የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርቲያን ታሪክ

መግቢያ

ታሪክ ኃላፍያት የሚጠኑበት የትምህርት ዘርፍ ነው። በታሪክ ውስጥ ያለፉ የምንላቸው ክስተቶች ጉልህ ትርጉም ይዘው ነገ ልንደርስበት ከምናስበው መዳረሻ አንጻር ይገመገማሉ። በተፈጥሮ ሥርዓት፣ በባህላዊ መስተጋብር፣ በሃይማኖት ትምህርት፣ በሥልጣኔ መሠረቶች ምርመራ፣ በውድመትና ኪሣራዎች ግምገማ፣ እንዲሁም በሌሎችም የሕይወት ክፍሎች ታሪክ መሠረታዊ ሚና አለው። በትናንትናው ስኬት መሠረቶች ላይ ቆመው ስለነገ የሚያልሙ ሰዎች በታሪክ ተጠቃሚ ይኾናሉ። የዚህኑ ያህል፤ ካለፉት መንገዶች የማይማሩ ደግሞ ስሕተቶችን ሲደጋግሙና ሲጎዱበት ይኖራሉ። History is a study about past events, a period in time and space; history of individuals, institution, places, countries …

ታሪክ በኃላፊ ጊዜ ውስጥ የተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ የተመሠረተ እውነታን የያዘ ነው። የታሪክ ትምህርትም ያንን እውነታ የመፈለግ ጉዞ ነው። ነገር ግን በታሪክ ጸሐፊዎችና መምህራን የተለየ ፍላጎትና ሥውር አጀንዳ ታሪክ ከእውነታው አፈንግጦ ሊነገርም ሆነ ሊጻፍ ይችላል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ለዚህ ምሳሌ መሆን የሚችሉ በርካታ ስመ ታሪኮች ወይም የፈጠራ ትርክቶች አሉ፡፡ “. . . የኢትዮጵያን ታሪክ ጻፍን እያሉ በሐሰት የኢትዮጵያን ታሪክ አጥፍተውት በዓለም ባለታሪኮች ዘንድ ስለተዘራ ይህን የሐሰት ስብከት ሳያስቡና ሳይጠረጥሩ የኢትዮጵያ ተወላጆችም ከዓለም ባለታሪኮች እየተቀበሉ . . .”[1] በማለት የሚያስረዱን በጎ ሊቃውንም አሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ ከሚገኙ ጥቂት ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያን መካከል አንዷ ናት፡፡ ይሁን እንጂ ታሪኳ በአግባቡ ተጽፎና በምምህራን ተዘጋጅቶ ቀርቦ ትውልድ የሚጠቀምበት ሁኔታ ላይ መሥራት ብዙም አይስተዋልም ይልቁንም ከላይ እንደተጠቀሰው ታሪኳ በተለያየ መንገድ እየተበረዘ ከመሠረቱ የተለየ ሆኖ ሲተረክ ኖሯል፡፡ ምሥራታዋን በተመለከተ እንኳን ከአንደኛ ወደ አራተኛ ክፍለ ዘመን ተስቦ ይጻፋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ለ1600 ዘመናት ያህል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት ተቋም ሆና ኖራለች። በእነዚህ ዘመናት ውስጥ የኢትዮጵያ ባህል የሚጠበቅባ ማዕከል፣ የትምህርት ሥርዓትና ሂደት የሚቀረጽባትና የሚተላለፍባት ማዕከል (በዛሬው አጠቃቀም የትምህርት ሚኒስቴር)፣ የሀገር ቅርስ የሚሠራባትና የሚጠበቅባት ተቋም፣ ወዘተ. ሆና ስታገለግል ኖራለች፡፡

“The Church of Ethiopia has been the repository of Ethiopian culture for the last 1600 years of her existence. The monasteries and churches have been not only places of ascetic life but also prominent centers of learning. ..”[2] በእነዚህ ዘመናት ውስጥ የነበሩ ስኬቶች፣ ፈተናዎች፣ እና ሌሎችም የታሪኩን ቤተ ክርስቲያናዊና ሀገራዊ ተያያዥነት የሚጠቁሙ ናቸው።

የታሪክ ጥቅም

በኦርቶዶክሳዊ ክርስትና ሕይወት ውስጥ ታሪክ ከፍተኛ ጠቀሜታ ካላቸው ጉዳዮች ይመደባል። ትክክለኛና ተገቢ የሆነ አረዳድ እንዲኖረውም ይመከራል። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሃይማኖትን ከመሠረተ እምነቱ ጀምሮ የሐዋርያዊ ቅብብሎሹን ሂደትና በዘመን ያጋጠሙ ፈተናዎች የታለፉበትን ሁኔታ ጠንቅቆ ለመረዳት የሚያስችል ታላቅ አስተዋፅኦ አለው። (Alexander Shememann, The Historical Road of the Eastern Orthodoxy, 2003, 3) ቤተ ክርስቲያን ያለፈችባቸውን የታሪክ መስመሮች ለይቶ ያወቀ ሰው በዛሬ ሕይወቱ እንቅስቃሴዎች ሁሉ አብነቶች አሉት። እውነተኛውን ታሪክ በፈጠራ ከሚነገሩት ለይቶ ለመጠቀም ዕድል ያገኛል፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ታሪክን በልዩነት አክብረው የሚመለከቱበት ምክንያትም አርአያነት ያላቸውንና በሕይወት የቀደሙ ምስክሮችን ማግኘት የሚቻልበት ስለሆነ ነው። ከእኛ የቀደሙ አበው የሠሯቸውን ሥራዎች፣ ተገድሏቸውንና የቅድስና ሕይወታቸውን መማር የምንችልበት ታሪክ ነው (Timothy Ware, The Orthodox Church, 2015, 1.) “The study of history is the best medicine for a sick mind” [የታሪክ ጥናት ለሕመምተኛ አእምሮ ፍቱን መድኃኒት ነው] (Livy/ሊቪ)።

ታሪክ ከማንነት ግንባታ መሠረቶች አንዱ ነው፡፡[3] ፕሮፌሠር ጌታቸው ኃይሌ ይህንን በተመለከተ ከጻፉት ብናነሣ፤ ደግሞ የሚከተለውን እናገኛለን።

አእምሮዬ፤ ሃይማኖትን ካደገበትና በጥልቀት ከተጣመረበት ባህል ለይቶ ሊረዳው አይችልም። እንደ አስተሳሰብ እና ባህል፤ ሃይማኖት ለሀገር ፍቅር፣ ለብሔራዊ ስሜትና ለግል ማንነት መሠረት ኾኗል። ሃይማኖትን መጉዳትና ከባህላዊው ጥምረት እንዲላቀቅ ማድረግ እነዚህን ሁሉ የማንነት ገበያዎች መጉዳት ነው። ይህም ወሳኝ ትስስርን ከማጥፋት እና በሌሎች ሰዎች የሕይወት ውሎች ላይ አዲስ ትስስር ለመፍጠር ከመጣር ጋር ተመሳሳይ ነው። ሁሉም ሰዎች እንደዚህ ላሉት ሙከራዎች ያላቸው ስሜት የጠላትነት ነው። ለምሳሌ፤ የካቶሊክ ፓትርያርክ [ነኝ ያለው] ሜንዴዝ በ1626 ኢትዮጵያ የዘመናት ሥርዓቷን (ባህሏን) ትታ የካቶሊክ (ላቲን) የአኗኗር ዘይቤ እንድትከተል በጠየቀ ጊዜ ህዝቡ ምን ዓይነት ምላሽ እንደሰጠ ሁላችንም የምናውቀው ነው።[4]

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የሃይማኖት አቋም ለማወቅ በምናደርገው ጥረት ውስጥ ታሪክ የላቀ ጠቀሜታ አለው። በታሪክ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ለዛሬ ህልውናዋ ትናንት ያለፈችባቸው ኹኔታዎች ምን እንደነበሩ ይታወቃል። በግለሰብ ደረጃ የሚገለጸውን ያህል፤ በቤተ ክርስቲያንም የዛሬ ማንነት መሠረት በታሪክ ውስጥ አለ። ነገሩ፤ “ አንተ ዛሬ የኾንከው ማንነትህ የተሠራው በታሪክህ ነው” እንደሚባለው ነው። “To understand the Orthodox Church is to understand how it has become what it is. … In this way, church history can be a privileged means of access to the inner truth of Christian confession. As for an individual so for a church, your history makes you what you are.”[5]

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የታሪክ መሠረት

“ወስሙ ለካልእ ፈልግ ግዮን ፡ ወውእቱ ዘየዐውድ ኲሎ ምድረ ኢትዮጵያ _ የኹለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ኹሉ ይከብባል” (ዘፍ. ፪፥፲፫)

የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው ኦርቲ ዘፍጥረት ውስጥ ኢትዮጵያ በዚህ መልኩ ተጠቅሳ ትገኛለች፡፡ ግዮንም አስፈላጊ በኾነ መጠቁም ስሙ የተነሣ ሲኾን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥቅሱን የተመለከተ የሊቃውንት ትርጓሜ “ይኸውም ዓባይ ነው” በማለት ያሳየዋል።[6] በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በቅርቡ ከተደረጉ ጥናቶች መካከል የሚከተለው ሐሳብ የተሠነዘረበት አንዱ ነው፡ “የግዮን ወንዝ የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል ይህም ሊኾን የሚችለው ጥቁር ዓባይ ነው። ምንም እንኳ ፊሶንና ግዮን የሚሉት ስሞች ጥንት የጠፉ ቢኾንም፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዋቢዎች በብርቱ እንደሚጠቁሙት፣ እነዚህ የኤደን ወንዞች በእርግጠኝነት ከኢትዮጵያ ተነሥተው በዛሬዋ ሱዳን በኩል የሚፈሱት ወንዞች ናቸው።”[7] ዮሲፈስም ግዮን ዓባይ በመኾኑ ላይ ስምምነቱን “በግብፅ ውስጥ የሚፈሰው፣ ማለትም ከተቃራኒው ዓለም የሚመነጨው፣ ግሪኮች ናይል የሚሉት ነው” እያለ አስፍሯል።[8]

እነዚህና መሰል በርካታ መረጃዎች ኢትዮጵያ ከብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓት በይፋ ወደኢትዮጵያ መግባት በፊት በሕገ ልቡና እግዚአብሔርን ሲያመልክ የነበረ ሕዝብ ሀገር መሆኗን ይጠቁማል፡፡ “ከሕገ ኦሪት በፊት ኢትዮጵያ ስለ ነበረችበት እምነት ብዙ ሰዎች በጻፉት ታሪክ ውስጥ እምነትና ክህደት ያወራሉ። . . . ኢትዮጵያ ፈጣሪን እንጂ ከቶ ፍጡርን ያመለከችበት ጊዜ የለም። ነገር ግን፤ የጽሑፍ ውሳኔ በሌለው ሕግ [ሕገ ልቡና] በሥነ ፍጥረት እየተመራመረች ፈጣሪዋን መፈለጓና መከተሏ እርግጥ ነው”[9]

ከንግሥተ ሳባ እና ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር የተያያዘው የክብረ ነገሥት ታሪክ ደግሞ ብሉይ ኪዳን በይፋ ወደ ኢትዮጵያ ለገባበት ታሪክ ተጠቃሽ ነው። የንግሥተ ሳባ ጉዞና ዝርዝር ሁኔታዎቹ የቀደመውን የሕገ ልቡናውን ነገር ይጠቁማሉ። የልጇ ቀደማዊ ምኒልክ ወደ አባቱ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ያደረገው ጉዞ ደግሞ ታቦተ ጽዮን በፈቃደ እግዚአብሔር ወደ ኢትዮፕያ ከመጣችበት ሁኔታ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በሃይማኖት ታሪካችን ውስጥ ጉልህ ለውጥ ካመጡ ጉዳዮች የሚመደብ ነው፡፡ ይህም ብቻውን በነጠላ ታሪክነት የሚነሣ ሳይሆን ከቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ መጀመር፣ ከባህልና ሥርዓት፣ እንዲሁም ከሌሎች ዛሬም ድረስ ተጠብቀው ከሚገኙ ገጽታዎች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹ፡

ግዝረት

ሕጻኑ በተወለደ ስምንተኛው ቀን መፈጸሙ ብሉይ ኪዳናዊ መሠረቱን ይነግረናል፡፡ (ዘፍ 17፡10፤ ዘጸ 12፡48…) ኢትዮጵያውያን የሥርዓቱን መነሻ እንደተጠበቀ ለክርስትናው ልዩ ገጽታ የሆነውን የብሉይ ኪዳን ሥርዓት ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል አድርገውታል፡፡ የሚከተለው ከሚሽነሪዎች ጋር ከተደረገ ክርክር በኋላ በዓጼ ገላውዴዎስ ዘመን የተያዘ አቋምም ለዚህ ምስክር ነው፡

“ወበእንተ ሥርዓተ ግዝረትኒ አኮ ዘንትገዘር ከመ አይሁድ። እስመ ንኅነ ነአምር ቃለ ምህሮሁ ለጳውሎስ . . . ዘይቤ ተገዝሮሂ ኢይበቁዕ ወኢተገዝሮሂ ኢያሠልጥ . . . ወባሕቱ ግዝረትሰ ዘኮነ በኀቤነ በልማደ ሀገር ከመ ብጥኀተ ገጽ ዘኢትዮጵያ ወኖባ” ማለታቸውን እናያለን። የግዝረትን ሥርዓት በተመለከተ፤ እንደ አይሁድ የምንገዘር አይደለንም። መገዘርም ኾነ አለመገዘር አይጠቅምም አይጎዳም የሚለውን የጳውሎስን አስተምህሮ እናውቃለንና። ነገር ግን በእኛ ኢትዮጵያውያንና ኑብያውያን ዘንድ ባህል/የሀገር ልማድ ነው ሲሉ ነው።”[10]

የቀዳሚት ሰንበት አከባበር

ምንጩ ከአይሁድ የተገናኘ ቢኾንም፤ አከባበሩ ከአይሁድ የሰንበት አከባበር ሥርዓት በእጅጉ ይለያል። እነርሱ ከምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ተቆጥበው፣ በጎ ሥራንም ቢኾን እንኳ እንደ ተወገዘ ተግባር ቆጥረውና ተከልክለው ያከብሩታል። ይህ ድርጊታቸው በጌታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስም የተነቀፈ ነው (ማቴ ፲፪፥፩-፲፬)። ይህን ሁሉ ቀደምት ኢትዮጵያውያን በዝርዝርና በጥራት ያውቁት፣ ያስተምሩትም ነበር። ክርስቲያናዊ አስተምህሮን ሥርዓትና ሕግን ጠብቆ እንዲከበርም አድርገውታል። ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ፤ “በዝንቱ ድርሳን ዘይሰመይ መጽሐፈ ብርሃን ጸሐፍነ ክብረ ክልኤሆን ሰንበታት በከመ ተአኃዛ በበይናቲሆን ከመ ኢይባእ ማእከሌሆን ግብረ እድ እምተግባረ ዓለም . . .” እንዳሉ ለመንፈሳዊ ተግባር ሊሰጥ ከሚገባው ጊዜ ጋር አያይዘው የኹለቱንም ሰንበታት ክብር ከተፈቀዱና ከተከለከሉ ተግባራት ጭምር ዘርዝረዋል። ይህም ማለት በጎ መሥራትን የማይከለክል በይዘቱ ክርስቲያናዊ የኾነ የሰንበት አከባበር በኢትዮጵያ የሚገኝ መኾኑን በግልጽ ያሳያል።

ሥርዓተ መባልዕት

ቅድመ ክርስትና በነበረው የሃይማኖት ሁኔታ ኢትዮጵያውያን የብሉይ ኪዳን ሥርዓትን ጠብቀው ለመኖራቸው ሌላኛው ምስክር የመባልዕት ሕግና ሥርዓት ነው፡፡ ይህም በዘሌዋውያን ከተደነገገው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ ፲፩፥፩-፵፯፣ ዘዳግም ፲፬፥፫-፳፩ የተከለከሉትን፣ ሰኮናቸው ያልተሰነጠቁና የማያመነዥኩ እንደ አሳማ ያሉ እንስሳትን ሥጋ አይበሉም”[11]

የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አሠራር (ሦስቱ ክፍሎች፡ ቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስት መቅደስ ከብሉይ ኪዳን ደብተራ ኦሪት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ናቸው)፣ አልባሳተ ክህነት፣ ንዋየ ማኅሌትና ሥርዓተ ማኅሌት፣ እነዲሁም በባሕላችን ውስጥ ያሉ ጥንታውያን በጎ ዕሤቶች ሁሉ ተጨማሪ ምስክሮች ናቸው፡፡

“በሕዝቡ የኑሮ ሥርዓትና ሃይማኖት ስሜት፣ በኃዘንና በደስታ ጊዜ ያለው ሁኔታ፣ የበዓላት አከባበር፣ የሴቶችና የሕፃናት ጌጣጌጥ ሁሉ የብሉይ ኪዳንን ሥርዓት . . . የሚያሳይ ነው። በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ የማኅሌት ሥርዓት የካህናቱ ልብሰ ተክህኖ፣ ካባው፣ መጠምጠሚያው የታቦቱ ክብርና ሌላውም ሁሉ ከብሉይ ኪዳን ሥርዓት ጋር ይመሳሰላል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው ከክርስትና በፊት ኢትዮጵያ የብሉይ ኪዳን ሀገር እንደ ነበረች ነው። በሌሎች ከአረማዊነት በተመለሱ ሀገሮች . . . ይህ ሁሉ አይታወቅም፡፡”[12]

ይቀጥላል!

 

 

 

[1] አስረስ የኔሰው፣ ትቤ አክሱም መኑ አንተ፣ 1951፣ 1፡፡

 

[2] The Church of Ethiopia: A Panorama of History and Spiritual Life, 1970, iii.

[3] Shang-Hui Shin, National Identity and National History: Role of Historical Narratives on Identity Construction, 2011, I. (PhD. Diss.

[4] Getachew Haile, Aasulv Lande and Samuel Ruberson, eds. The Missionary’s Dream: An Ethiopian Perspective on Western Missions in Ethiopia: Papers From A Symposium on the Impact of European Missions on Ethiopian Society,, in The Missionary Factor in Ethiopia, 1996, 3.

[5] Aidan Nichols, Light from the East: Authors and Themes in Orthodox Theology, 1995, 1.

[6] መጻሕፍተ ብሉያት ክልዔቱ፣ 1999፣ 24፡፡

[7] Gert Muller, Eden: The Biblical Garden Discovered in East Africa, 2013, kindle edition.

[8] Josephus, Jewish Antiquities: I:35-39, (V.I-IV) (With an English Translation by H. ST. Thakeray)

[9] አለቃ አያሌው ታምሩ፣ የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት፣ 1953፣ 35 – 36፡፡

[10] ተክለ ጻድቅ መኵሪያ፣ የግራኝ አሕመድ ወረራ፣ 1966 ዓ.ም፣ 775-776። Edward Ullendorff, Ethiopia  and the Bible, 1967, 106

[11] የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም.፣ 2000፣10።

[12]  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣1991፣ 14 -15።