አምስቱ አዕማደ ምሥጢር
አምስቱ አዕማደ ምሥጢር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት መሠረቶች የሆኑት አምስቱ አዕማደ ምሥጢር (ምሰሶዎች) የሚባሉት ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፣ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ቍርባን፣ እና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ናቸው።
እነዚህ ምሥጢራት የክርስትና እምነት መሠረት ሲሆኑ፣ የማይታየውን የሃይማኖት ምሥጢር በሚታይ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት የሚገልጹ ናቸው።
የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር አጭር ገለጻ፦
1.ምሥጢረ ሥላሴ /Mystery of Holy Trinity/
ይኸውም እግዚአብሔር በአካል፣በስም እና በግብር ሦስት እንዲሁም በመለኮት፣በፈቃድ በባሕርይ አንድ (አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ) መሆኑን የሚያስተምር ፍጹም አንድነት እና ፍጹም ሦስትነትን የሚያብራራ ነው።
2.ምሥጢረ ሥጋዌ/Mystery of Incarnation/
ይኸውም እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ባሕርይ በመዋሐድ ከድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆኖ መወለዱን፣ ያለመቀላቀልና ያለመለየት የፈጣሪና የፍጡር ባሕርይ በአንድ አካል መዋሐዳቸውን የሚያስተምር ነው።
3.ምሥጢረ ጥምቀት/Mystery of Baptism/
ይኸውም በዮርዳኖስ ወንዝ በጌታችን ጥምቀት ምሳሌነት፣ በውሃ እና በቃል አማካኝነት ሰው ዳግመኛ የሚወለድበት እና የኃጢአት ሥርየት የሚያገኝበት ምሥጢር ነው።
4.ምሥጢረ ቍርባን/Mystery of Holy Eucharist/
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ሥጋ እና ደም መሆኑን በማመን፣ ምዕመናን ከክርስቶስ ጋር የሚዋሐዱበትና የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበት ታላቁ ምሥጢር ነው።
5.ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን/Mystery of Resurrection of the dead/
ይኸውም በዓለም መጨረሻ የሞቱ ሰዎች ሁሉ አካላቸው ተለውጦና ተቀድሶ በነፍስ ተመልሰው፣ ለፍርድ እንደሚነሡና ከሞት በኋላ ስላለው የዘለዓለም ሕይወት የሚያስተምር ነው።
