❝ ልደታ ለማርያም ❞

ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፤ በማርያም ልደት ምክንያት ዛሬ ደስታ ኾነ! (ቅዱስ ያሬድ)
የንጽሕናችን መሠረት፤የመመኪያችን ዘውድ፤ ድንግል ማርያም ግንቦት ፩ ቀን ተወለደች፤ እግዚአብሔር ለአዳም የገባለትን የድኅነት ቃል ኪዳን ለማጽናት፣ ከሰማያት ሰማያት ዝቅ ብሎ የሚያድርባትን ንጽሕት ማደሪያውን በዚኽች ዕለት ከምድር አዘጋጀ።
የእመቤታችን ወላጆቿ ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፤ ይኹን እንጂ ለብዙ ዘመናት ልጅ በማጣት በሰዎች ዘንድ ይነቀፉና ይናቁ ነበር።
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፱ ላይ ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው አይተው ይህ ሰው ዕውር ኾኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ? ብለው መጠየቃቸውን ስናነብ፤ በዚያ ዘመን ዓይን ማጣት ይኽን ያኽል ካስባለ ልጅ ማጣት ደግሞ ምን ሊባል እንደሚችል መገመት አያዳግትም።
እነርሱ ግን እንደ እመ ሳሙኤል ሐና በፊቱ ዘወትር ማልቀስን አላቆሙም፤ እንዲኽ ያለ ነቀፌታ ሲደርስባቸው ከእግዚአብሔር ከእግሩ ስር ዝቅ ብለው በእንባ የሚናገሩ ልቦች እንዴት የታደሉና ያማሩ ናቸው።
በመጽሐፍ “…እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ።
(መዝ. ፴፱፥፱) ተብሎ ተጽፏልና የቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና ኀዘንና ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት መዓዛው እንደማይጠፋ ዕጣን አረገና ለዓለሙ ኹሉ ድኅነት የሚደረግባት ቡርክት ዘርን ሰጣቸወ።
“ሰጣቸው” ያልነው በሕገ ልደት ዘሥጋ እንጂ የተሰጠችውስ ለእኛ ለአዳም ልጆች ኹሉ ነው፤ ያማ ባይኾን እንዴት ያልወለደችውን ዮሐንስን”እናትህ እነኋት” (ዮሐ.፲፱፥፳፯) ይላል ጌታችን።
እመ አምላክ ድንግል ወላዲተ ቃል ከበዓሉ ረድኤት በረከት ታሳትፈን።