የአትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ለስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ቅዱሳት መጻሕፍትን አበረከተ!

ታኅሣሥ 7 ቀን 2018 ዓ.ም

የአትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱስ እና ሌሎች መጻሕፍትን አበረክቷል ።

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሊቀ ኅሩያን ይልማ ጌታሁን ማኅበሩ ለስብከተ ወንጌል መምሪያው ያበተከታቸው መጻሕፍት የግእዝ ቋንቋን ጨምሮ በ19 ቋንቋዎች የተተረጎሙ 21 ዓይነት መጻሕፍት እንዲሁም በድምጽ የተዘጋጁ መጻሕፍት መሆናቸውን በንግግራቸው ገልጸዋል።

የማኅበሩ ዋናጸሐፊው ከቤተክርስቲያናችን ጋር በተለይም ዋና ተልእኮዋን በቀጥታ ከሚያስፈጽመው የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ጋር በሥልጠናና በወንጌል ተደራሽነት ዙሪያ ላይ በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ በትብብር እንደሚሠራ ገልጸዋል።  የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ኃላፊ መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ ” መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ልዩ ልዩ መጻሕፍት ያበረከቱትን የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ የሥራ ኃላፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው ወቅታዊ የመምሪያው የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።

በገለጻቸውም መምሪያው የሚዲያ ዘርፉን በማጠናከር የስብከተ ወንጌል ተደራሽነትን ለማስፋት እያደረገ ያለውን ጥረት፣ የስምሪት ተልእኮውን በብቁ መምህራን ለማከናወን ያስቀመጠውን አቅጣጫ እንዲሁም የሰባክያኑን አቅም ለማጎልበት ከሚሰጠው ሥልጠና በተጨማሪ መጠነኛ ቤተ መጻሕፍት የማደራጀት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል። አክለውም የመምሪያ ሠራተኛ ተናቦ እና ተግባብቶ በሁነኛ የቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ በአንድነት እየሠራ መሆኑ ገልጸው በተለይም ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጋር በሥልጠናና በወንጌል ተደራሽነት ላይ በቅርብት ለመሥራት ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረዋል።

ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ሊቀ ጳጳስ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ያደረገውን የመጽሐፍት ልገሰ በእጅጉ አመስግነዋል።  ለዚህ መልካም ተግባር ምክንያት የሆኑትን መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድን ያበረታቱ ሲሆን ከተመደቡ ጀምሮ የሚያስመስገን ሥራዎችን እየሠሩ በመሆኑም ሊደነቁ ይገባል ብለዋል። ብፁዕነታቸው በቋንቋ መስበክ የቤተ ክርስቲያናችን ሁነኛ መንገዷ እንደሆነ የበዓለ ሃምሳን ታሪክ አስታውሰው ያብራሩ ሲሆን አጠንክራ ልትሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነውም ብለዋል።  መጽሐፍ ቅዱስ ያነበቡ በተግባርም በሕይወታቸው የገለጡ አባቶቻችን ከሰው አልፈው ከምድር አራዊት ጋር ተስማምተው የኖሩ በሕይወታችን ያላመዱ ሲሆኑ በዘመናችን ግን ከገዛ ወንድሙና እኅቱ ጋር መግባትና አብሮ በሰላም መኖር አልቻለም ለዚህም በቅድሚያ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በሕይወት በመኖር ራሳችንን አድነን ሌሎችን ለማትረፍና ለማቅናት የሰላም ወንጌልን በሕይወት መስበክ ይገባል ብለዋል። ያነበበ እና የኖረ ይስበክ የሚሉት ብፁዕነታቸው እንደ ነቢዩ ሙሴ ጸጋንና የተሰጠን ስጦታ አውቆ ተናጋሪው ሰሚ፤ ሰሚው ተናጋሪ በመሆኑ ጸጋን ባለማወቅ የመደባለቅ ስብራት መጠገን አለበት። ይህም የቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ በአግባቡ እንዳይፈጸም ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነም ጠቁመዋል።

በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ያበረከተልን መጻሕፍት የመምሪያውን ቤተመጻሕፍት ከማጠናከሩ በላይ ተቋማቱ በቀጣይ ለሚያከናውኗቸው የትብብር ሥራዎች ድልድይ እንደሚሆን ገልጸዋል። በመርሐ ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመምሪያው ሊቀጳጳስ ሊቀ ኅሩያን ይልማ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዋና ጸሐፊ፤ መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የመምሪያው ዋና ሐላፊ እንዲሁም የተቋማቱ የሥራሐላፊዎች እና ተወካዮች ተገኝተዋል።