ሥርዓተ አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ

ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ስንል “ሥርዓት፣ ቤትና ክርስቲያን” ከሚሉ ሦስት መሠረታዊ የግእዝ ቃላት የሚመሠረት ስያሜ ነው። እነዚህም ቃላት ቁልፍ በመሆናቸው በመጠኑ ልናያቸው ያስፈልጋል። “ቤተ ክርስቲያን፡” የሚለው ሐረጋዊ ቃል፤መነሻው የግእዝ ቋንቋ ሲሆን፤ “ቤተ” የሚለው ቃል ራሱን ችሎ በሁለት ይፈታል። ይህም “ቤተ”= አደረ እና ወገን ሆነ የሚል ነው። “ቤተ” አደረ ተብሎ ሲፈታ ቤተክርስቲያን የሚለው ሐረግ የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ የሆነውን እና ለቅዱሱ አምላክና ለቅድስና ዓላማ የተለየውን፣ በሜሮን የከበረውንና የመሰዊያ ታቦት ያለበትን ቅዱሱን ሥፍራ ያሳያል። ይህም ለመንፈሳዊው ተልእኮ መሰብሰቢያ የሆነውን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን1 (ሉቃ. ፩፡፳፩፤ኢሳ.፵፬፡፳፰) ሲያመለክት፤ ሁለተኛው የ”ቤተ” ፍች ደግሞ ፣ ቤተ – ወገን ሆነ2 የሚል ሲሆን፤ የክርስቲያን ወገን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ቤተ እስራኤል ስንል፦ የእስራኤል ሕዝቦች፣ እስራኤላውያን ማለት እንደሆነ ሁሉ ቤተክርስቲያን ስንልም ክርስቶሳውያን ማለታችን ነው። በዚህም ቤተክርስቲያን የሚለው ሐረግ፦

፩) የክርስቲያኖች አንድነት ወይም ስብስብ (ዕብ. ፲፪፡፩)
፪) የክርስቲያን ሰውነት (፪ ቆሮ. ፮፡፲፮፤ ሐዋ. ፲፩፡፳፮) በሚል ተገልጧል።

በአጠቃላይ ቤተክርስቲያን ስንል፣ በምድር ያለች ለሰማያዊው የምስጋና መቅደስ አርአያ የምትሆን ዳግሚት ኤዶም ወይም የኤዶም ገነት ምሣሌ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት፤ ልዩ የቅድስና ቦታ ናት፡፡ ለአምልኮ ወደ ቤተክርስቲያን ስንገባ ከበሩ ላይ ትልቅ መስቀል ይኖራል በተጨማሪም በትእምርተ መስቀል አማትበንና ተሳልመን እንገባለን። በተለይ በቅጽሯ ውስጥ በበስተምሥራቅ ክፍል ብዙ ጊዜ እድሜ ጠገብ የሆኑ አጸዶች ወደሚገኙበት ስፍራ ስንገባ፤ ይህም ቀድሞ ባለመታዘዝ ምክንያት
ከወጣንባት ከኤዶም ገነት በክርስቶስ መስቀል ወይም መታዘዝ ዳግመኛ የመመለሳችን ምሳሌ ነው። ቤተክርስቲያን ተቋም ሳትሆን በምድር ላይ ያለች የማትከፈል አንዲት የክርስቶስ መንግሥት ናት። “ወሶበ ቦእነ ውስተ ጽርህከ ንሔሊ ከመ ንህነ ቀዋምያን በውስተ መንግሥትከ፡፡” 4 ወደ ቤትህ በገባን ጊዜ በመንግሥትህ ውስጥ እንደቆምን እናስባለን። ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የሚገኘው በምድር ቢሆንም የሰማይ አምሳል (Image of the heavenly kingdom) ስለሆነ ሥርዓቱና አምልኮው ፍጹም ሰማያዊ ነው። ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የገባ ሰው በሥጋው በምድር ላይ ስሜቱን ይገልጻል፡፡ በነፍሱ ሲኖር ደግሞ ከነፍሱ ጋር በተዋሐደ መንፈሱ በቁሳዊው ዓለም (material) በአጸደ ሥጋ ካሉት ጋር ይሳተፋል፡፡ የቤተ
ክርስቲያን ምልአት የሚባለው የሰማያውያንና የምድራውያን ሕብረት ሲሆን በአንድነቷ በሥርዓተ ቅዳሴ በምትፈጽመው በምስጢረ ቁርባን የድል ነሺዎች ሕብረት ወይም የቅዱሳን ማሕበር እና እንዲሁም ቅዱሳን መላእክት በመንፈስ አንድነት ይገኛሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በግሪከኛ ኮሚኒዮሳንክቶረም ወይንም ካይኖኒክ ሀጊዮን /Communio Sanctorum or Koinoniahagion/ ተብሎ ይጠራል። በቅዳሴው ቡራኬም ካህኑ፦ ልዑል እግዚአብሔር ሁላችንንም ይባርክ በመንፈሳዊም በረከት ሁሉ ያክብረን። ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን መግባታችንንም ዘወትር በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ከሚያገለግሉት ከቅዱሳን መላእክት ጋራ በአንድነት ያድርግ። በየጊዜውና በየሰኣቱም ሁሉ ከሚያመሰግኑት ዛሬም ዘወትርም ለዘለዐለሙ
እንዲል። ስለዚህ አምልኮ ወይም ቅዳሴ በሰማይ የሆነውን ሀገራችንን በምድር እያለን መኖር የምንጀምርበት፣ እና ሰማያዊ የምንሆንበት፤ የመንግሥተ ሰማያትን ጣእም፣ የክርስቶስን ደስታ፣ የምንቀምስበት በምድር ላይ የሚከናወን ሰማያዊ ሥርዓት ነው።

ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ስንል የጋራ ሥራ አገልግሎት በጋራ መፈጸም፣ የቤተ ክርስቲያን እቅድ፣ የቤተ ክርስቲያን አሠራር፣ መርሐ ግብር ደንብ፣ የክርስቲያኖች የሕይወት መመሪያ የክርስቲያኖች የጸሎት ሥርአት፣ የአኗኗር ደንብ፣ የክርስትና ሕይወት የጉዞ መስመር፣ የሚያምኑትን የሚኖሩበት መንፈሳዊ ሕግ ማለት ሲሆን አንቀጸ ንስኃንና የምሥጢራትን አፈጻጸም በሙሉ አጠቃሎ የያዘ መመርያ ማለት ነው። አምልኮ የቤተ ክርሰቲያኒቱ ሁለነተናዊ ሕይወት ነው፡፡ አምልኮ ማለት የምናምነውን በመኖር የምንቀደስበት ማለት ነው። የክርስቶስ ጥሪ “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ስለሚል፣ ይህ የሚፈጸመው በአምልኮ በኩል ብቻ ነው። አምልኮ መጽሐፍ ቅዱስን እየጸለዩ መማር፣ እየተማሩ መጸለይ፣ እየጸለዩ መዘመር፣ እየዘመሩ ማመስገን፣ ማለት ነው። “liturgy is the celebration of faith”. ክርስቶስ በምድር ለኛ የከፈለውን ዋጋ እያሰብን በመገዛት ይምናመሰግንበት የምስጋና ሥርዓት አምልኮ ይባላል። ይህም ቅዳሴ ሲሆን፤ በአምልኮ ክርስቲያናዊ ሕብረት መፈጸም
ነው፣ አንድነት ነው፣ ሥርየት ነው፣ ዝማሬ ነው፣ ጸሎት ነው፣ ትምህርት ነው፣ ምስጋና ነው። ቅዳሴ በመገዛት የሚቀርብ ልዩ ሰማያዊ ምስጋና ስለሆነ በምድራዊያን ብቻ ያልሆነ በሕያውያንና ሰማያውያን አንድነት የሚቀርብ ልዩ ሰማያዊ ምስጋና ማለት ነው።

የቤተክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ ሕይወት የሆነው የምስጋና ክንውን ሥርዓት ያለው በመሆኑ ሥርዐተ አምልኮ ይባላል። ሥርአተ ቤተክርስቲያን ስንል ሥርአተ አምልኮ ማለታችን ነው። የአምልኮ ሥርዓት ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ነው። ስለዚህ ሥርዐተ አምልኮ ስንል፤ መንፈሳዊ የጋራ ሥራ ማለት ነው ወይም አምልኮን በጋራ በመሆን በሥርዐት መፈጸም ማለት ነው። ሥርዓተ አምልኮ በሌላ አነጋገር በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው የሚፈጸም ሰማያዊ አገልግሎት ሲሆን ሥርዐተ አምልኮ ማለት
ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ማለት ነው ይህም የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ማለታችን ነው፡፡ የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ የመጨረሻው የጸሎት ሥርአት ቅዳሴ ይባላል። የሐዲስ ኪዳን ሥርዓተ ኣምልኮ ማእከሉ ክርስቶስ ስለሆነ፤ የምናምነውን በመኖር ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆን ማለት ነው። የየትኛውም ቅዱስ ወይንም ሰማእት መታሰቢያ8 በዓል ቢሆን የቅዳሴ አላማው ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆን ነው። ለዛ አላማ ስኬት የቅዱሱ በረከት ረድኤትና ምልጃ እገዛ ለመጠየቅ ፍቅር ያስገድደናል። በክርስቶስ ቤዛነት የተዋጁ ክርስቲያኖች ዋና ሥራቸው የተቤዣቸውን በምስጋናና በአምልኮ በዝማሬ ማምለክ ነው። ቅዳሴ የክርስቶስን ሕማም፣ ሞትና ትንሳኤ እያሰብን እግዚአብሔር አብን በአንድ ልጁ በክርስቶስ ሞት ላሳየን ዘለዓለማዊ ፍቅር ምስጋና ምናቀርብበት የኦርቶድክሳዊ የሕይወት መንገድ ነው። እርሱም እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በሉቃስ ወንጌል ም1 “በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጓልና ስሙም ቅዱስ ነው” እንዳለች ይህንኑ መለኮታዊ ቃል እያስተጋቡ ስልተደረገው ታላቅ የማዳን ሥራ ቅዱስ የሆነውን ስሙን በማመስገን ጸንቶ መኖር ነው።

የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ምንጭ፦ የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዋናነት የተዘጋጀው ለአምልኮ ስለሆነ የአምልኮ መጽሐፍ ይባላል። ከሰማንያ አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መካከል በዋነኛነት ስምንቱ የሥርዓት መጻሕፍት በመባል ያታወቃሉ።መጽሓፍ ቅዱስ ሁለተኛም ሦስተኛም ጭማሪ የሌለበት አንድ ነው። ሌሎቹ የሊቃውንት መጻሕፍት የሚባሉት በተለያየ ዘመን ለተነሱ መናፍቃን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጎ ለተነሳው የምንፍቅና ጥያቄ በቂ ምላሽ የተሰጠባቸው ማብራሪያዎች ናቸው። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ ልንላቸው እንችላለን። በተጨማሪም እንደ ድርሳናትና ቅዱሳን ገድላት የመሳሰሉትን ስንመለከት ለምሳሌ ገድላት ስንል መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እንደኖሬው የቅዱሱን ሕይውት በማየት በረከት የምናገኝበት በረድኤት ለቅድስና የምንነሳሳበት “የተኖረ ወንጌል” ማለት እንጅ ሁለተኛ መጽሐፍ ቅዱስ ማለት አይደለም።

የሥርዓተ ቤተክርስቲያን አስፈላጊነት፦ አምልኮ ያለሥርዓት ሊከናወን አይችልም። ለአምልኮ ሥርዓት ለምን አስፈለገ ስንል፣ ሁሉም ሥራ ወጥና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመሥራትና ከየት ተነስቶ ወዴት እንደሚሄድ ለመከታተል ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሃሳብና አንድ ልብ ሆኖ ለማምለክ መንፈሳዊውን ሥራም ለመከታተል ሥርዓት የግድ አስፈላጊ ነው። ያለ ወጥ ሥርዓት፣ እርስ በእርሷ እንደምትለያይ መንግሥት፤ ሳይግባቡ ይቀሩና አንድ ሐሳብና አንድ ልብ ለመሆን አይቻልም። የሃይማኖት ምስጢራትን ለመፈጸም ሥርዓት የሃይማኖት መገለጫ ስለሆነና ማንኛውንም ነገር ወጥና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመሥራት ከየት ተጀምሮ በየት በኩል ሄዶ በየት በኩል እንደሚጠናቀቅ ወጥ የሆነ የአሠራር ሥርዓት
ይዘጋጅለታል። የአንድ ሥራ አሠራር በትክክል ካልተነደፈና አካሄዱ ካልተስተካከለ፤ ሥራው የተዘበራረቀ ይሆናል ፍጻሜውም አያምርም። ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፤ ብዙ ስንሆን አንድ ልቡና አንድ ሃሳብ እንዲኖረን የሚያደርገን ነውና። /ኤፌ. ፬፥፫፤ የሐዋ. ፬፥፴፪፤ ሮሜ. ፲፭፥፮/።

የሐዲስ ኪዳን ሥርዓተ አምልኮ አፈጻጸም፤ አምልኮ ማለት መገዛት ማለት ነው። መለከ የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙ ገዛ ማለት ነው። አምላክ ወይም መለኮት ስንል ትርጉሙ ፈጥሮ የሚገዛ ገዢ ማለት ሲሆን አምልኮ ማለት ለነፍስና ለሥጋ አስገኝ ለፈጣሪ ሰማያት ወምድር በነፍስና በሥጋ መገዛት ማለት ነው። በኦርቶዶክስ ክርስትና ሥርዓተ አምልኮ እግዚአብሔር በአንድነት በሦሥትነቱ ይመለካል።

በማትከፋፈል አንድነት በማትጠቀለል ሦስትነት ይመለካል። አንድነቱን በማይከፋፍልበት በሦስትነቱ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ወይም ሥላሴ በመባል በ3 ስም በ3 ልዩ አካላትና ገጻት እንዲሁም በ 3 ግብራት፤ ሲመለክ እንዲሁም ሦስትነቱን በማይከፋፍልበት አንድነቱ እግዚአብሔር፥ መለኮት፥ አምላክ ገዢ ፈጣሪ መጋቢ እየተባለ በአንድነቱ ይመለካል።

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌ ያከናወናቸው የመስቀል ጉዞዎች ዐበይት ዐበይት ክንውኖች የሥርዓተ አምልኮ መሪዎች ስለሆኑ ዐበይት በአላት ይባላሉ። በሐዲስ ኪዳን በነገረ ድኅነት አስተምህሮ ምስጢረ ሥላሴ በምስጢረ ሥጋዌ ይታወቃልና ሥርዓተ አምልኮው ምስጢረ ሥጋዌን (አምላክ ወሰብእ ሆኖ መውረድ መወለዱን፥ መራብ መጠማቱን፥ መሰደብ መገረፉን፥ መሰቀል መሞቱን፥ መነሳት ማረጉን፥) ማዕከል ያደረገ ነው። በአዲስ ኪዳን የዓለም መስዋእት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ ክርስቶስ ስለሁላችን ኃጢአት መስዋእት ሆኖ በመስቀል ላይ የተሰዋ በግ ወይም የሚሰዋ ቁርባን፣ እንዲሁም መስዋእት የሚሰዋ ሊቀካህን እንደዚሁም መስዋት የሚቀበል ሕያው አምላክ ነው።
በዚሁ ላይ ተመሥርቶ ስብሐተ ነግህ የማይደርስበት፥ ጸሎተ ኪዳን የማይጸለይበት እንዲሁም ለዓለም የተሰዋው ኢየሱስ ክርስቶስ በመስዋእት የማይከብርበት፥ ቅዳሴ የማይቀደስበት ዕለት የለም።

ከቅዱሳኑ ጋር ሕብረት ይፈጸማል። የድል ነሺዎች የጻድቃን የሰማእታት የተጋዳዮች ምእመናን። ነገረ ድኅነት ሒደት ነው። ጊታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እለት ተወልዶ እለት ተሰቅሎ የሰውን ልጅ ድኅነት እንዳልፈጸመ ሁሉ ነገረ ድኅነትም ሒደታዊ ነው። ሒደት እንደመሆኑ መጠን የነገረ ድኅነት ክንውኖች በአመቱ ኡደት ውስጥ አንኳር አንኳር ክንውኖቹ ይዘከራሉ ይታሰባሉ። እንደየ ክንውኖቹ ተግባራት አበይትና ንዑሳን ተብለው ከአመት እስከ አመት ባለው ሥርዓተ አምልኮ ማእከል ሆነው በመስዋእት ይዘከራሉ ይህም ዓበይትና ንዑሳን በዓላት ተብለው በሁለት ይከፈላሉ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ሲል የፈጸማቸውን የነገር ድኅነት የመስቀል ጉዞዎች በተለያየ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን የአምልኮ ርእስ ሆነው የዘከራሉ። በኦርቶዶክሳዊት ሥርዓተ አምልኮ መሠረት እነዚህ የነገረ ድኅነት አንኳር አንኳር ክንውኖች እንደየታሪካቸው ይዘት በጾምና በትፍስሕት ይዘከራል። ለምሳሌ በሰባቱ አጽዋማት ከሚታሰቡት የነገረ ድኅነት አንኳር ክንውኖች መካከል በዕለተ ረቡዕ እና አርብ የሚታሰበው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በምክረ አይሁድ የተፈጸመው የሐሰት ክስ፥ በደቀመዝሙሩ የተከዳበት፥ ይሁዳ በመሳም አሳልፎ ሊሸጠው በ30 ብር የተስማማበት እንዲሁም
የክርስቶስን መከራና የተዋጀንበትን የመስቀል ዋጋ ጌታየ ለኔ ሲል በመስቀል መራራ ሞትን ታገሰ ሲል አፉን እስኪመረው እየጾመ ፍቅሩን በተግባር ይገልጣል። በመገዛት የተዋጀውን አምላክ በተግባር ያመልካል። ይህም ተግባራዊ አምልኮ ይባላል። ሁሉን ትቶ ዝቅ ያለውን ክርስቶስን፤ ያለንን ማድረግ የምንችለውን ሳይቀር በመተው ከጌታው የሚበልጥበት ምንም እንደሌለ በኑሮው ያሳያል። ማድረግ የምንችለውን ትተን መገዛት በተግባር የተፈተነ ፍቅር መገለጫ ነው። ዝቅ ብሎ እየወደቀ እየተነሳ ወደቀደመ ክብራችን የመለሰንን እየወደቁና እየተነሱ በስግደት9 ፍቅሩን ማሰብ የእውነተኛ አምልኮ ማረጋገጫ ነው። ለክርስቶስ ኢየሱስ መገዛቱን በተግባር ያሳያል። ያረጋግጣልም። ጾም መከልከል ነው።

ሌሎቹ ደግሞ በትፍስሕት የሚዘከሩ የነገረ ድኅነት አንኳር ክንውኖች እንደ ትንሳኤ ልደት ጥምቀት የመሳሰሉት ሲሆኑ በተለይ ሞትና መቃብርን ድል ነስቶ የተነሳባት፥ ቅዱስ ዮሐንስ በደሴተ ፍጥሞ በነበረበት ጊዜ በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ10 ስላለ ከሐዋርያት ጌዜ ጀምሮ የጌታ ቀን ሆና በዋናነት መደበኛ የአምልኮ መፈጸመያ የሆነችው፤ በተለይም ቅዱሳን አባቶቻችን በሐይማኖተ አበው “በእሑድ ቀን በጧት እጅግ ማልደህ በሌሊት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሂድ፤ ስትሄድም ልቡናህን በማባከን ወዲያና ወዲህ አትይ፤ በንጹህ ቅዳሴም ጊዜ ሕማሙን፣ ሞቱንና ትንሣኤውን እያሰብክ በፍጹም ፍርሐት ቁም።” ሃይማኖተ አበው ዘሠለስቱ ምእት ፳፡፳፪፬. ብለው ሥርአቱን እንዳጸኑልን፣ የሐዲስ ኪዳን ታላቋ ሰንበት ዕለተ እሑድ ናት። ይህች ዕለት ከዕለታት ሁሉ የላቀችና የተለየች ናት ምክንያቱም ከሌሎች እለታት በተለየ፤ በመንፈስ ሆነን፣ መንፈሳዊ በሆነ ተግባር ተሰማርተን፣ በቅዳሴ የምናከብራት፤ የጸሎትና የሱታፌ ምሥጢራት ዕለት ናት። የጌታ ቀን የተባለችበትም ትልቁ ምክንያት፤ በመስቀል የሞተው ደግሞም ሕያው የነበረው የትንሳኤው ጌታ የክርስቶስ ሞቱና ቅድስት የምቶሆን ትንሳኤውን በመንፈስ ሆነን የምንዘክርበት፤ የአማናዊት እረፍት መገኛ ሆና ለሰው ልጆች ሁሉ የተፈጸመው የመስቀል ጉዞ ፍጻሜ ያገኘባት፣ ክርስቶስ ሞትና መቃብርን ድል ነስቶ የተነሳባት፤ በትንሳኤው የትንሳኤያችን አዋጅ የታወጀባት የድል ዕለት በመሆኗ ነው ስለዚህ ይህች እለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለከፈለው የመስቀል ዋጋ ምስጋና የሚቀርብበት፤ የመስቀል መከራው የትንሳኤውም ደስታ የሚዘከርበት በዝማሬ በምስጋናና በመስዋእት የሚከበር ታላቅ የትፍስሕት ዕለት ነው። የቅዳሴው የምስጋና ጸሎትም “ንዜኑ ሞተከ” “ጌታ ሆይ ሞትህንና ቅድስት የምትሆን ትንሳኤህን እንናገራለን። ዕርገትህንና ዳግመኛ መምጣትህን እናምናለን። እናመሰግንሀለን። እንታመንብህማለን። ጌታችንና አምላካችን ሆይ እንለምንሀለን። እንማልድህማለን።” እንዲል።

ስለዚህ ይህች ዕለት የመስቀል ጉዞውን፣ የተከፈለውን ዋጋ፣ ትንሳኤውን እያሰብን በቅድስት ቤተክርስቲያን በአንድነት ሆነን፣ በሰማይ የሆነውን ሀገራችንን በምድር እየኖርን ትንሳኤያችንን ተስፋ የምናደርግባት፣ በክርስትና ጉዟችን ታላቅና አምስቱን11 መስዋእቶች የምንሰዋባት ዕለት ናት። ከእርሱ ጋር አንድ ሆነን ሕያው የምንሆንበትን12 ሥጋውን ደሙን የምንቀበልበት፣ በሰማያውያን ሕብረት፣ በመላእክት ርደት13፣ በመንፈስ ቅዱስ ርበት14፣ በክርስቶስ ውሕደት፤ በምሥጢራት እየዋኘን የጌታን ደስታ የምንቀምስባት፤ በዝማሬ ሰማያዊነታችንን እያረጋገጥን በሰማያዊ ከፍ ያለ ኅሊና የምንተጋበት ዕለት ናት። በቅዳሴ ጸሎት በመሳተፋችን፤ ለበደላችን ይቅርታና ምሕረት የምንጠይቅበት፣ “እግዚኦ ተሣሃለነ” አቤቱ ይቅር በለን “ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ…” አቤቱ በመንግሥትህ አስበን “እኔ” ብለን ሳይሆን “እኛ” በምልጃ ጸሎት ከፈጣሪያችን ጋር የምንገናኝበት፣ የኃጢአት ስርየት፤ በረከተ ሥጋም በረከተ ነፍስም የምናገኝበት ነው። ከሁሉም በላይ በቅዱስ ሥጋውን በክቡር ደሙ አማካኘነት ክርስቶስ ጋር አንድ ሆነን በመስቀሉ ለታጨንለት ዘለዓለማዊ ሕይወት የምንዘጋጅበት፤ በምድር ላይ እየኖርን ሰማያውያን ይምንሆንበት15 በመስቀሉ ለተጋበዝንበት የእግዚአብሔር መንግሥት አካል
የምንሆንበት ሥርዓት ነው። ያለቅዳሴ የሚዘከር የነገረ መስቀል ጉዞም ሆነ የነገረ ድኅነት ክንውን የለምና እያንዳንዱ ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጸመው በቅዳሴ ነው። ቅዳሴ ማለት “ቀደሰ” ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ምስጋና ማለት ነው። በግእዝ ቋንቋ ምስጋናን የምንገልጥባቸው በቁጥር 11 የሚሆኑ ቃላትን እናገኛለን። ቀደሰ/ቅዳሴ፣ አእኮተ/አኮቴት፤ ወደሰ/ውዳሴ፤ ሰብሐ/ስብሐት፤ ዘመረ/ዝማሬ፤ ሀለየ/ማህሌት፟፤ ባረከ/ቡራኬ፣ ገነየ/ግናይ፣ ለጠነ/ምልጣን፣ ቀነየ/ምቅናይ፣ መዝገነ/ምዝጋን እያለ ይቀጥላል16። ቅዳሴ የሚለው ቃል ግን ሁሉንም የምስጋና ዓይነቶችን አጠቃሎ የያዘ ሰፊ ቃል በመሆኑ “ልዩ ምስጋና” ተብሎ ይተረጎማል።

ቅዳሴ ማለት የመንፈስ ሕግ መፈጸሚያ ነው። ቅዳሴ በየጊዜው የሚፈጽም ይህም በካህኑ መሪነት፣ በዲያቆኑ አስተባባሪነትና በምእመናኑ ተሳታፊነት የማኅበር ጸሎት ለእግዚአብሔር በማቅረብ የጋራ አምልኮ መፈጸም ማለት ነው፡፡ ቅዳሴ እኛ ኦርቶዶክሳዊያን ክርስቲያኖች የሁለነታናዊ ሕይወታችንና የቤተክርስቲያናችን ራስ በሆነው በክርስቶስ ራስነት ሥር በአንድ አካልነት የሚያቀርቡት ነፍስን ደስ የሚያሰኝ ልብን የሚነጥቅ ሰማያዊና የነፍስ ምግብ ነው። ቅዳሴ በተመስጦ እና በጽሞና ሆነን በምሥጢራት ሱታፌ በኩል የእግዚአብሔርን ድምጽ የምንሰማበት፣ እግዚአብሔርን የምናውቅበት ቅዱስ ሥርዓት ነው። ቅዳሴ፤ የመንፈሳዊነት እድገትና ሕይወትን ከመንፈስ ቅዱስ፣ የምንማርበት ትምህርት ቤት ነው። ቅዳሴ አኮቴተ ቁርባን ብሎ የሚቀርብ ምስጋና ስለሆነ ልብንና አእምሮን ከእግዚአብሔር ጋር በማገናኘት፣ ሥጋንና ነፍስን አስተባብሮ በመገዛትና በአንቃድዎ ኅሊና የሚቀርብ የመንፈስ አምልኮ ስለሆነ በአንክሮ፣ በተዘክሮ፣ በአንቃእድዎ፣ በንጹሕ ልቡና፣ በሰቂለ ሕሊና የሚፈጸም አምልኮ ነው። ሞቱና መከራው ጭምር የሚታሰብበት በመሆኑ፤ ከስሜታዊነት ይልቅ በመንፈሳዊነት፤ ከመንዘፍዘፍና ከመወራጨት ይልቅ በስክነት፤ በመፍራትና በመንቀጥቀጥና በረአድ የሚከናውን ነው። ስለሞቱ
ስለግርፋት ስለስቅላቱ ስናስብ እንደቅዱስ ዮሐንስ በመንፈስ ሆነን ነውና።

ከእግዚአብሔር ጋር ምሥጢራዊ አንድነትን ማሳደጊያ ሰማያዊ የሕይወት መንገድ ነውና በሥርዐተ ቅዳሴ የሚጠቃለሉ የአገልግሎት ዓይነቶች …ሥርዐተ ጸሎት (ምስጋና ልመናና ምልጃ)፣ ስብከተ ወንጌል፣ የአምልኮ ስግደት፤ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መሳተፍ/ ሱታፌ፣ ክብር ይእቲ፣ ዝማሬ እና እጣነ ሞገር ናቸው፡፡ በካህኑ መሪነት፣ (ይካ) በዲያቆኑ አስተባባሪነትና (ይዲ) በምእመናኑ ተሳታፊነት ይሕ) የማኅበር ጸሎት በአንድነት ለእግዚአብሔር በማቅረብ አምልኮ መፈጸም ማለት ነው፡፡
በስተመጨረሻም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መሳተፍና ለክርስቲያን ሕይወት የሚሆነውን የመንፈስ ቅዱስ ሀብት መቀበል ማለት ነው፡፡

በሥር ዓተ አምልኮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደረግ ክብርና ዝግጅት እንዲሁም ጥንቃቄ

በቅዳሴ ጊዜ መቀመጥ ማውራት የግል ጸሎት መጸለይ ክልክል ብቻ ሳይሆን ነውር ጭምር ነው። ምክንያቱም “እዩኝ ከሁላችሁም ጸሎት የኔ ይበልጣል” ብሎ እንደመታበይ ስለሆነ በኅብረት የሚጸለይ የኅብረት ጸሎት ማለት ነው፡፡ በምድር ባለች ሰማያዊት መንግሥት ለፈጣሬ ሰማያት ወምድር ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ሰማያዊ ምስጋና ስለሆነ ቀጥ ብሎ በመቆምና ስግዱ ሲል በመስገድ የሰውነት መስዋእት የሚቀርብበት ነው። ለቅዳሴ ስትዘጋጁ ወደቀራኒዮ እየተጓዛችሁ ስለሆነ 5ቱን የስሜት ሕዋሳት አስገዝተው 5ቱን መስዋእት እየሰዉ በምድር እያሉ ሰማያዊነታቸውን የሚያውጁበት ሥርዓት በክርስቶስን ስቅለት በመስቀሉ ሥር በእለተ አርብ የመገኘት መንፈሳዊ ሥርዓት ነውና ያችን የጭንቅ የአርብ ስቅለትን ከ 6 እስከ 9 ሰአት በመስቀል ላይ የቆየባትን የ3 ሰአት የጭንቅ ቆይታ በማሰብ ለኔ ሲል ተጨነቀ በማለት ለ 3 ሰአታት ያህል በጽሞና የምናስባት ጊዜ ናት።

አገልጋይ ካህናትም የሰማያዊ ሥርዓት አምባሳደሮች ስለሆኑ ሰማያውያን ናችው፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳን መላእክት ለእግዚአብሔር ንጹሕ ምስጋና ያለማቋረጥ ለማቅረብ እንደተፈጠሩ ሁሉ፤ አገልጋይ ካህናትም መንፈሳዊ አምልኮን ለመፈጸም የተለዩ ናቸው ሌትና ቀን ለእግዚአብሔር ያለማቋረጥ ምስጋና ያቀርባሉና፡፡ ስለዚህ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ጠንቅቆ ማወቅ እና መንፈሳዊ መልእክቱን ከፍ ባለ ዕውቀት ተረድቶ ማስረዳት፣ የካህናት ተቀዳሚ ተግባር ነው። ስለዚህ በላቀ መንፈሳዊነትና በሰማያዊት ክህነት፣ በትጋት በመጸለይ ቸርነቱን ያለማቋረጥ በማሰብ፣ በማድነቅ፣ እንዲሁም ለዐለም የምስራቹን ቃል መግለጥና ማስተማር፤ አምልኮው እንዲከናወን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። “ብዙ ከሰጡት ብዙ
ይጠበቅበታል”ና፣ ካህናትም በዚህ ሰማያዊ ክብር ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድ በክህነት ተጠርተዋልና ሀይማኖትን ከምግባር አዋህደው፣ እውቀት መንፈሳዊና ሥጋዊ ጭምር አደላድለው፣ ጸንቶ ለማጽናት፣ የተሾሙ የእግዚአብሔር መንግሥት ሰራተኞች ናችሁና በምድር አስራችሁ በሰማይ የምታጸኑ በምድር ፈታችሁ በሰማይ የምታስምሩ፣ መራራውና ጣዕም አልባው ዐለም የጣፈጠባችሁ የዐለም ጨው፣ ተላውያነ ሐዋርያት ናችሁ። በአምልኮ በኩል የሰውን ልጅ መንፈሳዊ ሕይወት በመገንባትና የድኅነት ስጦታን ተሳታፊ እንዲሆኑ ነፍሳትን ከዐለም እየነጠቁ ለክርስቶስ፣ በከርስቶስ መማረክ ነው።

በሥርአተ አምልኮ 3 ዋና ዋና አካላት ይገኛሉ እነርሱም ካህናት ዲያቆናትና ምእመናን18 ናቸው። ካህናትም ሆኑ ምእመኑ በሥርአተ አምልኮ የየራሳቸው ድርሻ ስላላቸው መጽሐፈ ቅዳሴ “ይካ” ይበል ካህን “ይዲ” ይበል ዲያቆን “ይሕ” ይበል ሕዝብ እያለ ድርሻ ድርሻውን ያስቀምጣል። በዚሁ መሠረት የከህናት ድርሻ በክህነት በእውቀትና አራያነት ባለው በፍም መንፈሳዊነት አምልኮውን ይመራል። ዲያቆኑ ደግሞ ቅዳሴውን ይራዳል። ጸልዩ፣ ተንሥኡ፣ ስግዱ፣ ፃኡ፣ አውስኡ፣ ነጽሩ…… እትዉ (10ጊዜ) እያለ ያስተባብራል፡፡ የምእመናን ድርሻ19፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማድመጥ፣ በምስጢራት ተሳትፎ መክበርና ቅዳሴው እስከሚፈጸምና እትዉ በሠላም የሚለው የማሰናበቻ ዜማ እስኪሰማ መታገስ ናቸው።

ስህተት

– ወኢሰምዐ = የሚነበቡትን ቅዱሳት መጻሕፍት ያልሰማ
– ወኢተዐገሠ= ቅዳሴው እስኪያልቅ መታገስ ያልቻለ
– ወኢተመጠወ= ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን መቀበል ያልቻለ

በደል
– እስመ አማሰነ ሕገ እግዚአብሔር = የእግዚአብሔርን ሕግ አጠፋ
– ወአስተሐቀረ ቁመተ ቅድመ ንጉስ ሰማያዊ ንጉሰ ሥጋ ወመንፈስ= የሥጋና የመንፈስ ንጉሥ
በሆነው ሰማያዊ ንጉሥ በሆነው በክርስቶስ ፊት መቆምን አቃሏልና

ቅጣት
– ይሰደድ እምቤተ ክርስቲያን ከቤተክርስቲያን ይለይ።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጸሙ ምሥጢራት ድኅነታችንን በጥንቃቄ የምንፈጽምባቸው ሃይል መንፈስ ቅዱስ የምንሞላባቸው እንዲሁም ለባሴ ክርስቶስ ወይም ሱታፌ አምላክ ወደመሆን የምናድግባቸው መንፈሳዊ ኃይላት ናቸው፡፡ በቅዳሴ የማይሳተፍና የክርስቶስን ሥጋና ደም የልተቀበለ ሰው በቤተ ክርስቲያን ኅብረት ውስጥ ስለሌለ የክርስቶስ አካል አልሆነም ቢሆንም አልጸናም አልጠበቀምም ማለት ነው። ቅዳሴ በቁሳዊ ዓለም ላይ በሚታይ ሥጋ ቆሞ በመንፈሳዊ ዓለም ውስጥ
በተመስጦ መገኘት ነው። የሰው ልጅ በሁለቱም ዓለሞት በአንድ ጊዜ መኖር የሚችለው በምስጢራት በኩል ባለው ተሳትፎ ነው፡፡ ይህም በቅዳሴ ጊዜ የምትታየው (Visible church) በመንፈስ በሰማይ ካለችው ከማትታየው (invisible) ከሆነችው ቤተ ክርስቲያን ራስ በሆነው በክርስቶስ ተገናዝበው ህብረት አንድነት ይሳተፋሉ ማለት ነው። ቅዳሴ ክርስቶስን ማዕከል አድርጎ በክርስቶስ ራስነት አካል ሆኖ መኖር ነውና። (ዮሐ 15፥2) ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ራስ የሆነላት የክርስቶስ መንፈሳዊ አካል (The spiritual body of Christ) ናትና። (ኤፌ 5፥23) ይህም አንድነት (Christian unity) እውን የሚሆነው የኅብረቷ ምስጢር በሆነው በቅዱስ ቁርባን (Holy Communion) ብቻ ነው።

ኦርቶዶክሳዊ አምልኮ ዋና ግቡ ሱታፌ አምላክ ነውና በጥምቀት ያገኘነው ልጅነት፣ በምሥጢረ ቁርባን በምናደርገው ኅብረት (ዮሐ.15፥4-7)፣ ከክርስቶስ ጋር ያለን ኅብረት በሱታፌ አምላክ (የመለኮታዊ ባሕርይ) ተካፋይነት(2ጴጥ 1፥4) የሚያደርሰን የሕይወት ስንቅ ነው። አንድ ስለምታደርግ ሥጋውና ደሙ እግዚአብሔር አንድ ያደርገን ዘንድ” በዲያቆኑ የሚጸለየው በእንተ ቅድሳት ያስረዳናል። መንፈሳዊ ሕይወት የማይቋረጥ የእድሜ ልክ ጉዞ ነው። በዚህ ዘለአለማዊ ጉዞ የክርስቶስ ሥጋና ደም መንፈሳዊ ኃይል የሚሰጠን ስንቃችን ሆኖ ቀረበልን24። ምሥጢረ ቁርባን ለመንግስተ ሰማያት የተገባን የምንሆንበት፤ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወትን የምናገኝበት፣ በክርስቶስ ቤዛነት ያገኘነውን ነፃነት በሥጋዊ ድካም በኃጢአት ስናሳድፈው ደግሞ ለዘለዓለም ሕያው ከሆነ መስዋዕት በመንፈስ ቅዱስ ጸጋን የምንካፈልበት ታላቅ ምሥጢር ነው። ያለ ምሥጢረ ቁርባን ምሥጢረ ጋብቻም ሆነ ምሥጢረ ንስሐ አይጸናም። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተግባራዊ ትምህርት በአጽኖዖት ያስተማረን ጽኑእ የእምነት መሠረት ነው። ዮሐ.6፥41-60፣ ማቴ. 26፥26-28። ለማጠቃለልም ሐዋርያው “1ኛ ቆሮንቶስ 9 ታገኙ ዘንድ ሩጡ።²⁵ የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ … እኛ ግን የማይጠፋውን። ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፥ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ ²⁷ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ።” ማሕሌት ወይም መዝሙር ቆመው አድረው ቅዳሴውን አቋርጠው በመውጣት የማያስቀድሱ መዘምራን፤ በአምልኮ ሳይሳተፉ አስቀዳሹን ሊያስተምሩ ቅዳሴው ሲያልቅ ዓውደ ምሕረት ላይ የሚከሰቱ ሰባክያን፣ እንዲሁም ሳያስቀድሱ በስተመጨረሻ ከየአዳራሹ ለዝማሬ ብቅ የሚሉ መዘምራንና ሰንበት ተማሪዎች እና የማያስቀድሱና የማይቆርቡ ምእመናን። ይሰደድ የሚለው ቃል በዋነኛነት ይመለከታቸዋል።

በቅዳሴ ጊዜ በቅዳሴ ጊዜ የሚስቅ ሰው ቅዱስ ባስልዮስ በጻፈው በ፸፪ኛው አንቀጽ ካህን ቢሆን የሚያቀብል ነውና ሥጋ ወደሙን ከተቀበለና ካቀበለ በኋላ ወጥቶ አንድ ሱባዔ ይቀጣ ይጹም ይስገድ፣ ምእመን ቢሆን ግን ሥጋ ወደሙን ሳይቀበል ያን ጊዜ ፈጥኖ ይውጣ ይላል። ምክንያቱም ካህኑ በቅዳሴ ጊዜ ቅዳሴውን ጥሎ ወጥቶ ሲሄድ መጥፎ አብነት እንዳይሆን ነው። ምዕመኑ ግን ሲስቅ ሁሉ ያየዋልና ለሌላ መቀጣጫ እንዲሆን፤ በቤተ መቅደስ የማይወደድ ሌላ ነገር አይናገር፤ በቤተ መቅደስ ጭንቅ፣ ደዌ ሳያገኘው አንዱን ስንኳ ምራቁን እንትፍ አይበል። ነገር ግን ደዌ ቢያስጨንቀው ድምፅ ሳያሰማ ምራቁን በመሐረቡ ተቀብሎ ያሽሸው።

በጸሎትና በአምልኮ የሚሳተፉ ባልና ሚስት ከተራክቦ መከልከል አለባቸው፡፡ (ዘጸ 19፡15) (1ቆሮ 7፡5-7) (ኩፋ 34፡12)። በማሕበር ጸሎት ለመሳተፍ የማያስችል እንደ ደም የሚሸት ቁስል ኃይለኛ ሳል የወር አበባዋ እና እንዲሁም በወንዶች ልማድ ሕልመ ሌሊት ወይም ተጻውሮ የመሳሰሉት ሲከሰቱ እስኪነጹ ድረስ መሳተፍ አይቻልም። በአምልኮ ሰአት በጸጥታ የሚነበበውን የሚተረጎመውን መስማት ተሰጥዖ መቀበል ይገባል እንጅ ወሬ ማውራት ማውካካት መንጫጫት ነውር ነው፡፡ ማንም ማን ዋዛ ፈዛዛ የሚናገር አይኑር፣ ቤተ ክርስቲያን በፈሪሃ እግዚአብሔር ሆነው የሚጸልዩባት የጸሎት ቦታ ናትና ቅዳሴው ሳይፈጸም አቋርጦ መውጣት አይቻልም፣ በጣም ጭንቅ ወይም በሕመም ምክንያት ካልሆነ በቀር። በቅዳሴ ጊዜ ካህናት የሚቀድሱባቸው አልባሳት ነጫጭ ይሁኑ። የመጋረጃ ቀለሞችም በዐበይት በአላት ነጫጭ እንዲሁም በዘወትር ቀይ በሰሙነ ሕማማት ደግሞ ጥቁር ብቻ ነው። እነዚህም በዘፈቀደ ሳይሆን ምሳሌ ስላላቸው ነው።

አንድ ሰው እንኳ ጫማ አድርጎ ከቤተ መቅደስ አይግባ ልዑል እግዚአብሔር የምትቆምባት ደብረ ሲና የከበረች ናትና ጫማህን አውልቅ ብሎ ለሙሴ ተነግሮታልና። /ዘጸአት ፫-፭/ ።

በቅዱስ ቁርባን ጊዜም አስቀድሞ ሊቃነጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ በቁምስና መዓርግ ያሉ መነኮሳት፣ ቀጥሎ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ ወንዶች በአርባ ቀን የሚጠመቁ ሕፃናት ከሁሉ አስቀድመው ይቀበሉ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይእ መላእክትን ይመስላሉና። ከነዚህ ቀጥሎ ከአርባ ቀን በኋላ እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉት ሕፃናት ትንሾቹ በፊት እየሆኑ እንደየዕድሜያቸው ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው /ክህነት የሌላቸው/ በድንግልና ኑረው የመነኮሱ ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው ሃያ፣ ሃያ ሁለት ዓመት የሆናቸው ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው በሹመት ያሉ ናቸውና ንፍቀ ዲያቆናት፣ አናጉንስጢሳውያን፣ መዘምራን ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው የንስሐ ሕዝባውያን በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።

በሴቶችም በኩል ከሁሉ አስቀድሞ የተጠመቁ የሰማንያ ቀን ሕፃናት ይቀበላሉ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይእ መላእክትን ይመስላሉና፤ ከነዚያ ቀጥሎ ከሰማንያ ቀን እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉ ሕፃናት እንደየዕድሜያቸው ሕፃናቱ አስቀድመው ታላላቆች ቀጥለው ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው አሥራ ሁለት፣ አሥራ አምስት የሆናቸው ደናግል ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው የቀሳውስት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በሕግ ኑረው የመነኮሱ እናቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያው ቀጥለው የዲያቆናት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በንሰሐ ተመልሰው የመነኮሱ መነኮሳት እና መነኮሳይያትይቀበላሉ፤ ከነዚያ በኋላ የንፍቀ ዲያቆናት፣ የአናጉንስጢሳውያን፣ የመዘምራን ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በሕግ ጸንተው ያሉ ሕጋውያን እናቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው የንስሐ ሕዝባውያን ሚስቶች በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ። ከዚህ በኋላ ካህኑ ሥጋ ወደሙን በፈተተበት እጁ ሕዝቡን ፊታቸውን ይባርካቸው። ቀሳውስት ግን እጅ በእጅ ተያይዘው እርስ በርሳቸው ይባረኩ። ቀዳሹ ካህን ቀሳውስትን ሲያሳልም “የጴጥሮስን ሥልጣን ባንተ አለ” ይበል፣ ተሳላሚው ቄስም “መንግሥተ ሰማያት ያውርስህ ከሾመ አይሻርህ” ይበል። ለዲያቆናትም “ልዑል እግዚአብሔር ያክብርህ ይባርክህ፣
ለማስተማር ዓይነ ልቡናህን ያብራልህ፣ ምሥጢሩን ይግለጥልህ” እያለ ይባርካቸው። ለምዕመናንም “ልዑል እግዚአብሔር ያክብርህ፣ ይባርክህ፣ ገጸ ረድኤቱን ይግለጽልህ” እያለ ይባርካቸው። ለሴቶችም “ልዑል እግዚአብሔር ይባርክሽ፣ ያክብርሽ ገጸ ረድኤቱን ይግለጽልሽ” ብሎ በእጁ ይባርክ።

በአባ ጌዴዎን ብርሀነ መነኮስ ዘደብረ ሊባኖስ
የረዳን ሁሉን ያከናወነ አምላክ ስሙ ይክበር ይመስገን።

20/01/2018 ዓም