ባሕረ ሐሳብ ቁጥር ያለው ዘመን

ክፍል አንድ፡- መግቢያ

ባሕረ ሐሳብ የሚለው ቃል ሐሰበ ቆጠረ ከሚለው ግስ የወጣ ዘር ሲሆን ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን (ዓመተ ዓለም) ማለት ነው፡፡ ሐሳበ ባሕር የሚልም አለ፤ የዘመን ቁጥር ማለት ነው፡፡ በባሕር የተመሰለው ዘመን ነው፡፡ ‹‹እስመ በመዳልው ተደለወ ዓለም ወበመስፈርት ሰፈሮ ለባሕር፡፡›› (ዕዝራ ሱቱኤል ፪÷፴፯) (ይኽ ዓለም በሚዛን ተመዝኗልና ባሕሩንም በመስፈሪያ ሰፍሮታልና) እንዲል፡፡ ባሕር በውስጡ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ከጥቃቅን ነፍሳት እሰከ ግዙፋን ዓሣ ነባሪዎች ወስኖ ይይዛል፡፡ ‹‹ዛቲ ባሕር ዐባይ ወረሓብ፤ህየ ዘይትሐወስ ዘአልቦ ኊልቍ፡፡ እንስሳ ዐበይት ምስለ ደቃቅ›› (መዝ ፻፫፥፳፭) (ይኽች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት፡፡ በዚያ ሥፍር ቁጥር የሌለው ተንቀሰቃሽ ታላላቆችና ታናናሾች እንስሳዎች አሉ) እንዲል፡፡ ዘመንም በውስጡ ከዓመቶች እስከ የደቂቃ ክፍልፋዮች ይወስናልና ዘመንን በባሕር ብለውታል፡፡ ባሕረ ሐሳብ በሚለው መርሐ ዕውር የሚሉ አሉ፡፡ የዕውር መመሪያ ዕውርን የሚመራ እንደ ማለት ሲሆን አቡሻኽርም ይባላል፡፡ አቡሻኽር በ13ኛው ምእት ዓመት የነበረና ባሕረ ሐሳብን የመረመረ (ያጠና) የቁጥር ሊቅ ሲሆን ድርሰትን በደራሲው ስም መጥራት አዲስ ነገር አይደለምና  ትምህርቱ በደራሲው ስም አበሻኽር ተብሏል፡፡

ባሕረ ሐሳብን በመጀመሪያ ሙሴ፣ በኋላም ሐዋርያት፣ ከሐዋርያት ቀጥሎ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ድሜጥሮስ፣ በመጨረሻም አቡሻኽር እንዳቀነባበሩት የባሕረ ሐሳብ መምህራን ያስተምራሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ አርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀምበትን የጊዜ መቁጠሪያ ያዘጋጀው ከ፪፻ እስከ ፪፻፵ ዓ.ም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ድሜጥሮስ ነው፡፡

ቅዱስ ድሜጥሮስ በዓላት እና አጽዋማት በጥንተ ተርክቧቸው የሚውለሉበትን የቁጥር ሕግ ለማግኘት ተመኝቶ ሱባዔ ቢገባ የመጥቅዕና የአበቅቴ መንገድ እንዴት እንደሆነ ተገለጾለታል፡፡ የኽን ሱባዔ ገብቶ የተገለጸለትን ለሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት ጽፎ ልኮላቸው ተቀብለውታል፤ በአገራችንም ሲሠራበት ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዘመን አቆጣጠር መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈውን መሠረት በማድረግ ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ብሎ ነው የሚጀምረው፡፡ በዚህ መሠረት ዓለም ከተፈጠረበትና ዘመን ከተቆጠረ ከተቆጠረበት ጊዜ ጀምሮ አሁን እስካለንበት 2018 ዓ ም ያለው ዘመን 7518 ሆነ ይሏል በዘመነ ማርቆስ ወንጌላዊ፡፡

ከኢየሰስ ክርስቶስ ልደት በፊት ነበረው ዘመን 5500 ዓመታት ሲሆን ይኽ ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኵነኔ ይባላል፡፡ ከልደተ እግዚእ እስከ አሁን ያለው 2018 ዘመን ዓመተ ምሕረት ዓመተ ሥጋዌ ነው የሚባለው፡፡ መላው 7518 ዘመን ግን ዓመተ ዓለም ይባላል፡፡ ለዚኽም መሥፈሪያ መቁጠሪያ 7 አዕዋዳት (ዐውዶች) አሉት፡፡ እነሱም፡-

 

(1) ዐውደ ዕለት፣

(2) ዐውደ ወርኅ፣

(3) ዐውደ ዓመት፣

(4) ዐውደ አበቅቴ፣

(5) ዐውደ ፀሐይ፣

(6) ዐውደ ማኅተም እና

(7) ዐውደ ቀመር ናቸው፡፡

ዐውድ ማለት በአማርኛ ዙሪያ ክብ እንደ ቀለበት እንደ አምባር ዙሮ የሚገጥም የጊዜ መቁጠሪያ ማለት ሲሆን ሲበዛ አዕዋድ (አውዶች) ይሆናል፡፡ አዕዋዳት ይፈጸማሉ እንጂ አያልቁም፡፡ አንድ ዐውድ ሲፈጸም እሱን የሚመስል ሌላ ዐውድ የተካበታል፡፡ እንዲህ እያለ አንዱ ሲፈጸም ሌላው እየተተካ ይቀጥላል እንጂ አዕዋድ መለቂያ የላቸውም፡፡

  • ዐውደ ዕለት፡- ዐውደ ዕለት ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ያሉት ሰባቱ ዕለታት ናቸው፡፡ እነዚህም ወሮችን ለማስግኜት በ7 በ7 ዕለታት ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡
  • ዐውደ ወርኅ፡- ዐውደ ወርኅ በፀሐይ ዘወትር 30 ቀን ነው፡፡ በጨረቃ አንድ ጊዜ 29 አንድ ጊዜ 30 ዕለታት ይሆናል፡፡ እነዚኽም ዓመታትን ለማስገኘት በ30 በ30 ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡
  • ዐውደ ዓመት፡- ዐውደ ዓመት በፀሐይ 365 ዕለት ከስድስት ሰዓቶች ሲሆን በጨረቃ 354 ዕለት ከኻያ ሁለት ኬክሮስ ነው፡፡ እነዚህ ሦስቱ ዐውዶች በዕለት ሌሎቹ አራቱ ደግሞ በዓመት ይለካሉ፡፡
  • ዐውደ አበቅቴ፡- ዐውደ አብቅቴ 19 ዓመት ሲሆን ዐውደ ንዑስ ቀመር በመባልም ይታወቃል፡፡ በዚህም ፀሐይና ጨረቃ መንገዳቸውን ፈጽመው በተፈጠሩት ኆኅት ተራክበ ያደርጉበታል፡፡ ፀሐይ በየዓመቱ 365 ሰትዞር ጨረቃ ግን በየዓመቱ 354 ዕለታት ብቻ ትዞራለች፡፡ ሁለቱ በየዓመቱ ተለያይተው ሲዞሩ ቆይተው በአሥራ ዘጠነኛው ዓመት አንድ ጊዜ በተፈጠሩበት ኆኅት የገናኛሉ፤ የህም ዐውደ አበቅቴ ይባላል፡፡
  • ዐውደ ፀሐይ፡- ዐውደ ፀሐይ ማለት 28 ዓመት ሲሆን በየኻያ ስምንት ዓመቱ ዙሮ የሚመጣ ማለት ነው፡፡ በዚህም ዕለትና ወንጌላዊ ይገናኙበታል፡፡ ዕለቱ ፀሐይ የተፈጠረችበት ረቡዕ ነው፡፡ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ ነው፡፡
  • ዐውደ ማኅተም፡- ዐውደ ማኅተም 76 ዓመት ሲሆን ዐውደ ማዕከላዊ ቀመርም ይባላል፡፡ በዚህም አበቅቴና ወንጌላዊ የገናኙበታል፡፡ አበቅቴው 18ት ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው፡፡ ‹‹ጥንቱ ለቀመር ዕለተ ሠሉስ ወወንጌላዊ ማቴዎስ ወፍጻሜሁ ዕለተ ሰኑይ ወወንጌላዊ ዮሐንስ›› (የቀመር መነሻው ማክሰኞ ዕለት ወንጌላዊው ማቴዎስ ሁኖ መጨረሻው ዕለተ ሰኑይ ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው፡፡) ዐውደ ማኅተም መባሉም አበቅቴው ለአበቅቴ ወንጌላዊዉም ለወንጌላውያን ፍጻሜ ስለሆነ ነው፡፡
  • ዐውደ ቀመር፡- ዐውደ ቀመር 532 ዓመት ሲሆን ዐውደ ዐቢይ ቀመርም ይባላል፡፡ በዚህም ዕለት፣ ወንጌላዊ እና አበቅቴ ሦስቱም ይገናኙበታል፡፡ ዕለቱ ሠሉስ፣ ወንጌላዊው ማቴዎስ፣ አበቅቴው አልቦ ነው፡፡ ነገረ ግን በዐውደ ፀሐይ ቦታ ዐውደ ማኅተም በዐውደ ማኅተም ቦታ ዐውደ ፀሐይ የሚል አበነት የገኛል፡፡ ከሁለቱ አንዱ የቀረ እንደሆነ ባሕረ ሐሳብ ለማውጣት ከቀመር ገብቶ የቆጠራል፡፡ እስከዚህ መቅድም ነው፡፡

ክፍል ሁለት ፡- መጥቅዕ እና አበቅቴ

በዓላት የሚውሉበትና አጽዋማት የሚገቡበትን ዕለት ለማግኘት ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን 6 መሠረታዊ ነገሮች መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እነሱም፡- (1) መደብ፣ (2) ወንበር፣ (3) አበቅቴ፣ (4) መጥቅዕ፣ (5) መባጃ ሐመር እና (6) ተውሳክ ናቸው፡፡

  • መደብ፡- መደብን ለማግኘት ዓመተ ዓለምን (7518) ለ19 በማካፈል እናገኛለን፡፡
  • ወንበር፡- ወንበርን ለማገኘት ከመደብ 1ን ለዘመን በመተው ወንበርን እናገኛለን፡፡
  • አበቅቴ፡- አበቅቴ ማለት ስፍረ ሌሊት ቁጥረ ሌሊት ተረፈ ዓመት ማለት ነው፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ያሉትን የሌሊቱንና የጨረቃን ኅድረት ከመዓልት ለይቶ ለማወቅ ይጠቅማል፡፡
  • መጥቅዕ፡- መጥቅዕ ማለት ደወል ማለት ነው፡፡ ደወል ሲመታ ሕዝብ ይሰበሰባል፡፡ በዓላት የሚውሉበት፣ አጽዋማት የሚገቡበት ዕለት የሚታወቀውም በመጥቅዕ ነውና መጥቅዕ ደወል ይባላል፡፡ በዚህ መሠረት መጥቅዕ ከዕለታት ተውክ ጋር ተደምሮ መባጃ ሐመርን ያስገኝልናል፡፡
  • ባጃ ሐመር፡- መባጃ ሐመር ባጀ ቆየ ካለው ግስ የተገኝ ቃል ሲሆን፡፡ ማቆያ ማክረሚያ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል፡፡ መባጃ ሐመር ከመጥቅዕ እና ከዕለታት ተውሳክ ጋር ተደምሮ አጽዋማትና በዐላት የሚውሉበትን ዕለት ያስገኝልናል፡፡ ከሰባቱ አጽዋማት ማካከል በመባጃ ሐመር የሚወጡት አራቱ (ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያትና ጾመ ድኅነት) ብቻ ናቸው፡፡
  • ተውሳክ፡- ተውሳክ ማለት ለአንድ ዕለት ወይም በዓል እና ጾም የተሰጠ ልዩ ቁጥር ማለት ነው፡፡ በዓላት የሚውሉበትንና አጽዋማት የሚገቡበትን ዕለት ማወቅ የሚቻለው በተውሳክን ከመባጃ ሐመር ጋር ደምረን  በምናገኘው ስሌት ነው፡፡

የዕለታት ተውሳክ

የሳምንቱ ዕለታት እንደ በዓላቱና አጽዋማቱ ሁሉ ተውሳክ አላቸው፡፡ ተውሳክ መባላቸውም ከበዓለ መጥቅዕ ጋር ተደምረው መባጃ ሐመርን ስለሚያስገኙ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ የዕለታት ተውሳክ በቅዳሜ የጀምራሉ፡፡ እነሱም፡-

ተ.ቁ ዕለታቱ ተውሳካቸው
1 ቅዳሜ     8
2 እሑድ     7
3 ሰኞ     6
4 ማክሰኞ     5
5 ረቡዕ     4
6 ሐሙስ     3
7 ዐርብ     2

ናቸው፡፡ የዕለታት ተውሳክ ከበዓለ መጥቅዕ ጋር ተደምሮ መበጃ ሐመርን ያስገኝልናል፡፡

መባጃ ሐመር= መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ዕለት ተውሳክ ነው፡፡ መባጃ ሐመርን ለማግኘት መጥቅዕን፣ መጥቅዕና አበቅቴን ለማግኘት ወንበረን፣ ወምበርን ለማወቅ ደግሞ የመደብን ዓመታዊ ስሌት ማወቅ አለብን፡፡ በዚህ መሠረት በዘመነ ማርቆስ የ2018 ዓመተ ምሕረትን መባጃ ሐመር ለማግኘት መጀምሪያ መደብን ማግኘት አለብን፡፡

መደብን ለማገኘት፡- መደብ = ዓመተ ፍዳ ዓመተ ከነኔ + ዓመተ ምሕረት ዓመተ ሥጋዌ÷ 19

5500 + 2018 =7518 ÷ 19 = 395 ቀሪ 13፣ በዘመነ ማርቆስ 2018 ዓ ም መደብ 13

ወንበር ለማወቅ፡- ወምበር = መደብ – 1 = 13 -1 = 12 በ2018 ዓ ም ወምበር 12 ወጣ፡፡ ከዚህ በመነሣት መጥቅዕንና አበቅቴን ማግኝት እንችላለን፡፡

መጥቅዕን ለማገኘት፡- መጥቅዕ = ወምበር × ጥንተ መጥቅዕ ÷ 30

12 × 19 = 228 ÷ 30 = 7 ቀሪ 18 ስለዚህ በ2018 ዓ ም መጥቅዕ 18 ሆነ፡፡

አበቅቴን ለማግኘት፡- አበቅቴን ለማግኜት፡- ጥንተ አበቅቴን ከወምበር ጋር ማባዛት ከዚያም በ30 መግደፍና ቀሪውን መያዝ፡፡ አበቅቴ = ጥንተ አበቅቴ × ወምበር ÷ 30 = 11 × 12 = 132 ÷30 = 4 ደርሶ 12 የቀራል፡፡ በ2018 ዓ ም በዘመነ ማርቆስ አበቅቴ 12 ሆነ፡፡

አበቅቴ የሚጠቅመን ከዕለትና ከሕጸጽ ጋር ተደምሮ ሌሊትን ለማሰገኘት ነው፡፡ መጥቅዕ ቢያንስ አበቅቴ ቢበዛ ወይም አበቅቴ ቢያንስ መጥቅዕ ቢበዛ ሁል ጊዜ አበቅቴና መጥቅዕ ተደምረው ከ30 አያንሱም፤ ከ30 አይበልጡም፡፡ ‹‹መጥቅዕ ወአበቅቴ ኢይበዝኁ ወኢይውሕዱ እም ፴ ወትረ ይከውኑ ፴›› (መጥቅዕና አበቅቴ በኅብረታቸው ከ30 አይበዙም ከ30ም አይጎድሉም ዘወትር 30 ይሆናሉ) እንዲል፡፡

መባጃ ሐመር ለማገኘት፡- መባጃ ሐመር = መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ዕለት ተውሳክ

አሁን መጥቅዕ 18 መሆኑን ስላወቅን መባጃ ሐመርን ለማግኘት በዓለ መጥቅዕ የሚውልበትን ዕለት ተውሳክ ማግኘት አለብን፡፡ መጥቅዕ ሲበዛ ከመስከረም ንዛ፤ መጥቅዕ ሲያንስ ጥቅመትን ዳስ (መጥቅዕ ሲበዛ በዓለ መጥቅዕን በመስከረም ዐውል፡፡ መጥቅዕ ሲያንስ በዓለ መጥቅዕን በጥቅምት ዐውል፡፡) በሚለው መርሕ ተመሥርተን በዓለ መጥቅዕ የሚውልበትን ዕለት ማገኘት እንችላለን፡፡ መጥቅዕ በዛ የሚባለው ከ14 በላይ፣ አነሰ የሚባለው ከ14 በታች ሲሆን ነው፡፡ በዚህ ዓመት መጥቅዕ ከ14 በላይ 18 ስለሆነ በዓለ መጥቅዕ መስከረም 18 እሐድ ዕለት ይውላል፡፡ በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ዕለት የእሑድ ተውሳክ 7 + 18 = 25 ይሆናል፡፡ መባጃ ሐመር የሚባለው በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ዕለት ተውሳክ እና የመጥቅዕ ድምር ሰለሆነ፣ በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ዕለት ተውሳክ እና የመጥቅዕ ድምር (7 + 18) ደግሞ 25 በመሆኑ በዘመነ ማርቆስ 2018 ዓ ም መባጃ ሐመር 25 ይሆናል፡፡

መባጃ ሐመር ዋነኛ አገልግሎቱ ከበዓላትና አጽዋማት ተውሳክ ጋር እየተደመረ በዓላትና አጽዋማትን ማስገኘት ነው፡፡ በተለይ ጾመ ነነዌ የራሱ ተውሳክ ስለሌለው የሚወጣው በመባጃ ሐመር ነው፡፡ ጾመ ነነዌ የሚጀምርበትን ቀን ፈለጎ ለማገኘት የሚየገለግለን በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ወር ነው፡፡ ምክንያቱም በዓለ መጥቅዕ በመስከረም በሚውልበት ጊዜ የነነዌ ጾም በጥር ይውላል፡፡ በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት በሚውልበት ጊዜ የነነዌ ጾም በየካቲት የውላልና ነው፡፡ በ2018 ዓ ም በዘመነ ማርቆስ በዓለ መጥቅዕ በመስከረም ስለዋለ የነነዌ ጾም በጥር ወር ይጀምራል፡፡ ጾመ ነነዌ ተውሳክ ስለሌለውና በመባጃ ሐመር የሚወጣ ስለሆነ መባጃ ሐመር ደግሞ 25 በመሆኑ ጥር በባተ በ25 ዘመነ ማርቆስ (2018 ዓ ም) ጾመ ነነዌ ይጀምራል፡፡

ክፍል ሦስት ፡- በመባጃ ሐመር የሚንቀሳቀሱ በዓላትና አጽዋማት

በመባጃ ሐመር የሚወጡ በዓላትና አጽዋማት የሚገኙት አራት ነገሮችን በመደመር ነው፡፡ እነሱም፡- (1) መጥቅዕ፣ (2) መጥቅዕ የሚውልበት ዕለት ተውሳክ፣ (3) የበዓላትና አጽዋማት ተውሳክ እና (4) የነነዌ መባጃ ሐመር ናቸው፡፡ የዐቢይ ጾምን ተውሳክ ለማግኘት ከነነዌ መግቢያ እስከ ዐቢይ ጾም ያሉትን ዕለታት መቁጠር ነው፡፡ ከነነዌ መግቢያ እስከ ዐቢይ ጾመ መግቢያ ያሉት ዕለታት 14 ስለሆኑ የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14 መሀኑን በቃላሉ ማግኘት እንችላለን፡፡

የበዓላትና አጽዋማት ተውሳክ

በዓላትና አጽዋማት ተውሰካቸው ተውሳክ ሲደመር መባጃ ሐመር በዐላትና አጽዋማት

የመውሉበት ዕለት

ጾመ ነነዌ መባጃ ሐመር      25 ጥር 25 ጾመ ነነዌ
ዓቢይ ጾም 14 14 + 25 = 39 – 30 = 9 የካቲት 9 ዓቢይ ጾም
ደብረ ዘይት 11 11 + 25 = 36 – 30 = 6 መጋቢት 6 ደብረ ዘይት
ሆሣዕና 2  2 + 25 = 27 =      27 መጋቢት 27 ሆሣዕና
ስቅለት 7  7 + 25 = 32 – 30 = 2 ሚያዝያ 2 ስቅለት
ትንሣኤ 9  9 + 25 = 34 -30 = 4 ሚያዝያ 4 ትንሣኤ
ርክበ ካህናት 3  3 + 25 = 28 ሚያዝያ 28 ርክበ ካህናት
ዕርገት 18 18 + 25 = 43 -30 = 13 ግንቦት 13 ዕርገት
ጰራቅሊጦስ 28 28 + 25 = 53 – 30 = 23 ግንቦት 23 ጰራቅሊጦስ
ጾመ ሐዋርያት 29 29 + 25 = 54 – 30 = 24 ግንቦት 24 ጾመ ሐዋርያት
ጾመ ድኅነት 1  1 + 25 = 26 ግንቦት 26 ጾመ ድኅነት

ክፍል አራት፡- ኢየዐርግና ኢይወርድ

  • ጾመ ነነዌ ከጥር 17 አትወርድም ከየካቲት 21 አትወጣም፡፡
  • ዐቢይ ጾም ከየካቲት አንድ ወደታች አይወርድም ከመጋቢት 5 ወደላይ አይወጣም፡፡:
  • ደብረ ዘይት ከየካቲተት 28 ወደታች አይወርድም ከሚያዝያ 2 ወደላይ ፤አይወጣም፡፡
  • ሆሣዕና ከመጋቢት 19 ወደ ታች አይወርድም ከሚያዝያ 23 ወደላይ አይወጣም
  • በዐለ ስቅለት ከመጋቢት 24 ወደታች አይወርድም ከሚያዝያ 28 ወደላይ አይወጣም፡፡
  • ትንሣኤ ከመጋቢት 26 ወደታች አይወርድም ከሚያዝያ 30 ወደላይ አይወጣም፡፡
  • ርክበ ካህናት ከሚያዝያ 20 ወደታች አይወርድም ከገንቦት 24 ወደላይ አይወጣም፡፡
  • ዕርገት ከግንቦት አመስት ወደታች አይወርድም ከሰኔ 9 ወደላይ አይወጣም፡፡
  • ጰራቅሊጦስ ከገንቦት 15 ወደታች አይወርድም ከሰኔ 19 በላይ አይወጣም፡፡
  • ጾመ ሐዋርያት ከግንቦት 16 በታች አይወርድም ከሰኔ 20 በላይ አይወጣም፡፡
  • ጾመ ድኅነት ከግንቦት 18 ባታች አይወርድም ከሰኔ 22 በላይ አይወጣም፡፡

ክፍል አምስት ፡- ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘመን አቆጣጠር የተሰየመው የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በጻፉ አራቱ ወንጌላውያን ነው፡፡ ስያሜውም ዓመቱ ዘመነ ማቴዎስ፣ ዘመነ ማርቆስ፣ ዘመነ ሉቃስ እና ዘመነ ዮሐንስ እየተባለ የሚሰየም ሲሆን ስያሚው በየ4 ዓመቱ ከአራቱ ወንጌላውያን ለአንዱ የሚደርስ ይሆናል፡፡ በዚህ መሠረት በያዝነው ዓመት 2018 ዓመተ ምሕረት ተሿሚው ወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ በመሆኑ ዘመኑ ዘመነ ማርቆስ ወንጌላዊ ይባላል፡፡ የቆየን!

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር!!!

 በዕውቀቱ ይልማ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርቲያን ታሪክ

መግቢያ

ታሪክ ኃላፍያት የሚጠኑበት የትምህርት ዘርፍ ነው። በታሪክ ውስጥ ያለፉ የምንላቸው ክስተቶች ጉልህ ትርጉም ይዘው ነገ ልንደርስበት ከምናስበው መዳረሻ አንጻር ይገመገማሉ። በተፈጥሮ ሥርዓት፣ በባህላዊ መስተጋብር፣ በሃይማኖት ትምህርት፣ በሥልጣኔ መሠረቶች ምርመራ፣ በውድመትና ኪሣራዎች ግምገማ፣ እንዲሁም በሌሎችም የሕይወት ክፍሎች ታሪክ መሠረታዊ ሚና አለው። በትናንትናው ስኬት መሠረቶች ላይ ቆመው ስለነገ የሚያልሙ ሰዎች በታሪክ ተጠቃሚ ይኾናሉ። የዚህኑ ያህል፤ ካለፉት መንገዶች የማይማሩ ደግሞ ስሕተቶችን ሲደጋግሙና ሲጎዱበት ይኖራሉ። History is a study about past events, a period in time and space; history of individuals, institution, places, countries …

ታሪክ በኃላፊ ጊዜ ውስጥ የተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ የተመሠረተ እውነታን የያዘ ነው። የታሪክ ትምህርትም ያንን እውነታ የመፈለግ ጉዞ ነው። ነገር ግን በታሪክ ጸሐፊዎችና መምህራን የተለየ ፍላጎትና ሥውር አጀንዳ ታሪክ ከእውነታው አፈንግጦ ሊነገርም ሆነ ሊጻፍ ይችላል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ለዚህ ምሳሌ መሆን የሚችሉ በርካታ ስመ ታሪኮች ወይም የፈጠራ ትርክቶች አሉ፡፡ “. . . የኢትዮጵያን ታሪክ ጻፍን እያሉ በሐሰት የኢትዮጵያን ታሪክ አጥፍተውት በዓለም ባለታሪኮች ዘንድ ስለተዘራ ይህን የሐሰት ስብከት ሳያስቡና ሳይጠረጥሩ የኢትዮጵያ ተወላጆችም ከዓለም ባለታሪኮች እየተቀበሉ . . .”[1] በማለት የሚያስረዱን በጎ ሊቃውንም አሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ ከሚገኙ ጥቂት ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያን መካከል አንዷ ናት፡፡ ይሁን እንጂ ታሪኳ በአግባቡ ተጽፎና በምምህራን ተዘጋጅቶ ቀርቦ ትውልድ የሚጠቀምበት ሁኔታ ላይ መሥራት ብዙም አይስተዋልም ይልቁንም ከላይ እንደተጠቀሰው ታሪኳ በተለያየ መንገድ እየተበረዘ ከመሠረቱ የተለየ ሆኖ ሲተረክ ኖሯል፡፡ ምሥራታዋን በተመለከተ እንኳን ከአንደኛ ወደ አራተኛ ክፍለ ዘመን ተስቦ ይጻፋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ለ1600 ዘመናት ያህል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት ተቋም ሆና ኖራለች። በእነዚህ ዘመናት ውስጥ የኢትዮጵያ ባህል የሚጠበቅባ ማዕከል፣ የትምህርት ሥርዓትና ሂደት የሚቀረጽባትና የሚተላለፍባት ማዕከል (በዛሬው አጠቃቀም የትምህርት ሚኒስቴር)፣ የሀገር ቅርስ የሚሠራባትና የሚጠበቅባት ተቋም፣ ወዘተ. ሆና ስታገለግል ኖራለች፡፡

“The Church of Ethiopia has been the repository of Ethiopian culture for the last 1600 years of her existence. The monasteries and churches have been not only places of ascetic life but also prominent centers of learning. ..”[2] በእነዚህ ዘመናት ውስጥ የነበሩ ስኬቶች፣ ፈተናዎች፣ እና ሌሎችም የታሪኩን ቤተ ክርስቲያናዊና ሀገራዊ ተያያዥነት የሚጠቁሙ ናቸው።

የታሪክ ጥቅም

በኦርቶዶክሳዊ ክርስትና ሕይወት ውስጥ ታሪክ ከፍተኛ ጠቀሜታ ካላቸው ጉዳዮች ይመደባል። ትክክለኛና ተገቢ የሆነ አረዳድ እንዲኖረውም ይመከራል። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሃይማኖትን ከመሠረተ እምነቱ ጀምሮ የሐዋርያዊ ቅብብሎሹን ሂደትና በዘመን ያጋጠሙ ፈተናዎች የታለፉበትን ሁኔታ ጠንቅቆ ለመረዳት የሚያስችል ታላቅ አስተዋፅኦ አለው። (Alexander Shememann, The Historical Road of the Eastern Orthodoxy, 2003, 3) ቤተ ክርስቲያን ያለፈችባቸውን የታሪክ መስመሮች ለይቶ ያወቀ ሰው በዛሬ ሕይወቱ እንቅስቃሴዎች ሁሉ አብነቶች አሉት። እውነተኛውን ታሪክ በፈጠራ ከሚነገሩት ለይቶ ለመጠቀም ዕድል ያገኛል፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ታሪክን በልዩነት አክብረው የሚመለከቱበት ምክንያትም አርአያነት ያላቸውንና በሕይወት የቀደሙ ምስክሮችን ማግኘት የሚቻልበት ስለሆነ ነው። ከእኛ የቀደሙ አበው የሠሯቸውን ሥራዎች፣ ተገድሏቸውንና የቅድስና ሕይወታቸውን መማር የምንችልበት ታሪክ ነው (Timothy Ware, The Orthodox Church, 2015, 1.) “The study of history is the best medicine for a sick mind” [የታሪክ ጥናት ለሕመምተኛ አእምሮ ፍቱን መድኃኒት ነው] (Livy/ሊቪ)።

ታሪክ ከማንነት ግንባታ መሠረቶች አንዱ ነው፡፡[3] ፕሮፌሠር ጌታቸው ኃይሌ ይህንን በተመለከተ ከጻፉት ብናነሣ፤ ደግሞ የሚከተለውን እናገኛለን።

አእምሮዬ፤ ሃይማኖትን ካደገበትና በጥልቀት ከተጣመረበት ባህል ለይቶ ሊረዳው አይችልም። እንደ አስተሳሰብ እና ባህል፤ ሃይማኖት ለሀገር ፍቅር፣ ለብሔራዊ ስሜትና ለግል ማንነት መሠረት ኾኗል። ሃይማኖትን መጉዳትና ከባህላዊው ጥምረት እንዲላቀቅ ማድረግ እነዚህን ሁሉ የማንነት ገበያዎች መጉዳት ነው። ይህም ወሳኝ ትስስርን ከማጥፋት እና በሌሎች ሰዎች የሕይወት ውሎች ላይ አዲስ ትስስር ለመፍጠር ከመጣር ጋር ተመሳሳይ ነው። ሁሉም ሰዎች እንደዚህ ላሉት ሙከራዎች ያላቸው ስሜት የጠላትነት ነው። ለምሳሌ፤ የካቶሊክ ፓትርያርክ [ነኝ ያለው] ሜንዴዝ በ1626 ኢትዮጵያ የዘመናት ሥርዓቷን (ባህሏን) ትታ የካቶሊክ (ላቲን) የአኗኗር ዘይቤ እንድትከተል በጠየቀ ጊዜ ህዝቡ ምን ዓይነት ምላሽ እንደሰጠ ሁላችንም የምናውቀው ነው።[4]

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የሃይማኖት አቋም ለማወቅ በምናደርገው ጥረት ውስጥ ታሪክ የላቀ ጠቀሜታ አለው። በታሪክ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ለዛሬ ህልውናዋ ትናንት ያለፈችባቸው ኹኔታዎች ምን እንደነበሩ ይታወቃል። በግለሰብ ደረጃ የሚገለጸውን ያህል፤ በቤተ ክርስቲያንም የዛሬ ማንነት መሠረት በታሪክ ውስጥ አለ። ነገሩ፤ “ አንተ ዛሬ የኾንከው ማንነትህ የተሠራው በታሪክህ ነው” እንደሚባለው ነው። “To understand the Orthodox Church is to understand how it has become what it is. … In this way, church history can be a privileged means of access to the inner truth of Christian confession. As for an individual so for a church, your history makes you what you are.”[5]

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የታሪክ መሠረት

“ወስሙ ለካልእ ፈልግ ግዮን ፡ ወውእቱ ዘየዐውድ ኲሎ ምድረ ኢትዮጵያ _ የኹለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ኹሉ ይከብባል” (ዘፍ. ፪፥፲፫)

የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው ኦርቲ ዘፍጥረት ውስጥ ኢትዮጵያ በዚህ መልኩ ተጠቅሳ ትገኛለች፡፡ ግዮንም አስፈላጊ በኾነ መጠቁም ስሙ የተነሣ ሲኾን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥቅሱን የተመለከተ የሊቃውንት ትርጓሜ “ይኸውም ዓባይ ነው” በማለት ያሳየዋል።[6] በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በቅርቡ ከተደረጉ ጥናቶች መካከል የሚከተለው ሐሳብ የተሠነዘረበት አንዱ ነው፡ “የግዮን ወንዝ የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል ይህም ሊኾን የሚችለው ጥቁር ዓባይ ነው። ምንም እንኳ ፊሶንና ግዮን የሚሉት ስሞች ጥንት የጠፉ ቢኾንም፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዋቢዎች በብርቱ እንደሚጠቁሙት፣ እነዚህ የኤደን ወንዞች በእርግጠኝነት ከኢትዮጵያ ተነሥተው በዛሬዋ ሱዳን በኩል የሚፈሱት ወንዞች ናቸው።”[7] ዮሲፈስም ግዮን ዓባይ በመኾኑ ላይ ስምምነቱን “በግብፅ ውስጥ የሚፈሰው፣ ማለትም ከተቃራኒው ዓለም የሚመነጨው፣ ግሪኮች ናይል የሚሉት ነው” እያለ አስፍሯል።[8]

እነዚህና መሰል በርካታ መረጃዎች ኢትዮጵያ ከብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓት በይፋ ወደኢትዮጵያ መግባት በፊት በሕገ ልቡና እግዚአብሔርን ሲያመልክ የነበረ ሕዝብ ሀገር መሆኗን ይጠቁማል፡፡ “ከሕገ ኦሪት በፊት ኢትዮጵያ ስለ ነበረችበት እምነት ብዙ ሰዎች በጻፉት ታሪክ ውስጥ እምነትና ክህደት ያወራሉ። . . . ኢትዮጵያ ፈጣሪን እንጂ ከቶ ፍጡርን ያመለከችበት ጊዜ የለም። ነገር ግን፤ የጽሑፍ ውሳኔ በሌለው ሕግ [ሕገ ልቡና] በሥነ ፍጥረት እየተመራመረች ፈጣሪዋን መፈለጓና መከተሏ እርግጥ ነው”[9]

ከንግሥተ ሳባ እና ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር የተያያዘው የክብረ ነገሥት ታሪክ ደግሞ ብሉይ ኪዳን በይፋ ወደ ኢትዮጵያ ለገባበት ታሪክ ተጠቃሽ ነው። የንግሥተ ሳባ ጉዞና ዝርዝር ሁኔታዎቹ የቀደመውን የሕገ ልቡናውን ነገር ይጠቁማሉ። የልጇ ቀደማዊ ምኒልክ ወደ አባቱ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ያደረገው ጉዞ ደግሞ ታቦተ ጽዮን በፈቃደ እግዚአብሔር ወደ ኢትዮፕያ ከመጣችበት ሁኔታ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በሃይማኖት ታሪካችን ውስጥ ጉልህ ለውጥ ካመጡ ጉዳዮች የሚመደብ ነው፡፡ ይህም ብቻውን በነጠላ ታሪክነት የሚነሣ ሳይሆን ከቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ መጀመር፣ ከባህልና ሥርዓት፣ እንዲሁም ከሌሎች ዛሬም ድረስ ተጠብቀው ከሚገኙ ገጽታዎች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹ፡

ግዝረት

ሕጻኑ በተወለደ ስምንተኛው ቀን መፈጸሙ ብሉይ ኪዳናዊ መሠረቱን ይነግረናል፡፡ (ዘፍ 17፡10፤ ዘጸ 12፡48…) ኢትዮጵያውያን የሥርዓቱን መነሻ እንደተጠበቀ ለክርስትናው ልዩ ገጽታ የሆነውን የብሉይ ኪዳን ሥርዓት ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል አድርገውታል፡፡ የሚከተለው ከሚሽነሪዎች ጋር ከተደረገ ክርክር በኋላ በዓጼ ገላውዴዎስ ዘመን የተያዘ አቋምም ለዚህ ምስክር ነው፡

“ወበእንተ ሥርዓተ ግዝረትኒ አኮ ዘንትገዘር ከመ አይሁድ። እስመ ንኅነ ነአምር ቃለ ምህሮሁ ለጳውሎስ . . . ዘይቤ ተገዝሮሂ ኢይበቁዕ ወኢተገዝሮሂ ኢያሠልጥ . . . ወባሕቱ ግዝረትሰ ዘኮነ በኀቤነ በልማደ ሀገር ከመ ብጥኀተ ገጽ ዘኢትዮጵያ ወኖባ” ማለታቸውን እናያለን። የግዝረትን ሥርዓት በተመለከተ፤ እንደ አይሁድ የምንገዘር አይደለንም። መገዘርም ኾነ አለመገዘር አይጠቅምም አይጎዳም የሚለውን የጳውሎስን አስተምህሮ እናውቃለንና። ነገር ግን በእኛ ኢትዮጵያውያንና ኑብያውያን ዘንድ ባህል/የሀገር ልማድ ነው ሲሉ ነው።”[10]

የቀዳሚት ሰንበት አከባበር

ምንጩ ከአይሁድ የተገናኘ ቢኾንም፤ አከባበሩ ከአይሁድ የሰንበት አከባበር ሥርዓት በእጅጉ ይለያል። እነርሱ ከምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ተቆጥበው፣ በጎ ሥራንም ቢኾን እንኳ እንደ ተወገዘ ተግባር ቆጥረውና ተከልክለው ያከብሩታል። ይህ ድርጊታቸው በጌታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስም የተነቀፈ ነው (ማቴ ፲፪፥፩-፲፬)። ይህን ሁሉ ቀደምት ኢትዮጵያውያን በዝርዝርና በጥራት ያውቁት፣ ያስተምሩትም ነበር። ክርስቲያናዊ አስተምህሮን ሥርዓትና ሕግን ጠብቆ እንዲከበርም አድርገውታል። ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ፤ “በዝንቱ ድርሳን ዘይሰመይ መጽሐፈ ብርሃን ጸሐፍነ ክብረ ክልኤሆን ሰንበታት በከመ ተአኃዛ በበይናቲሆን ከመ ኢይባእ ማእከሌሆን ግብረ እድ እምተግባረ ዓለም . . .” እንዳሉ ለመንፈሳዊ ተግባር ሊሰጥ ከሚገባው ጊዜ ጋር አያይዘው የኹለቱንም ሰንበታት ክብር ከተፈቀዱና ከተከለከሉ ተግባራት ጭምር ዘርዝረዋል። ይህም ማለት በጎ መሥራትን የማይከለክል በይዘቱ ክርስቲያናዊ የኾነ የሰንበት አከባበር በኢትዮጵያ የሚገኝ መኾኑን በግልጽ ያሳያል።

ሥርዓተ መባልዕት

ቅድመ ክርስትና በነበረው የሃይማኖት ሁኔታ ኢትዮጵያውያን የብሉይ ኪዳን ሥርዓትን ጠብቀው ለመኖራቸው ሌላኛው ምስክር የመባልዕት ሕግና ሥርዓት ነው፡፡ ይህም በዘሌዋውያን ከተደነገገው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ ፲፩፥፩-፵፯፣ ዘዳግም ፲፬፥፫-፳፩ የተከለከሉትን፣ ሰኮናቸው ያልተሰነጠቁና የማያመነዥኩ እንደ አሳማ ያሉ እንስሳትን ሥጋ አይበሉም”[11]

የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አሠራር (ሦስቱ ክፍሎች፡ ቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስት መቅደስ ከብሉይ ኪዳን ደብተራ ኦሪት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ናቸው)፣ አልባሳተ ክህነት፣ ንዋየ ማኅሌትና ሥርዓተ ማኅሌት፣ እነዲሁም በባሕላችን ውስጥ ያሉ ጥንታውያን በጎ ዕሤቶች ሁሉ ተጨማሪ ምስክሮች ናቸው፡፡

“በሕዝቡ የኑሮ ሥርዓትና ሃይማኖት ስሜት፣ በኃዘንና በደስታ ጊዜ ያለው ሁኔታ፣ የበዓላት አከባበር፣ የሴቶችና የሕፃናት ጌጣጌጥ ሁሉ የብሉይ ኪዳንን ሥርዓት . . . የሚያሳይ ነው። በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ የማኅሌት ሥርዓት የካህናቱ ልብሰ ተክህኖ፣ ካባው፣ መጠምጠሚያው የታቦቱ ክብርና ሌላውም ሁሉ ከብሉይ ኪዳን ሥርዓት ጋር ይመሳሰላል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው ከክርስትና በፊት ኢትዮጵያ የብሉይ ኪዳን ሀገር እንደ ነበረች ነው። በሌሎች ከአረማዊነት በተመለሱ ሀገሮች . . . ይህ ሁሉ አይታወቅም፡፡”[12]

ይቀጥላል!

 

 

 

[1] አስረስ የኔሰው፣ ትቤ አክሱም መኑ አንተ፣ 1951፣ 1፡፡

 

[2] The Church of Ethiopia: A Panorama of History and Spiritual Life, 1970, iii.

[3] Shang-Hui Shin, National Identity and National History: Role of Historical Narratives on Identity Construction, 2011, I. (PhD. Diss.

[4] Getachew Haile, Aasulv Lande and Samuel Ruberson, eds. The Missionary’s Dream: An Ethiopian Perspective on Western Missions in Ethiopia: Papers From A Symposium on the Impact of European Missions on Ethiopian Society,, in The Missionary Factor in Ethiopia, 1996, 3.

[5] Aidan Nichols, Light from the East: Authors and Themes in Orthodox Theology, 1995, 1.

[6] መጻሕፍተ ብሉያት ክልዔቱ፣ 1999፣ 24፡፡

[7] Gert Muller, Eden: The Biblical Garden Discovered in East Africa, 2013, kindle edition.

[8] Josephus, Jewish Antiquities: I:35-39, (V.I-IV) (With an English Translation by H. ST. Thakeray)

[9] አለቃ አያሌው ታምሩ፣ የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት፣ 1953፣ 35 – 36፡፡

[10] ተክለ ጻድቅ መኵሪያ፣ የግራኝ አሕመድ ወረራ፣ 1966 ዓ.ም፣ 775-776። Edward Ullendorff, Ethiopia  and the Bible, 1967, 106

[11] የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም.፣ 2000፣10።

[12]  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣1991፣ 14 -15።

ነገረ መላእክት

«መላእክት» የሚለው ቃል «ለአከ…ላከ» ከሚለው የግእዝ ሥርወ ግሥ የተገኘ ቃል ነው፤ ትርጕሙም እግዚአብሔርን ያለማቋረጥ የሚያመሰግንኑ ኀያላንና ረቂቃን መልእክተኞች ማለት ሲሆን «ነገር» የሚለው የግእዝ ቃልም፡- ሐሳብንና ምሥጢርን በጽሕፈት በአንደበት መግለጥ፣ በንባብ ማስጌጥ፣መልክ እያወጡ፣ ምሳሌ እየሰጡ ማብራራት ማለት ነው፡፡ /ኢሳ.6፥2፣ መጽ ሰዋ.ወግስ/

«ነገረ መላእክት» የሚሉት ሁለቱ ጥምር ቃላት ደግሞ የቅዱሳን መላእክቱን ተፈጥሮ፣ ክብር፣ ሀልዎት፣ አገልግሎት፣ ሥልጣን፣ ኀይልና ዕውቀት በስፋት የሚያጠናው ትምህርተ ሃይማኖት የሚብራራባቸው የተዋቡ ቃላተ ጽድቅ ናቸው፡፡

በመሆኑም በእግዚብሔር ፊት የተመረጡትን፣ የራሳቸውን አለቅነት በመጠበቅ የሚኖሩትን ቅዱሳን መላእክት ትምህርተ ሐተታ በሚቀጥሉት ንዑሳን አርእስት፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት በቅደም ተከተል እናያለን፡፡ /1.ጢሞ.5፥21፣ ይሁ..6/

ተፈጥሮተ መላእክት፡-

የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን ሲፈጥር እንደ ሰው በነቢብ በገቢር ሳይሆን በአርምሞ ነው፡፡ የተፈጠሩበትም ዓላማ እግዚአብሔርን ለማመስገን፣ የሰውን ልመና፣ ጸሎት፣ ንስሐ ወደ እግዚብሔር፣ የእግዚአብሔርን ምሕረትና ይቅርታ ወደ ሰው ለማድረስ ነው፡፡ /መዝ.90፥11፤103፥4/

መላእክትን በነገድ 100 አድርጎ ለአንድ ውዳሴ እና ቅዳሴ እና ቅዳሴ፣ለአንድ ኅብረትና ለአንድ ሃይማኖት፣ አንድ ጥበብ ባለበት ኅብረት ይኖሩ ዘንድ ፈጥሯቸው የነበረ ቢሆንም አንዱ ነገድ በራሱ ምርጫ ዓመፅን ሠርቶ፣ ከሉዓላዊ ክብር፣ ከመላእክት ማኅበር ተለይቶ እስከ ተላቁ ፍርድ ድረስ ከጨለማ በታች በእሥራት ለዘላለማዊ ውርደት ተዳርጓል፡፡ /2.ጴጥ.2፥2፣ራእ 12፥7-10/

በዕለተ እሑድ ሲፈተኑ «ንቁም በበህላዌነ እስከንረክቦ ለአምላክነ…አምላካችንን እስክናገኘው ድረስ በያለንበት ሆነን እንጽና» በሚለው አዋጅ በጽናት የለፉት 99ኙ ነገደ መላእክት ግን በማይናወጥ ኅሊና ለተፈጠሩለት ዓላማ በመታመን በአንድነት ጸንተዋል፡፡/አክሲማሮስ ዘእሑድ/

ተፈጥሯቸውም «ግብር እምግብር…ከተፈጠረ የተፈጠረ» ሳይሆን ያለምንም የፍጥረት ግኝት እምኀበ ወኢምንት ግብር /ካለመኖር ወደ መኖር/በርቀት የተፈጸመ መሆኑ ግልጥ ነው፡፡ /ሮሜ4፥17/

ከተልእካ ፍጥነተቸው፣ ከማይደክመው ኀይላቸው አንጻር በቅዱስ መጽሐፍ «ዘይሬስዮሙ ለመላእክቲሁ መንፈስ ወለእለ ይትለአክዎ ነደ እሳት…መላእክቱን መንፈስ፣ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸው» ተብሎ ይጻፍ እንጂ ቅዱሳን መላእክት ከባሕርያ ነፋስና ከባሕርያ እሳት አልተፈጠሩም፡፡ /መዝ104፥4/

ከነፋስና ከእሳትም እንዳልተፈጠሩ “እመሰ ተፈጥሩ እምነፋስ ወነድ እሞቱ ወእማሰኑ ከማነ… ከእሳትና ከነፋስ ተፈጥረውስ ቢሆን እንደእኛ በሞቱ በጠፉም ነበር”ተብሎ ተጽፏል፡፡ /መጽ፣ አክሲማሮስ/

ከተፈጠረ የተፈጠረ ሁሉ ይራባል፣ ይጠማል፣ ያረጃል፣ ይታመማል ይሞታል፡፡ መልእክት ግን በተፍጥሮአቸው የማያረጁና የማይመቱ ሕያዋን ስለሆኑ አይራቡም፣ አይጠሙም፣ አይታመሙም፣ ለዘመናቸውም ፍጻሜ አይነገርለተም፡፡

ኢመዋትያን መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ወአልባሙ መፍቅደ መብልዕ ሥጋዊ እስመ ኢካኑ ሥጋውያን … ረቂቃን መናፍስት እንጂ ግብር እምግብር የተፈጠሩ ግዙፋን አይደሉምና ሥጋዊ መብልንና መጠጥን መሻት በባሕርያቸው የለባቸውም፡፡ /ሃይ.አበ.36፥36፣ዜና ስክንድስ/

«ወሲሳዮሙኒ ለመላእክት ቅዳሴ ወስብሐት ወስቴሆሙኒ ፍቅረ መለካት… የመላእክት ምግባቸው ፈጣሪያቸውን ማመስገን፣ መጠጣቸውም የአምላካቸው ፍቅር ነው» ተብሎ መጻፉ የታመነና መጽሐፋዊ ምስክርነት ያለው እውነታ ነው፡፡ /መጽሐፈ አክሲማሮስ/

ሀልዎተ መላእክት፡-

በባሕርያቸው ኢ-መዋትያን ሆነው የተፈጠሩት፣ ለዘላለም አኰቴት /ምስጋና/ ጸንተው የሚኖሩት ቅዱሳን መላእክት የማይዳሰሱ ረቂቃን ቢሆኑም የማይለወጥ አካላዊ ህልውና አላለቸው፡፡ ለመንፈስ ሥጋና አጥንት ባይኖረውም ሀልዎተ መላእክት በረደኤተ ጻድቃን፣ በቅዱሳት መጻሕእት የተረጋገጠ ረቂቅ አካላዊ ህልውና ነው፡፡/ሉቃ 4፥39/

ዮሐንስ ዘደማስቆ የተባለው አባት ይኽን ሲያብራራ፡- «መላእክት ረቂቃን ናቸው የምንላቸው ከእኛ አንጻር ነው እንሀዳ ከማንም ጋር ከማይነጻጸተው ከእግዚብሔር አንጻር ሲታዩ ግን ግዙፋን ናቸው»ብሏል፡፡

ከፈጣሪያቸው አንጻር ግዙፋን ናቸው ቢባልም የወንድሃ የሰት ምልክት፣ አጥንት፣ ሥጋና ጅማት የሌላቸው ረቂቃን፣ የማያንቀላፉ ትጉሃን፣ የማይደክሙ ጽኑዓን ፍጥረታት ናቸው፡፡

«እነዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው» የተባሉበት፣ እነደ ፀሐይ ደምቀው ከሰማይ ሲወርዱ የተዩበት ህልውሃቸውን የሚገልጠው፣ ግሩምና ድንቅ የሆነው አሰተርእዮ /መገለጥም/ በታላቁ መጸሐፍ ተመዝግባ ይገኛል፡፡ /ዘፍ32፥1-2፤ ዳን10፥6፤/

በመሆኑም በኀይል ብርቱዎችና በህላዌ ኢ-መዋትያን የሆኑት የብርሃናውየን መላእክቱ ህልውና በእውነተኛ ተፍጥሮ የተገኘ ክብርን የተሞላ እውነታ እንጂ የምናባችን ውጤት አይደለም፡፡

አለቅነተቸውንና ቦታቸውን የጠበቁት የቀዱሳን መላእክት ህልውና በዚህ መልኩ የሚገለጥ ቢሆንም በአንድ ጊዜ በሁሉም ቦታ የሚገኙ ምሉዓን አይደሉም፡፡

በአንድ ጊዜ ሁሉም ባታ ላይ እነደማይገኙም “እሙንቱሰ ሶበ ይትፌነው ለመልእክት ይትኀጥኡ እመካኖሙ…እነርሱስ መልእክት ለማድረስ በተላኩ ጊዜ ከቦታቸው ይታጣሉ”በማል ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ ገልጣታል፡፡/ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ/

ነገር ግን መላእክት በጊዜ በቦታ የሚወሰኑ፣ በመጠንና በልክ የተፈጠሩ ፍጡራን ቢሆኑም በሑሰት /በአሉበት ቦታ/ ሆነው በሌላው ቦታ ያለውን ሁኔታ የማየት፣የቦታ ርቀት ሳይጎርዳቸው የመረዳት ጸጋ የተሰጣቸው ግሩማን ፍጥረታት ናቸው፡፡/መጽ.መነኰሳት/

በመላእክት ህልውና ማመን ከፋርሶችና ከባቢሎናውያን ተወርሶ ወደ አይሁድ እምነት የገባ «የብዙ አማልክት ተረፍ ነው» በሚል አሰተሳሰብ በትንሣኤ፣ በመልአክና በመንፈስ መኖር እንደማያምኑት ረሲዓን /ዝንጉዎች/ ዛሬም በዚህ ዘመን የመላእክትን የምልጃ አገልገሎትና ህልውሃ የማይቀበሉ ስሑታን አሉ፡፡ /ሐመረ ክርስትና በመዋገደ ፍልስፍና/

ነገር ግን በምርጦቹ ቃል ኪዳን የምተምነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከቅዱሳት መጻሕፍት የተመነ ምስክርነት የተነሣ የቀዱሳን መላእክትን ህልውሃ አምና ታስተምራለች፡፡ /መዝ 86፥/

ለመታሰቢያም በስማቸው ሕንጻ ቤተክርስቲያን አንጻ፣ ታቦተ ሕግ ቀርጻ፣ መጻሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ ክብራቸውን፣ አገልግሎታቸውን፣ቀል ኪዳናቸውን እና ተራዳኢነታቸውን የሚያስተምረ ድርሳናቸውን ጽፋ በዓላቸውን ተከብራለች፡፡

የመላእክት ምልጃና ምስጋና፡-

ትጉሃን የማያንቀላፉት፣ ቅዱሳን መላእክት መልኩ በረድ በሚመሰለው መነበረ ስብሐት ያለ ድካም እንበለ ዕረፍት፣ አርምሞ ዕርዐት በሌለበት ፈጣሪያቸውን የሚያገለግሉ፣ ስለእኛ የሚማልዱ ኃያላን ፍጥረታት ናቸው፡፡ /ዕብ.1፥14/

ለአገልግሎትም ሲላኩ ሶበሰ ይወርዱ መላእክት እምሰማይ ዲበ ምድር አልቦሙ ድምፅ በኢይሰማዕ ድምፀ ክነፊሆሙ… መላእክት ከሰማይ ወደ ምድር በማወርዱበት ጊዜ ድምፅ የላቸውም፣ የክንፋቸው ድምፅም አይሰማም፡፡ ይቀልል ሩጸቶሙ እምነፋሳት…ሩጫቸውም ከነፋሳት ይልቅ የፈጠነ ነው፡፡/ራእይ 18፥1፣ ቅዱስ ያሬድ/

የዓለመ መንፈስ አካል የላቸው ብርሃናውያን መላእክት ወደ ላይ እስከ ጽርሐ ዓርያም ወደታች እስከ በርባሮስ ከመ ቅጽበተ ዓይን /እነደ ዓይን ጥቅሻ/ ደርሰው፣ መልእክታቸውን ፈጽመው ወደ ቦታቸው ይመለሳሉ፡፡ /ቅዱስ ኤጲፋንዮስ/

ለአገልግሎት ሲንቀሳቀሱም ከአካላቸው ረቂቅነት የተነሣ መገፋፋት እንደሌለባቸው ወየሐውር መልአክ በመልአክ.. መልአክ በመልአክ የልፋል፡፡/አክሲማሮስ/

በምልጃቸው የምናምነውን ሁሉ የሚጠብቁን፣ በኃጢአት ስንወድቅ «ለዛሬ ተዋት» እያሉ ስለእኛ መዳነ የሚማልዱልን፣ በእኛ ንስሐ መግባት በሰማያት ምስጋና የሚያቀርቡና ደስ የሚሰኙ ርኅሩኃን ፍጥረታት ናቸው፡፡ /ሉቃ.13፥7-9፣15/

በመሆኑም የመላእክት አገልግሎት፣አማላጅነት፣ተራዳኢነትና ሀልዎት ከ273 ጊዜ በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰ ጥንታዊሃ ሐዋርያዊ መሠረት የለው ርቱዕ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ነው፡፡

ከምልጃ አገልገሎተቸውም ጋር ምስጋናቸው አርምሞ ጽርዐት የሌለበት ሲሆን “ዘወትር በዙፋኑ ዙሪያ ሆነው ያመሰግኑታል የማያርፉ መላእክትን ሁሉ በፊቱ ቆመው ሲየመሰግኑ ዓይኖቼ አዩ” ብሎ ረኣዬ ኅቡኣት /የተሰወረውን የሚያየው /ሄኖክ በዚህ መልኩ ገልጣታል፡፡/ራእ 4፥4-11/

ቅዱሳን መላእክት ፈጣሪያቸውን ሲያመስግኑ፣ሰውንና እግዚአብሔርን ሲያገለግሉ ተልእኳቸውን ዐውቀው የሚወጡ የሚወርዱ ስለሆነ «አልባቱ መልአክ ለመልአክ∙∙∙ለመልአክ» ደክሞሃል ብሎ የማየጸናው፣ውጣ ውረድ ብሎ የሚያዘው መልአክ የለውም፡፡/ድር∙ቄር∙61፥1/

የአገልግሎታቸው ኅብረ መልክም ልዩ ልዩ ነው፡፡ በየማዕረጋቸው፣ በየሠራዊተቸው፣ በየሥርዓታቸውና በየስማቸው የሚጋርዱ፣ የሚከቡ፣ የማያጠኑ፣ የሚዘምሩ፣ በልብ የሚየመሰግኑ፣ በቃል የሚያመሰግኑ ስፍር ቁጥር የሌላቸው በመንበሩ ዙሪያ የሚሰለፉ የቅዳሴ ማኅበርተኞች ናቸው፡፡ /ቅዱስ አትናቴዎስ/

ቁጥራቸው እልፍ አእላፍ የብዙ የሆነው ሰባሕያን መላእክቱ ከላይ በራእየ ሄኖክ እንደተገለጠው ቅዱስ ዮሐንስም «ወሰማዕኩ ቃለ መላእክት ብዙኃን በዓውዱ ለውእቱ መንበር∙∙∙ በዚያ መንበር ዙሪያ የመላእክትን ቃል ሰማሁ፤ የአራቱ እንስሳንና የ24ቱን ሊቃናት ድምፅ ሰማሁ፣ ቁጥራቸውም እልፍ አእላፍ የብዙ ብዙ ነው፤ በተላቅ ቃል ባዕል፣ ጠቢብ፣ ጽኑዕ፣ ንጉሥ፣ ክቡር፣ ስቡሕ፣ ቡሩክ መባል፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይገባዋል አሜን እያሉ ሲናገሩ ሰማሁ» በማለት አብራርቶታል፡፡/ራእ∙5፥12/

ከማያቋርጠሙ ምስጋና ጋር በየማነ ምስዋዕ /በመሠዊያው ቀኝ/ቆመው «እለ ይስእሉ ምሕረተ ለውሉደ ሰብእ∙∙ለሰው ልጆች ሁሉ ምሕረትን የሚለምኑ፣ ለነፍሳት መዳን የሚቆሙ» ለይቅርታ የተዘጋጁ፣ ለምሕረት የሚላኩ ናቸው፡፡ /ሉቃ 1፥11-2ዐ/

በአምላካቸው ፊት በባለሟልነት የሚቆሙት፣ጸሎተ ቅዱሳንን የሚያሳርጉት ቅዱሳን መላእክት ምልጃ ለሰው ብቻ ሳይሆን «ለእንስሳ ሣዕረ ለሰብእ ተግባረ∙∙∙ለእስሳ ሣርን፣ለሰው በጎ ተግባርን» ይለምናሉ የሰውን በጎ ሥራ ሁሉ ያሳርጋሉ፡፡/ቅዱስ ጋሬድ/

ለዘለዓለም ያለ ድካም የለ ዕረፍት ቅዱስ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ይኖራሉ፡፡ ምስጋናቸው እና ጸሎተቸውም ሁል ጊዜም በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ ነው፡፡/ኢሳ∙6፥1-5፣ራእ 4፥8/

ክብረ መላእክት፡-

በተለየ ክብር የማማለድና የመተደግ ሥልጣን ያላቸው በባለሟልነት በእግዚአብሔር ፊት የማቆሙት መላእክት ንዑዳን ክቡራን፣ ረቂቃንና ምሉዓነ ኀይል ናቸው፡፡ /ሉቃ∙1፥∙∙1∙ጢሞ 5፥21/

ሰዎች ድኅነትን በሚየገኙ ጊዜ ደስ የሚሰኙት ብርቱዎቹና ኀያላኑ የከበሩት መላእክት የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱ ጋር በክብሩ ዙዳን ይቀመጣሉ፡፡/መዝ∙1ዐ3፥2ዐ፣ማቴ∙25፥31/

ፍጥረተ ሰብእ በከተማ ኀጢአት እንዳይጠፋ በማያደርጉት ትድግና፣በትሕትናቸው በአገኙት ልዕልና ለዘላለም የከበሩ ብርሃናውያን ናቸው፡፡/ዘፍ∙19፥15፣ቅዱስ ያሬድ/

ቅዱሳን መላእክት ድል ነሺዎቹና ለራሳቸው ክብር የማይኖሩት የከበሩት ፍጥረታታ የሚሰግዱላቸውና የከበሩ መሆናቸውበቅዱሳት መጻሕእት የተመዘገበ፣ በእውነት ያለ ሐሰት የተረጋገጠ ነው፡፡ /ራእ 19፥1ዐ/

«የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል ከመንግሥቱም እንቅፋትን ዓመፃን የሚያደርጉትን ሁሉ ይለቅማሉ፣ ከዐራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን በክብር ይሰበስባሉ»ተብሎ እራደተጻፈው በክብራቸው የተመረጡትን ለክብር ይሰበስባሉ፣ ዓመፀኛውንም ለይተው ለዘላለም ፍርድ ያቀርባሉ፡፡/ማቴ∙13፥41፣24-31/

ክቡራን መላእክቱ ሰውን ከሚያስጨንቀው፣ ከክብር ከሚያሳንሰው ነገር እና ዝንጋዔ የራቁ፣ ባለአእምሮ የኾኑ፣ ዕውቀት የላቸው፣ ይዋሄንና ትዕግሥትን ገንዘብ ያደረጉ፣ ለዘለዓለም በማይነጥፍና በማያቋርጥ ዘወትር እንደዥረት ውኃ በሚወርድ ምስጋና ይኖራሉ፡፡ በመሆኑም የቀዱሳን መላእክት ክብራቸው ታላቅ ስለሆነ ኀጢአጽ ስንሠራ ይቅር የማይሉ ናቸውና እንዳናስመርራቸው በፊታቸው ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ /ዘጸ23፥2ዐ/

የመላእክት ኅይልና ሥልጣን፡-

የቅዱሳን መላእክት ኀይልና ሥልጣን ምንጩ ገባሬ መላእክት እግዚአብሔር ነው፡፡/2∙ጴጥ∙2፥11/ የእግዚአብሔር ስም በእነርሱ የሆነላቸው መላእክት የሥልጣናቸውና የኀይላቸው መጠነ ክሂል «በፊቱ ተጠንቀቁ ፣ቃሉንም አድምጡ ኀጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልም» በሚል የተገለጠ፣ማንም ሊሽረው የማይችለው ሥልጣን መሆኑ የታወቀ ነው፡፡/ዘጸ 23፥2ዐ/

የመላእክቱ ኀይልና ሥልጣን በግብር ሲታይ ለተቀበሏቸው የምሥራች፣ ምሕረትን፣ ከእስራት መፈታትን የሚያድል፣ ክብርንና ሞገስን የሚያሰጥ ሲሆን በጊዜው የሚፈጸመውን ቃል /ነገር/ ለማይቀበሉት ደግሞ ዲዳ እስከመሆን የሚያደርስ፣ ለእግዚአብሔርና ለመላእክቱ ክብር ባልሰጡ መጠን በእደ መላእክት ተመትቶ፣ በትል ተበልቶ መሞትን ያስከትላል፡፡ /ሉቃ 1፥19፤የሐ∙ሥ 12፥23/

የመላእክቱን ኀይልና ሥልጣን ማከበር የሚያሰደንቀውን እንዲህ ያለ ሥልጣን የሰጠውን እግዚአብሔርን ማከበር ነው፡፡ /ማቶ 9፥8/ ይህም ሥልጣን ለመላእክት የተሰጠው ፍጥረተ ሰብእን ለመጠበቅና ለማገልገል ነው፡፡ክቡር ሆኖ የተፈጠረው የሰው ልጅ ሲፈጠር ጠባቂን አይሻም ነበር፡፡

ሰው በኃጢአት ከወደቀ በኋላ ግን እግዚብሔር መላእክትን ጠባቂ አደረገለት፡፡ ምክንያቱም ዲያብሎስ ሰውን ለማጠፋት ሁል ጊዜ ምክንያቶችን ስለሚፈልግ ነው፡፡/ቅዱስ ጎርጎርዮስ/

በመሆኑም መጎደላችን ከሥጋና ከደም ጋር ሳይሆን ከመንፈሳዊ ክፋት ኃይላትና ከጨለማ ገዢዎች ጋር ነውና ቅዱሳን መላእክት በሰይጣን እንዳንታለል የሚጠብቁን፣ ይልቁንም የእግዚአብሔርን ፍቅርና እንክብካቤ በምናይበት ሁኔታ ያለመታወክ በጸጥታ ኖረን መዳንን እንወረስ ዘንድ በረድኤታቸው የሚያግዙንና የሚያገለግሉ መናፍስት ናቸው፡፡/2ቆሮ 2፥11፤ዕብ 1፥11/

ነገር ግን ሰይጣን ራሱን የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና በመላእክትና በአጋንንት መካከል የለውን ልዩነት ማወቀ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡/2ቆሮ 11፥14-5/

ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራን እግዚአብሔር በዘመን ፍጻሜ ወደ እርሱ እስኪጠቀልለነ ድረስ በማያሰናክለው ዓለም ስንኖር የሚረዱንን ቅዱሳን መላእክት በተመለከተ የተሟላ መንፈሳዊ ዕውቀት ያስፈልገናል፡፡

ለማወቅም «ወአንተሰ ለእመ ትፈቀድ ታእምር ኀድግ ኅሊና ዘበምድር ∙∙∙አንተ ግን ማወቅ ከፈልግህ ምድራዊ አስተሳሰብን ተው» ተብሎ ተጽፏል፡፡/1ጴጥ 5፥1ዐ፤ ኤፌ 6፥12፣ ቅዱስ ያሬድ/

በአጠቃላይ የምድራዊ አሰተሳሰብን በመተው የምንረዳው የመላእክት ተልእኮ በጥቅሉ ሲገለጥ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሆነው የሰውን ጸሎት፣ ምጽዋትና ምሥዋዕት ማሳረግ፣ በመከራና በችግር ጊዜ ለተራዳኢነት ወደ ሰዎች መላክ፣ ሰዎች ዘዚህ ዓለም በሞት ወደ እግዚአብሔር ሲሄዱ ነፍሶቻቸውን ወደ እርሱ ማቀረብና በፍጻሜ ዘመንም ኀጥዓንን ከጻድቃን ለመለየት የሚላኩ ናቸው፡፡ /ማቴ∙24፥31፤ሐዋ2፥7፤ሮሜ∙9፥22/

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

 

 

 

 

ዕቅበተ እምነት

በመምህር ሽፈራው

ምንነትና ይዘት

ዕቅበተ እምነት የሚለውን ተናባቢ የግእዝ ሐረግ፣ ሃይማኖትን መጠበቅ፣ መከላከል፣ ወይም የሃይማኖት ጥበቃ በሚል የአማርኛ ቀጥተኛ ፍቺ ይታወቃል። ዕቅበተ እምነት ሁለት ተናባቢያን ቃላት፣ ከሁለት የተለያዩ የግእዝ ግሶች የተገኙ ዘሮች ናቸው። እነዚህም፦ አንደኛው “ዕቅበት”፣ መጠበቅ፣ ጥበቃ፣መከላከል ፤ “ዐቀበ”፣ ጠበቀ ከሚለው ግስ የተገኘ ነው። ሁለተኛው “እምነት”፣በቁሙ ሃይማኖት፣ ማመን፣ መታመን፣ መቀበል፣ ተስፋ ማድረግ ሲሆን ግኝቱም፤ “አምነ”፣ አመነ፣ተቀበለ፣ተስፋ አደረገ ከሚለው ግስ ነው።
ይሁን እንጂ ዕቅበተ እምነት በክርስትና ነገረ መለኮት ዓውድ ሲተረጐምና ሲታይ ሰፋ ያለ ይዘትና መልክ አለው። ይህም፦ ዕቅበተ እምነት በተግባራዊ የክርስትና ነገረ መለኮት ከሚመደቡት ከነገረ መለኮት ጥናት ዘርፎች መካከል አንዱ ነው።

የትምህርቱ ይዘትም በመሠረታዊ የክርስትና እምነትና ትምህርት ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎችና ነቀፋዎች (ሒሶች) የእምነትን ድንበር ሳያልፍ፤ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መልስን ለመስጠት፤ ዐቃቢያነ እምነት በከፍተኛ የነገረ መለኮት ተቋማት ገብተው በሥርዓት የሚማሩት፣ ሥነ ጥበብንና ዕውቀትን በአንድነት አጣምሮ የያዘ የትምህርት ዓይነት ነው። ዕቅበተ እምነት በአጭሩ ሲገለጽ በሃይማኖት ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎችና ሒሶች መልስ በመስጠት መጠበቅን (መከላከልን) የሚያመላክት ተግባር-ተኮር ትምህርተ ክርስትና ነው።

ትምህርተ ዕቅበተ እምነት ዐቃቢያነ እምነትን ብቁ ለማድረግ በኢአማንያንና በተጠራጣሪዎች የሚነሡ ጥያቄዎችንና ነቀፌታዎችን መልስ በመስጠትና በማረም፤ ትምህርተ ክርስትናና እምነትን እንዴት እንደሚጠብቁና እንደሚከላከሉ ይዘቱንና መንገዱን በመፈተሽ በተግባር፤ መንገደኞች (ተከታዮች) ዐቃቢያነ እምነት አቅጣጫቸውን ለማመላከት መንገዳቸው (ቃለ ወንጌል፣ክርስቶስ) ላይ የተተከለ ደማቅ መብራት ይመስላል። ዐቃቢያነ እምነት፣ ዕቅበተ እምነት በሚለግሳቸው ዕውቀትና ጥበብ በመጠቀም፣ የሥነ አመክንዮ ሕግጋትን ሳያፋልሱ፣ መልስ መስጠትን በሚሠለጥኑበት ጊዜ የሚከተሉትን ዋና ዋና የኢአማንያና ተጠራጣሪዎች ጥያቄዎቻቸውንና ነቀፌታዎቻቸውን ከነህጸጻቸው (ጉድለታቸው) በጥልቀት በመመለስና በማረም ብቃትን ይይዛሉ። ተገቢ ምላሽና እርምት ከሚያገኙ ጥያቄዎችና ነቀፌታዎች መከካል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ፦ ፍልስፍናዊ ይዘት ካለቸው ፣ እግዚአብሔር አለን? ካለ እንዴት ክፋት ምድር ላይ ኖረ? ከሞት በኋላ ሕይወት አለ? በሕይወት የመኖር ዓላማው ምንድን ነው?… እንዲሁም ነገረ መለኮታዊ ይዘት ከቋጠሩት መካከል፣ ተአምራት መከናወን ይችላሉን? ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቷልን? እውነተኛ ሃይማኖት ክርስትና ባቻ ነውን? ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ብቻ ነውን? ምክንያትና እምነት ይጣላሉ? ወይስ ይዋደዳሉ? የአንድን ደርጊት ሠናይነትና እኩይነት የሚለካው በመገለጥ ላይ በተመሠረተ ሥነ ምግባር መርህ ወይስ በምክንያታውነት ላይ ትኩረት ባደረገ ሌላ መርህ? ወዘተርፈን ያካትታል።

አመጣጥና ምክንያት

እይታቸው እንደየሁኔታው ሊጠብም ሊሰፋም ይችል ይሆናል እንጂ፤ ሰዎች ሁሉ ሕይወትን የሚያዩበት ውስጣዊ መነጽር ገንዘብ ያደረጉ ፍጡራን መሆናቸው በአሳብያን ሰዎች ዘንድ ፈጽሞ ሊካድ የሚችል እውነታ አይደለም። በሂደት እይታቸው ወደ እምነት አቋምነት ያድግና ከሌላው የሚለዩበት የማንነታቸው መገለጫ ሆኖ ይከሠታል። ይህ አቋማዊ ክሥተት ከሌሎች ሰዎች ጋራ በሚኖራቸው ዕለታዊ ግንኙነትና እንቅስቃሴ ምክንያት፤ ያመኑትን ሐቅ ለማስረዳትም፤ የያዙትን አቋም መነሻ አድርገው አድማጮች ለሚያቀርቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠትም ሲነሡ፤ ሥነ አመክንዮአዊ ሕግጋትን መጠቀማቸው የማይቀር ተግባር ነው። የያዙትን እውነት፣ እምነት (አቋም) ሌላውን ለማስረዳት ዕቅበተ እምነት ውስጥ ያሉትን ሁነኛ መርኆችንና መንገዶችን ይጠቀማሉ። ስለዚህ ዕቅበተ እምነት ለሐሳባቸው ማስተላለፊያ መሣሪያ ሆኖ አገለገለቻው ማለት ነው።

ዕቅበተ እምነት ከሚገለጽባቸው ሕዝባዊ ተቋማት አንዱና ዋነኛው ፍርድ ቤት አደባባይ ነው። ዳኞች፣ ዐቃቢያ ሕጎችና ጠበቆች ጉዳያቸውን ይዘው ዳኞች ፊት ሲቀርቡ፤ የዳኞችን የውሳኔ ሐሳብን ለማስለወጥ ለዕቅበተ እምነት አገልግሎት ወሳኝ ሚና የሚጫወተውን የሥነ አመክንዮ መርኆችንና መንገዶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የውዴታ ግዴታ ይሆንባቸዋል። አብነት ለማቅረብ፦ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ469-399 ዓ.ዓ መኖሩን የተነገረለት የግሪክ ፈላስፋ ተከሶ ፍርድ ቤት በቀረበበት ጊዜ በዳኞች ፊት ቀርቦ ሲከራከር (ሲሞግት) ለዕቅበተ እምነት (አቋሙን ለመከላከል) የሚያገለግለውን ሥነ አመክንዮ መርኆን አሳማኝ በሆነ መንገድ ተጠቅመዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን ከሶቅራጥስ በአንዳንድ ነገሮች ስምምነት ያልነበራቸው የንግግር ጥበብ መምህራን፣ ሶፊስቶቸ በየፍርድ ቤቶች አካባቢ የሥነ አመክንዮ መርኆችን በሕዝቡ ዘንድ ልማድ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርገዋል። በተጨማሪም በሃይማኖት ታሪክ ሰፍረው የምናገኛቸው የሃይማኖት የዜና መዋእል ድርሳናትና ገድላት በግልጥ የሚመሰክሩት እውነት፣ የሃይማኖቱ አስተማሪዎች መሠረታዊውን እምነትና ትምህርት ለተከታዮቻቸው ያስረከቡበት ባህል ዕቅበተ እምነት ትምህርት ባቀረባለቸው ጥበብና ዕውቀትን ዋቢ በማድረግ (በመጠቀም) ነው።
በቤተ ክርስቲያን የእምት አባቶች ታሪክና ሥራ (ነገረ አበው) ምሥከርነት፣ 2ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያን ዐቃቢያነ እምነት የታዩበት ዘመን ነው። ዓላማቸውም የአሕዛብን ነገሥታትንና ሕዝቦቻቸውን (ተከታዮቻቸውን) በክርስትናና በክርስቲያኖች ላይ የነበራቸውን የተንሸዋረረ እይታን በጽሑፍና በቃል ሞግቶ ማስተካከል ነበረ። በዚሁም ተግባር ዐቃቢያነ እምነት ያለ ፍርሃት ለአሕዛብ ነገሥታትና ሕዝቦቻቸው (ተከታዮቻቸው) ክርስትና በፖለቲካ ላይ ምንም ጉዳት የማያመጣ ፤ በግብረ ገብነትና በባህል ትምህርቱ ከአረማውያን (አሕዛብ) የተሻለ መሆኑን በዕቅበተ እምነት እንቅስቃሴዎቻቸው በግልጽ አስመስክረዋል። በቤተ ክርስቲያን ታሪከ ጐልተው ከሚነሡ ዐቃቢያነ እምነት መካከል፦ ኳድራተስ፣አሪስቲደስ፣ጀስቲን ዘማርቲር፣ቴሻን… ወዘተርፈ ናቸው። የክርስቲያን ዐቃቢያነ እምነት ዋናው ፍላጎታቸው ግልጽ ነው። በሐሳብና እምነት ዓውደ ውጊያ (ሐሳብንና እምነትን በፍቅር መወያየት) ፍልስፍናን በራሱ መሣሪያ (ምክንያታዊነት) በክርስትና ግዛት ሰማይ ሥር ምርኮኛ እንዲሆን ማድረግ ነበር።

በተለያዩ ሰዎች የቀረቡ የስሕተት ትምህርቶችን ለማረም የተካሔዱ ዓለም አቀፍ 0በይት የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት (በ325 ዓ.ም በኒቅያ፣ በ381 ዓ.ም በቁስጥንጥንያ፣ በ431 ዓ.ም ኤፌሶን) በዐቃቢያነ እምነት አማካኝነት ዕቅበተ እምነትን የተገለጸባቸው ጉባኤያት ናቸው።
ወደ ኋላ መለስ ብለን የአገራችን ታሪክ ስንቃኝም በትምህርተ ሃይማኖት አቋማቸው ልዩነትን ያንጸባረቁ የእምነት አባቶች፤ ልዩነቶቻቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሙግትን (ክርክርን) በጉባኤ የማቅረቡ ልማድ (ባህል) እንደነበረን ያሳየናል። ይህም በካራና በጸጋ መካከል በታየው የትምህርተ ሃይማኖት መለያየት፣ በ1870 ዓ.ም ቦሩ ሜዳ ላይ ከሁለቱም የእምነት አቋሞች ተወከለው የቀረቡ ዐቃቢያነ እምነት ዕቅበተ እምነታቸው በጉባኤ መካከል ሰላማዊ ክርክር (ሙግት) ማድረጋቸው በአገራችን የታሪክ ጽሑፋት በታሪክነቱ ሰፍሮ ይገኛል።

ሰዎች በሕይወት ጉዞቸው አንድም ከአእምሯቸው ሁለትም ከነፍሳቸው የሚመነጩ መሠረታውያን ሕይወት-ተኮር ጥያቄዎች ይገዳደሯቸዋል። ሰዎች ከጥያቄዎቹ የሚነሡ ተግዳሮቶቻቸውን ለመቋቋም (የጥያቄዎቻቸውን መልሶች ለማግኘት) በግልም ሆነ በኅብረት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። በዚህ ሰዓት የጥያቄዎቹ ምላሾች ሳይገኙ ሲቀሩ ጠያቂዎች በሕይወታቸው የሥነ ልቡና፣ የመንፈስ፣ የዕውቀትንና የግብረ ገብ፣ እንዲሁም የማኅበራዊ ሕይወት ግንኙነት አለመረጋጋት (ቀውስ) ይታይባቸዋል። መሰል ችግር በማኅበረ ሰቡ ዘንድ ሲታይ ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ዐቃቢያነ እምነት ግንብር ቀድም ተዋናዮች (ተሳታፊ) በመሆን ዘመን አይሽሬ የዕቅበተ እምነትን ፋይዳ ያስገነዝባሉ።

አምላካዊ ትእዛዝ

አንደኛው፣ ከግእዘ (ባሕርየ) ሰብእ የሚነሣ ትእዛዝ ነው። ሰዎች ባለ አእምሮ ፍጡራን መሆናቸው አስቀድመን ባነሣናቸው ሓሳቦች ተጠቅሷል። ስለዚህም አእምሯቸው ምክንያታዊ በሆነው መንገድ ሐሳቦችን ያስባል፤ ያደራጃልም። ሐሳቦቻቸውም የሥነ አመክንዮ ሕግጋት የሚያቀርቡላቸውን ማዕቀቦች በጽናት ተቋቚመው በማለፍ ለአቅመ ነጽሮተ ዓለምና እምነት ሲደርሱ፤ ከአድናቂዎቻቸውም ይሁን ከነቃፊዎቻቸው ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠትንና የማስረዳትን ኀላፊነት በላያቸው ላይ ይወድቃል። እንደዚህ ያለውን ክስተት በልዩነት ሰው ላይ ብቻ የሚንጸባረቅ ደማቅ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ይህም ለሰው ልጅ ኅሊና የሚመለከትና በሰው ልጅ ኅሊና መልስ የሚሰጥበት ነው።

ሁለተኛው፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት ምሥክርነት የሚመነጭ ትእዛዝ ነው። ሐዋርያትን የተከተሉ ጥንታውያን ዐቃቢያነ እምነት፣ በጽሑፋትና በቃላት መያዣዎች የቀረቡ የዕቅበተ እምነት መልካም ዘሮች በተከታዮቻቸው ማሳ ልብ ውስጥ ዘርተው አልፏል። ይህ መልካም ተግባር በአበው ገድላትና ጽሑፋት በሰፊው ተመዝግበው ይገኛሉ። ተግባራቸውም ልበ ሰማዕያንን አበርትቷል። በተመሳሳይ ይዘትና መንገድ በአሁኑ ዘመን ባሉት ዐቃቢያነ እምነት ምላሽ የመስጠቱን ተግባር በመቀጠል ላይ ይገኛሉ። ለዚሁ ተግባር አንቀሳቃሽ ሞተር ዘፈቀዳዊ የግል ስሜት ሳይሆን አምላካውያት መጻሕፍት ውስጥ በሚገኝ ግልጽ መለኮታዊ ትእዛዝ (ኀላፊነት) መሠረትነት ነው። ይህም በ፩ጴጥ.፫፥፲፭ እንዲህ ተጽፎ እናገኘዋለን፦ “በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።”
ዓውደ ንባቡን ሳንለቅ የጥቅሱን ቃላት በትኲረት ከተገነዘብናቸው መልእክቱ በዘመኑ ለነበሩና ተከትለው ለሚመጡ አድማጮችን ትኩረት ያደረጉ፣ ትላልቅ ቊም ነገሮችን ያስተላልፋል። ግዚያዊ አድማጮች ማለትም ቅዱስ ጴጥሮስ መልእክቱ የጻፈላቸው፣ በዘመኑ በግሪካውያንና ሮማውያን ዘንድ በክርስቶስ ምክንያት መከራ ሲደርስባቸው ለነበሩ ለእስያ ክርስቲያኖች የሚያመላክት ነው። ነገር ግን ሐሳቡ ጊዚያዊ አድማጮችን ተሻግሮ ለዘለቄታዊ አማኞች (ለመጭዎቹ አደማጮች) የተጻፈ መሆኑን ከሚያመላክቱን የጥቅሱ ሐረጋት፦ “ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ” እና “ዘወትር የተዘጋጃችሁ” የሚሉትን ናቸው። ስለዚህ ቃሉ አሁን ላለን ክርስቲያኖች የተነገረ አምላካዊ ኀላፊነት መሆኑን ያስታውሰናል።

አማኞች ለክርስቶስ ካላቸው ጥልቅ ልባዊ ፍቅር ባገኙት ድፍረት ምክንያት በመከራ መካከልም እንኳን ቢሆኑ ለመመሥከር ወደ ኋላ ማለት እንደሌለባቸው የመልእክቱ ሐሳብ ይገልጻል። ቀረብ ብለን የጥቅሱን ማእከላዊ ሐሳቦች ስንመረምር በሕግ አግባብ ውንጀላን (ክስን) መከላከልና መልስ መስጠትን የሚመለከት ትርጉም አለው። ይህም አግባብነት ወደ አለው የሙግት አቀራረብና ሥነ ሥርዓት ዕውቀት ይመራናል።
ክርስቲያናዊ ዕቅበተ እምነትን በሚመለከት በተቀራራቢ ትርጉም በማስረጃነት ሥራ ላይ የዋለባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍላት የሐዋርያት ሥራንና የሐዋርያው ጳውሎስ መልእክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ለጊዜው እንመልከት። ይኸውም፦ አንደኛው ምሥክርነት በሐዋ. ሥራ ፳፭፥፲፮፣ “እኔም፦ ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ለፊት ሳይቆም ለተከሰሰበትም መልስ ይሰጥ ዘንድ ፈንታ ሳያገኝ፥ ማንንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት አይደለም ብዬ መለስሁላቸው።” እና በሐዋ. ሥራ ፳፮፥፪-፫፦ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ የአይሁድን ሥርዓት ክርክርንም ሁሉ አጥብቀህ አውቀሃልና በአይሁድ በተከሰስሁበት ነገር ሁሉ ዛሬ በፊትህ ስለምመልስ ራሴን እጅግ እንደ ተመረቀ አድርጌ እቈጥረዋለሁ፤ ስለዚህ በትዕግሥት ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።” ሲሆን ሁለተኛው ምሥክርነት ደግሞ በ፩ቆሮ.፱፥፫-፬፣ “ለሚመረምሩኝ መልሴ ይህ ነው። ልንበላና ልንጠጣ መብት የለንምን?”ለተጠየቅሁት መልሴ ይህ ነው ብለን አቋምን የምንገልጸው ቃል ነው። ለምንጠየቀው መልሴ ይህ ነው ብለን አቋማችንን የምንገልጥበት ቃል ነው።
ከርስቲያኖች እምነታቸውን (በክርስቶስ ላይ ያለቸው አቋም ሲገልጹ) ሲከላከሉና ሲያብራሩ በየዋህነትና በፍርሃት መሆን እንዳለበት የመልእክቱ ጥቅስ በ፩ጴጥ.፫፥፲፭፣ ይህንንም፦ “ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።” በማለት የአቀራረብን ሥነ ሥርዓት እንዴት መሆን እንዳለበት እውነት ፈላጊ ተዋያዮችን ያስገነዝባል።

አቀራረብና መፍትሔ

የዕቅበተ እምነት ትምህርት፣ እምነታችንን ለመከላከል ሙሉ ዕውቀት መኖሩን (መያዛችን) ባቻ ሳይሆን እንዴትም ማቅረብ እንዳለብንም ያስተምረናል። በተለይ በክርስትና እምነት ሰዎች ወደ ክርስቶስ ሊመጡ ከሆነ መጀመሪያ እንደጋሬጣ ሁኖ ከልክሏቸው ያለውን ድንጋይ መጀመሪያ መጠረግ አለበት። ዘለን ስለ ክርስቶስ ከማስተማራችን በፊት መጽዳት ያለባቸው ያልጠሩ ሐሳቦች ከሰዎች አእምሮ ውስጥ መጠረግ አለባቸው።

በክርስትና ያለው እምነት በፍቅር የሚሠራ እምነት ነውና የሐዋርያው ጳውሎስ መልእክት ወደ ገላትያ ሰዎች ምዕራፍ ፭ ቍጥር ፮ በአስቀመጠው መንገድ ፦”በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና።” እውነቱን በፍቅር አለዝበን ተከራካሪውን በጨፍን ስሜት ድል ለመንሳት የሚለው መንፈስ አስወግደን፣ያለ ማጨበርበርና ያለ መሸንግል ክርስቶስ ለእርሱ ሲል እንደሞተለት ማስረዳት ነው። ሌላኛው ምክርና መመሪያም በውይይታችን ጊዜም ይሁን በሌላ የሰዎችን እምነትና አመለካከት ማንቋሸሽና ማጥላላት ከዕቅበተ እምነትና ሥነ አመክንዮ ሥነ ሥርዓት ያፈነገጠ መሆኑን በተዘዋዋሪ መንገድ፣ ፩ተሰ.፩፥፭፦ “ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ።” ሲል ያስረዳናል። ከዚህ ጥቅሱ መረዳት የምንችለው በሙግት ጊዚያት ተሟጓቾች ሐሳባቸውን ሲያቀርቡ፣ የሐሳባቸው መልእክትና አካሄድ ቃል (ምክንያት)፣መሠጠትና ግብረ ገብ ያጠቃለለ መሆን አለበት።

በሥነ አመክንዮም ታየ በዕቅበተ እምነት፣ የሥነ አመክንዮ ህጸጸታትን ተጠቅመን እውነትን ለመግለጥና ተቀባይነትን ለማግኘት መሞከር ፍጹም ስሕተት ነው። ዐቃቢያነ እምነትና ተከራካሪዎቻቸው መከተል ያለባቸው አንዱና ዋነኛው አሰረ ፍኖት ሰዎች ክርስቶስ እንደሞተላቸው በትሕትና ማሳየት ነው።

የተነሣንበትን ርእሰ ጉዳይ ስንቋጭ፣ ዕቅበት እምነት በቀጥታ ፍቺ (ብይን) ሲሰጠው ሃይማኖትን (እምነትን) መጠበቅ ነው። ተግባራዊ ነገረ መለኮት ምድብ ውስጥ የሚመደብ፣ ዐቃቢያነ እምነት በነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች በጥልቀት የሚማሩትና የሚሠለጥኑት ነው። ዕቅበት እምነት አስፈላጊ መሆን የቻለበት ዋና ምክንያት በአማንያን በኢአማንያን ሰዎች በሚነሡ በአእምሮና በነፍስ ዙሪያ በሚፈጠሩ ጥያቄዎች ናቸው። ዕቅበት እምነት ተግባር-ተኮር ትምህርት በመሆኑ ሥራ ላይ ሲውል የሥነ ምግባርን መርኆዎችን ይከተላል። ታሪካዊ አመጣጡም በተመለከተ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መነሻ አድርጎ ወደ አባቶችና አሁን ስካለን አማኞች ደርሷል። የዚህ ትልቅ ተልእኮና ኀላፊነት ሰጪውና የበላይ ጠባቂው አምላክና የሰዎች ኅሊና ናቸው። መገለጥን (ቅዱስ መጽሐፍን) መነሻ ያደረገ እምነትና ሕይወት በአንድ ጎን፣ በሌላው ደግሞ ምክንያታዊነትና ነባራዊ ሐቅ በማጣርያ መሣሪያ ተፈትሸው በቅብብሎሽ መልክ አሁን ላለነው ትውልድ የተቀበልነውን እውነታ በጥያቄና ሒሶች የበረዶ ዶፍ ሲወርድነት ኅሊናንና አፍን ለጉሞ መቀመጥ ለክርስትናውም ለሀገርም ከፍተኛ ጉዳት የሚያመጣ ተግባር ነው። ስለዚህ በአማንያንና በኢአማንያን ለሚነሡ ጥያቄዎች ቤተ ክርስቲያን በዐቃቢያነ እምነት ምሁራኖቿ በኩሉ ተገቢውን መልስ መስጠት ይኖርባታል። ዓላማውም፦ “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን።”፪ቆሮ.፲፥፭።

ራሱ ኑና እንዋቀስ ብሎ የመነጋገርን በር ለከፈተልን አምላክ ክብር ምስጋና ይግባው!

መምህር ሽፈራው

ዳግሚት ሔዋን (ኹለተኛዪቱ ሔዋን) Second Eve

በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

ሐሰተኛ የኾነ የእባብ ክፉ ምክርን በመስማቷ በመቀበሏ ለሰው ልጆች ኹሉ የውድቀትና የሞት ምክንያት ከኾነችው ከሔዋን ተለይታ፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ለእግዚአብሔር ታዛዥ በመኾን ፲፪ት ዓመት በቤተ መቅደስ ኖራ፤ እውነተኛ መልእክት የያዘውን የቅዱስ ገብርኤል ብሥራትን በእምነት ተቀብላ፤ የሰው ልጆችን ወደ ቀደመ ክብራቸው ወደ ቀደመ ቦታቸው የመለሰ ክርስቶስን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ወልዳ ያስገኘችልን የተስፋ ምንጭ ናትና፤ የቤተ ክርስቲያን ታላላቅ የነገረ እግዚአብሔር ምሁራን ሔዋንና ቅድስት ድንግል ማርያምን በማነጻጸር ድንግል ማርያምን “ዳግሚት ሔዋን” (Second Eve) ወይም “ዐዲሲቱ ሔዋን” (New Eve) የሚል ሥያሜን ሰጥተዋታል፡፡

ለሊቃውንት መነሻ ኾኖ ያለፋቸው (በዘፍ ፫፥፩-፯) ያለው ቅዱስ ቃል ሲኾን፤ በታሪኩ እንደተጠቀሰው አዳምና ሔዋን በገነት የጌታን ሕግ ጠብቀው ሰባት ዓመት ከቆዩ በኋላ፤ ዲያብሎስ ሔዋንን አካለ ከይሲን ማደሪያ ልሳነ ከይሲን መናገሪያ በማድረግ፤ ዕፀ በለስን ብትበሉ የባሕርይ አምላክ ትኾናላችኊ፤ ቢላት የእባብ የሐሰት ምክሩን በመቀበል አምላክነትን ሽታ የእግዚአብሔርን ሕግ በማፍረስ፤ የተከለከሉት ዕፀ በለስን በልታ ለባሏ ለአዳም አብልታ ለባሏና ባጠቃላይ ለሰው ዘር ኹሉ መውደቅ ምክንያት ኾናለች (ዘፍ ፫፥፩-፮)፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያም ግን የአምላኳን ሕግ ካፈረሰችው ከሔዋን ግብር ተለይታ፣ በሃይማኖት፣ በምግባር፣ በንጽሕና፣ በቅድስና ጸንታ ከእግዚአብሔር ተልኮ የመጣ፤ የጨለማ መልአክ ያይደለ የብርሃን መልአክ ቅዱስ ገብርኤል የነገራትን የእውነት የብሥራት ቃልን በታላቅ እምነት ተቀብላ፤ ለአምላክ ቃል ታዛዥ በመኾን እንደቃልኽ ይደረግልኝ (ሉቃ ፩፥፴፰) በማለት ታማኝነቷን በማሳየቷ ቅድስት ድንግል ማርያም (ኹለተኛዪቱ ወይም ዐዲስቱ ሔዋን) ተብላ ተጠርታበታለች፡፡
ይኽነን በሔዋንና በድንግል ማርያም መኻከል ያለውን ታላቅ የታማኝነት ልዩነት ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በጥልቀት ሲገልጽ ፡-

“እስመ ቀዳሚኒ ሔዋን ኮነት ድንግል ወአስሐታ ዲያብሎስ ለማርያምሂ ድንግል አብሠራ ገብርኤል ወባሕቱ ለሔዋንሰ አስሐታ ዲያብሎስ ወወለደት ቃየልሀ ዘውእቱ ምክንያተ ሞት ወማርያምሰ ሶበ አብሠራ መልአክ ወለደት ቃለ በሥጋ ዘውእቱ መራሔ ኲሉ ኀበ ሕይወት ዘለዓለም”
(ቀድሞም ሔዋን ድንግልን ነበረችና ዲያብሎስ አሳታት እንጂ፤ ድንግል ማርያምን ግን ገብርኤል አበሠራት፤ ነገር ግን ሔዋንን ዲያብሎስ አሳታት፤ የሞት ምክንያት የሚኾን ቃየልን ወለደች፤ ማርያም ግን መልአክ ባበሠራት ጊዜ ኹሉን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ አካላዊ ቃልን በሥጋ ወለደች) በማለት ሔዋንና ድንግል ማርያም ያላቸውን ልዩነት በማነጻጸር ገልጾታል፡፡

ዳግመኛም ይኸው ሊቅ ሔዋን አምላክነትን ሽታ እንብላ ያለችው ቃሏ ለኹሉ ምክንያተ ሞት የኾነ ዕፀ በለስን አስገኝቶ፤ በዚኹ ምክንያት አዳም ከገነት ቢባረር እንኳን፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተገኘ አካላዊ ቃል ግን ዕፀ ሕይወት መስቀልን አስገኝቶ፤ በዕፀ በለስ ምክንያት ከገነት የወጣውን አዳምን በዕፀ ሕይወት በመስቀሉ ወደጥንት ቦታው ገነት እንደመልሰው በትምህርቱ፡-

“ቃላ ለሔዋን ከሠተ ዕፀ ወበውእቱ ዕፅ ወፅአ አዳም እምገነተ ተድላ ወቃልሰ ዘተወልደ እምድንግል ከሠተ መስቀለ ወቦቱ ቦአ ፈያታዊ ውስተ ገነተ ተድላ ዘምስለ አቡሁ አዳም ወኲሎሙ አበው ቀደምት”

(የሔዋን ልብላ ልብላ ማለቷ ዕፀ በለስ የሞት ምክንያት እንደኾነ አስረዳ፤ በዚያም ዕፅ አዳም ተድላ ደስታ ካለበት ከገነት ወጣ፤ ከድንግል የተወለደ አካላዊ ቃል ግን መስቀል የድኅነት ምክንያት እንደኾነ ገለጠ፤ በዚያም መስቀል ቀማኛ ወንበዴ የነበረው ሰው ከአባቱ ከአዳምና ከቀደሙ አባቶች ኹሉ ጋር ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት ገባ) በማለት እያነጻጸረ አስተምሯል (ዘፍ ፫፥፳፬፤ ሉቃ ፳፫፥፵፩-፵፬፤ ፩ኛ ቆሮ ፩፥፲፰)፡፡

ሔዋንንና ድንግል ማርያምን እያነጻጸሩ ሊቃውንት ያስተማሩትን ጥልቅ ትምህርት ኹሉ በዚኽ ማጠቃለል ባይቻልም ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ድንግል ማርያም ዳግሚት ሔዋን የመባሏን ምስጢር በስፋትና በጥልቀት ያስተማረውን ትምህርት ለማየት እንሞክራለን፡፡

ይኽ ሊቅ የሐሰትንና የሞት መልእክትን የያዘውን እባብንና፤ የእውነትና የሕይወት መልእክትን የያዘውን ቅዱስ ገብርኤልን፤ የሐሰት የዲያብሎስን መልእክት በደስታ በመቀበል ለሰው ኹሉ ውድቀት መነሻ የኾነችውን ሔዋንንና፤ ከእግዚአብሔር ተልኮ የመጣውን መልእክት በፍጹም እምነት ተቀብላ ሕይወት የሰጠን ጌታን የወለደችው ድንግል ማርያምን ሲያነጻጽር፡- “The evil time which had killed Adam was changed, another good time came…” (አዳምን እንዲሞት ያደረገች ያቺ ክፉ ቀን ተለወጠች፤ ርሱም ከሞት የሚድንባት ሌላ ቀን መጣች፤ እባቧ ሳትኾን ገብርኤል ሊናገር ተነሣ፤ ሔዋን ሳትኾን ድንግል ማርያም ቃሉን ልትቀበል ተዘጋጀች፤ በተንኰል ቃል የሚያሳስተው ሳይኾን ሕይወትን የሚያውጅ እውነተኛ ቃል ወጣ፤ በሞት ዛፍ መኻከል የሞት ዕዳዋን በጻፈችው እናት (ሔዋን) ፈንታ፤ ልጇ (እመቤታችን) የአባቷን ዕዳ ኹሉ ከፈለች፤ ሔዋንና እባቡ በመልአኩና በድንግል ማርያም ተተኩ፤ ያ ከመዠመሪያው የተበላሸውም ጉዳይ እንደገና ተስተካከለ፤ የሔዋን ዦሮና ቀልብ አታላዩ በሚናገርበት ጊዜ ምን ያኽል እንዳዘነበለ አስተውል፤ ነገር ግን ያ በገነት ሲመለከታቸው የነበረ መልአክ አኹን በማርያም ዦሮ የድኅነት የተስፋ ቃል ሲያሠርጽ የእባቡን ክፉና መርዛማ ቃል ሲያጠፋ ርሷንም ሲያጽናና ተመልከት፤ ያነን እባብ ያፈረሰውን ሕንጻ ገብርኤል ገነባው፤ በዔደን ሔዋን ያፈረሰችውን ድንግል ማርያም መሠረቱን ገነባች፤ ከኹለት መልእክተኞች መልእክት የተቀበሉ ኹለት ደናግል ኹለት ኹለት ኾነው ትውልዶችን ቀጠሉ፤ አንዱ የአንዱ ተቃራኒ ኾነ፤ በእባብ አማካኝነት ሰይጣን ምስጢርን ለሔዋን ላከ፤ በመልአክ አማካኝነት ደግሞ ጌታ የምሥራቹን ወደ እመቤታችን ማርያም ላከ፤ እባብ የሐሰትን ቃል ለሔዋን ስትናገር ገብርኤል ግን የእውነትን ቃል ለድንግል ማርያም ተናገረ፤ እውነትን በሚናገር አንደበቱ መልአኩ ቃሉን አደሰው፤ እውነትን ተናገረ በዚኽም ሐሰትን ኹሉ አስወገደው፤ ተንኰልን ከራሱ ባወጣ በሰይጣን በዔዴን ገነት ድንግሊቷ ተታለለች፤ ታላቁ ስሕተት በዦሮዋ ዐልፎ እንዲሰማት ዐደረገች፤ በመዠመሪያዋ ድንግል ፈንታ ሌላ ድንግል ተመረጠች፤ በዚኽችም ድንግል ዦሮ ከአርያም የመጣ የእውነት ቃል ገባ፤ ሞት በገባበት በዚያው በር ደግሞ ሕይወት ገባ፤ ክፉው ያጠበቀውን ጽኑዕ የሞት ማሰሪያ ፈታ፤ ኀጢአትና ሞት ከመዠመሪያው እጅግ እንደሰለጠኑ ኹሉ፤ እንዲኹ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በዝቶ በአዳም ታየ፤ እባብ ከሔዋን ጋር ስትነጋገር ሔዋን አልተንበረከከችም አልሰገደችም፤ ሞት በመላበት ጐዳና ሰላምና ትሕትና አይገኙምና፤ እባብ የስሕተትን ዜማ ለሔዋን ዘመረ ሐሰትን ረጨባት፤ በተፈጥሮዋ ገና ድንግል በኾነች ሔዋን ላይ ክፉ ምክርና ስሕተት ፈሰሱ፤ ለመግደል የኾነ ጠላትነትና ክፉ ምክር ደምን የተጠማ መርዙን በንግግሩ ውስጥ በአዳም ቤት ውስት አስገባ፤ በወልድ የተላከው መልአክ እነዚኽን የክፋት ሰይፎች ለመቋቋም ኼደ፤ ለድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር የኾነውን የመዳን ብሥራትን ነገረ፤ ሰገደላት፣ ሕይወትን በውስጧ አሠረጸ፤ ሰላምን ዐወጀላት፤ በፍቅር ቀረባት የቀደመውን የሞት ዳባ በጣጠሰ፤ እባብ የገነባው የማታለል ግንብ ዳግመኛ ላይገነባ በእግዚአብሔር ልጅ በወልድ ተናደ፤ በእባብ የታጠረው የሞት ቅጥር በወልድ መውረድ ተሰባበረ፤ በሰማያትና በምድር በሚኖሩ ኀይላት መኻከል ሰላም ይወርድ ዘንድ) በማለት ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የቀደመችቱ ሔዋን ሐሰተኛ የኾነውን የእባቡን መርዝ የመላበት ንግግሩን ተቀብላ ባሏን በአጠቃላይ የሰው ልጆችን በዲያብሎስ የክሕደት መርዝ እንዲወጉ ስታደርግ፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ግን የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል የእውነት ብሥራትን በእምነት በመቀበሏ፤ ዲያብሎስ የተከለውን የኀጢአት መርዝን ነቃቅሎ ያጠፋ ወሀቤ ሕይወት ጌታን ያስገኘችልን መኾኗን አስረድቷል፡፡

በዚኽ ትምህርቱም ሔዋን ለታማኝነት የማትበቃ ተወቃሽ ስትኾን፤ ድንግል ማርያም ግን አስተዋይ የአባቷን ዕዳ የከፈለች ፍጹም እምነትን የተመላች መኾኗን ሳያስተምር አላለፈም፤ ይኽነንም በጥልቀት ስናየው ሔዋን የሐሰት መልእክትን ከሐሰተኛው በሰማች ጊዜ ከመጠየቅ ይልቅ ዝምታን በመምረጥ የሚያባብል የተንኰልና የክፋት ቃሉን በደስታ ተቀብላ፤ አምላክ መኾንን ፈልጋ በስሕተት ስትወድቅ፤ በተቃራኒው ግን ቅድስት ድንግል ማርያምን የአምላክ እናት እንደምትኾን ቅዱስ ገብርኤል ሲያበሥራት፤ ይኽነን ልዩና ከኅሊናት ኹሉ በላይ የኾነውን ምስጢር ለመረዳት አጥብቃ የጠየቀች አስተዋይ ናት፡፡

ይኸውም በድንግል ማርያም መናገር ሕይወት፣ ብርሃን ሲኾን በሔዋን ዝምታ ግን ኀጢአት፣ ውርደት፣ ሞት መምጣቱንና ዳግመኛ የሔዋን ዦሮ የሞትና የውድቀት መልእክትን ሲሰማ የድንግል ማርያም ዦሮ ግን ታላቅ የኾነ የሕይወትና የድኅነት መልእክትን መስማቱን ይኽ ቅዱስ ያዕቆብ ሲመሰክር፡-
“On this account, the watcher had saluted Mary as a pledge of great peace for the whole world…”

(በዚኽም መልአኩ ድንግል ማርያምን አከበራት፤ ለዓለም ኹሉ ሰላም ታላቅ ቃል ኪዳን ነውና፤ “ማርያም ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ በድንግልና ትፀንሻለሽ በድንግልናም ወንድ ልጅን ትወልጃለሽ” አላት፤ ድንግል ማርያም መለሰች እንዴት ይኽ ሊኾን ይችላል? እኔ ድንግል ነኝ እንዴት እፀንሳለኍ? በዚኽ ቅጽበት መጠየቋ እጅግ ግድ ነበር፤ የወልድ በእርሷ ማሕፀን የማደር ምስጢርን መልአኩ ይገልጥላት ዘንድ፤ እመቤታችን ማርያም ጠየቀች ከመልአኩ መልስ እንማር ዘንድ፤ ስለመፅነሷ እንድትረዳ ዐደረጋት፤ ትርፋ የርሷንና ርሷን ለሚሰሙ ኹሉ ነውና) ሲል እመቤታችን ከመልአኩ ጋር ያደረገችው ምልልስ እንደ ዘካርያስ በመጠራጠር እንደ ኒቆዲሞስ በመከራከር ሳይኾን፤ ብልኅ ደቀ መዝሙር ምስጢር ለመረዳት ሲል ከመምህሩ ጋር ክርክር እንደሚያነሣ ኹሉ ድንግል ማርያም በማስተዋል እየጠየቀች መልአኩ እየመለሰ ብዙ ምስጢር በመገለጹ፤ በጥያቄዋ ለስዉሩ ምስጢር መታወቅ ምክንያት የኾነች መኾኗን አስተምሯል፡፡

ሔዋን ግን የሐሰትና የሞት መልእክትን ስትሰማ ለምን? እንዴት? ብላ ሳትጠይቅ ሐሰትን በማመኗ ፈጽማ ተወቃሽ መኾኗን ሊቁ ሲያነጻጽር፡- “Eve had not questioned the serpent when he led her astray…” ሔዋን እባብ ወደሞት ሲመራት ለምን? አላለችም ነበር፤ ነገር ግን በፈቃዷ ዝምታን መረጠች፤ የሚያባብል የተንኰል ቃልንም ሳትጠራጠር አመነች፤ ኹለተኛዋ ሴት (እመቤታችን) ግን የእውነት ቃል ከሚታመነው ሰማች፤ ቢኾንም ነገሩ የተረዳ እንዲኾንላት አጥብቃ ጠየቀች፤ የቀደመችው ሴት ሔዋን የዛፍን ፍሬ በመብላት አምላክ እንደምትኾን ሰማች፤ እንዴት ይኽ ሊኾን ይችላል? ብላ ግን አልጠየቀችም፤ ድንግል ማርያም ግን መልአኩ የእግዚአብሔር ልጅን እንደምትፀንስ በነገራት ጊዜ ግን የበለጠ እስክትረዳው ድረስ አልተቀበለችውም፡፡ አምላክ እንደምትኾን የአዳም ሚስት የኾነችው ድንግሊቷ ሔዋን ሳትጠራጠር የሐሰተኛውን ቃል ተቀበለች፤ የእግዚአብሔርን ልጅ ትፀንሳለች የተባለላት ግን መረመረች፣ ጠየቀች፣ ተማረች ግን ዝም አለች፤ ኹለተኛዋ ከመዠመሪያዋ ሴት እጅግ ውብ እንደነበረች አስተውሉ፤ ስለውበቷ ምክንያትም ጌታ መረጣት እናቱ እንድትኾን ዐደረጋት፤ ለእርሷ ዝም ማለት ቀላል ነበር ጥያቄ ማቅረብም እንዲኹ፤ ግን በማስተዋሏ ከመልአኩ የሰማችውን እውነት ዐወቀች ተረዳች፤ ሔዋን በምርጫዋ ተወቃሽ እንደኾነች፤ እንዲኹ ድንግል ማርያም በምርጫዋ የከበረች ኾነች፤ እንደመዠመሪያዋ ጥበብ ማነስ ኹሉ የኹለተኛዋ ጥበብ ተገለጠ፤ የመዠመሪያዋ ሴት ክፉን በፈቃዷ ስታመጣ እንዳላፈረችበት የኹለተኛዋ ስለ ወልድ በማሕፀኗ በግብረ መንፈስ ቅዱስ መፀነስ አላፈረችበትም፤ የቀደመችው ጥበብ እንደጐደላት ኹሉ ኹለተኛዋ ለሚያስተውል እጅግ ጥበብ የመላባት ኾነች፤ በቀደመችው የነበረባትን ዕዳ ኹሉ ይኽቺ ከፍላለችና፤ በቀደመችው ውድቀት፤ በኹለተኛዋ ትንሣኤ ለዘራችን ኹሉ ደረሰ፤ ኀጢአት በሔዋን ቢመጣም ጽድቅ ግን ከድንግል ማርያም ተገኘ፤ በሔዋን ዝምታ ኀጢአትና ውርደት፤ በእመቤታችን ማርያም መናገር ሕይወትና ብርሃን ከድል መንሣት ጋር ኾነ፤ እንዲኽ ብላ ለመልአኩ መለሰች “እንዴት የምትለው ይኾናል?” የወልድን ከሰማያት መውረድ በእርሷም የማደሩን አሠራር ገለጠላት፤ “የተባረክሽ ሆይ መንፈስ ቅዱስ ወደ አንቺ በክብር ይመጣል፤ የልዑል ኀይልም ይጸልልሻል” አኹን የምላስ ንግግር ኹሉ የማያስፈልግ ትርፍ ነገር ነው ስለሚያስደንቅ እምነቷ ካልኾነ በቀር ማንም አይናገርም) በማለት የመዠመሪያዪቱ ሔዋንና ዳግሚት ሔዋን የተባለች ቅድስት ድንግል ማርያምን በማነጻጸር ያስተማረው ትምህርት እጅግ አድርጐ የሚረቅ የሚያስደንቅ መኾኑን ከልብ እናስተውለዋለን፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ኑሮ

የሰው ልጅ በተፈጥሮው ማኅበራዊ ፍጡር ነው፤ ማኅበራዊነት ከሌለ የዚህ ዓለም ጉዞውን በውጤት መፈጸም አይችልምና በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ታሳቢ በማድረግ የአካልና የአእምሮ ሀብታትን ተቀብሏል ። የሚያየው ነገር ባይኖር ዓይን አስፈላጊ እንዳልሆነ ሁሉ የሚሰጠው ሰው ባይኖርም እጅ አስፈላጊ አይሆንም ነበር ። ሕይወትን በነጻነት፣ ኑሮንም በቀላሉ ለመምራት የሚጠቅመው ማኅበራዊነት በግድ ሳይሆን በውዴታ የሚደረግ በረከት፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ።

ከማኅበረሰቡ የምንቀበለውና የምንሰጠው ነገር በመኖሩ እና የዚህ ዓለም መከራ ለሁሉም በአንድ ጊዜ የማይመጣ በመሆኑ ማኅበራዊነት መገለጫ መንገድ አግኝቷል፤ ሁሉም ሰው በአንድ ቀን ቢያገባ ደስታን የሚካፈል ፣ ሁሉም ሰው በአንድ ቀን ቢያዝን ኀዘንን የሚካፈል ወገን ባልተገኘ ነበር፤ እግዚአብሔር አንዱ ወገን ሌላኛውን ወገን ይረዳው ዘንድ አስጨናቂ ቀኖች በሁሉም ላይ በአንድ ቀን እንዳይወጡ ከልክሎአል፤ የአየር ትራፊክ አውሮፕላኖችን በተለያየ ርቀት ደርድሮ መንገድ እንደሚመራቸው ሁሉ እግዚአብሔር አምላክም እኛ በተለያየ ከፍታ ውስጥ እንድንጓዝ በማድረጉ ሕይወት አንድ ታላቅ እጅ የሚቆጣጠራት እንጂ እንዲሁ የተለቀቀች ስጋት አለመሆንዋን እንረዳለን፡፡

ቤተ ክርስቲያን በምሥጢራዊ ትርጓሜ የተቀደሰችና አንዲት ማኅበር ናት፤ ቤተ ክርስቲያንን ከማኅበራዊ ስብስብ ልዩ የሚያደርጋትም እግዚአብሔርን የበላይ በማድረግዋ ነው፤ ማኅበራዊነት አንድ ጉዳይን የበላይ የሚያደርግ ስብስብ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ግን ርእሷ አምልኮተ እግዚአብሔር ነው፤ የማኅበራዊ ኑሮ መነሻም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ጀማሪ እግዚአብሔር ነው ። ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ያመኑ ምእመናን የተጠለሉባት ጥላ ስትሆን ማኅበራዊነት የቀለም ወሰን ሳይኖርበት ሰው መሆንን ብቻ ማዕከል ያደረገ ነው፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ከሃይማኖት አጥር ውጭ ላሉትም ጭምር የእግዚአብሔርን ፍቅር የመግለጥ ተልእኮ አላት፤ በዚህም ርቀው ላሉት እግዚአብሔር ምን ያህል እንደሚወዳቸው ከቃል እስከ ተግባር ትሰብካለች ።

ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናት፤ እርሱም በአካሉ የሚሠራ አምላክ ነው፤ በቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ተግባራት ፣ መለኮታዊ ተአምራት ፣ ሕይወትን አድራሻ ያደረጉ ምሥጢራት ይፈጸማሉ ። ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻ ግብዋ ሰማይ ስለሆነ ሰማያዊት ተብላ ስትጠራ ስለ ምድርም ግድ ይላታልና የሰው ልጆች እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲቆሙ ትጨነቃለች፤ ስለ ለሰዎች ኅብረት ብቻም ሳይሆን ስለ አፍላጋት ጽኑ ልመና ታቀርባለች፤ እናት እንደመሆኗ ሕዝብ በቀጣይ ዓመት እንዳይራብ ስለ ዝናብ ትማልዳለች፤ በመዝሙራትና በትምህርትዋ አማካኝነትም ገበሬው ዘሩን በምስጋና እንዲዘራ በማነሣሣት ስንፍናን ትዋጋለች ።

የሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የመሠረተልን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ተዋሕዶ ለድኅነተ ዓለም በተገለጠበት ወቅት አንድ መቶ ሃያ ቤተሰብን እያስከተለ ያስተምርና ይመግብ ነበር፤ እርሱ የቤቱ ራስ፣ ሐዋርያት ተተኪ አባቶች፣ ቅዱሳት አንእስት እናቶች፣ ሰባ አርድእትም አጋዥ ልጆች ነበሩ። በዚህም የቤተ ክርስቲያን መነሻ ግላዊነት ሳይሆን ማኅበራዊነት መሆኑን እንረዳለን፡፡ ግላዊነት ሰይጣናዊ ፍልስፍና ሲሆን ማኅበራዊነት ግን የሰው የተፈጥሮውና የመንፈሳዊነት መልክ ነው ።

ዘመናዊው ዓለም ከጎረቤት በፍቅር የሚገኘውን ነገር ከሱቅ በገንዘብ የሚገኝ በማድረግ ሁሉን ነገር ሸቀጥ አድርጎት የሰው ልጆችን ተስፋ አስቆርጧል፤ ማኅበራዊነት ግን ሰው መምሰል ሳይሆን ሰው መሆን ነው፤ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ማዘኑ፣ በሰዎች መጠላቱ፣ የግፍ ፍርድ መቀበሉ እና የመሳሰሉት በኑሮአችን ውስጥ እንደ ገባ ማሳያዎች በመሆናቸው ማኅበራዊነት በክርስቶስ ተቀድሷል፤ ሕይወት ብርቱ ሰልፍ መሆኗም ለጎረቤታችን ያለንን ፍቅር ለመግለጥ መልካም አጋጣሚ ሆኗል ። እግዚአብሔር ከጨለማው ውስጥ ብርሃን ማውጣት እንደሚችል ለማስረዳት ሰዎች ስለ ወዳጆቻቸው ሲናገሩ ‹‹እገሌ እኮ የክፉ ቀኔ ነው›› ይላሉ፤ በዚህ መልኩ የገለጹትን ሰውም አንገታቸውን ለሰይፍ፣ ጀርባቸውን ለጅራፍ እስከ መስጠት ድረስ እንደሚወዱት ግልጽ በመሆኑ፤ በክፉ ቀን መልካሙ ፍቅር ይገለጣልና ማኅበራዊነት መሠረቱ እግዚአብሔር፤ የሚያድገውም በጉድለት ምክንያትነት እንደሆነ እንገነዘባለን ።

ቅዱሳን ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል ተልእኮ ወደ ዓለም በተሠማሩ ጊዜ ለማኅበራዊነት ትልቅ ዋጋ ከፍለዋል፤ ለዚህም ሦስት ነገሮችን መጥቀስ እንችላለን፡-

1- ማኅበረ እስጢፋኖስ

‘ወውእተ አሚረ በዝኁ ሕዝብ ወግዕዝዎሙ እለ እምአረሚ አርድእት ለአይሁድ እስመ ይሬእይዎን ለመበለታቲሆን እንዘ ኢይፀመዳ ኵሎ አሚረ ወያሰትታ ተልእኮቶን፡፡ ወጸውዕዎሙ ፲ወ፪ ለኵሉ ሕዝብ ወይቤልዎሙ ኢይደልወነ ከመ ንኅድግ ቃለ እግዚአብሔር ወንፀመድ ማእዳተ፡፡ ኅረዩ እምውስቴትክሙ ፯ ዕደወ እለ ምሉአን መንፈሰ ቅዱሰ ወጥበበ እለ ንሠይም ዲበ ዝግብር፡፡ ወንሕነሰ ንፀመድ ጸሎተ ወመልእክተ ቃሉ ወኀብሩ ኵሎሙ ሕዝብ፡-

በዚያም ወራት ደቀ መዛሙርት በበዙ ጊዜ ከግሪክ የመጡ ደቀመዛሙርት በአይሁድ ምእመናን ላይ አንጐራጐሩባቸው፥ የዕለት የዕለቱን ምግብ ሲያካፍሉ ባልቴቶቻቸውን ቸል ይሉባቸው ነበርና። ዐሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ሕዝቡን ሁሉ ጠርተው እንዲህ አሉአቸው። የእግዚአብሔር ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ አይደለም። ወንድሞቻችን ሆይ፥ ከእናንተ ወገን በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን ሰባት ሰዎችን ምረጡ፥ ለዚህ ሥራም እንሾማቸዋለን፤ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማስተማር እንተጋለን።” (የሐዋ. 6፡1-6) ።

ሰባት ዲያቆናት እንዲመረጡ ምክንያት የሆነው ፣ ሊቀ ዲያቆናት እስጢፋኖስንም በታላቅ ጸጋና በቀዳሜ ሰማዕትነት እንዲገኝ ያደረገው ማኅበራዊ ክስተት ነው ፡፡ በጊዜው ነዋሪና እንግዳ የሚል ልዩነት ተነሥቶ ፣ በማዕድም አድልኦ ተፈጽሞ ነበርና ሐዋርያት የምእመናንን ቅሬታ ለመስማትና ለመፍታት ዝግጁ ነበሩ፤ ነገር ግን ይህን ተግባር ሥራዬ ብለው ቢያከናውኑት የወንጌሉ ሥራ ሊቆም እንደሆነ ስለገባቸው ሌሎች ሊሠሩት የሚችሉት ተግባር ሆኖ ባገኙት ጊዜ ሰባት ዲያቆናትን ሾሙ ። ማኅበራዊ ደኅንነት የሚባለው ራሳቸውን ለመከላከል አቅም የሌላቸውን ሕፃናትን ፣ ሴቶችንና አረጋውያንን መከላከል ሲሆን የአንድ መንግሥት የመንግሥትነቱ መገለጫ አቅም የሌላቸውን መጠበቅ በመቻሉ ነውና በየትኛውም አገር የሚደራጅ መንግሥታዊ የጸጥታ አካል ለእነዚህ ወገኖች የደኅንነት ዋስትና ይሰጣል፡፡

በመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን አድልኦና ማግለል እንዲሁም መገለል ፈተና ሆኖ በተከሰተ ጊዜም የቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ ተልእኮ ሁሉንም በእኩል ማስተናገድ መሆኑን ተረድተው ዲያቆናትን ሾመዋል፤ ዛሬም ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያሉ ክስተቶች ሲነሡ ፈጥና ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ይገባታል ። የክርስቶስ መስቀል ልዩነትን ፣ በሰውነት ላይ ደረጃ የሚያወጣውን አስተሳሰብ አሸንፎ ሁሉንም በእኩልነት የምንመለከትበት ነው ።

2- የእርዳታ ተቋም

‹‹ወበእንተ አስተጋብኦሰ ለቅዱሳን በከመ ሠራዕክዎሙ ለቤተ ክርስቲያን ዘገላትያ ከማሁ አንትሙሂ ግበሩ፡-

“ለቅዱሳን ስለሚደረገው አስተዋፅኦ፥ በገላትያ ላሉት ምእመናን እንደ ደነገግሁት እናንተም እንዲሁ አድርጉ።” 1ቆሮ. 16፡1 ።

ሐዋርያትና ቅዱስ ጳውሎስ ከተግባራቸው መካከል ዋነኛው ድሆችን መርዳት ስለነበር የመጀመሪያው የእርዳታ ድርጅት ተመሥርቷል፤ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን አባላትም ንብረታቸውን ሸጠው ፣ በጋራ በመጠቀምና በአንድነት በመኖር እስከ ዛሬ ድረስ ለክርስቲያኖችና ለገዳማውያን ምሳሌ ሆነዋል ። የእኔ ንብረት የሁሉም ወገኔ ነው ብሎ ማሰብ ለክርስቶስ ፍጹም መሰጠትን የሚጠይቅ ነው፤ የራሱ ያልሆነውን በሚቀማው ዓለም ዘንድ ይህ ተግባር ሞኝነት ቢመስልም ለሥጋዊነት ብርቱ፣ ለመንፈሳዊነት ግን ቀላል ነውና የእርዳታ ድርጅቱ በችግር ላይ ወድቀው የተገኙትን፣ በስደት ምክንያት የተራቡትን ደጋግ አማንያን በዋናነት በመደገፍ አይሁድንና አሕዛብን ለማያስማማት ይጥር ነበር ። በዚህም ቤተ ክርስቲያን የመደጋገፍን ድልድይ ስትዘረጋ፣ የሚለያየውን ግንብ ደግሞ በእግዚአብሔር ቃል እያፈረሰች ከእኛ ዘመን ደርሳለች።

ሰዎች በትንሽ ነገር እንደሚጣሉ ሁሉ በትንሽ በጎነትም ፍቅርን ይመሠርታሉና ዛሬም የተጣሉትን ለማስታረቅ ፣ የተጎዱትን ለመካስ ፣ ያለቀሱትን ለማበስ እንዲህ ዓይነቱን መንገድ መጠቀም በእጅጉ አስፈላጊ ነው ።

3- ከሰዎች ጋር ያለውን ሰላም መጠበቅ፡-

‹‹ወእመሰ ይትከሀለክሙ ምስለ ኵሉ ሰብእ ተአኀዉ፡- ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።›› ሮሜ. 12፡18 ።

ሰው ከሰውና ከእግዚአብሔር ጋር በኅብረት የሚኖር ፍጡር ነው፤ አእዋፋት በመልካቸው ይበራሉ ፣ ወይም ከሚመስላቸው ጋር ይጓዛሉ፤ ሰውን የሚመስለው ግን ሰው ብቻ ነው፤ ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነትም እንዲሁ በቀላሉ የሚሳለጥ ካለመሆኑ በተጨማሪ ሥጋ፣ ዓለምና ሰይጣን ይረብሹታል ። ሥጋ ‹‹እኔ ብቻ›› ይላል፤ ዓለም ‹‹ብልጥ ሁን›› ትላለች፤ ሰይጣን ‹‹ሰው ጠላትህ›› ነው ይላል ። ከሰው ጋር መኖር ብዙ ዋጋ ቢያስከፍል እንኳ ከሰው ጋር አለመኖር ስለማይቻል እንደቅዱስ ቃሉ ከሰዎች ጋር በሰላም መኖር ብንችል እግዚአብሔር ይደሰታል፤ የአእምሮ ዕረፍትም እናገኛለን ።

ቤተ ክርስቲያን የማኅበራዊነት የጀርባ አጥንት እንደመሆኗ ማኅበራዊ ኑሮ ከተዳከመ ተልእኮዋ ስለሚቀዛቀዝ ከሰው ሁሉ ጋር ማለትም በቀለም፣ በሃይማኖት፣ በጎሣ ከማይመስሉን ጋር በሰላም እንድንኖር ትጥራለች፤ በየዕለቱ የምታስተላልፈው ምክሯም ውሉደ ክህነትና ምእመናን ለሰላም መሣሪያነት ይበቁ ዘንድ ነው ።

ማጠቃለያ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰው ልጆችን ደስታ፣ መከራና ኀዘን እየተካፈለች በዓለም ዘንድ የእግዚአብሔርን ፍቅር የምትገልጥ እንደመሆንዋ ከግላዊ አስተሳሰብ ይልቅ የጋራ የሆነ አመለካከት ለቤተሰብእ እና ለማኅበረሰብ ጠቃሚ መሆኑን ታስተምራለች፤ በክርስቶስ የተገለጠውን የእውነትና የነፃነትን መልእክት፣ የፍትሕና የሰላምን አስፈላጊነት በሰዎች ልቡና ለማስረፅም በስብከተ ወንጌል አገልግሎትዋ ታስተጋባለች፡፡

ዘመኑን በዋጀ አገልግሎት ተደራሽነትን የማስፋት ተስፋን ሰንቆ የሚበረታታ አፈጻጸም እያሳየ በሚገኘው የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በኩልም ኦርቶዶክሳዊ የሕፃናት አስተዳደግ፣ የወጣቶች መንፈሳዊ ሕይወት አጠባበቅ፤ የአረጋውያን እንክብካቤ፣ የመልካም ቤተ ሰብእ ግንባታ እና ምግባረ ሠናይ ላይ በትኩረት እየሠራች፤ ምእመናንንም እያሰናዳች፤ ሙሽራዋን ትጠባበቃለች፡፡

”ትሰግድ ለከ ቤተ ክርስቲያንከ፤ ወታሌዕለከ መርዓትከ፡-
ቤተ ክርስቲያንህ ትሰግድልሃለች፤ ሙሽራህም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፡፡‘
(ቅ.ቄርሎስ)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
አሜን፡፡

መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ (ቆሞስ)
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጸሓፊ
መስከረም 2018 ዓ.ም.

 

መምሪያው በ25 አህጉረ ስብከት ላይ የቅዱስ ወንጌል ስምሪት ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ገለጸ።

ታኅሣሥ ፲/፳፻፲፰ ዓ/ም

የአትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ለስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ቅዱሳት መጻሕፍትን አበረከተ!

ታኅሣሥ 7 ቀን 2018 ዓ.ም