በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በተደረገው ስምሪት በጎፋ ሳውላ ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና እና የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ተጠናቀቀ!!

ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም
ስ/ወ/ሐ/ተ ሚዲያ /አዲስ አበባ/
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ካለፈው የካቲት 26 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ በተመረጡ 32 አህጉረ ስብከት ሲያካሂድ የቆየው ስምሪት በአብዛኛው አህጉረ ስብከት እጅግ ስኬታማ በሆነ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን በቀሪዎቹ ደግሞ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ስምሪቱ በዋናነት ትኩረት ያደረገው ምዕመናንን በሃይማኖታቸው ለማጽናት፣ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ለማስፋፋትና ወንጌል በስፋት እንዲደርስ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ቀደም ሲል ተገልጿል።
ከሚያዝያ 12 እስከ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት ቀናትም በጎፋና ባስኬቶ ሳውላ በጋሞና አካባቢው አርባ ምንጭ አህጉረ ስብከቶች ለአህጉረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ ካህናትና ለ/ሰ/ት/ ቤት ወጣት ተወካዮች በመ/ሐ ቃለ ጽድቅድ አሰፋ እና በመ/ር ዘማርያም ጌጡ ፦ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ፣ዕቅበተ እምነት ፣የወንጌል አገልግሎታችንና የቤተክርስቲያን ታሪካዊ ጉዞ በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሥልጠና ተሰጥቷል።
በመጨረሻ በአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በተሰጠው መልእክት ስብከተ ወንጌልን ማጠናከር ሥራ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ባለ ድርሻ አካላት መሆኑን ተገልጾና መመሪያ ተላልፎ ሥልጠናው ተጠናቋል።
©የመረጃው ምንጭ ጎፋ ሳውላ ሀገረ ስብከት