምክንያት አገልግሎቱ እንቅፋት እንዳይገጥመው የማድረግ ሥራ፣ የስብከተ ወንጌል ስምሪትና የመምሪያውን ሥራ የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ ልዩልዩ ጥናቶችም ተደርገዋል።በመደረግም ላይ ይገኛሉ።
በሸገር ከተማና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ አህጉገረ ስብከት ደረጃ በብፁዕነታቸው አመራር ሰጪነት የተቋቋመው ወጣትነት ለቤተክርስቲያን በተሰኘው ማኅበር አማካኝነትም ታላላቅ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብሮችም ተካሒደዋል።
በአጠቃላይ በስብከተ ወንጌል ዘርፍ የተከናወኑና በመከናወን ላይ የሚገኙ ስኬታማ ሥራዎች በዘርፉ ቤተክርስቲያን የበለጠ ውጤታማ ሥራን ማከናወን እንድትችል የሚያደርጋት ነው።
2ኛ. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅትን አሠራር ማዘመን ይቻል ዘንድ ብፁዕነታቸው የሰጡትን አመራር ተከትሎ ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል።
በዚህም የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ ዘመናዊና ዲጃታል እንዲደረግ፣ድርጅቱ የራሱ የሆነ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲኖረውና በድርጅቱ የሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ በየጊዜውም ውጤታቸው ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ ተደርጓል፣የድርጅቱን ገቢ የሚጎዱና ግለሰቦችን የሚጠቅሙ የኪራይ አሰባሰብ ሥርዓቶችን በማስወገድ የቤተ ክርርቲያን ገቢ በአግባቡ የሚሰበሰብበት ሥርዓት ተፈጥሯል፣ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር የድርጅቱ ቢሮ በዘመናዊና የቤተክረስቲያናችንን ክብር በሚመጥን መልኩ እንዲታደስ ተደርጓል።
በአጠቃላይ በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃትና የሥራ ተነሳሽነት እንዲጎለብት፣አሠራሩ እንዲዘምንና ውጤታማ ተቋም እንዲሆን የማድረግ ሥራ በማከናወን ድርጅቱን ግንባር ቀደም የቤተክርስቲያናችን የልማት ተቋም ማድረግ ተችሏል።
3.ኛ እጅግ በጣም ለበርካታ ዓመታት ከዕቅድ፣ከፍላጎትና ከሥርጭት ጋር ሳይጣጣሙ በከፍተኛ ወጪ ታትመው የተከማቹ መጻሕፍቶችን የመለየት፣የማደራጀት፣
የማሰባሰብና የማሰራጨት ሥራ መላውን የቤተክህነት ሠራተኛን በማሳተፍ እንዲከናወን በማድረግ መጻሕፍቶቹ በጨረታ ተሸጠው የቤተክርስቲያን ገቢ በአግባቡ እንዲሰበሰብ፣መጻሕፍቱም አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የማድረግ ታሪካዊ ሥራ ተሰርቷል።
4ኛ.የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ታሪኮቿ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎችን፣ልዩ ልዩ ሃብቶቿን፣የቤተክርስቲያናችንን ሁለንተናዊና ተቋማዊ ሕልውናን የሚመሰክሩ ማኅደሮች በተበታተነና ለአያያዝ ምቹ ባልሆኑ ሥፍራዎች ተከማችተው ለአደጋ ተጋልጠውና ለመጥፋት ተቃርበው የነበሩ ሲሆን እነዚህን ፋይሎች በሚገባ ተለይተው፣ተደራጅተውና በዘመናዊ መልኩ ወደ ዲጂታል ፋይል ተቀይረው ለታሪክና ለትውልድ እንዲተላለፉ እንዲደረግ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የተሰጠውን መመሪያ ተከትሎ ፋይሎቹን ወደ ዲጂታል የመቀየሩ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ቀደም ሲል የቤተክርስቲያናችንን አሠራር ወደ ዘመናዊና በICT የተደራጀ እንዲሆን ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ ማስቀጠል እንዲቻልም ከፍተኛ ባለሙያዎችን የያዘ ኮሚቴ በማደራጀትም ትርጉም ያለው ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
5ኛ. ለበርካታ ዓመታት ሳይጸዳ የኖረው ለእይታ የማይመቸውና የቤተክርስቲያንን ክብርና ልዕልናን የማይመጥነውን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ቅጽር ጊቢ በሚገባ ጸድቶ፣አምሮና ተውቦ፣
ለዕይታ የሚማርክ፣የቤተክርስቲያንን ክብር የሚመጥን፣የሥራ ተነሳሽነትን የሚፈጥር፣ቅጽረ ጊቢ እንዲሆን ተደርጓል። የቅጽረ ጊቢው ማማር እጅግ በጣም ከፍተኛ በሆነ ወጪ በመገንባት ላይ ለሚገኘው ዘመናዊው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተጨማሪ ውበትን ያጎናጸፈ ሲሆን የዘመናዊ አዳራሽ ግንባታው አፈጻጸምም እስከዛሬ ከነበረው እጅግ በተሻለ ሁኔታና ፍጥነት መከናወን በመቻሉ እነሆ የማጠቃለያ ሥራ ላይ ይገኛል።
የግንባታ ሥራው ሙሉበሙሉ ተጠናቆ ሥራ በሚጀምርበት ወቅትም ታላላቅ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብሮችን በማከናወን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴዎችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ሀገራችን
የምታከናውናቸውን ዓለም ዓቀፋዊ ስብሰባዎችን ጭምር በማስተናገድ የቤተክርስቲያን እና የሀገር ኩራት የሚሆን ተቋም በመሆን እንደሚያገለግል ይታመናል።
6ኛ. ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ በነበሩ ጊዜ በተለምዶ አሮጌው ቄራ በመባል በሚታወቀው ቦታ ላይ በመሠራት ላይ የነበሩት ሁለት ግዙፋን ሁለገብ ሕንጻዎችም ትኩረት ሰጥቶ ለውጤት የሚያበቃቸው አጥተው ለበርካታ ዓመታት የቤተክርስቲያን ሀብት ሲባክንባቸው ከርመው በአሁኑ ወቅት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ በመሆን ዳግም ወደ አመራርነት ሲመጡ በልዩ ትኩረትና በፍጥነት እንዲሠሩ በመደረጋቸው እነሆ በአራት መቶ ሰማኒያ ካሬ ላይ ያረፈው ሕንጻ ግንባታ ተጠናቆ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት በደማቅ ሥነሥርዓት ለምርቃት ሲበቃ በአንድ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ሕንጻ ግንባታ ደግሞ የግንባታ ሥራው በመፋጠን ላይ ይገኛል።
©EOTC PR

