መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች
የቤተክርስቲያን መሠረታዊ ተልእኮ ለሰው ልጆች መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን መስጠት ነው ለዚህም ነው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለዘመናት ያለምንም የሃይማኖት፣ የዘር፣ የጾታ ልዩነት ከሕዝቦች ሁሉ ጋር ተቀራርባ በመሥራት ሰብአዊ ተግባራትን የሞትፈፅመው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ልማት መስፋፋት የራሷን ልዩ አስተዋፅኦ በማድረግ የሀገሪቱን ልማት የምታለማና የምትደግፍ ብሔራዊት ቤተክርስቲያን ናት፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የትምህርት ታሪክ እንደሚያስረዳን ቤተክርስቲናችን የትምህርታዊ ሥነጽሑፍ ሥርዓት ምንጭ እንደሆነች ያስረዳል፤ ይህም የቤተክርስቲያኒቱ ትምህርታዊ አገልግሎት በኢትዮጵያ የግዕዝ ፊደላትን ፣ የቀን መቁጠሪዎችና ቋንቋዎችን ከመቅረጽና ከማሳደግ ይጀምራል፤ የታሪክ ቅርሶች፣ የጥናትና ምርመር ሊቃውንት እንዲሚያረጋግጡት በኢትዮጵያ የጽሕፈት ሥራ የተጀመረው ከክርስቶስ ልደት ከ1000 ዓመት በፊት ጀምሮ ነው፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የፅህፈት ሥራ ላይ ያዋለችው እምነቷን ማስፋፋት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ስለሆነም የግዕዝ ቋንቋና ፊደላት በአክሱም ዘመነ መንግስት የበላይነትን እያገኙ በሀውልቶችና በሌሎች ነገሮች የሚጻፉ ጽሑፎች በግዕዝ ቋንቋና ፊደላት በመጠቀም የትምህርት ሥርዓቷን ማሳደግ ችላለች፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በህዝቦቿ ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊና ትምህርታዊ ህይወት ውስጥ ታላቅ ድርሻ አበርክታለች እያበረከተችም ትገኛለች፡፡
የጥንቱ ትምህርት መለያ ባህሪ ያገኘው ልዩ ከሆነው ከሀገሪቱ ክርስቲያናዊ ውርስ ነው ክርስትና በተሰፋፋባቸው የኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ቤተክርስቲያኒቱ ዋናውን የኢትዮጵያን ጥንታዊ ባህል መሥርታለች ከዚህም የተነሳ ለብዙ መቶ ዓመታት ጥንታውያን ትምህርት ቤቶችን ማቋቋምና ማስፋፋት ችላለች የቤተ ክርስቲያን የትምህርት ሥርዓት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ትምህርት ጠብቆ ለማቆየት አገልግሏል ለትውልድም ሊተላለፍ የቻለው በዚህ ሥርዓት አማካንነት ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያን የትምህርት ሥርዓት የሚከተሉት ዋና ክፍሎች አሏት እነርሱም፡-
• ንባብ ቤት
• ቅዳሴ ቤት
• ዜማ ቤት
• ቅኔ ቤት
• መጽሐፍ ቤት ናቸው
መንፈሳዊ ዜማ ቤት
የቤተክርስቲያን መዝሙር በሰፊው የሚሰጥበት ት/ቤት ዜማ ቤት በመባል ታወቃል፣ ዜማ ማለት በግዕዝ፤
በዕዝል እና በዓራራይ የሚነገር ከሰማየ ሰማያት የተገኘ መንፈሳዊ የመላእክት መስጋና ማለት ነው፤ ይህም ግዕዝ በአብ፤ዕዝል በወልድ እና ዓራራይ በመንፈስ ቅዱስ የሚመሰል ነው፡፡ በታወቀው የዜማ ደራሲ በቅዱስ ያሬድ እንደተደረሱ የሚነገርላቸው የተለያዩ የዜማ ዓይነቶች አሉ ከእነዚህም መካከል አንዱና ዋናው ድጓ ነው፡፡
ቅዳሴ ቤት
ይህ ትምህርት ቤት ዲያቆናትና ቀሳውስት የቅዳሴን ዜማ በጥልቀት የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነው፤ የቅዳሴ ትምህርት ሰደድኩላና ደብረ ዓባይ በሚል በ2 የዜማ ዓይነቶች ተከፍሎ የሚሰጥ ነው፡፡
ቅኔ ቤት
በዚህ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በግዕዝ ቋንቋ ግጥምችን እንዲገጥሙ ትምህርት ይሰጣቸዋል፤ ቅኔ ፣ የዜማና የግጥም ምጣኔ ያለው በእንግሊዝኛ ናፖይትሪን ከተሰኘው ቃል ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው በቅኔ ቤት ተማሪዎች የሚማሩት የቅኔ ግጥም መግጠም ብቻ ሳይሆን የግዕዝ ቋንቋን ከሰዋሰዋዊ ህግጋቱ ጋር ነው በመሆኑም ቅኔ ማጥናት /መማር የግዕዝን ሥነ ጽሑፍ ለመረዳት ዋና ቁልፍ ነው፡፡
መጽሐፍ ቤት
ይህ ትምህርት ቤት የብሉይና የሐዲስ የመፃሕፍተ ሊቃውንትና የመፃህፍተ መነኮሳት ትርጓሜ የሚሰጥበት ትምህርት ቤት ነው፡፡በዚህ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የቤተክርስቲያንን ትውፊት፣ ዶግማ፣ታሪክና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በእያንዳንዱ ትርጓሜ አማካኝነት ይማራሉ፡፡
የቤተክርስቲያን ት/ቤቶች ጠቀሜታና አስፈላጊነት እስከ 19ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ቤቶች በሀገሪቱ ውስጥ ለማበራዊም ሆነ ለመንፈሳዊ ትምህርት ብቸኞች የትምህርት ተቋማት ሆነው አገልግለዋል ቀሳውስቱና የሀገሪቱ ሚኒስትሮች የእነዚህ ት/ቤት ተቋማት ውጤቶች ነበሩ፡፡
የሕግ ባለሙያዎች፣ ዳኞች፣ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ጸሐፊዎች ወዘተ ሥልጠና የሚያገኙት ከእነዚህ ት/ቤቶች ወይማ ገዳማት ነበር በአጠቃላይ ከዚህ መረዳት የምንችለው የቤት ክርስቲኒቱ ት/ቤቶች ለሃይማኖታዊ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ለማህበራዊ፣ ህጋዊ ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ አገልግሎቶች እጅግ በጣም አስፈላጊዎች እንደነበሩና እንደ ሆኑም ነው፡፡
በመሆኑም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሚያስተዳድራቸው ገዳማትና አድባራት የታወቁ የቅዳሴ፣ ቅኔ፣ የአቋቋም፣ የድጓና የመጽሐፍ መምህራን መድቦ የመማር ማስተማሩ ሂደት በተሳካ ሁኔታ ትምህርትን በመስጠት ላይ ገኛል፡፡
