ዕቅበተ እምነት
በመምህር ሽፈራው
ምንነትና ይዘት
ዕቅበተ እምነት የሚለውን ተናባቢ የግእዝ ሐረግ፣ ሃይማኖትን መጠበቅ፣ መከላከል፣ ወይም የሃይማኖት ጥበቃ በሚል የአማርኛ ቀጥተኛ ፍቺ ይታወቃል። ዕቅበተ እምነት ሁለት ተናባቢያን ቃላት፣ ከሁለት የተለያዩ የግእዝ ግሶች የተገኙ ዘሮች ናቸው። እነዚህም፦ አንደኛው “ዕቅበት”፣ መጠበቅ፣ ጥበቃ፣መከላከል ፤ “ዐቀበ”፣ ጠበቀ ከሚለው ግስ የተገኘ ነው። ሁለተኛው “እምነት”፣በቁሙ ሃይማኖት፣ ማመን፣ መታመን፣ መቀበል፣ ተስፋ ማድረግ ሲሆን ግኝቱም፤ “አምነ”፣ አመነ፣ተቀበለ፣ተስፋ አደረገ ከሚለው ግስ ነው።
ይሁን እንጂ ዕቅበተ እምነት በክርስትና ነገረ መለኮት ዓውድ ሲተረጐምና ሲታይ ሰፋ ያለ ይዘትና መልክ አለው። ይህም፦ ዕቅበተ እምነት በተግባራዊ የክርስትና ነገረ መለኮት ከሚመደቡት ከነገረ መለኮት ጥናት ዘርፎች መካከል አንዱ ነው።
የትምህርቱ ይዘትም በመሠረታዊ የክርስትና እምነትና ትምህርት ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎችና ነቀፋዎች (ሒሶች) የእምነትን ድንበር ሳያልፍ፤ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መልስን ለመስጠት፤ ዐቃቢያነ እምነት በከፍተኛ የነገረ መለኮት ተቋማት ገብተው በሥርዓት የሚማሩት፣ ሥነ ጥበብንና ዕውቀትን በአንድነት አጣምሮ የያዘ የትምህርት ዓይነት ነው። ዕቅበተ እምነት በአጭሩ ሲገለጽ በሃይማኖት ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎችና ሒሶች መልስ በመስጠት መጠበቅን (መከላከልን) የሚያመላክት ተግባር-ተኮር ትምህርተ ክርስትና ነው።
ትምህርተ ዕቅበተ እምነት ዐቃቢያነ እምነትን ብቁ ለማድረግ በኢአማንያንና በተጠራጣሪዎች የሚነሡ ጥያቄዎችንና ነቀፌታዎችን መልስ በመስጠትና በማረም፤ ትምህርተ ክርስትናና እምነትን እንዴት እንደሚጠብቁና እንደሚከላከሉ ይዘቱንና መንገዱን በመፈተሽ በተግባር፤ መንገደኞች (ተከታዮች) ዐቃቢያነ እምነት አቅጣጫቸውን ለማመላከት መንገዳቸው (ቃለ ወንጌል፣ክርስቶስ) ላይ የተተከለ ደማቅ መብራት ይመስላል። ዐቃቢያነ እምነት፣ ዕቅበተ እምነት በሚለግሳቸው ዕውቀትና ጥበብ በመጠቀም፣ የሥነ አመክንዮ ሕግጋትን ሳያፋልሱ፣ መልስ መስጠትን በሚሠለጥኑበት ጊዜ የሚከተሉትን ዋና ዋና የኢአማንያና ተጠራጣሪዎች ጥያቄዎቻቸውንና ነቀፌታዎቻቸውን ከነህጸጻቸው (ጉድለታቸው) በጥልቀት በመመለስና በማረም ብቃትን ይይዛሉ። ተገቢ ምላሽና እርምት ከሚያገኙ ጥያቄዎችና ነቀፌታዎች መከካል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ፦ ፍልስፍናዊ ይዘት ካለቸው ፣ እግዚአብሔር አለን? ካለ እንዴት ክፋት ምድር ላይ ኖረ? ከሞት በኋላ ሕይወት አለ? በሕይወት የመኖር ዓላማው ምንድን ነው?… እንዲሁም ነገረ መለኮታዊ ይዘት ከቋጠሩት መካከል፣ ተአምራት መከናወን ይችላሉን? ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቷልን? እውነተኛ ሃይማኖት ክርስትና ባቻ ነውን? ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ብቻ ነውን? ምክንያትና እምነት ይጣላሉ? ወይስ ይዋደዳሉ? የአንድን ደርጊት ሠናይነትና እኩይነት የሚለካው በመገለጥ ላይ በተመሠረተ ሥነ ምግባር መርህ ወይስ በምክንያታውነት ላይ ትኩረት ባደረገ ሌላ መርህ? ወዘተርፈን ያካትታል።
አመጣጥና ምክንያት
እይታቸው እንደየሁኔታው ሊጠብም ሊሰፋም ይችል ይሆናል እንጂ፤ ሰዎች ሁሉ ሕይወትን የሚያዩበት ውስጣዊ መነጽር ገንዘብ ያደረጉ ፍጡራን መሆናቸው በአሳብያን ሰዎች ዘንድ ፈጽሞ ሊካድ የሚችል እውነታ አይደለም። በሂደት እይታቸው ወደ እምነት አቋምነት ያድግና ከሌላው የሚለዩበት የማንነታቸው መገለጫ ሆኖ ይከሠታል። ይህ አቋማዊ ክሥተት ከሌሎች ሰዎች ጋራ በሚኖራቸው ዕለታዊ ግንኙነትና እንቅስቃሴ ምክንያት፤ ያመኑትን ሐቅ ለማስረዳትም፤ የያዙትን አቋም መነሻ አድርገው አድማጮች ለሚያቀርቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠትም ሲነሡ፤ ሥነ አመክንዮአዊ ሕግጋትን መጠቀማቸው የማይቀር ተግባር ነው። የያዙትን እውነት፣ እምነት (አቋም) ሌላውን ለማስረዳት ዕቅበተ እምነት ውስጥ ያሉትን ሁነኛ መርኆችንና መንገዶችን ይጠቀማሉ። ስለዚህ ዕቅበተ እምነት ለሐሳባቸው ማስተላለፊያ መሣሪያ ሆኖ አገለገለቻው ማለት ነው።
ዕቅበተ እምነት ከሚገለጽባቸው ሕዝባዊ ተቋማት አንዱና ዋነኛው ፍርድ ቤት አደባባይ ነው። ዳኞች፣ ዐቃቢያ ሕጎችና ጠበቆች ጉዳያቸውን ይዘው ዳኞች ፊት ሲቀርቡ፤ የዳኞችን የውሳኔ ሐሳብን ለማስለወጥ ለዕቅበተ እምነት አገልግሎት ወሳኝ ሚና የሚጫወተውን የሥነ አመክንዮ መርኆችንና መንገዶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የውዴታ ግዴታ ይሆንባቸዋል። አብነት ለማቅረብ፦ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ469-399 ዓ.ዓ መኖሩን የተነገረለት የግሪክ ፈላስፋ ተከሶ ፍርድ ቤት በቀረበበት ጊዜ በዳኞች ፊት ቀርቦ ሲከራከር (ሲሞግት) ለዕቅበተ እምነት (አቋሙን ለመከላከል) የሚያገለግለውን ሥነ አመክንዮ መርኆን አሳማኝ በሆነ መንገድ ተጠቅመዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን ከሶቅራጥስ በአንዳንድ ነገሮች ስምምነት ያልነበራቸው የንግግር ጥበብ መምህራን፣ ሶፊስቶቸ በየፍርድ ቤቶች አካባቢ የሥነ አመክንዮ መርኆችን በሕዝቡ ዘንድ ልማድ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርገዋል። በተጨማሪም በሃይማኖት ታሪክ ሰፍረው የምናገኛቸው የሃይማኖት የዜና መዋእል ድርሳናትና ገድላት በግልጥ የሚመሰክሩት እውነት፣ የሃይማኖቱ አስተማሪዎች መሠረታዊውን እምነትና ትምህርት ለተከታዮቻቸው ያስረከቡበት ባህል ዕቅበተ እምነት ትምህርት ባቀረባለቸው ጥበብና ዕውቀትን ዋቢ በማድረግ (በመጠቀም) ነው።
በቤተ ክርስቲያን የእምት አባቶች ታሪክና ሥራ (ነገረ አበው) ምሥከርነት፣ 2ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያን ዐቃቢያነ እምነት የታዩበት ዘመን ነው። ዓላማቸውም የአሕዛብን ነገሥታትንና ሕዝቦቻቸውን (ተከታዮቻቸውን) በክርስትናና በክርስቲያኖች ላይ የነበራቸውን የተንሸዋረረ እይታን በጽሑፍና በቃል ሞግቶ ማስተካከል ነበረ። በዚሁም ተግባር ዐቃቢያነ እምነት ያለ ፍርሃት ለአሕዛብ ነገሥታትና ሕዝቦቻቸው (ተከታዮቻቸው) ክርስትና በፖለቲካ ላይ ምንም ጉዳት የማያመጣ ፤ በግብረ ገብነትና በባህል ትምህርቱ ከአረማውያን (አሕዛብ) የተሻለ መሆኑን በዕቅበተ እምነት እንቅስቃሴዎቻቸው በግልጽ አስመስክረዋል። በቤተ ክርስቲያን ታሪከ ጐልተው ከሚነሡ ዐቃቢያነ እምነት መካከል፦ ኳድራተስ፣አሪስቲደስ፣ጀስቲን ዘማርቲር፣ቴሻን… ወዘተርፈ ናቸው። የክርስቲያን ዐቃቢያነ እምነት ዋናው ፍላጎታቸው ግልጽ ነው። በሐሳብና እምነት ዓውደ ውጊያ (ሐሳብንና እምነትን በፍቅር መወያየት) ፍልስፍናን በራሱ መሣሪያ (ምክንያታዊነት) በክርስትና ግዛት ሰማይ ሥር ምርኮኛ እንዲሆን ማድረግ ነበር።
በተለያዩ ሰዎች የቀረቡ የስሕተት ትምህርቶችን ለማረም የተካሔዱ ዓለም አቀፍ 0በይት የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት (በ325 ዓ.ም በኒቅያ፣ በ381 ዓ.ም በቁስጥንጥንያ፣ በ431 ዓ.ም ኤፌሶን) በዐቃቢያነ እምነት አማካኝነት ዕቅበተ እምነትን የተገለጸባቸው ጉባኤያት ናቸው።
ወደ ኋላ መለስ ብለን የአገራችን ታሪክ ስንቃኝም በትምህርተ ሃይማኖት አቋማቸው ልዩነትን ያንጸባረቁ የእምነት አባቶች፤ ልዩነቶቻቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሙግትን (ክርክርን) በጉባኤ የማቅረቡ ልማድ (ባህል) እንደነበረን ያሳየናል። ይህም በካራና በጸጋ መካከል በታየው የትምህርተ ሃይማኖት መለያየት፣ በ1870 ዓ.ም ቦሩ ሜዳ ላይ ከሁለቱም የእምነት አቋሞች ተወከለው የቀረቡ ዐቃቢያነ እምነት ዕቅበተ እምነታቸው በጉባኤ መካከል ሰላማዊ ክርክር (ሙግት) ማድረጋቸው በአገራችን የታሪክ ጽሑፋት በታሪክነቱ ሰፍሮ ይገኛል።
ሰዎች በሕይወት ጉዞቸው አንድም ከአእምሯቸው ሁለትም ከነፍሳቸው የሚመነጩ መሠረታውያን ሕይወት-ተኮር ጥያቄዎች ይገዳደሯቸዋል። ሰዎች ከጥያቄዎቹ የሚነሡ ተግዳሮቶቻቸውን ለመቋቋም (የጥያቄዎቻቸውን መልሶች ለማግኘት) በግልም ሆነ በኅብረት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። በዚህ ሰዓት የጥያቄዎቹ ምላሾች ሳይገኙ ሲቀሩ ጠያቂዎች በሕይወታቸው የሥነ ልቡና፣ የመንፈስ፣ የዕውቀትንና የግብረ ገብ፣ እንዲሁም የማኅበራዊ ሕይወት ግንኙነት አለመረጋጋት (ቀውስ) ይታይባቸዋል። መሰል ችግር በማኅበረ ሰቡ ዘንድ ሲታይ ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ዐቃቢያነ እምነት ግንብር ቀድም ተዋናዮች (ተሳታፊ) በመሆን ዘመን አይሽሬ የዕቅበተ እምነትን ፋይዳ ያስገነዝባሉ።
አምላካዊ ትእዛዝ
አንደኛው፣ ከግእዘ (ባሕርየ) ሰብእ የሚነሣ ትእዛዝ ነው። ሰዎች ባለ አእምሮ ፍጡራን መሆናቸው አስቀድመን ባነሣናቸው ሓሳቦች ተጠቅሷል። ስለዚህም አእምሯቸው ምክንያታዊ በሆነው መንገድ ሐሳቦችን ያስባል፤ ያደራጃልም። ሐሳቦቻቸውም የሥነ አመክንዮ ሕግጋት የሚያቀርቡላቸውን ማዕቀቦች በጽናት ተቋቚመው በማለፍ ለአቅመ ነጽሮተ ዓለምና እምነት ሲደርሱ፤ ከአድናቂዎቻቸውም ይሁን ከነቃፊዎቻቸው ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠትንና የማስረዳትን ኀላፊነት በላያቸው ላይ ይወድቃል። እንደዚህ ያለውን ክስተት በልዩነት ሰው ላይ ብቻ የሚንጸባረቅ ደማቅ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ይህም ለሰው ልጅ ኅሊና የሚመለከትና በሰው ልጅ ኅሊና መልስ የሚሰጥበት ነው።
ሁለተኛው፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት ምሥክርነት የሚመነጭ ትእዛዝ ነው። ሐዋርያትን የተከተሉ ጥንታውያን ዐቃቢያነ እምነት፣ በጽሑፋትና በቃላት መያዣዎች የቀረቡ የዕቅበተ እምነት መልካም ዘሮች በተከታዮቻቸው ማሳ ልብ ውስጥ ዘርተው አልፏል። ይህ መልካም ተግባር በአበው ገድላትና ጽሑፋት በሰፊው ተመዝግበው ይገኛሉ። ተግባራቸውም ልበ ሰማዕያንን አበርትቷል። በተመሳሳይ ይዘትና መንገድ በአሁኑ ዘመን ባሉት ዐቃቢያነ እምነት ምላሽ የመስጠቱን ተግባር በመቀጠል ላይ ይገኛሉ። ለዚሁ ተግባር አንቀሳቃሽ ሞተር ዘፈቀዳዊ የግል ስሜት ሳይሆን አምላካውያት መጻሕፍት ውስጥ በሚገኝ ግልጽ መለኮታዊ ትእዛዝ (ኀላፊነት) መሠረትነት ነው። ይህም በ፩ጴጥ.፫፥፲፭ እንዲህ ተጽፎ እናገኘዋለን፦ “በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።”
ዓውደ ንባቡን ሳንለቅ የጥቅሱን ቃላት በትኲረት ከተገነዘብናቸው መልእክቱ በዘመኑ ለነበሩና ተከትለው ለሚመጡ አድማጮችን ትኩረት ያደረጉ፣ ትላልቅ ቊም ነገሮችን ያስተላልፋል። ግዚያዊ አድማጮች ማለትም ቅዱስ ጴጥሮስ መልእክቱ የጻፈላቸው፣ በዘመኑ በግሪካውያንና ሮማውያን ዘንድ በክርስቶስ ምክንያት መከራ ሲደርስባቸው ለነበሩ ለእስያ ክርስቲያኖች የሚያመላክት ነው። ነገር ግን ሐሳቡ ጊዚያዊ አድማጮችን ተሻግሮ ለዘለቄታዊ አማኞች (ለመጭዎቹ አደማጮች) የተጻፈ መሆኑን ከሚያመላክቱን የጥቅሱ ሐረጋት፦ “ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ” እና “ዘወትር የተዘጋጃችሁ” የሚሉትን ናቸው። ስለዚህ ቃሉ አሁን ላለን ክርስቲያኖች የተነገረ አምላካዊ ኀላፊነት መሆኑን ያስታውሰናል።
አማኞች ለክርስቶስ ካላቸው ጥልቅ ልባዊ ፍቅር ባገኙት ድፍረት ምክንያት በመከራ መካከልም እንኳን ቢሆኑ ለመመሥከር ወደ ኋላ ማለት እንደሌለባቸው የመልእክቱ ሐሳብ ይገልጻል። ቀረብ ብለን የጥቅሱን ማእከላዊ ሐሳቦች ስንመረምር በሕግ አግባብ ውንጀላን (ክስን) መከላከልና መልስ መስጠትን የሚመለከት ትርጉም አለው። ይህም አግባብነት ወደ አለው የሙግት አቀራረብና ሥነ ሥርዓት ዕውቀት ይመራናል።
ክርስቲያናዊ ዕቅበተ እምነትን በሚመለከት በተቀራራቢ ትርጉም በማስረጃነት ሥራ ላይ የዋለባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍላት የሐዋርያት ሥራንና የሐዋርያው ጳውሎስ መልእክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ለጊዜው እንመልከት። ይኸውም፦ አንደኛው ምሥክርነት በሐዋ. ሥራ ፳፭፥፲፮፣ “እኔም፦ ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ለፊት ሳይቆም ለተከሰሰበትም መልስ ይሰጥ ዘንድ ፈንታ ሳያገኝ፥ ማንንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት አይደለም ብዬ መለስሁላቸው።” እና በሐዋ. ሥራ ፳፮፥፪-፫፦ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ የአይሁድን ሥርዓት ክርክርንም ሁሉ አጥብቀህ አውቀሃልና በአይሁድ በተከሰስሁበት ነገር ሁሉ ዛሬ በፊትህ ስለምመልስ ራሴን እጅግ እንደ ተመረቀ አድርጌ እቈጥረዋለሁ፤ ስለዚህ በትዕግሥት ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።” ሲሆን ሁለተኛው ምሥክርነት ደግሞ በ፩ቆሮ.፱፥፫-፬፣ “ለሚመረምሩኝ መልሴ ይህ ነው። ልንበላና ልንጠጣ መብት የለንምን?”ለተጠየቅሁት መልሴ ይህ ነው ብለን አቋምን የምንገልጸው ቃል ነው። ለምንጠየቀው መልሴ ይህ ነው ብለን አቋማችንን የምንገልጥበት ቃል ነው።
ከርስቲያኖች እምነታቸውን (በክርስቶስ ላይ ያለቸው አቋም ሲገልጹ) ሲከላከሉና ሲያብራሩ በየዋህነትና በፍርሃት መሆን እንዳለበት የመልእክቱ ጥቅስ በ፩ጴጥ.፫፥፲፭፣ ይህንንም፦ “ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።” በማለት የአቀራረብን ሥነ ሥርዓት እንዴት መሆን እንዳለበት እውነት ፈላጊ ተዋያዮችን ያስገነዝባል።
አቀራረብና መፍትሔ
የዕቅበተ እምነት ትምህርት፣ እምነታችንን ለመከላከል ሙሉ ዕውቀት መኖሩን (መያዛችን) ባቻ ሳይሆን እንዴትም ማቅረብ እንዳለብንም ያስተምረናል። በተለይ በክርስትና እምነት ሰዎች ወደ ክርስቶስ ሊመጡ ከሆነ መጀመሪያ እንደጋሬጣ ሁኖ ከልክሏቸው ያለውን ድንጋይ መጀመሪያ መጠረግ አለበት። ዘለን ስለ ክርስቶስ ከማስተማራችን በፊት መጽዳት ያለባቸው ያልጠሩ ሐሳቦች ከሰዎች አእምሮ ውስጥ መጠረግ አለባቸው።
በክርስትና ያለው እምነት በፍቅር የሚሠራ እምነት ነውና የሐዋርያው ጳውሎስ መልእክት ወደ ገላትያ ሰዎች ምዕራፍ ፭ ቍጥር ፮ በአስቀመጠው መንገድ ፦”በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና።” እውነቱን በፍቅር አለዝበን ተከራካሪውን በጨፍን ስሜት ድል ለመንሳት የሚለው መንፈስ አስወግደን፣ያለ ማጨበርበርና ያለ መሸንግል ክርስቶስ ለእርሱ ሲል እንደሞተለት ማስረዳት ነው። ሌላኛው ምክርና መመሪያም በውይይታችን ጊዜም ይሁን በሌላ የሰዎችን እምነትና አመለካከት ማንቋሸሽና ማጥላላት ከዕቅበተ እምነትና ሥነ አመክንዮ ሥነ ሥርዓት ያፈነገጠ መሆኑን በተዘዋዋሪ መንገድ፣ ፩ተሰ.፩፥፭፦ “ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ።” ሲል ያስረዳናል። ከዚህ ጥቅሱ መረዳት የምንችለው በሙግት ጊዚያት ተሟጓቾች ሐሳባቸውን ሲያቀርቡ፣ የሐሳባቸው መልእክትና አካሄድ ቃል (ምክንያት)፣መሠጠትና ግብረ ገብ ያጠቃለለ መሆን አለበት።
በሥነ አመክንዮም ታየ በዕቅበተ እምነት፣ የሥነ አመክንዮ ህጸጸታትን ተጠቅመን እውነትን ለመግለጥና ተቀባይነትን ለማግኘት መሞከር ፍጹም ስሕተት ነው። ዐቃቢያነ እምነትና ተከራካሪዎቻቸው መከተል ያለባቸው አንዱና ዋነኛው አሰረ ፍኖት ሰዎች ክርስቶስ እንደሞተላቸው በትሕትና ማሳየት ነው።
የተነሣንበትን ርእሰ ጉዳይ ስንቋጭ፣ ዕቅበት እምነት በቀጥታ ፍቺ (ብይን) ሲሰጠው ሃይማኖትን (እምነትን) መጠበቅ ነው። ተግባራዊ ነገረ መለኮት ምድብ ውስጥ የሚመደብ፣ ዐቃቢያነ እምነት በነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች በጥልቀት የሚማሩትና የሚሠለጥኑት ነው። ዕቅበት እምነት አስፈላጊ መሆን የቻለበት ዋና ምክንያት በአማንያን በኢአማንያን ሰዎች በሚነሡ በአእምሮና በነፍስ ዙሪያ በሚፈጠሩ ጥያቄዎች ናቸው። ዕቅበት እምነት ተግባር-ተኮር ትምህርት በመሆኑ ሥራ ላይ ሲውል የሥነ ምግባርን መርኆዎችን ይከተላል። ታሪካዊ አመጣጡም በተመለከተ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መነሻ አድርጎ ወደ አባቶችና አሁን ስካለን አማኞች ደርሷል። የዚህ ትልቅ ተልእኮና ኀላፊነት ሰጪውና የበላይ ጠባቂው አምላክና የሰዎች ኅሊና ናቸው። መገለጥን (ቅዱስ መጽሐፍን) መነሻ ያደረገ እምነትና ሕይወት በአንድ ጎን፣ በሌላው ደግሞ ምክንያታዊነትና ነባራዊ ሐቅ በማጣርያ መሣሪያ ተፈትሸው በቅብብሎሽ መልክ አሁን ላለነው ትውልድ የተቀበልነውን እውነታ በጥያቄና ሒሶች የበረዶ ዶፍ ሲወርድነት ኅሊናንና አፍን ለጉሞ መቀመጥ ለክርስትናውም ለሀገርም ከፍተኛ ጉዳት የሚያመጣ ተግባር ነው። ስለዚህ በአማንያንና በኢአማንያን ለሚነሡ ጥያቄዎች ቤተ ክርስቲያን በዐቃቢያነ እምነት ምሁራኖቿ በኩሉ ተገቢውን መልስ መስጠት ይኖርባታል። ዓላማውም፦ “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን።”፪ቆሮ.፲፥፭።
ራሱ ኑና እንዋቀስ ብሎ የመነጋገርን በር ለከፈተልን አምላክ ክብር ምስጋና ይግባው!
መምህር ሽፈራው
