በበርካቶች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ድረ-ገጽ አገልግሎት ጀመረ
ሚያዚያ ፲፭ ቀን ፳፻፲ወ፰ዓ.ም.
ኢኦተቤክ ቤሕአልድ
አዲስአበባ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለዘመናት በመኳንንት፣ በወይዛይርትና በግለሰቦች አማካኝነት በውርስ፣ በኑዛዜና በስጦታ መልክ የተሰጧትንና በይዞታ አስከብራ ያቆየቻቸውን ቤቶች፣ ሕንፃዎችና ይዞታዎች ረጅም ዘመናት በድርጅቱ ባሳለፉ ቅን የድርጅቱ ሠራተኞች አእምሮ ከመያዝ ባሻገር የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲያውቁት በሚስችል መልኩ ተሰንዶ አለመቀመጡ ድርጅቱ በሥሩ የሚገኙ ደንበኞችን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚቸገር ከመሆኑም በላይ የሚባክኑ ይዞታዎች መኖራቸውን ይነገራል ።
ይህንን የተረዱት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪጅ ሊቀ ስዩማን እስክንድር ገብረክርስቶስ በድርጅቱ ሥር የሚተዳደሩ ቤቶች ፣ ሕንጻዎችና ይዞታዎች መላ ታሪካቸው ተመዝግቦና ተሰንዶ ለሚመለከታቸው አካላት ከማቅረብ ባሻገር በዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተጫኑ እንዲሰነዱ ለማድረግ ለድርጅቱ የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ክፍል ከማቋቋም ጀምሮ በመላው ዓለም ተዳራሽነቱን ለማስፋት የድርጅቱን ድረ-ገጽ ማበልጸግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ወደ ሥራ ተገብቷል።
በዚህ ሥራ ላይ ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ቆርጠው የተነሱ ቅን የቤተክርስቲያን ልጆችን በማስተባበር የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የሚል ድረ-ገጽ በልፅጎ በዛሬው እለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፤
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብጰት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንና የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣
ክቡር ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ የጠቅላይ ቤተክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ፤
ክቡር ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ባቱ የጠቅላይ ቤተክህነት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ፤ ክቡራን የጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎችና የየድርጅቶች ሥራ አስኪያጆች፤ ክቡራን እና ክቡራት የድርጅቱ ሠራተኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በታላቅ መንፈሳዊ ስነ-ስርዓት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
©የቤቶችና ሕንጻዎች ሚዲያ
